39 ዓመታት በባቡር ቴክኒሺያንነት

አሁን አሁን መጠነኛ መሻሻሎች ያሉ ቢሆንም ቀደም ባለው ጊዜ ግን ሴቶች ከማጀት አልፈው ተምረው ትልቅ ደረጃ ደርሰው አደባባይ እንዲታዩ፤ ሠርተው ገቢ እንዲያገኙ የሚፈቅድ ማኅበረሰብ እምብዛም አልነበረም። ከዛ ይልቅ ሚስት፤ እህት፤ እናት ሆነው ቤታቸው ውስጥ ተወስነው እንዲቀመጡ ልጆቻቸውንና የትዳር አጋራቸውን እንዲሁም መላ ቤተሰባቸው መንከባከብ ሥራቸው እንዲሆን ነበር ያልተጻፈው በማኅበረሰቡ ልብ ውስጥ ያለው ሕግ የሚያዘው።

በዚህ ጎታች አስተሳሰብ ደግሞ ብዙዎች ወደ ሕልማቸው መድረስ ሳይችሉ ብዙ እምቅ ችሎታን ይዘው ቤታቸው እንዲቀመጡ ተገደዋል። በተቃራኒው ችግሮችን ጎታች ሁኔታዎችን ተቋቁመው አቅማቸውን አውጥተውና አትችሉም ለሚሏቸው ሁሉ መቻላቸውን በተግባር አሳይተው እጅን በአፍ ያስጫኑ ከራሳቸው አልፈው ለብዙዎች የእንጀራ በርን የከፈቱ በርካታ ሴቶችም አሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ ግን የሴቶችን መብት ለማስከበር መብታቸውን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መስኮች ላይ እኩል ተሳታፊነታቸውን ለመጨመር መንግሥትን ጨምሮ በራሳቸው ተነሳሽነት ተቋማትን መሥርተው የሚንቀሳቀሱ ብዙ አካላት አሉ፤ ምናልባት እነዚህ ወገኖች በዘርፉ ምን ያህል ሠርተው ምን ውጤት አመጡ የሚለውን ለመመለስ ጥናት የሚፈልገው ቢሆንም ባለው ሁኔታ ግን ጥቂትም ቢሆን ተጨባጭ የሚባሉ ለውጦችን ማየታችን አልቀረም ።

ሴቶችን ማብቃት በትምህርታቸው እንዲሁም በሚፈልጓቸው ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ ማድረግ ግን ለመንግሥት አልያም ለግብረሠናይ ድርጅቶች የሚተው ሳይሆን ሁላችንም ከቤታችን ጀምረን ልንሠራው እና ልንወጣው የሚገባ ኃላፊነት መሆኑን መገንዝብ ያስፈልጋል።

የዛሬ የሕይወት ገጽታ ዓምድ እንግዳችን ከወንዶች በላይ ብርቱና ጠንካራ ሴት ናቸው። ያሰቡበት ለመድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለ39 ዓመታት ከባድ የሚባለውን የባቡር ቴክኒሺያንነትን ሙያ የሠሩ ናቸው።

ወይዘሪት አማረች ቦጋለ ተወልደው ያደጉት በፍቅር ተምሳሌቷ በድሬዳዋ ከተማ ነው። እናትና አባታቸው ወንድም ሴትም ልጆች ያሏቸው ቢሆኑም በተለይ አባታቸው እሳቸውን ወንድ አድርገው ለማሳደግ ከፍ ያለ ፍላጎት ነበራቸው። በዚህም አማረች ውሎዋቸው ከወንድማቸው ጋር ሆነ፤ አባታቸውም እናታቸውም በዚህ ተቃውሞ አልነበራቸውም። ወንድማቸው የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ ያደርጋሉ፤ እንደ ወንድማቸው ብርቱ ሠራተኛ ናቸው። በትምህርትም የሚታሙ አልነበሩም፤ ከሁሉም በላይ ግን አባታቸው “……የእኔ ልጅ ጀግና ነሽ ፤ምንም አያቅትሽም” እያሉ ያሳደጓቸው ጠንካራ ሴት ናቸው።

“…..ትውልዴ ሁሉም በሚወዳት የፍቅር ተምሳሌት በሆነችው ድሬዳዋ ከተማ ለገሃሬ አካባቢ ሲሆን ያደግሁት ደግሞ ገንደቆሬ ቀበሌ ነው። ከአባትና ከእናቴ እንዲሁም ከእህት ወንድሞቼ ጋር ነው የኖርኩት” ይላሉ።

ወይዘሪት አማረች የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ድሬዳዋ ከተማ አቡነ እንድሪያስና ሚካኤል ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምሀርታቸውን ደግሞ በድሬዳዋ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መከታተላቸውን ይናገራሉ።

ወይዘሪት አማረች በትምህርት የማይታሙ ብሎም ለራሳቸው የማያንሱ ነበሩ። ነገር ግን ወንዳወንድ ሆነው ማደጋቸው እሳቸውም የወንድማቸውን ፈለግ ለመከተል መመኘታቸውና በጠቅላላ ነገረ ሥራቸው ሁሉ የወንድ መሆኑ በትምህርታቸው ላይ ከፍ ያለ ደረጃ እንዳይደርሱ የድርሻውን የተወጣ ይመስላል ።

የአንደኛ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆነው ለጓደኝነት የሚመርጧቸውም ወንዶች ነበሩ። ውሎዋቸውም ከወንዶች ጋር ነበር። ምንም እንኳን የሴት ጓደኞች ቢኖሯቸውም ልክ ከወንዶቹ ጋር ተስማምተው እንደሚኖሩት አይነት ግንኙነት አይፈጥሩም። በጠቅላላው እሳቸው የሚያደሉት ለሴታዊ ሳይሆን ለወንዳዊ ባሕርያቸው እንደነበር ይናገራሉ።

ድሬ ከምትታወቅበት ነገር አንዱና ግንባር ቀደሙ ባቡሯ ነው። ከአዲስ አበባ ተነስቶ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ በበረሃና በጫካ ውስጥ የሚያልፈው ባቡር ደግሞ ለድሬ መታወቂያዋ ከመሆኑም በላይ ብዙዎች ብዙ ትዝታ ያፈሩበት እንጀራ ፈጥሮ ብዙ አባወራዎችን ያኖረና በርካታ ቤተሰብ በሁለት እግሩ እንዲቆም ምክንያት የሆነ ስለመሆኑ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚረዳው ነው።

አማረችም አባታቸው በምድር ባቡር ውስጥ ተቀጥረው ያገለግሉ ነበር። በወቅቱ እሳቸውም ሆኑ አባታቸው ሥራውን እንደ ገቢ ማግኛና ቤተሰብ ማስተዳደሪያ ያዩታል እንጂ ከትውልድ ትውልድ ይወራረሳል ብለው በፍጹም አላሰቡም ነበር። ነገር ግን የሕይወት አጋጣሚ ወዴት እንደሚወስድና ምን እንደሚፈጥር አይታወቅምና በአባታቸው የሚያውቁትን ምድር ባቡር እሳቸውም የእንጀራ ቤታቸው ያደርጉት ዘንድ እድሉን ማግኘታቸው አልቀረም ።

“……በማንኛውም መንገድና ሁኔታ እኔ ከወንድሜ ስር ጠፍቼ አላውቅም እሱ ያደረገውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ፤ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪም ሆኜ ብዙ ነገሬ እሱ ነበር፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼም አብዛኛው ነገሬ ከቀለሙ ትምህርት ይልቅ ለሙያ ትምህርት ትኩረት አደርግ ነበር” ይላሉ።

አማረች ከልጅነታቸው ጀምሮ ከወንድማቸው ጋር በመዋል የለመዷቸውን ኋላም በወንድማቸው አበረታችነት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብተው የብረታ ብረት ሥራ ትምህርት (ጂ ኤምን) ተማሩ።

“………ትምህርቱን እንደነገርኩሽ ከወንድሜ ተማክሬ እኔም ወድጄው የገባሁበት በመሆኑ ስማረው ምንም አልከበደኝም፤ እንደውም ከወንድ ልበልጥ ሁሉ እችላለሁ። የንድፈ ሃሳቡንም፤ የተግባሩንም ትምህርት በሚገባ በመማር በዲፕሎማ ለመመረቅ ችያለሁ” በማለት የትምህርት ቤት ቆይታቸውን ያስታውሳሉ።

አማረች ወንድማቸው በዚህ መልኩ ሲያግዟቸው እናትና ሌሎች የቤተሰባቸው አባላትም አልተቃወሟቸውም፤ ነገር ግን ሁለተኛ ደረጃን እየተማሩ ባለበት ወቅት ግን የትምህርት ቤቱ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም ) ለሴቶች ቀሚስ ለወንዶች ደግሞ ሱሪ ያዝ ስለነበር እሳቸው ደግሞ ቀሚስ ለብሰው አላደጉምና ሁኔታ በጣም ፈታኝ ሆነባቸው፤ ትምህርት ለማቋረጥ ሁሉ ፈልገው እንደነበር ያስታውሳሉ።

“…….እኔ ቀደም ብዬም እንደነገርኩሽ አባቴ ሱሪ እያለበሰ በርቺ እያለ ወንዶች የሚያደርጉትን ነገር እንዳደርግ እየፈቀደልኝ እንደውም እያበረታታኝ ወንድሜም እንደዛው የሚሄድበት ሁሉ ይዞኝ እየሄደ ነው ያደኩት። ይህ ሁኔታ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት ቤት ቆይታዬ ምንም አልረበሸኝም፤ ነገር ግን ወደሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስገባ በተለይም የደንብ ልብስ ቀሚስ ልበሺ ስባል ነገሮች ከበዱኝ። እንደዛ ለብሼ ልማር እንደማልችል ለቤተሰቤም ለመምህራኖቼም አሳወኩ፤ ነገሩ በጣም ከባድ ቢሆንም ቤተሰቦቼ ትምህርት ቤቱን ነግረውልኝ ከሁሉም ሴቶች በተለየ እኔ ብቻ ሱሪ ለብሼ እንድገባ ተፈቅዶልኝ ነው የተማርኩት” ይላሉ።

አማረች ምድር ባቡር ላይ ይሠሩ የነበሩት አባታቸው በጡረታ ሲገለሉ ድርጅቱ ባለው አሠራር መሠረት አባታቸውን ተክተው ተቋሙን አራት ዓመት በተማሩት የብረት ሥራ ትምህርት ሊያገለግሉ ፈተና ተፈትነው በማለፋቸው ተቋሙን ስለመቀላቀላቸውም ነው የሚናገሩት።

እሳቸው የብረት ሥራ ሙያን ይዘው ምድር ባቡርን ሲቀላቀሉ አንድም ሴት የሌለ ሁሉም ወንዶች ብቻ የነበሩ ቢሆንም እሳቸው ግን አቅሜን አሳያለሁ እጅ አልሰጥም ሠርቼ ለውጥ አምጥቼ ሴቶች በተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ ውጤታማ መሆን እንደማይሳናቸው አሳያለሁ ብለው ሥራውን በልበ ሙሉነት የዛሬ 39 ዓመት ገደማ ጀመሩት።

ብቸኛዋ ሴት የማሽን ባለሙያ ሆነው በጀመሩበት ምድር ባቡር ላይም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ብዙ ሥራዎችን ስለማከናወናቸው የሚያውቋቸው አብረዋቸው የሠሩ ሁሉ የሚመሰክሩላቸው ሐቅ ነው።

አማረች በምድር ባቡር ውስጥ ያሉ የብረታ ብረት ሥራዎችን በሙሉ ይሠራሉ፤ ባቡሩ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀስ በፉርጎዎቹ መካከልም ይሁን በሐዲዱ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በሚገባ ይጠግናሉ፤ በዚህም የበቁ ፤የነቁ ባለሙያ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።

“……እኔ ድርጅቴን በሙያዬ ለማገልገል ደክሞኝ አያውቅም፤ ሁሌም ሥራ ካለ መሥራት የማውቀውን ለሌሎች ማሳወቅ ከእነሱም የምወስዳቸውን ትምህርቶች በንቃት ማየትና በተግባር መቀየር የሥራ መርሔ ነው” ይላሉ።

በአንድ ወቅት እንደውም ለአየር ኃይል የዳቦ ቤት እቃን በመገጣጠም ባበረከትኩት አስተዋፅዖ ከእኔ አልፎ ድርጅቴን የሚያስመሰግን ሥራ ሠርቻለሁ የሚሉት አማረች ከዛም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየቦታው ያሉ ኪዮስኮቹ ጥገና ሲያስፈልግቸው በብቃት በመጠገናቸው በአየር መንገዱም እውቅናና ምስጋና እንደተቸራቸው ያብራራሉ።

“…….ምድር ባቡር ልጅ ሆኜ የተቀላቀልኩት መሥሪያ ቤት ነው፤ የልጅነትና የወጣትነት ጊዜዬንም አሳልፌበታለሁ፤ ለእኔ ቤቴ ማለት ነው። በሥራዬም ብዙ መልካም ነገሮችን አበረክቻለሁ ብዬ አስባለሁ፤ ብዙ ወጣቶችም እውቀትን አግኝተዋል የሚል እምነት አለኝ። ለ39 ዓመት ገደማ ሥራም አንድም ቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ብዬ አላውቅም። እንደ ሳይንሱ ከሆነ እኔ በምሠራው ዓይነት ሙያ ውስጥ ሴቶች ከአራት ዓመት በላይ ባይቆዩ ተብሎ ነው የሚመከረው። እኔ ግን ይህንን ሁሉ ዓመት ሠርቻለሁ። በዚህም ደስተኛ ነኝ። አሁንም የሥራው ፍቅርና ፍላጎት አብሮኝ ነው” በማለት ስለሥራቸው ይናገራሉ።

በድሬዳዋ ምድር ባቡር ታሪክ የመጀመሪያዋም ብቸኛዋም የሴት ቴክኒሻን ይሁኑ እንጂ የልፋታቸውን ያህል ወይም የሚገባቸውን ያህል ጥቅምም፤ እውቅናም ስላለማግኘታቸው ይናጋራሉ። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የከፍተኛ አመራሩ ለሴቶች ያላቸው ማበረታቻ በጣም የወረደ መሆኑ እንደሆነም ግምታቸውን ይናገራሉ።

“………እኔ ሥራ በጀመርኩበት ወቅት እንኳን ድሬዳዋ ምድር ባቡር ቀርቶ ጅቡቲና ፈረንሳይ ሀገርም ሴት ቴክኒሻን አልተቀጠረም ነበር። ከእኔ በኋላም አንዲት ሴት የመጣች ቢሆንም በሥራው ላይ ብዙ መቀጠል ሳትፈልግ ለቃለች። ከዛ በኋላም የመጣች አለች ነገር ግን ያን ያህል አይቆዩም። ምክንያቱ ሥራው ከባድ ስለሆነ ነው” ይላሉ።

በአንድ ሥራ ላይ ከፍ ያለ ዓመታትን ለመቆየት ዋናው ነገር ሥራውን ከልብ መፈለግና መውደድ ነው። ከዛ ደግሞ ራስን ለጥቅም ተገዢ አለማድረግ ወሳኝነት አለው የሚሉት አማረች ሰው ፍቅር ሳይኖረው ሥራ ቢጀምር ውጤታማ አይሆንም። ዛሬ ላይ ደግሞ ወጣቶች ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ፍቅር ስላላቸው ደመወዝ ይላሉ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ብዙ ርቀት አይወስዱም በማለት ያብራራሉ ።

“……እኔ ሥራ የጀመርኩት በ 285 ብር ደመወዝ ነው፤ ዛሬ ላይ ይህ ብር ይከፈል ወይም ሰው በዝቅተኛ ገንዘብ ሥራ ይሥራ እያልኩ አይደለም። ይህንም ቢባል ኑሮው ድሮና ዘንድሮ የሚገናኝ ባለመሆኑ ችግር ነው። ነገር ግን ወጣቶች ሴቶችም ይሁኑ ወንዶች ለፍታ ላስተማረቻቸው ሀገራቸው ምን ላበርክት ብለው ማሰብ ሲገባቸው ሙያቸውን በገንዘብ መቀየር ብቻ ከሆነ ሕልማቸው ችግር ይፈጠራል። በመሆኑም እነሱም ሳይጎዱ ያስተማረቻቸውም ሀገር ከእነሱ ማግኘት ያለባትን ነገር ሳታጣ አጣጥሞ መሄድን ማወቅ ያስፈልጋል” በማለት ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።

ምድር ባቡርን እሳቸው እንደ ሁለተኛ ቤታቸው የሚያዩት ቢሆንም ሲቀጠሩ ጀምሮ ያለው የአሠራር ሂደት ግን እሳቸውን ያገለለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንደውም ‹‹የሚሠራ ሰው የሚፈለግ አይመስልም›› በማለት ይናገራሉ። እኔ የምሠራውን ሥራ ጥቅምና ጉዳቴን ተቋሙ ያውቃል ጓደኞቼ ደግሞ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው። ነገር ግን መሥሪያ ቤቱ ለእኔ ሴት ሆኜ ከባዱን የሥራ ዘርፍ መርጬ እየሠራሁ ምንም ያደረገልኝ ነገር የለም።›› በማለት የሚናገሩት አማረች ‹‹አንዳንዶች ትላንት ገብተው ዛሬ ቤት ተሰጥቷቸው፤ ሌላም ሌላም ነገር ተደርጎላቸው ይታያል ይህ ግን ሞራል የሚነካ ነገር መሆኑ ቢታወቅልኝ እወዳለሁ›› ይላሉ።

“……በዚህ ዘመን ሴት ልጅ ከወንድ እኩል ከሠራች ወንዱ ሲሠራ የነበረውን አስበልጣ ሠርታ ከተገኘች የማትበረታታበት ምክንያት ምንድን ነው፤ መንግሥት ሴቶችን ማብቃት ማበረታታት እያለ የሚያወራው እኮ በየመሥሪያ ቤቱ ያሉ ጠንካራ ሴቶችን እያበረታቱ ወደፊት ማምጣት እንዲቻል ነው እንጂ እየሠራች፤ እየለፋች ያለችን ሴት ትኩረት መንፈግ አይመስለኝም “ በማለት ይናገራሉ።

አማረች ያለፉትን 39 ዓመታት በጥንካሬ በከፍተኛ ወኔና በደስታ ነው ሲሠሩ የኖሩት። ዛሬም በሥራው ላይ ናቸው። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ግን አንድም ቀን አሟቸው ወይም ደግሞ ሥራውን ልተወው በቃ ብለው አያውቁም። ለዚህ ብርታታቸውና ጥንካሬያቸው ዋናው ምክንያት የሰው ፍቅር ቢሆንም ጎን ለጎን ደግሞ በየቀኑ ከሥራ ወደቤት ከቤት ወደሥራ የሚያደርጉት የብስክሌት ጉዞም ስለመሆኑ ይናገራሉ።

ወንድ የሥራ ባልደረቦቻቸው እንደ ራሳቸው እንደሚያዪዋቸው የሚናገሩት አማረች እነሱ የሚሠሩትን ሁሉ ስለምሠራ ይደክማታል፤ ቆይ ይሄ ለሴት አይሆንም ብለው ተጨንቀውም አያውቁም፤ እኔም እንደዛ እንዲሰማቸው ስለማልፈልግ የምሠራውን ሥራ በከፍተኛ ሞራልና ቁርጠኝነት ነው የማከናውነው በማለት ይናገራሉ።

አማረች ውጪ የሚውሉ በተለይም የወንድ ሥራ እየሠሩ ከወንዶች ጋር የሚውሉ ከመሆኑ አንጻር እንደው ማኅበራዊ ሕይወቱንስ እንዴት እየገፉት ነው ስላቸው እየሳቁ”…….ማኅበራዊ ኑሮ ላይ ተሳትፎ አደርጋለሁ፤ በቀበሌም ይሁን በሴቶች ማኅበር በኩል ያሉ ተሳትፎዎችን እሳተፋለሁ ነገር ግን እንደ ሴቶች ወጥ መሥራት አልያም ለመሥሪያ የሚሆን ግብዓቶችን ማዘጋጀት ላይ ሰነፍ ነኝ፤ የሚገርምሽ በሥራ ቦታ ላይ ሆነን በዓል ከሆነ እርድ ይፈጸማል በዚህ ሂደት ውስጥ የእኔ ሚና የሚሆነው ቁጭ ብዬ መከታተልና ምግቡ ተሠርቶ ሲጠናቀቅ መመገብ እንጂ በሥራው ላይ ተሳትፌ አላውቅም፤ እነሱም ስሪ አይሉኝም” በማለት ይናገራሉ።

“…….ሴት ልጅ ጥፍሯን ፀጉሯን አሳምራ ሥራ ብትሄድ ነው የምትመርጠው የኅብረተሰቡም አመለካከት ይኸው ነው፤ እኔ ግን እንደ ወንዶች ቱታ ለብሼ፤ እጄም ግሪስ ነክቶ መሬት ላይ ተንደባልዬ ነው ሥራዬን በአግባቡ የምወጣው እንደእኔ አይነት ሴት ቴክኒሻንም አለ ብዬ ለማለት ይከብደኛል፤ እኔ ግን በሥራዬ በጣም ደስተኛ ነኝ አቅሜ እስከፈቀደም ድረስ እሠራለሁ” ይላሉ።

ድሮ በእኛ ጊዜ ሴት እንኳን እንደ እኔ አይነት ሥራ ቀርቶ ሌሎቹንም ሥራዎች ልሥራ ስትል ብዙ የሚገጥሟት መሰናክሎች ነበሩ፤ ዛሬ ላይ መጠነኛ መሻሻሎች ይታያሉ። ሴቶች የወንዶች የሚባሉ ሥራዎችን እየሠሩ ነው። በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ ላይ የማያቸው ሴት አሽከርካሪዎች በጣም ደስ ይሉኛል፤ ያኮሩኛልም በማለት ሴቶች እየተሳተፉባቸው ስላሉ የሥራ መስኮች ይናገራሉ።

አማረች የሚወዷቸው አባታቸው ሕመምና ሞት ብዙ እንደጎዳቸው ይናገራሉ፤ በተለይም አባታቸው ካረፉ በኋላ እናታቸውን የመንከባከብ አብሮ የመሆን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ እሳቸው ላይ መውደቁ በትምህርታቸው እንዳይገፉ በተለይም ደግሞ ከሀገር ውጪ ሄዶ የመኖር የመለወጥ ሕልማቸውን እውን እንዳያደርጉት እንዳደረጋቸውም ነው የሚናገሩት።

ሌላው አማረች የባቡር አሽከርካሪ ለመሆን ፍቃደኝነቱም ፍላጎቱም ነበራቸው፤ ነገር ግን እስከ አሁን በሙያው ያልገቡት እሳቸው የሚፈልጉት ሰዎችን አሳፍሮ የሚሄደውን ባቡር ማሽከርከር ነው፤ ድርጅቱ ደግሞ አሽከርካሪ ከሆኑ የሰውንም የእቃም ማጓጓዣ ባቡርን ማሽከርከር ግዴታ ነው ማለቱ ወደሙያው እንዳይገቡ እንዳራቃቸውም ይናገራሉ።

“…….ባቡር እንዳሽከረክር አዲስ አበባ ያሉ ሴት ሠራተኞች ሳይቀሩ ሀሳብ አቅርበዋል፤ እንዲሁም ብዙ ድጋፎችና ማበረታቻዎችን ሲያደርጉልኝ ነበር። ነገር ግን ድርጅቱ የእቃና የሰው ማጓጓዣ ባቡሮች ያሉት በመሆኑ ባቡር መንዳት ከፈለኩ ሁለቱም ላይ ተሳታፊ መሆን አለብሽ ብሎኛል። የእቃ ማጓጓዣ ባቡሮች ደግሞ ሁለትና ሦስት ቀን መንገድ ላይ ይቆያሉ (ያድራሉ) ለእኔ ደግሞ ያ ነገር ብዙም አይመቸኝም፤ ከዚህ አንጻር የሰው ማጓጓዣው ላይ ብቻ ልሥራ ብልም ተቀባይነት ባለማግኘቴ እስከ አሁን ባቡር አላሽከረከርኩም” በማለት የባቡር አሽከርካሪ ያልሆኑበትን ምክንያት ያስረዳሉ።

ምንም እንኳን አማረች በድርጅቱ ውስጥ ከ39 ዓመት ያላነሰ የአገልግሎት ጊዜ ቢኖራቸውም ተቋሙ ግን በደንብ ይዟቸዋል ለማለት የሚያስደፈር አይደለም። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ለሌሎች ባለሙያዎች በጅቡቲና በሌሎች አገሮች የሚደረገው የልምድ ልውውጥ ሥልጠናና ሌሎች ነገሮች እሳቸው ጋር ደርሰው አያውቁም። በዚህ ቅር ቢላቸውም መሥሪያ ቤታቸውን ግን ወደውት እስከ አሁን እየሠሩ ነው።

“……..እውነት ለመናገር ምድር ባቡር ያሉ አመራሮች ተፅዕኗቸው ከባድ ነው እንጂ በተቋሙ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያዋ የሴት ቴክኒሽያን ሆኜ ጅቡቲን እስከ አሁን አላየኋትም፤ ምክንያቱም አለቆቻችን ጥሩ አመለካከት የላቸውም፤ እስከ አሁን በሥራዬም አገኘሁት የምለው ነገር ድርጅቱን በቅንነት ማገልገሌን እኔ ለወንዶቹ ጓደኞቼም ብርታት መሆኔን እንጂ በጥቅም ደረጃ ከደመወዜ በቀር የማውቀው ምንም ሽልማትም ሆነ ስጦታ የለም” በማለት ሁኔታውን በኃዘን ይገልጹታል።

አማረች እስከ አሁን ድረስ ትዳር ይዘው ቤተሰብ ለመመሥረት አልቻሉም ለዚህ ደግሞ “……ብዙ ጊዜ ከወንዶች ጋር መዋሌ ፤ ሥራዬም የወንድ መሆኑ አብዛኛውም ሰው ከወንድ እንጂ ከሴት እኔን መመደብ አለመቻሉ ምናልባት ተፅዕኖ አሳድሮብኝ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፤ ግን ደግሞ እኔም በዛ ውስጥ እያለፍኩ ስመጣ ለሁኔታው ፍላጎት እያጣሁ መጣሁና ትዳርም ቤተሰብም ለመመሥረት የነበረኝ ጉጉት በዛው ቀረ” በማለት ይናገራሉ።

አሁን ላይ ምድር ባቡር ውስጥ የተለመደ ሥራቸውን እያከናወኑ የሚገኙት ብርቱዋና ጠንካራዋ አማረች ዛሬ ላይ ድርጅቱ ውስጥ የሠራተኞችን ኅብረት እንደሚመሩ በሙሉ ድምፅ ተመርጠው ከሥራቸው ጎን ለጎን በማገልገል ላይ ናቸው።

አማረች ወደፊት ቢሆንልኝ ብለው የሚመኙት ይህንን ነው፤”……ሰዎች ተበድለው በደላቸውን የሚክስ ፍትሕ አጥተው ሳይ በጣም አዝናለሁ፤ እኔም ቢሆንልኝና ቢሳካልኝ የእነዚህን ሰዎች እንባ የማብስበት አቅም ቢኖረኝ ብዬ እመኛለሁ፤ ከፈጣሪ ጋርም ወደፊት የምሠራው ይመስለኛል “።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You