
የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች አዲስ ረቂቅ ሕግ አውጥተው ቲክቶክ መታገድ አለበት አሊያ ደግሞ ባለቤቱ የቻይናው ኩባንያ ሊሸጠው ይገባል የሚል ክርክር ገጥመዋል።
የቪዲዮ ማጋሪያ የሆነው መተግበሪያ በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች አሉት።
ነገር ግን የደንበኞቹ የመረጃ ደኅንነትን እየጠበቀ አይደለም፤ ከቻይና መንግሥት ጋር ግንኙነት አለው የሚሉ ክሶች ይቀርቡበታል።
ከሁለቱም የአሜሪካ አውራ ፓርቲ የተውጣጡ ፖለቲከኞች አዲስ ያረቀቁት ሕግ የቲክቶክ ባለቤት የሆነው ባይትዳንስ መተግበሪያውን ቻይናዊ ላልሆነ ኩባንያ ካልሸጠ ይዘጋል ይላል።
ሕግ አውጪዎቹ ቲክቶክ በአሜሪካ የሚገኙ 170 ሚሊዮን ደንበኞችን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
ቲክቶክ ግን የውጭ ሀገር መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፌ አልሰጥም ሲል ያስተባብላል።
የአሜሪካ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት በ352 የድጋፍ ድምፅ እና በ65 ተቃውሞ ሕጉን አፅድቋል።
አሁን ረቂቅ አዋጁ ወደ ላይኛው ምክር ቤት (ሴኔት) ተሸጋግሯል። ነገር ግን ሴኔቱ እንደ እንደራሴዎቹ ምክር ቤት ሕጉን በቀላሉ ያፀድቀዋል የሚል ግምት የለም።
አብዛኞቹ የሴኔት አባላት ሕጉን ይደግፉታል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግልፅ ምላሽ አላገኘም።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሕጉ በሴኔቱ ከፀደቀ ፈርማቸውን እንደሚያሰፍሩበት ተናግረዋል።
አዋጁ በሴኔቱ ፀድቆ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ፊርማ ካረፈበት፤ ባይትዳንስ ቲክቶክን ለመሸጥ የስድስት ወራት ዕድሜ ይሰጠዋል፤ ካልሆነ ከአሜሪካ ገበያ ይታገዳል።
ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ ታገደ ማለት ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን ከሚያወርዱበት የአፕ ስቶር እና የጎግል ፕሌይ ይወገዳል ማለት ነው።
ረቂቅ አዋጁ “በውጭ አካላት የሚመሩ መተግበሪያዎችንም” አሜሪካ ውስጥ አፕዴት ማድረግ እና መጠገን አይቻልም ይላል።
ቲክቶክ አዲሱን ረቂቅ አዋጅ በጥብቅ እያወገዘው ነው።
የቲክቶክ ሥራ አስኪያጅ ሹ ዚ ቺው፤ ረቂቅ አዋጁ “ለሌሎች ማኅበራዊ ሚድያ የበለጠ ኃይል መስጠት ነው” አልፎም በሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን ከሥራ ውጪ ማድረግ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ባይትዳንስ፤ ቲክቶክን መሸጥ ከፈለገ ከቻይና መንግሥት ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል። ነገር ግን ቤይጂንግ ይህን እንደማታደርግ እያስጠነቀቀች ነው።
አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች አዲሱን ረቂቅ አዋጅ እየተቃወሙት ይገኛሉ።
ቲክቶክ 170 ሚሊዮን የሚሆኑ በአሜሪካ የሚገኙ ተጠቃሚዎቹ ወደ ግዛቶታቻቸው ተወካዮች ደውለው ረቂቁን ሕጉን ውድቅ እንዲያደርጉት እንዲጠይቁ መክሯል።
ቲክቶክ ሕንድ ውስጥ ታግዷል። ሕንድ የቲክቶክ ትልቋ ገበያ ነበረች። ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 2020 መተግበሪያውን አግዳዋለች።
መተግበሪያው በኢራን፣ በኔፓል፣ በአፍጋኒስታን እና በሶማሊያ ጥቅም ላይ እንዳይውል እግድ ተጥሎበታል።
በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ የመንግሥት ሠራተኞች እና የፓርላማ አባላት በሥራ ስልካቸው ቲክቶክን እንዳይጠቀሙ ባለፈው ዓመት ተነግሯቸዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽንም በተመሳሳይ በሥራ ስልክ ቲክቶክን መጠቀም አግዷል።
ቢቢሲ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ሠራተኞቹ ከድርጅቱ የተሰጣቸውን ስልክ ተጠቅመው ቲክቶክን እንዳይገለገሉ ከልክሏል።
የቲክቶክ ዋናው መሣሪያ አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር) ነው።
ይህ መተግበሪያው የተጠቃሚዎችን ታሪክ ተመልክቶ የትኛውን ዓይነት ይዘት ይወዳሉ የሚለውን የሚለይበት ዘዴ ነው።
ወደ ቲክቶክ ሲገቡ ከላይ ሦስት ንዑስ ርዕሶችን ያገኛሉ። ፎሎዊንግ፣ ፍሬንድስ እና ፎር ዩ ይባላሉ።
ፎሎዊንግ እና ፍሬንድስ ተጠቃሚዎች ከሚከተሏቸው ሰዎች እና ከጓደኞቻቸው የሚያገኟቸው ይዘቶች ናቸው።
ፎር ዩ የተሰኘው ደግሞ በራሱ መጥኖ ተጠቃሚዎች ይህን ይዘት ይወዱታል በሚል የሚለቀቅ ነው።
ተቺዎች ቲክቶክ ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች በላይ የተጠቃሚዎችን መረጃ ይሰበስባል፤ ለዚህም ነው የተመረጡ ይዘቶችን የሚያቀርበው ይላሉ።
የተጠቃሚዎች አድራሻ፣ የሚጠቀሙበት ስልክ፣ የሚወዷቸው ይዘቶች እና ሲፅፉ የሚያሳዩት ባሕሪን ይሰበስባል የሚል ትችት ያቀርባሉ።
ነገር ግን ሌሎች እንደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ይህን በማድረግ ይታወቃሉ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2016 ዓ.ም