የሰው በልቶ – አያድሩም ተኝቶ

ዕለተ- ቅዳሜ እንደተለመደው ማለዳውን ወደ ሥራ ልሄድ ከቤት ወጥቻለሁ። ቅዳሜ ለአብዛኞቹ የሥራ ቀን አይደለም። ይህ እውነት የትራንስፖርቱን ግርግር ጥቂትም ቢሆን ቀለል ያደርገዋል። አጋጣሚ ሆኖ እኔ ያለሁበት አካባቢ ከወትሮው ልማድ አይለይም።

ገና በጠዋቱ ታክሲ ለመያዝ ከሰልፉ የሚገኝ ይበረክታል። አውቶቡስ ለመሳፈር የሚቆመው ደግሞ ቁጥሩ ላቅ ያለ ነው። የሰሞኑ የሕንፃዎች ፈረሳና የመንገድ ላይ ቁፋሮ መደመራቸው ለጉዞው ውጥረት አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ከተደረደሩት መኪኖች መሀል ለመንገዴ የሚያመቸኝን መሰመር ጠይቄ ወደ አንደኛው አልፌያለሁ። የታክሲው የኋለኛ ወንበሮች በመሙላታቸው ጋቢና ልቀመጥ ነው። ጥሎብኝ የፊት ወንበር ምርጫዬ አይደለም። አሁን ግን ሰዓቱን ለመሻማት ስል አድርጌዋለሁ። ለመንቀሳቀስ ብዙ አልቆየንም። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሞተሩ ተነስቶ ጉዞው ተጀመረ።

ከሾፌሩ አጠገብ የተከፈተው ቴፕ ለስለስ ያለ ሙዚቃውን እያደረሰ ነው። ድምጹ አይረብሽም። የክራሩ ቅኝት ለማለዳው ተስማሚ ሆኖ ይንቆረቆራል። ግማሽ ልቤን ለሙዚቃው የተረፈውን ለመንገዴ ሰጥቻለሁ። እሱን ተሻግሮ ከበስተኋላዬ የምሰማው ጨዋታ ግን ጆሮዬን ይዞታል። የጉዳዩ የጋራ መሆን ደግሞ እንደዋዛ ሰምቼ የማልፈው አልሆነም።

ሁሉም ተመሳሳይ ርዕስ አንስተው የራሳቸውን መላ ምት እየሰጡ ነው። ደጋግመው የአንድን ባንክ ስም ማንሳት ይዘዋል። ባንኩ የትኛው እንደሆነ ለመስማት ጓጓሁ። ብዙ አልጠበኩም። ተጠሪው ‹‹የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ›› መሆኑን ተረዳሁ። የዓመታት ደንበኛው ነኝና ልቤ ደንገጥ አለ። ስሙን ተከትሎ እየሰማሁት ያለው አይታመኔ ጉዳይ ግራ እያጋባኝ ነው።

ሰዎቹ ስለዘመኑ ቴክኖሎጂ፣ ስለ መጭበርበር ወዘተ እያወሩ ነው። አሁንም የሚሉት ሁሉ አልገባኝም። እንደውስ እኔ ምን አገባኝ? አልኩና ፊቴን ወደ መንገዴ መለስኩ። አሁን የውስጤ ሃሳብ የእኔና የእኔ ብቻ ሆኗል። መውረጃዬ ደርሶ ቢሮ እስገባ ተጣድፌያለሁ።

ዕለቱ ቅዳሜም አይደል? ብዙ ነገር ይታሰባል። ለዚህ ደግሞ እጅ ባዶ መሆን የለበትም። እሱኑ እያሰብኩ ከቢሮዬ ገባሁ። ከሰዓት በኋላ ስለምከውናቸው ጉዳዮች ማቀዴን አልተውኩም። ከሥራ መልስ ሁሌም ወደምጠቀምበት ንግድ ባንክ ጎራ ማለት ግድ ብሎኛል ።

ይህ ከመሆኑ በፊት ለጆሮዬ አዲስ መረጃ ደረሰ። መለስ ብዬ ሳስበው ጠዋት ከሰማሁት ጨዋታ ጋር አንድ ሆነብኝ። የዚህኛው የሚለየው ሙሉ መረጃ መያዙ ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ፈፀመውታል ስለተባለው የሳይበር ጥቃት፣ ሌሊቱን ተወሰደ ስለተባለው በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ፣ ስለ ኤቲኤምና ገንዘብን ማስተላለፍ ወዘተ…ብዙ እየተባለ ነው።

ጉዳዩ በወጉ ሳይገባኝ ፣ የሰማሁትን በግማሽ ልብ ይዤ ወደ ኋላ አጠነጠንኩ። ነጥቦቹ ሲገጣጠሙ ቀድሞ የሰማሁት ከአሁኑ ጋር አንድ ሆነብኝ። ከዚህ በኋላ በቂ ነገር ለማወቅ ቀላል ነበር። የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቹ በሙሉ ይህ ጮማ ወሬ የጠዋት ቁርሳቸው ሆኗል። ከግርምታዬ መልስ ወደራሴ ተመልሼ አሰብኩ። የዕለቱ ዕቅዶቼ፣ የባከኑ መሰለኝ። ከባንኩ ገንዘብ የማግኘቴ ህልሜ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖ ታየኝ።

ከሥራ መልስ አቅራቢያዬ ወደሚገኙ ባንኮች አመራሁ። ለእኔና ባንኩን ለከበቡት ደንበኞች ‹‹ሲስተም የለም›› በሚል አገልግሎት እንደማይኖር ተነገረን። ተስፋ ሳልቆርጥ ወደሌሎቹ አዘገምኩ። አዲስ ምላሽ አልነበረም። በዚህ መሀል የሚናፈሱት ወሬዎች በአብዛኛው ስለባንኩ መዘረፍ፣ በተለይም ስለሳይበር ጥቃት የሚያመላክቱ ናቸው።

ጊዜው ከሰዓትን ተሻግሯል። ተስፋ ሳልቆርጥ ሜክሲኮ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ባንክ ደረስኩ። እንደሌሎቹ ሁሉ ደጃፉ በሰው አጀብ ተጨናንቋል። ጥያቄውም የዛን ያህል በርክቷል። ከበር የቆመው ጥበቃ ለሁሉም በትህትና ተመሳሳዩን ምላሽ እያደረሰ ነው። ‹‹ሲስተም የለም›› ።

ሲስተም የለም መባል ብርቅ አይደለም። ሁሌም ለደንበኞች ጆሮ የተለመደ ነው። ዕለቱን ግን የሰማው ላልሰማው ፈጥኖ ተቀባበለ። ለአፍታ አካባቢው ቀለል ከማለቱ ግን በድንገት ሲስተም መመለሱ ተሰማ። ብዙም ሳይቆይ የባንኩ ማስተናገጃ ሁሉ በበርካታ ሰዎች ተሞላ።

አገልግሎቱ የሚሰጠው ደብተር ለያዙ፣ ይበልጥ ደግሞ ተቀማጭ ለሚያስገቡ ደንበኞች መሆኑን አስተዋልኩ። ሁሉም ገንዘቡን ለማውጣት የተሰለፈ ነው። በአንዳንዱ ገጽታ ላይ ጭንቀት፣ በሌላው ላይ ደግሞ ቁጣና ንዴት ይነበባል። እኔ ተቀማጩን ባላስበውም በደብተሬ የወጪ አገልግሎት አግኝቼ ከሥፍራው ወጣሁ። አለመንኩም። እውነት ምስጋናዬ የላቀ ነበር።

ቤት ገብቼ ዕለቱን ይዞ እስከ ምሽቱ የነበሩ መረጃዎችን ፈታተሽኩ። ባንኩ ስለተፈጠረው ችግር ደንበኞችን ይቅርታ ጠይቆ አገልግሎት መጀመሩን የገለጸበትን መግለጫ አነበብኩ። ከዚሁ ተያይዞ ካጋጠመው የሲስተም ችግር ጋር ተያይዞ ሲናፈስ የቆየው የሳይበር ጥቃት ያለመሆኑ ተገልጿል። ባንኩ ጠንካራ የተሻለ ሲስተም ካላቸው ተቋማት መካከል አንዱ ስለመሆኑ መረጃዎችን ሰጥቷል።

ጉዳዩ ግን በዚህ ብቻ አልበቃም። ባገኙት አጋጣሚ ገንዘቡን መዝብረዋል የተባሉ ሰዎች ማንነት ከባንኩ መረጃ አላመለጠም። የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ የወሰዱትን ሰዎች እንደወሰዳችሁ መልሱ መባላቸው አልቀረም። ይህ እውነት ደግሞ በዋዛ የሚታይ አልሆነም። በሕግ የሚያስጠይቅ፣ የሀገርን ጥሪት በሟሟጠጥ በወንጀለኛነት የሚያስፈርጅ ነው።

ወደራሴ ትዝብት ልመለስ ፣ እስከዛሬ በርካታ ታማኝ ሰዎችን አይተናል። በአጋጣሚ ከእጃቸው የደረሰን በርካታ ገንዘብ አንዳች ሳይቆነጥሩ ለተገቢው የሕግ አካል ያስረከቡ ጥቂቶች አይደሉም።

ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ እንደስተዋልነውም አፋር አካባቢ ተበትኖ የተገኝ ቁጥሩ የማይታወቅ ገንዘብ ‹‹የባለቤት ያለህ›› እየተባለ ነው። ይህ ብቻ አይደለም፣ በሚያሽከረክሩት ታክሲ አልያም ባጃጅ ውስጥ ከተሳፋሪዎች ተረስቶ ያገኙትን ወርቅ፣ ላፕቶፕ፣ ገንዘብ፣ ዶላርና ሌሎች ንብረቶች ፣ ባለቤቱን አፈላልገው የሚሰጡ በርካታ ታማኞችን አይተናል።

በባንኮች የአሠራር ታሪክም በድንገት ከእጃቸው የገባን በርካታ ገንዘብ የኔ አይደለም ብለው የሚመልሱ ምስጉን ደንበኞች ስለመኖራቸው ደጋግመን አስተውለናል። ምስጋና ለእንዲህ ዓይነቶቹ መልካሞች ይሁንና አንዳንዶች ገንዘብ ንብረታቸውን በጣሉ፣ ጊዜ ይህን ሀቅ በመተማመን ‹‹ያገኛችሁ እባካችሁ መልሱልን›› ሲሉ በሙሉ አፋቸው ለመናገር ያስችላቸዋል።

ወደሰሞኑ አጋጣሚ እንመለስና በሲስተም ምክንያት ከኤቲ ኤም ሳጥን ገንዘብ መዝብረዋል የተባሉ አካላት ዛሬ በመብራት እየተፈለጉ ነው። በተፈጠረው የሲስተም ችግር ገንዘብ ያህልን ጉዳይ እንደጥገት ላም ሲያልቡ የነበሩ አንዳንዶች ዛሬ ላይ ወተቱ አርጎ አልሆናቸውም። የራስ ያልሆነ ሁሉ የራስ አይደለምና በድብቅ የወሰዱትን ሀብት በአደባባይ እንዲመልሱት አስገዳጅ ሁኔታ ላይ ደርሰዋል።

እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ተመዝብሯል? ለሚለው በቂ መረጃ ባይገኝም ለምላሹ ግን ስም ዝርዝራቸው በግልጽ ከወጣው አካላት በስተጀርባ እውነቱ እንደሚገለጽ መገመቱ ቀላል ነው። የተባለው ይሆን ዘንድም ለመላሾቹ ቀን ተቆርጦ ጊዜው ተወስኖላቸዋል። የሆነው ሆነና ‹‹የሰው በልቶ አያድሩም ተኝቶ›› ይሉት አባባል መተግበሩ አይቀሬ ሊሆን ነው።

እውነታውን መለስ ብለን ስንቃኘው ያለወጉ የተወሰደው ገንዘብ የግል ሳይሆን የሕዝብና የሀገር ሀብት ነው። ያለ አግባብ በእጅ የገባ ገንዘብ ደግሞ እንደራስ ላብና ጉልበት እንዳሻው መንዝረው ቢበሉት ጤና አይሆንም። ይህ ዓይነቱ ገንዘብ ኮቴ በተሰማ ፣ ኮሽታ በቀረበ ቁጥር ከስጋት ይጥላል። ከምንም በላይ ለራስ፣ ለወገን፣ ለሀገር የመታመን እውነታን ያሳጣል።

የራስ ባልሆነ ገንዘብ እየሰጉ፣ እየተሸማቀቁ መኖር ደግሞ አግባብ አይደለም። ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› ይሉት ብሂል እዚህ ላይ ትርጉም ያለው ይመስላል። ጎበዝ! እንግዲህ ቁርጡ ቀን መጥቷል። ሂሳብ ለማወራረድ ባይመችም ግድ የሆነ ይመስላል። በጨለማ የተወሰደ ገንዘብ በፀሐይ ተቆጥሮ ሊመለስ ጊዜው ደርሷል። ለምን ካሉ የሰው በልቶ በሰላም መተኛት የለምና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You