እስራኤል በዌስት ባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት ነጥቃ ከለለች

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስትባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት ነጥቃ መከለሏ ተነገረ።

በ10 ዓመት ውስጥ ከፍልስጤም ከፍተኛው የመሬት ዝርፊያ ነው የተባለለትን ድርጊት የመብት ተሟጋቾች እየተቃወሙት ነው።

የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች፥ በሰሜናዊ ዮርዳኖስ ሸለቆ የሚገኘው መሬት በእስራኤል መንግሥት ባለቤትነት እንዲተዳደር መወሰኑ “ወሳኝና ስትራቴጂካዊ ነው” ብለዋል።

ውሳኔው በስፍራው የሰፈራ ቤቶችን እና የንግድ ሕንጻዎችን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን መግለጻቸውንም ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል።

እስራኤል በኃይል በያዘችው የፍልስጤም መሬት ላይ የምታከናውነው የሰፈራ ፕሮግራም በዓለማቀፉ ሕግ ተቀባይነት የለውም።

የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም በ2016 ባወጣው መግለጫ የእስራኤል የሰፈራ ፕሮግራም የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭትን ለመቋጨት ይረዳል የተባለውን የሁለት መንግሥታት መፍትሔ ወይም “ቱ ስቴት ሶሊዩሽን” ተግባራዊ ለማድረግ “እንቅፋት” ነው በሚል መቃወሙ ይታወሳል።

በዌስት ባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም የሚካሄዱ የሰፈራ ቤቶች ግንባታን የሚቃወመው የእስራኤሉ “ፒስ ናው”፥ እስራኤል በዌስት ባንክ ከፍልስጤማውያን ነጥቃ የከለለችው መሬት ከ1993ቱ የኦስሎ ስምምነት በኋላ ሰፊው መሆኑን ጠቅሷል።

እስራኤል በ2024 በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም መሬቶች ላይ የምታካሂደው ግንባታና ወረራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስም ውሳኔውን ተቃውሟል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር በዌስት ባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም 3 ሺህ 400 የሰፈራ ቤቶች እንዲገነቡ የወጣውን እቅድ በዚህ ወር መግቢያ ማጽደቁ ይታወሳል።

ይህም የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ኔታንያሁ እንደሚሉት ሃማስን የመደምሰስ ሳይሆን የፍልስጤም መሬትን የመቀራመት የረጅም ጊዜ እቅድ ማስፈጸሚያ ነው የሚለውን ትችት አጠናክሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክም የእስራኤል የፍልስጤም መሬት ወረራ በዌስትባንክ ያለውን ውጥረት ይበልጥ ቀውስ ውስጥ የሚከት መሆኑን ነው ለፀጥታው ምክርቤት ባቀረቡት ሪፖርት ያመላከቱት።

የእስራኤሉ የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች በበኩላቸው የሰፈራ ፕሮግራሙ እስራኤል በታጣቂዎች የሚደርስባትን ጥቃት ለመመከት ወሳኝ ድርሻ አለው በማለት የሚነሱ ተቃውሞዎችን አጣጥለዋል።

እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት በኃይል በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም የቀድሞ ግዛቶች ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም ቤቶች ገንብታ 700 ሺህ አይሁዳውያንን ማስፈሯ ይታወቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You