የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቡና ግብይትን ቀልጣፋና ምቹ ማድረግ ያስችሉኛል ያላቸውን የተለያዩ የግብይት አማራጮች ተግባራዊ በማድረግ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ /ኢ ሲ ኤክስ/ ገበያ እንዲወጣ ሪፎርም በማድረግ ወደ ትግበራ ሥራ ከገባም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ካሻሻላቸው የግብይት አማራጮች መካከል ወደ ሥራ ያስገባው የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ አንዱ ነው፡፡ ይህ የግብይት አማራጭ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በቡና ግብይት ውስጥ ያሉ የተንዛዙ አሠራሮችንና ረጅም ሰንሰለቶችን ማሳጠር እንደተቻለና ውጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጩ በግብይት ውስጥ የሚስተዋሉ መጓተቶችንና የተለያዩ ውስብስብ አካሄዶችን ማስቀረት ያስቻለ ቢሆንም፣ ውስንነቶች እንዳሉበትም የዘርፉ ተዋናዮች ይጠቁማሉ፡፡ ባለሥልጣኑም በቀጥታ የግብይት አማራጩ እያጋጠሙ ያሉትም እነዚህን ችግሮች ለመለየትና መፍትሔ ለመስጠት በሚል በቅርቡ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱም ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ቡና አምራቾች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎች ተሳትፈዋል፡፡
አቶ ናስር አብዱ፤ ከጅማ አካባቢ የመጡ ቡና አምራች፣ አቅራቢና ላኪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል በግብይት ሰንሰለቱ በርካታ ውስብስብ ችግሮች ይስተዋሉ ነበር፡፡ በተለይም ግብይቱ በምርት ገበያ በኩል በሚፈጸምበት ወቅት ቡናው በ20 ቀናት ውስጥ ካልተሸጠ የወደቀና የሞተ ተብሎ በርካሽ ዋጋ ይሸጣል፤ በዚሀም አርሶ አደሩ ለጉዳት ይዳረግ ነበር፡፡
በዚሁ የገበያ አማራጭ አርሶ አደሩም ሆነ አቅራቢው ተጠቃሚ አልነበሩም የሚሉት አቶ ናስር፤ በወቅቱ የቡናውን ዘርፍ የሚመራው አካል ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የገጠሙት እንደነበርም ያስታውሳሉ። በተለይ አርሶ አደሩ የልፋቱን ውጤት ያገኝ እንዳልነበር ይጠቁማሉ፡፡ በቡና ሥራ ውስጥ ከ25 ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸው በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በዝርዝር እንዲያውቁ አስችሏቸዋል። ከብዙ ትግል በኋላ አሁን ላይ የቡናውን ዘርፍ ብቻ የሚመራው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ተቋቁሟል፤ በዚህም ችግሮቹ እየተፈቱ ናቸው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ባለሥልጣኑ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በመወጣት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም የግብይት ሥርዓቱን ለማዘመን ሪፎርም ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል፡፡ በዚህም አርሶ አደሩን፣ አቅራቢውንና ላኪውን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ የግብይት አማራጮችን በመዘርጋት በግብይት በኩል ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ብርቱ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ነው አቶ ናስር የገለፁት፡፡
የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ ተግባራዊ በመሆኑ በግብይቱ ውጤታማ መሆን ያመለክታሉ። አርሶ አደሩ ያለማውን ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክ በቀጥታ መላክ አልያም ለላኪዎች ማቅረብ የሚችልበት ዕድል መፈጠሩንም ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ረገድ የእርሳቸውን ተሞክሮ በአብነት አድርገው ‹‹እኔ ለምሳሌ በቡና ሥራ 25 ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፤ ይሁንና አንድም ቀን ያለማሁትን ቡና ለውጭ ገበያ ልኬ አላውቅም፡፡ ቡናውን ተሸክሜ ለአቅራቢና ለላኪዎች ነበር የማቀርበው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም ቡና ወደ ውጭ ገበያ መላክ ችያለሁ›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
የቀጥታ ትስስር ግብይት አማራጭ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የቻለና ውጤት ያሳየ ቢሆንም፤ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉበት ይጠቁማሉ፡፡ አርሶ አደሩ በቀጥታ ቡና ከመላክ ባለፈ ከላኪው ጋር በመቀራረብና በመተማመን አስፈላጊውን ክፍያ እንደሚያገኝ ጠቅሰው፤ በዚህ ግብይት አልፎ አልፎ ከክፍያ ጋር በተያያዘ አቅራቢዎችና ላኪዎች ቡናውን ከተረከቡ በኋላ ክፍያውን በአግባቡ የማይፈጽሙበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራሉ። እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት መፍትሔ ማፈላለግ ተገቢ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡
ከጌዲዮ ዞኑ ቡና አቅራቢ ነጋዴ አቶ እያሱ ፍቃዱ በበኩላቸው፤ በቡና ግብይት ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት ያደንቃሉ። ቡና በምርት ገበያ አማካኝነት ሲሸጥ ከነበረበት ጊዜ አሁን ላይ የተሻለ የግብይት ሥርዓት እንዳለም ይናገራሉ። ቡና በምርት ገበያ በኩል በሚገበያይበት ወቅት በርካታ ፈተናዎች ይገጥሙ እንደነበር አስታውሰው፤ በምርት ገበያ ውስጥ ወንበር በሚለው አሠራር ምክንያት ያቀረቡትን ቡና ማየት አለመቻላቸውና ቡናቸው ሳይራገፍ ከ15 ቀናት በላይ ይቆይ እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ በተለይም ጅማሬው ላይ በጣም ጥሩ እንደነበር ገልጾ፤ አሁን አንዳንድ ችግሮች እየገጠሙ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ቡና ላኪዎች አቅም ያላቸው በመሆናቸው አቅራቢውና አምራቹ ገንዘብ ሲያጥራቸው ከላኪው በብድር የሚወስዱበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህን ሁኔታ መነሻ በማድረግ ቡና ላኪዎች ታች ድረስ በመውረድ ቡናውን ከአርሶ አደሩ በቀጥታ ለመግዛት የተለያዩ ተጽዕኖዎችን ያደርሳሉ፡፡ እነዚህን አካላት መንግሥትም ‘የውጭ ምንዛሪ በቀጥታ የሚያመጣው ቡና ላኪው ነው’ በሚል ይደግፋቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በአቅራቢዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ከማድረስም በላይ ከገበያ እንዲወጡ እያደረገ ነው፡፡
‹‹አቅራቢዎች ያቀረቡት ቡና መጀመሪያ በምርመራ ማዕከል ተመርምሮ ደረጃ የሚሰጠው ቢሆንም ላኪዎች ዘንድ ሲደርስ ደግሞ በድጋሚ ተመርምሮ ቀድሞ ደረጃ አንድ የነበረው ቡና ደረጃ ሁለትና ሶስት የሚሆንበት አጋጣሚ አለ›› ያሉት አቶ እያሱ፤ ይህ ለምን ሆነ ብለው ቢጠይቁም አጥጋቢ ምላሽ እንደማያገኙ ያመለክታሉ። በዚህ የተነሳም ቡናቸውን በዝቅተኛ ዋጋ ለመሸጥ የሚገደዱበት አጋጣሚ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም ቡና አምርቶ የሚሸጠው ገበሬ ሕይወቱ አልተለወጠም፤ የገበሬ ቡና ተጠርጎ ወደ ከተማ ይመጣል። በመሆኑም ቡና አምራች ከሆነው አርሶ አደሩ ይልቅ ቡና ላኪው የበለጠ ተጠቃሚ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ የሚባለው በአቅራቢና በላኪ መካከል የሚደረግ የገበያ ትስስር መሆኑን አስረድተው፤ የቀደመው የግብይት አማራጭ በፖሊሲና በአዋጅ ጸድቆ ሲሰራበት መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ በዚያ አሠራርም አርሶ አደሩ ምንም ዓይነት አማራጭ እንዳልነበረው ጠቅሰው፤ ምርቱን ማሳው ላይ ብቻ ሲሸጥ እንደነበር ይገልፃሉ። አርሶ አደሩ ዋጋ መቀበል እንጂ ዋጋ ተደራድሮ መሸጥ የሚችልብት ዕድል እንዳልነበር ተናግሮ፤ ቡና ሰብሳቢው በሚሰጠው ዋጋ ብቻ ቡናውን ማሳው ላይ ሲሸጥ እንደነበርም ያመለክታሉ፡፡
እርሳቸው እንዳብራሩት፤ አርሶ አደሩ ቡናውን ለሰብሳቢ ሲያስረክብ ሰብሳቢው ደግሞ ለመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከል ያቀርባል፡፡ በመቀጠልም ወደ አቅራቢው ይደርሳል፡፡ ይሁንና በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የሚያልፉ ተዋናዮች በቡናው ላይ ምንም ዓይነት እሴት የሚጨምሩ አልነበሩም፡፡ በተቃራኒው የቡና ጥራት እንዲቀንስና እንዲባክን ያደርጋሉ፡፡ ይህ የግብይት ሥርዓቱም እጅግ የተንዛዛና ምንም እሴት የማይጨምርበት አድርጎት ቆይቷል፡፡ የቡናው ቤተሰብ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ችግሩን መፍታት የሚያስችሉ የግብይት አማራጮችን ለማምጣት ሪፎርም ተደርጓል።
በዚህም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበትን ዕድል ጭምር በመፍጠር የተለያዩ የግብይት አማራጮች ቀርበዋል፡፡ በተለይም አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚል ሁለትና ከዛ በላይ ሄክታር መሬት ያለው አርሶ አደር ተምሮና ከገበያ ጋር የሚገናኝበት ዕድል ተመቻችቶለት ቡናውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ መላክ የሚችልበት ዕድል መፈጠሩን ያስረዳሉ፡፡ ይህ ካልሆነለትም አርሶ አደሩ ቡናውን ለአቅራቢዎች በማቅረብ የአቅራቢ ላኪ ሆኖ ቡናውን በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያቀርብበት የገበያ አማራጭ መዘርጋቱን ያመለክታሉ፡፡ ካልሆነም አቅራቢው ከላኪው ጋር ተሳስሮ ቡናውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርብበትን የቀጥታ ትስስር ግብይት አማራጭ በሪፎርሙ ተግባራዊ ተደርጓል ይላሉ።
ይህ የግብይት አማራጭ የቡናን ጥራት በማስጠበቅ ብክነትን በማስቀረትና የተንዛዙ አሠራሮችን በማስወገድ የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር አዱኛ፤ ለሀገርም የተሻለ ገቢ ከማስገኘት አንጻር ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ያመለክታሉ፡፡ አጠቃላይ የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ መኖሩ የተሻለ ጥራትና እንዲሁም ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ዓለም ገበያ እንዲቀርብ አስችሏል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የግብይት አማራጩ ችግሮች እንደታዩበትም ጠቅሰው፣ አልፎ አልፎ በአምራቹና በአቅራቢው እንዲሁም በላኪው መካከል የመካካድ አዝማሚያዎች እንደሚታዩ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም አቅራቢው ብር ይዞ የመጥፋት፤ ላኪውም እንዲሁ ከአቅራቢው ቡና ከወሰደ በኋላ ገንዘቡን በጊዜው ያለመክፈል ችግሮች በተደጋጋሚ መታየታቸውን፤ ይህን ተከትሎም መተማመን የሌለበት የንግድ ልውውጥ መፈጠሩን ያብራራሉ፡፡ ‹‹መመሪያው አቅራቢም ሆነ ላኪው ቡናውን ሲረካከቡ ክፍያ ተፈጽሞ መፈጸም እንዳለበት ያስቀምጣል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን መፍታት እንደሚቻልም ነው ያስረዱት፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ ቡና ማለት እንደማንኛውም ሸቀጥ ሳይሆን ወሳኝ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ምርት ነው። በአሁኑ ወቅትም ቡና ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ዩኒየን ስትራቴጂክ ምርት ሆኗል፡፡ ቡና በዚህ ደረጃ ዕውቅና እንዲያገኝ የተፈለገበት ዋናው ምክንያትም አሁን በጸደቀው ኢንተር አፍሪካ ኮንቲኔንታል ንግድ ውስጥ ቡና የግብይቱ አካል እንዲሆን ተፈልጎ ነው፡፡
‹‹ቡና የሀገር ሀብት ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ በቡና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ እየተሳተፉ አርሶ አደሮች፣ ላኪዎችና አቅራቢዎች በቡና ንግድ ሥራው ውስጥ ገብተው የተወሰነ ትርፍ ቢያገኙም ከዚያም በላይ ለሀገር ወሳኝ የገቢ ምርት መሆኑን ታሳቢ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ከሀገርም አልፎ የአፍሪካ ትልቅ ሀብት በመሆኑ ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ። ስለዚህ ይህን ሥራ ስንሰራ ትልቅ ሀገራዊ ተጽዕኖ ያለውን ሥራ እየሠራን መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል›› ሲሉም አክለው ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ ቡና ወደ ገበያ በተለይም ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርብበት መንገድ አንድ ብቻ መሆን የለበትም፤ አማራጭ የግብይት መንገዶች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የግብይት አማራጭ መንገዶቹ እየተገመገሙ፣ እየታረሙና እየተሻሻሉ ሊሄዱ ይችላሉ። የትኛውም አማራጭ የበቃና ምንም እንከን አልባ ባለመሆኑ እንደ መንግሥት የፖሊሲ አማራጮችን፣ የስትራቴጂና የሕግ አማራጮችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ አማራጮቹ ለራሳቸው ሲሉ ይጣፍጡ፤ ለራሳቸው ሲሉ ስህተቶቻቸውን እያረሙ ይሂዱ፤ ካልሆነ በወጣው ሕግ መሠረት ሊሻሻሉና ሊሰረዙ ይችላሉ፡፡ በዋናነት በቡና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚሰራ ማንኛውም ሥራ አምራቹን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል የሚፈለገውን ጥራትና መጠን ማምጣት ይቻላል።
የመንግሥት ስትራቴጂና ፖሊሲ አንዱና ዋነኛው ማዕከል የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑንም ተናግረው፣ ሁለተኛው በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋናዮች አቅራቢው፣ ላኪውና ሌሎች አካላትም በጨመሩት እሴት ልክ ፍትሃዊ ተጠቃሚ ማድረግ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ምንም እሴት ሳይጨምር የምርቱን ወጪ ብቻ እየጨመሩ ያሉ አካላት ግን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ልንቆጣጠራቸው ይገባል ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡
የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ በአሁኑ ወቅት አማራጭ ሆኖ እያገለገለ ያለና አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን እሳቸውም ጠቅሰው፣ ሕግና መመሪያውን ተግባራዊ ባላደረጉ ጥቂት ግለሰቦች ግን የግብይት አማራጩ የቡናውን ግብይት እያወከ እንደሆነ መነገሩ ተገቢነት እንደሌለው ያመለክታሉ። የግብይት አማራጩ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት እንዲታረሙና እንዲስተካከሉ በማድረግ የቀጥታ ትስስር የግብይት አማራጭ ወደፊት እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም