ሰሞኑን አብዛኞቹ የከተማችን ማዕከላዊ ቦታዎች በመልሶ ግንባታ ላይ ናቸው። በየቀኑ መንገዶች ይቆፈራሉ፣ ሕንፃዎች ይፈርሳሉ፣ ዛፎች ይቆረጣሉ። ስራው ድንገት ከመጀመሩ ጋር አንዳንድ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ ይጠበቃል። ሰሞኑን በግልጽ እንደሚስተዋለውም በርካታው እግረኛና ተሽከርካሪ ባሰበው ጊዜ ካሻው ቦታ መድረስ አልተቻለውም።
ግንባታው የሚካሄደው ቀኑን ሙሉ በመሀል መንገድ ላይ ነው። ትላልቅ ማሽኖች ከአስፓልቱ ወገብ ቆመው ይውላሉ። በአብዛኛው ይህን የሚያደርጉት መንገዱን ዘግተውና አጨናንቀው ነው። በየአፍታው ግዙፍ ድንጋዮችን፣ የወደቁ ዛፎችን ያነሳሉ፣ ይጥላሉ። አፈር የሞላ ባለጥርስ መዛቂያቸው ከመሬት ከፍ ብሎ ባንዣበበ ጊዜ እግረኛ ሆኖ አለመገኘት ነው። ማንም ይሁን ማን ተጣድፎና ተሯሩጦ ማለፉ አይቀሬ ይሆናል።
ለወትሮው ገና ሲታዩ የሚያስጨንቁት ሲኖትራኮች በየዕለቱ ከእግረኛው ጎን እየተጋፉ፣ አፈር ድንጋዩን እንጨት ኮረቱን ይጭናሉ። መንገደኞችም ከእነሱ ተተግነው ማለፍን እየለመዱት ነው።
ጠልቀው ከተቆፈሩ ጉድጓዶች ተዝቆ የሚወጣው አፈር ለእግረኛውም ለመኪናውም መጨናነቅ መፍጠሩ ይታያል። ፍርስራሾች፣ ግንድ ቅጠላ ቅጠሎች ፈጥነው ካልተነሱ ለእግረኞች መጨናነቅ ምክንያት ናቸው። ችግሩ ግን ይህ ብቻ አልሆነም። ቀን አቧራ የነበረው ስፍራ መሸት ሲል ዝናብ ካገኘው የሚሆነውን መገመት ነው። በአፍታ መልኩን ቀይሮ ጭቃ ሊሆን አይዘገይም። እርግጥ ነው በግንባታ ወቅት ይህ አይነቱ ገጠመኝ ይከሰታል። አንድ ውጤት እስኪገኝ በውጣ ውረድ ማለፍ ግድ ነውና።
የሰሞኑ የመንገዶች እንቅስቃሴ ለአንዳንዶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን እያየን ነው። ከፍርስራሾች መሀል የሚገኘውን ብረታብረት ለሚለቃቅሙ ሰዎች የገቢ ምንጭ ሆኗል ። እንደውም አንዳንዶቹ በአርማታ የተጠቀጠቁ ሙሊቶችን ተሸክመው ሲሮጡ ድካም አይሰማቸውም። በመሀል የተተከለውን ብረት እየነቀሉ፣ ዓይናቸው ሌላውን ያማትራል። ለእነሱ እንደዋዛ የተጣለው ብረታብረት ጥቅሙ የበዛ ነው ፣ ሲሸጡት ጥሬ ገንዘብ ሆኖ ይመለሳል።
የሚገርመው ግን ይህ የመሆኑ ጉዳይ አይደለም። የሰሞኑ ግንባታና የመንገድ መጨናነቅ ሰበብ የሆናቸው አንዳንድ ባለ ታክሲዎች አጋጣሚውን እየተጠቀሙበት ነው። እነሱ አያደርጉትም፣ አይሞክሩትም እንጂ ደንበኛን አክብሮ መገኘት ለራስም መከበር ነበር። ልማደኞቹ ባለታክሲዎች ግን ዛሬም ስለራሳቸው ጥቅም ብቻ ይሮጣሉ።
አሁን ላይ ከፒያሳ፣ አራት ኪሎ መገናኛ ለመጓዝ ታክሲ መጠየቅ ሀጢያት የሆነ ይመስላል። አራት ኪሎን ረግጦ ላለማለፍ የሚጥሩ ሾፌርና ረዳቶች የራሳቸውን መንገድ ቀይሰዋል። ማንም የትም ይሂድ፣ የትም ይውረድ ጉዳያቸው አይደለም። በራሳቸው ስልጣን ቦታ ይመርጣሉ፣ መንገድ ያቋራርጣሉ።
እንዲህ አይነቶቹ ሞገደኞች ሁሌም ጊዜና አጋጣሚን ጠባቂዎች ናቸው። የእነሱ ጉዙ ሁሌም ሻካራውን አይወድም። እርምጃቸው ሁሉ በለስላሳ መንገድ ላይ ነው። ኮሽ ባለ ቁጥር ህሊናቸውን ሸጠው ኪሳቸውን ለማስፋት የሚያህላቸው የለም።
በእነሱ የሥራ ባህል በዕድሜው የገፋ፣ አካሉ የተጎዳ፣ ርቆ መሄድ የማይችል ሰው ዓይናቸው አይገባም። ለምን የሚላቸው ቢገኝ ምላሻቸው ‹‹አትጨቅጭቀን›› ይሆናል። የተጠየቀውን ከፍሎ ካሻቸው ቦታ የሚጥሉት ሰው ብቻ ይመቻቸዋል።
ችግሩን የሚያባብሰው ደግሞ እንዲህ ባደረጉ ጊዜ ለምን ብሎ የሚጠይቃቸው አካል ያለመኖሩ ነው። ሁሌም ባሻቸው መንገድ ተመርተው ተሳፋሪውን ሲያንገላቱ በድርጊታቸው ተማምነው ፣ በራሳቸው እርግጠኞች ሆነው ነው። ተጠቃሚውም ቢሆን ዕለቱን አዝኖና ደክሞ ጉዳዩን እንደሚተወው አሳምረው ያውቁታል። እናም ይህ አይነቱ አጋጣሚ ዋጋ ለመጨመርና ተሳፋሪውን እንደፈለጉ ለማሽከርከር ዕድል ይሰጣቸዋል።
በእኔ እሳቤ ልማቱም ሆነ ሥራውን ተከትሎ የሚከሰቱ አንዳንድ ችግሮች የጋራ ሊሆኑ ይገባል። ነገ የታሰበው ተጠናቆ ፍሬው መታየት ሲጀምር ጠቀሜታው የእኩል ይሆናልና። አሁን ላይ ግን በአንዳንድ ለውጦች ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች ለሌሎች በጎ አጋጣሚን እየፈጠሩ ነው። መተዛዘን፣ መተሳሰብ የሚባል ቃል ድራሹ የጠፋ እስኪመስል።
ከሰሞኑ ካለው የመንገድ ቁፋሮ ጋር ተያይዞ ሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች የሉም ። ለምሳሌ ሥራዎቹ በሚከወኑባቸው ስፍራዎች የኔትወርክ ሽቦና ገመዶች በመነካካታቸው አብዛኛው የዘርፉ አገልግሎት ተቋርጧል። በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች የዋይፋይና መሰል ቴክኖሎጂዎች እየሠሩ አይደለም።ጥቂት ባንኮችም ችግሩን አሳውቀው አገልግሎት አቁመዋል። የመብራትና ውሃ ጉዳይም እንዲሁ።
እነዚህ እውነታዎች በግልጽ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች ታዲያ የሆነውን አስተውለው ችግሩን ተጋሩት እንጂ በማንአለብኝነት አልሸሹትም። በአካባቢው ያሉ ሌሎች ባንኮች ከአቅማችን በላይ ነው ብለው ደንበኞችን አልመለሱም። መንገድ የተቆፈረባቸው፣ ትራንስፖርት ያጠራቸው፣ በእግራቸው የሚጓዙ ብዙ ሠራተኞች ሁኔታው ‹‹ሰለቸን›› ብለው በየቤታቸው አልቀሩም። ሁሉም ችግሮችን በእኩል ተጋርተዋል። ሥራና ደንበኞቻቸውን አክብረዋል።
ብዙ ጊዜ ይህ መሰሉ ለውጥ ሲኖር የራሱን ሌላ ለውጥ ይዞ መምጣቱ የተለመደ ነው። ሁኔታዎችም እንደቀድሞው በነበሩበት ላይቀጥሉ መቻላቸው ይገመታል። አንዳንድ አገልግሎት ሰጪዎች ራሳቸውን ብቻ ባማከለ መልኩ የሚከውኑት ተግባር ግን ለበርካቶች የሚመች አይሆንም። ልክ እንደ ባለታክሲዎቹ ሁሉ ባሻቸው መንገድ በራሳቸው ሕግ ይመራሉና።
እንዲህ በሆነ ጊዜ ድርጊታቸው ሁሉ ከሚመለከታቸው አካላት ዓይን የራቀ እንደማይሆን ግልጽ ነው። እነዚህ ወገኖች ተጠቃሚው ሲንገላታ፣ ጊዜው፣ ጉልበት ገንዘቡ ሲመዘበር ያያሉ፣ ይሰማሉ። እንዲያም ሆኖ ለውሳኔ የዘገዩ ናቸው። ሕግና መመሪያው ፣ መቀጫና መሻሪያው በእጃቸው ሳለ ለተግባራዊነቱ አይፈጥኑም።
ይህ እውነት ደግሞ ዝምታ በበዛ ቁጥር የሕግ መጣሱ ችግር እንዲስፋፋ በር ይከፍታል። አጋጣሚዎች በተፈጠሩ ጊዜ ሰዎች እርስ በርስ እንዳይደጋገፉ፣ አንዳንዶችም ባልተገባ ሕግ እንዲመሩ ያደርጋል። የሕገወጦች ድርጊት ሕጋዊ መስሎ እስኪታይ ድረሰ በሌሎች አእምሮ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም የዋዛ አይደለም።
ሁሌም እንደሚባለው በእኛነታችን ዘንድ ደስታን የጋራ ማድረግ የተለመደ ነው። ሀዘንና ችግር ሲያጋጥምም እንዲሁ። ይህ አይነቱ ልማድ ደግሞ የጋራ የሚባሉ አጋጣሚዎች በሚከሰቱም ጊዜ ሊተገበር ግድ ይላል። የአንዱ መንገድ ሳይመች ሲቀር የሌላውን አመቻችቶ፣ የሌላው በጎደለበት አጋጣሚ ከአንዱ ወስዶ አሟልቶ ቀንን መልካም ማድረግ ቢጠቅመን እንጂ አይጎዳንም።
አሁን ላይ በአንዳንዶች ዘንድ የሚታየው ማንነት ግን ራስን መውደድና ማክበር ላይ ብቻ ያመዝናል። መደጋገፍ፣ መተዛዘን፣ ለሌላው ማሰብ ይሏቸው እውነታዎች ነውር የሆኑ ያህል እየተገፉ፣ እየተረሱ ነው። ይህን ሀቅ ደግሞ በየጊዜው በምናያቸው አጋጣሚዎች ማረጋገጥ ከጀመርን ቆይተናል።
እንደ እኔ ግን ሁኔታዎችን መጋራት፣ መካፈል፣ ሲባል በደስታ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ሊሆን አይገባም። የመንገዱንም፣ የውሃና መብራቱንም፣ የትራንስፖርቱንም ችግር ችግራችን ልናደርገው፣በእኩል ልንካፈለው ግድ ይለናል።
ልማትና ዕድገት ሲመጣ የጋራ ነው እስከተባለ ወደዚህ መንገድ በሚያደርሱን ጎዳናዎች ስንራመድም አንዳችን ሌላችንን ገፍትረን፣ ቀድመንና መንገድ አቋርጠን ሊሆን አይገባም። መልካም ውጤት ሲገኝ እንደምንጋራው ሁሉ ፈታኝ አጋጣሚዎች ሲገጥሙንም እንደ ዳቦ እኩል ልንካፈላቸው ይገባል። እንዲህ ካደረግን ይዘነው የቆየነው ስምና ማንነታችን ይደምቃል። የመተሳሰብ ልምዳችን ከእኛው ዘንድ ይዘልቃል። ‹‹አበቃሁ!›
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም