ሁለቱ ራሶች

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወታደርነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነት፣ በዲፕሎማትነት… በአጠቃላይ ለሀገራቸው ሕይወታቸውን የገበሩ ብዙ ጀግኖች አሉ። እነዚህንም ጀግኖች የጀግንነት ታሪክ የፈጸሙበትን፣ የተወለዱበትን ወይም በተፈጥሮ ሞትም ሆነ በጀግንነት ሲዋጉ መስዋዕት የሆኑበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ታሪካቸውን እናስታውሳለን። በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ወታደር፣ ግዛት አስተዳዳሪ እና ዲፕሎማት የሆኑትን ራስ መኮንን እና በጀግንነታቸው በሁሉም ልብ ዘንድ የሚታወሱት አጼ ቴዎድሮስ የሚፈሯቸውን ራስ ዳርጌን እናስታውሳለን።

ከዚያ በፊት ግን እንደተለመደው ሌሎች የዚህ ሳምንት ክስተቶችን እናስታውስ።

ከአራት ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም በ60 ዓመታት ወርቃማ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕይወት የሰጡት አንጋፋዋ የፅንስና የማህጸን ስፔሻሊስት ሐኪም ዶክተር ኤሊኖር ካትሪን ሐምሊን አረፉ። በዚህ ውለታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙዎች ዘንድ ሲታወሱ ይኖራሉ። የዶክተር ካትሪን ሐምሌንን ዝርዝር ታሪክ ከዚህ በፊት በሳምንቱን በታሪክ እና በሌሎች ዓምዶቻችን ጭምር በዝርዝር አይተናል።

ከ78 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 11 ቀን 1938 ዓ.ም ለሺህ ዘመናት የኖረውን ንጉሣዊ ሥርዓት በመቃወም፣ የተማሪዎችን ንቅናቄ በመፍጠርና አብዮት በማስጀመር፣ የብሄር ፖለቲካን በማቀንቀን የሚታወቀው ዋለልኝ መኮንን ተወለደ። ዋለልኝ፤ የብሄር ፖለቲካን በሚደግፉ ወገኖች የብሔሮችን መብት አስከብሯል በሚል የሚደነቅ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን በብሔር በመከፋፈል ለሀገራዊ ቀውስ ምክንያት ሆኗል በሚል ከፍተኛ ወቀሳና ውግዘት ይደርስበታል። በምሁራን እና በአንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ ‹‹ዋለልኝን አልተረዱትም›› የሚል ክርክር አለ። ያም ሆነ ይህ ዋለልኝ መኮንን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም የብሄር ፖለቲካን በማቀንቀን በደጋፊዎቹም በወቃሾቹም ሲታወስ ይኖራል።

ከ50 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም በየካቲት ወር ተጀምሮ የነበረው አብዮት ተቀጣጥሎ መምህራን የሥራ ማቆም አድማ አደረጉ። ይህ አድማ የተማሪዎችን እና የሥራ አጥ ወጣቶችን ድጋፍ በማግኘቱ ወዲያውኑ ወደ አመጽ እና ሁከት ተሸጋገረ። የዘውዳዊውን ሥርዓት እድሜ አፋጥነው

ካሳጠሩት ክስተቶች አንዱ ይኸው አድማ ነበር።

ከ52 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 12 ቀን 1964 ዓ.ም በአትሌትነት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማቀንቀን እና በብዙ የማህበራዊና ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች የምትታወቀው ደራርቱ ቱሉ ተወለደች።

Marcus, Menelik II, የመርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ዕለታዊ የታሪክ ድርጊት እና የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ መጻሕፍትን እንዲሁም የተለያዩ ድረ ገጾችን ዋቢ አድርገን በዝርዝር ወደምናየው የሁለቱ ራሶች ታሪክ ስንሄድ በመጀመሪያ የራስ መኮንንን እናገኛለን።

የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የንጉሥ ሳህለሥላሴ የልጅ ልጅ ናቸው። የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የአክስት ልጅ ናቸው። እኚህ ሰው የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አባት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ናቸው።

የዚህ ሳምንት ክስተት የሆኑት ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ያረፉት ከ118 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ነበር።

ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል የተወለዱት ግንቦት 1 ቀን 1844 ዓ.ም በሸዋ ግዛተ አፄ፣ ጎላ ወረዳ፣ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ነው። ገና በወጣትነታቸው ወደ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሄደው ከአጎታቸው ልጅ ከንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) ጋር ተዋውቀው ቤተሰባዊ ዝምድናቸውን አጸኑ።

በፀባያቸው ታጋሽና አስተዋይ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ልዑል ራስ መኮንን ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ጠንካራ ወዳጆች በመሆን እንደ አባትና ልጅ ይተያዩ ጀመር። የሐረርጌን ግዛት በሚገባ በማስተዳደር ለንጉሥ ምኒልክ ሀገር የማቅናት ተግባር ብርቱ አጋዥ ሆኑ። ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ተነስተው በዘመኑ ከንጉሥ በመቀጠል ከፍተኛ ለሆነው የ‹‹ራስ›› ማዕረግም በቁ።

ልዑል ራስ መኮንን የአጼ ምኒልክ ተወካይ በመሆን ሁለት ጊዜ ወደ አውሮፓ ሀገራት ተጉዘዋል። ወደ ኢጣሊያ በሄዱ ጊዜም የኢጣሊያ ጋዜጦች የውጫሌ ውልን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ጥገኝነት ስር እንዳለች አድርገው የሚጽፉትን ጽሑፍ በመመልከታቸው ራስ መኮንን ተቃውሟቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የውሉን መበላሸት ለአጼ ምኒልክም አሳውቀዋል።

የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሄው

 

 

ጦርነት ሲሆንም ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ ዓድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ታሪክ የማይዘነጋው ታላቅ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል። ልዑል ራስ መኮንን ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ እንደሚያደርጓቸውም ይወራ ነበር።

ነገር ግን ምኒልክ ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ልዑል ራስ መኮንን መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሞታቸው በንጉሰ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት (አዲስ አበባ) በተሰማ ጊዜም ከፍተኛ ሀዘን ሆነ። ንጉሥ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክም አምርረው አለቀሱ። በወቅቱም ይህንን የተመለከቱ ሰዎች እንዲህ ብለው ገጠሙ።

‹‹ዋ! አጤ ምኒልክ እግዚአብሔር ያጥናዎ፣

በየበሩ ቋሚ ከልካይ ሞተብዎ።

ሲታሰር አየነው ብረቱ ሲመታ፣

ምን ዋስ አገኘና ሐረርጌ ተፈታ።

ጃንሆይ ምኒልክ ጠጉራቸው ሳሳና በራ ገለጣቸው፣

እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው።››

ከአልቃሾቹ መካከል አንደኛው ደግሞ የልዑል ራስ መኮንንን ደግነት ለማስታወስ እንዲህ ብሎ ሙሾ አወረደ።

«ስልከኛው ሲያረዳ ነገር ተሳሳተው፣

መኮንን አይደለም ድሀ ነው የሞተው።»

ተብሎላቸዋል። ‹‹እንግዲህ ንጉሡ ምን ራስ አላቸው!›› የሚለው ሰምና ወርቅ ያለው መሆኑ ነው። ራስ መኮንን ከውጫሌ ውል ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦርነት ድረስ የነበራቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ እና የጦር ጀግንነት ለአጼ ምኒልክ ትልቅ ቦታ ነበረው። ስለዚህ አጼ ምኒልክ የራስነት ማዕረግ ያለው አንድ ትልቅ ሰው አጡ ማለት ነው።

ዲፕሎማቱ፣ የግዛት አስተዳዳሪውና ወታደሩ ራስ መኮንንም እነሆ በታሪክ ሲታወሱ ይኖራሉ።

ዋለልኝ አየለ

 

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You