በድንገት ያጣነው አንጋፋው ጋዜጠኛ

የአንድ ሀገር ሚዲያ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ የላቀ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ተፈፃሚ ሊሆኑ የሚገባቸውን ሀገራዊ ትልሞችን በማሳወቅና በማስተማር በኩል ሚናው የጎላ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

በሌላ በኩልም መገናኛ ብዙኃንና የሀገራቸው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ነጸብራቅ መሆናቸውም ግልጽ ነው። ምክንያቱም ባለቤትነታቸውና ሚናቸውም የሚወሰነው በሥርዓቱ ስለሚሆን። በዚህ ውስጥ ደግሞ የጋዜጠኝነትን ከባድ ኃላፊነትን የተሸክመው ባለአራት ዓይን ሙያተኛ ሆነው የሚያገለግሉ ሰዎች በጣሙን ያስፈልጋሉ። እንደ ጋዜጠኛ ወይም ዘጋቢ ያገኘውን መረጃ እውነትነቱንና ፍትሃዊነቱን ደጋግሞ ማጣራትና መመርመር የእነዚህ ባለሙያዎች ሥራም ነው። የሰማውን፣ ያየውንና ያነበበውን ሁሉ እንደ ትክክለኛ ዘገባ የሚወስድ ጋዜጠኛም በስተመጨረሻ የከፋ ስህተት ውስጥ ሊገባ ከራሱ አልፎም ሀገሩንና ሌሎችን ሊጎዳ የሚችልበት ዕድልም ሰፊ ነው።

በመሆኑም የሙያው ሥነ ምግባር በሚያዘው ልክ ማንኛውንም ዘገባ ትክክለኛና ፍትሃዊ እንዲሆን ይፈለጋል። ዘጋቢው ባለሙያ ስሜትና አድሎ ሳያሸንፈው በታማኝነት የሚሠራ እንዲሁም መረጃ ሲሰበስብና ሲመረምር ከዚህ ጋር ሚዛናዊነትን ለመሆን የማይታክት መሆን ይኖርበታል። ጋዜጠኛ በሙያው ጠንካራ ካልሆነ የሚገኘው መረጃ በተሳሳተ መልኩ ሊተላለፍበት ከመቻሉም ባሻገር በቀላሉ የማይታጠፍ ስህተት ሊሠራ ይችላል።

በተሰማሩበት ሙያ ወይም ኃላፊነት ያለመታከት ለሀገርና ሕዝብ የሠሩ ባለውለታዎቻችንን ታሪክ አቅርበን እውቅናና ምስጋና በምንቸርበት በባለውለታዎቻችን አምዳችን ላይ ለዛሬ የሚናመሰግነው በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየንን አንጋፋውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ እዮብ ግደይን ነው። ለ34 ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ በሚታተመው አልዓለም የዓረብኛ ጋዜጣ ላይ ከአራሚነት እስከ ዋና አዘጋጅነት የሠራ ሲሆን በሙያው ሀገር በምትፈልገው ጊዜ ሁሉ በመገኘት ያገለገለ ብርቱ ሰው ነበር።

ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ መጋቢት 11 ቀን 1958 ዓ.ም. ከአባቱ ከአቶ ግደይ አምባዬ እና ከእናቱ ሃረጉ ጎይትኦም በሱዳን ሀገር ከሰላ ግዛት ነበር የተወለደው። እድሜው ለትምህርት እንደደረሰ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበት ሀገር ሱዳን በሚገኘው አልሜሪያ ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እዛው ሱዳን በሚገኘው ዑመር ሃጂ ሙሳ ትምህርት ቤት ተምሯል።

ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ በመምጣትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ኮሌጅ የዲፕሎማ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ በጆርናሊዝም እና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱንም እዛው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊይዞሎጂ ትምህርት ዘርፍ ተከታትሏል።

በሥራው ዓለም ከመጋቢት 15 ቀን 1982 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወቱ እስካለፈበት መጋቢት 01 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአልዓለም ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በተለያዩ የሥራ መደቦች አገልግሏል።

ባገለገለባቸው 34 ዓመታት ውስጥ ከመጋቢት 15 ቀን 1982 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 30 ቀን 1990 ዓ.ም. በአልዓለም ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አራሚነት ከየካቲት 01 ቀን 1990 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 1996 ዓ.ም በአልዓለም ጋዜጣ በከፍተኛ ሪፖርተርነት ከሰኔ 01 ቀን 1996 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መጋቢት 30 ቀን 1998 ዓ.ም. በአልዓለም በጋዜጣ ሜክአፕ ኤዲተርነት ከሚያዚያ 01 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2006 ዓ.ም በአልዓለም ጋዜጣ በከፍተኛ አዘጋጅነት እንዲሁም በምክትል ዋና አዘጋጅነት ከጥቅምት 01 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ሕይወቱ እስካለፈበት ድረስ ሰርቷል።

ጋዜጠኛ እዮብ በአልዓለም ጋዜጣ ከሚሰራቸው ሥራዎች ባሻገር በዓረቡ ዓለም መገናኛ ብዙኃን የሀገሩን ጥቅም በሚያስከብር መልኩ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያና ተያያዥ ሀገራዊ ጉዳዮች የትንታኔ ጽሑፎችን በመፃፍና በመሞገት ይታወቃል፡፡ ለአብነትም ለአራ ኩባ ፤ ኑባ ታይምስ አልሚሌን እና ሱዳናይል በተባሉ የሱዳን መገናኛ ብዙኃን፤ እንዲሁም አል ዓረብ በተባለ የኳታር እና በሌሎችም ጋዜጦችና ድረ ገፆች ላይ የትንታኔ ጽሑፎችን በመፃፍ በሙያው ለሀገሩ አገልግሏል።

ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ተግባቢ፤ ሁሉንም ሰው እኩል የሚያይ፤ ሥራ ወዳድና ታታሪ ሠራተኛ የነበረው ጋዜጠኛ እዮብ እሁድ መጋቢት 01 ቀን 2016 ዓ.ም በተወለደ በ58 ዓመቱ በድንገተኛ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሥርዓተ ቀብሩም መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም አስኮ አካባቢ በሚገኘው አቡነ ሃብተማርያም ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡ ጋዜጠኛ እዮብ ከወይዘሮ መሠረት ገብረ ማርያም ጋር ትዳር በመመስረት ሁለት ልጆችንም አፍርቷል።

የጋዜጠኛ እዮብን ህልፈት በተመለከተ ወዳጆቹና የሥራ ባልደረቦቹ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ የአልጄዚራ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ጋዜጠኛ መሐመድ ጠሃ ተወከል አንዱ ሲሆን እርሱ እንደሚናገረው፤ « ጋዜጠኛ እዮብ ግደይን ከማውቀው ጊዜ ጀምሮ ግብዝነትና አስመሳይነት የሌለበት ሰውን ሁሉ እኩል የሚያይ ትክክለኛና የመርህ ሰው ሆኖ ነው የማውቀው። በቁርጠኛነት ከግል ጥቅሙ ይልቅ ሀገሩን በማስቀደም በሙያው ለሀገሩ ያለውን ሁሉ የሰጠ ሀገር ወዳድነትን በተግባር ያረጋገጠ ሰው ነበር» ይላል።

በሱዳን የተወለደው ጋዜጠኛ እዮብ ሙያውን ተጠቅሞ የሁለቱን ሀገራት ማለትም የኢትዮጵያና ሱዳን መልካም ግንኙነት እንዲቀጥል ሰርቷል የሚለው ጋዜጠኛ መሐመድ፤ የዓልአለም ጋዜጣን በመጠቀም በዓረቡ ዓለም ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚሰራጩ የተዛቡ ዘገባዎችን በመሞገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሙያውን ተጠቅሞ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅም የተፋለመ ጀግና እንደነበር ይናገራል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ደራሲና ጋዜጠኛ አንዋር ኢብራሂም ናቸው እሳቸው እንደሚናገሩት፤ «መጋቢት አንድ እሁድ አመሻሽ ላይ አሳዛኝ ዜና ደረሰኝ በህልም ውስጥ ያለሁ ነው የመሰለኝ ዜናው የወዳጄ ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ህልፈት ነበር። በአረብኛ ቋንቋ የሚታተመው የአልዓለም ጋዜጣ በምስራቅ አፍሪካ በዓረብኛ ቋንቋ የሚታተም አንጋፋ ጋዜጣ እንደመሆኑ የኢትዮጵያን እውነት ለዓረቡ ዓለም በማሳወቅ ረገድ የእዮብ አበርክቶ ከፍተኛ ነበር» ይላሉ።

እዮብ ግደይን ሁሉም ሰው የሚያውቀው በደስተኛነቱ ነው የሚሉት ደራሲ አንዋር፤ ለሁሉም ሰው እኩል ቦታ ያለው ሰውን በሰውነቱ የሚያከብር የትልቅ ስብዕና ባለቤት ነበር፤ እዮብን በመኖሪያውም ሆነ በሥራ አካባቢው የሚያውቁት ሰዎች ስለ እርሱ የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው ይላሉ።

የጋዜጠኛ እዮብ አስተዋጽኦ ከመተረካችን በፊት የዓልአለም ጋዜጣን መነሻና ዓለማ ማንሳት አስፈለጊ ነው የሚሉት ደግሞ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ አንተነህ ኃይለብርሃን ናቸው። ዓልአለም ጋዜጣ መሰራጨት የጀመረችው የዓረቡ ዓለም ስለኢትዮጵያ የተሻለ መረጃ እንዲያገኝ ለማስቻል ነው።

የዓረቡ ዓለም ለኢትዮጵያ ቅርብ ነው ኢትዮጵያ በዙሪያው ብዙ ፍላጐቶች አሏት በተለይ ከቀይ ባህርና ከአጠቃላይ ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጧ ጋር ተያይዞ ብዙ ነገሩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ ባሻገር በታሪክም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የነበራት ግንኙነት የሚታወቅ ነው። እነዚህን ታሪካዊ ትስስሮችን ለማስቀጠልና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት ለማፅናት ትክክለኛ መረጃ ለዓረቡ ዓለም ለመስጠት ታስቦ መዘጋጀት የጀመረ ጋዜጣ ነው።

አቶ አንተነህ እንደሚናገሩት፤ አልዓለም ጋዜጣ ላለፉት ረዥም ዓመታት ኢትዮጵያን በዓረቡ ዓለም መግለጥ የሚያስችል መሣሪያ በመሆን ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ነበረው፤ በዓረቡ ዓለም የሚታወቅ ጋዜጣ ነው። ስለ ኢትዮጵያ መረጃ ሲፈልግ የሚታይ ጋዜጣ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለዓረቡ ዓለም የምትለቃቸው መረጃዎች አሉ የፖለቲካ ግልፅነትን መስፈን፣ ጥቅሟን ማስጠበቅ የሚችሉ መረጃዎችን በዚህ ጋዜጣ አማካኝነት ታሰራጫለች፤ ከዚህ ባሻገር ጋዜጣው ከዓረቡ ዓለም የሚነሱ የሀገርና የሕዝብ ጥቅም የሚጎዱ ጉዳዮችን እንደ አንድ የሚዲያ መሣሪያ ሆኖ ሲመክት ቆይቷል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ግድቡ በተለይ ግብጾች በዓረቡ ዓለም የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸውና ከእውነት የራቁ መረጃዎችን በስፋት ሲለቁ የነበረበት ሁኔታ አለ፤ ይህንን በመገዳደር ሂደት ውስጥ ዓልአለም ጋዜጣ ትልቁን ሚና ተጫውታለች። ከዚህ አኳያ ነው እዮብ ግደይ እንደ አንድ ጋዜጠኛ ወይም ሀገሩን እንደሚወድ ሁልጊዜም ለሀገሩ ጥቅም እንደሚቆም ወታደር በሙያው ያበረከተውን አስተዋጽኦ መመዘን የሚገባው ነው ይላሉ።

አቶ አንተነህ እንደሚናገሩት፤ ጋዜጠኛ እዮብ ሀገር ወዳድ ነው፤ እንደ ወታደር ተሰጥቶ ሀገሩን ያገለገለ ነው። በዚህ ስብዕናው ላለፉት 20 ዓመታት በዓልአለም ጋዜጣ ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል። በተለይም ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ የነበረው እውነታ ጋዜጣዋ አቅም ገዝታ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ማስጠበቅ እንድትችል እንደባለሙያ ትልቅ ሥራዎችን ሠርቷል። በዓረቡ ሚዲያ የሚነሱ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ከመዳሰስ ጀምሮ ለጉዳዮቹ ተገቢ የሆነ ምላሽ በመስጠት፣ ሁለተኛ በራሱ ተነሳሽነት የሀገርን ፍላጐትና ጥቅም የሚያስከብሩ ጽሑፎችን በዓረብ በሚገኙ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመፃፍ የሀገርን ጥቅም ሲከላከል የነበረ ሰው ነበር ይላሉ።

እዮብ እውነተኛ የሀገር ፍቅር የነበረው ጠንካራ ጋዜጠኛ ነበር የሚሉት አቶ አንተነህ፤ ከሥራ ሰዓቱ ውጪ ወደ መኖሪያ ቤቱም ከሄደ በኋላ የዓረብ ሚዲያዎችን በመዳሰስ ነው የሚያመሸው የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ ዘገባዎችን ሲመለከት ወዲያው በማንኛውም ሰዓት ምላሽ መስጠት የሁልጊዜ ተግባሩና የሕይወቱ አካል ነበር፤ እንደ እዮብ ዓይነት ጋዜጠኛ በቀላሉ ማግኘት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ጋዜጠኛ እዮብን ስምና ገንዘብ ያላቸው ትላልቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አብሯቸው እንዲሰራ ይፈልጉ ነበር የሚሉት አቶ አንተነህ፤ የሚዲያዎቹ ባህርይ ከሀገርና ሕዝብ ጥቅም አኳያ በመመዘን በሌላ በኩል ለሀገሩ የተሻለ ነገር ማድረግ የሚችልበት ዕድል ስላገኘ ያንን ዕድል ላለማጣት ጥያቄያቸውን ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል፤ ሀገርና ተቋሙ ባለው አቅም ሀገሩን ለማገልገል የወሰነ ሰው ነበር፤ ይህም ለብዙዎች ጥያቄ ሆኖባቸዋል ምክንያቱም ከገንዘብ ይልቅ ሀገርን ማስቀደም ብዙም ያልተለመደ ስለሆነ ነው ይላሉ ፤ ስለዚህ እዮብ ከሚያገኘው ከፍተኛ ጥቅም ይልቅ ሀገሩን ያስቀደመ ጀግና እንደነበር፤ ቋንቋውን የሚናገር ጋዜጠኛ መተካት እንጂ እዮብ የማይተካ ብርቱ ሰው እንደነበር ተናግረው፤ በድንገተኛ ህልፈቱ ሀዘን ለገጠማቸው ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹና የሥራ ባልደረቦቹ መፅናናትን ተመኝተዋል።

እኛም በሥራ ባልደረባችን አንጋፋው ጋዜጠኛ እዮብ ግደይ ህልፈት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን፤ ለቤተሰብና ወዳጆቹ መፅናናትን እንመኛለን።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You