የደግነት ጥግ- የመልካምነት ዋጋ

እንደ መነሻ …

ወይዘሮዋ የትናንት ሕይወታቸውን አይረሱም። ሁሌም ልጅነታቸውን ያስባሉ፣ አስተዳደጋቸውን ያስታውሳሉ። ውልደት ዕድገታቸው ሐረር ላይ ነው። ቤተሰቦቻቸው ሀብታም አልነበሩም። ድህነትን ማጣት ማግኘትን አሳምረው ያውቁታል ።

ያኔ ገና ልጅ ሳሉ በብዙ ውጣውረዶች አልፈዋል። ራሳቸውን ለመቻል፣ ቤተሰቦቻውን ለማገዝ ያልሆኑት የለም። በየሰው ቤት እየሠሩ ላዘዟቸው እየተላኩ የልጅነት ጉልበት ከፍለዋል›። የዛኔዋ እንቦቅላ የዛሬዋ የዕድሜ ባለጸጋ ወይዘሮ ወይንሸት ከበደ።

ወይዘሮዋ የአስራ ሁለተኛ ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ አርቀው ማሰብ ያዙ። ልጅ ቢሆኑም እየኖሩበት ካለው ሕይወት የተሻለ ኑሮ እንደሚገባቸው ያውቃሉ። ይህን ሕልም ለማሳካት ባሉበት መቆየትን አልፈለጉም። ወላጅ እናታቸው ሳያዩ፣ ሳይሰሙ ከቤት ወጥተው ራቁ። መጥፋታቸው የታወቀው ውሎ አድሮ ነበር። መንገደኛው እግራቸው ርቆ ተጓዘ። ከቀናት በኋላ ራሳቸውን አዳማ ላይ አገኙት።

የአዳማ ልጅ…

ወይንሸት ቀልጣፋና ተጫዋች ናቸው። ሀገሬውን አውቀው፣ ከበርካቶች ለመላመድ አልዘገዩም። ለሥራ የሚያህላቸው የለም። አዳማ ላይ እንግዳ አይደሉምና ዘመደ ብዙ ሆነዋል። አዛኝና ርህሩህነታቸውን ብዙዎች ያውቁታል።

ልጅነትን ተሻግረው ወጣትነትን ሲጀምሩ ለትዳር ከሚሻቸው ሰው ተገናኙ። የሁለቱም ሀሳብ ቁምነገር ሆነ። ጥንዶቹ ተጋብተው ጎጆ ቀለሱ። እንዲህ በሆነ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ቤታቸው በልጅ በረከት ተሞላ። የመጀመሪያውን ፍሬ በዓይናቸው አይተው ሳሙ።

የወይንሸት ባለቤት የጋራዥ ባለቤት ናቸው። እሳቸውን ላሉ ደንበኞች የመኪኖቻቸው ሐኪም ሆነው ዓመታትን ሠርተዋል። ጋራዡ በርካታ መኪኖች ይጠገኑበታል። በሥሩ ያሉ ሠራተኞች ደሞዝ ተከፋይ ናቸው። ወይዘሮዋ በየቀኑ የሚጠገኑ፣ ጤናቸው የሚፈተሽ መኪኖችን ያያሉ። የባለሙያዎቹ እጆች፣ የደንበኞቹ እርካታና ምስጋና ሁሉ ከእሳቸው ዓይን አይርቅም።

ወይንሸት አሁን የሀያ ሁለት ዓመት ወጣትና የሦስት ልጆች እናት ናቸው። እንደ እማወራ ጎጇቸውን በወጉ ይመራሉ፣ ባለቤታቸውን ያከብራሉ። ከምንም በላይ የእሳቸው የደስታ ምንጭ የሰፊው እጃቸው ሚስጥር ነው። ካላቸው አይሰስቱም፣ የወደቀ ቢያዩ ያነሳሉ፣ የተራበን ያጎርሳሉ፣ ማንም የተቸገረ ቢኖር እሳቸው ፊት ደርሶ አይመለስም። የአቅማቸውን ለግሰው ዕንባውን ያብሳሉ። በትዳራቸው ደስተኛ ናቸው። በሚያደርጉት ሁሉ አይጎድልባቸውም።

የሕይወት ስብራት…

ውሎ አድሮ የወይንሸትን ሕይወት የሚፈትን ታላቅ ኃዘን ቤታቸው ገባ። ባለቤታቸው ሦስት ልጆች ትተውባቸው በድንገት አለፉ። ይህ ጊዜ ለወጣቷ ወይዘሮ የከበደ ሆነ። ራሳቸውን ያልቻሉ ሕጻናትን ለብቻ ማሳደግ አንገዳገዳቸው። እስካሁን የቤት እመቤት ናቸውና የእኔ የሚሉት ሥራ የለም። የመልካም አባወራውን ሞት ተከትሎ ሕይወታቸው ጭንቅ ገባ። የወጣትነት ጫንቃቸው ቤተሰቡን እንደቀድሞ ለመምራት አልቻለም። ስጋት ያዛቸው። ከውሳኔ ደረሱ። ዝቅ ብለው ሊያድሩ ጎንበስ ብለው ሊሠሩ ራሳቸውን አዘጋጁ።

የትናንቷ መልካም እመቤት ሌሎች ዘንድ ሄደው እንጀራ ለመጋገር ጠየቁ። አሠሪዎቻቸው ምጣዱንም እሳቱንም አሳይተው ሊጡን ሰጧቸው። በየቤቱ በርሜል ሙሉ እየጋገሩ እንደ ዳረጎት የሚሰጣቸውን ጥቂት እንጀራ ለልጆቻቸው አጎረሱ። ጥሩ ሕይወት የለመዱት ልጆች ይህ አይነቱን ኑሮ መተዋወቅ አልቻሉም። እናታቸው በጓደኞቻቸው ቤት እንደሠራተኛ መታየታቸው ውስጣቸውን ጎዳው።

አንደኛው ልጅ በዚህ ስሜቱ ቢነካ ትምህርት ቤት እስከ መቅረት ደረሰ። ወይንሸት ለልጆቻቸው አንዲት ዳቦ ያጡበትን ግዜ አይረሱትም። ስለቤተሰቡ በብዙ ፈተናዎች መሐል ተመላልሰዋል። ያን ዘመን አሁን ላይ ሆነው በዕንባ ቢያስተውሱትም ለዛሬ ማንነታቸው ሰበብ ሆኗልና ስለ አጋጣሚዎቹ ምስጋናቸው የላቀ ነው።

ወይንሸት ከብዙ ውጣውረድ በኋላ መበርታት እንዳለባቸው ከራሳቸው መክረዋል። ዛሬ ከባለቤታቸው እጅ የሚገኝ አንዳች ነገር የለም፣ ገቢያቸው ነጥፏል። ጎጇቸው ጎድሏል። በጀመሩት መንገድ ብቻ ሕይወትን ለመዝለቅ አዳጋች መሆኑ እየገባቸው ነው።

ውሎ አድሮ ወይዘሮዋ እጃቸውን የሚያዩ ሕጻናትን በወጉ ለማኖር ምርጫ ያደረጉትን ሀሳብ ዕውን ሊያደርጉት ቆረጡ። ባለቤታቸው ሥራ ላይ ሳሉ ሙያቸውን በጥልቅ ቃኝተዋል። ትናንት ያዩትን ዛሬ ሊቀጥሉበት ግድ ነው። በድካም ቢተጉ ልጆቻቸው ከርሀብ እንደሚያመልጡ ገብቷቸዋል።

መካኒኳ …

አንድ ማለዳ ወይንሸት የሥራ ቱታቸውን ለብሰው ወደ ጋራዡ አመሩ። ለስላሳው እጃቸው ብረት ጨብጦ አያውቅም። ልብሳቸው ፀዓዳ አካላቸው ንጹሕ ነው። ለእሳቸው ይህ ሁሉ እውነት አላስጨነቃቸውም። አሁን ስለልጆቻቸው መልፋት፣ መድከም አለባቸው። መካኒኳ ወይንሸት ሙያውን ጠንቅቀው ያዙት። ከጋራዥ ውለው ቤት ሲደርሱ ለልጆቹ ጉሮሮ ከጓዳ ከማጀቱ ይባክናሉ። ልጆቻቸው እንዳሻቸው በልተው አደሩ። እናት ወይንሸት በላባቸው ፍሬ ‹‹እፎይ!›› ማለት ያዙ። የእናትነት አንጀታቸው ለልጆቻቸው ብቻ አልሆነም። አብሯቸው የኖረው ቅንነት የሌሎችን ውስጠት መቃኘት ጀመረ ።

ወይንሸት በሰፈር መንደሩ ያሉ ችግረኞችን አያልፉም። የተጣለ ሕጻን ቢገኝ ከጉያቸው ነው። ከወደቀበት አንስተው በወጉ ያሳድጉታል። አራስ ሆና የተቸገረች እናት ብትኖር የሚያሻትን ይዘው፣ የጎደላትን ሞልተው ከጎኗ ይገኛሉ። ለታመመ ሰው ደግሞ ምልክታቸው ይለያል። ወርቃቸውን ሸጠውም ቢሆን ለሕክምናው ወጪ ይደርሱለታል።

አሁን ወይዘሮ ወይንሸትና የጋራዥ ሥራቸው አልተለያዩም። ቀኑን ሙሉ መኪኖችን ሲያክሙ፣ሲጠግኑ ይውላሉ። በዚህ ሁሉ መሐል የቤት የጓዳቸውን ጉዳይ አይዘነጉም። ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ፣ ያስተምራሉ። የሙት ልጆች ሲያገኙ ከእሳቸው ልጆች ተለይተው አያድጉም። በአንድ ቤት ውለው ያድራሉ። በአንድ ትሪ በልተው በእኩል ለብሰው ይወጣሉ። ልጆቹ መማር ካለባቸው ወይንሸት ወደ ኋላ አይሉም። ደብተር እስክሪብቶ ገዝተው ከትምህርት ይልካሉ። ከጋራዡ ሙያን ለሚሹትም በራቸው ሰፊና ክፍት ነው።

ጃክሰንና ወይንሸት…

በአንድ ወቅት ወይንሸት እናት አባቱ የሞቱበትን አንድ ጨቅላ ለማሳደግ ከቤታቸው ወሰዱ። ‹‹ጃክሰን›› ይባላል። እሳቸውን ‹‹እናቴ፣ ባላቸውን ‹‹አባቴ›› እያለ እያለ አደገ። ልጆች በፍቅር ቀርበው ወንድሞቹ ሆኑለት። ጃክሰን ለዚህ ቤተሰብ ባዕድ ሆኖ አያውቅም። ከቤታቸው በረከት በእኩል ተካፍሎ የመኖር መብት አግኝቷል። ወይንሸት ስለእሱ ያላቸው ፍቅር ለየት ያለ ነው። ዛሬም በጨዋታ መሐል ስሙን በሰበብ ያነሱታል ።

እንደ ጃክሰን ሁሉ በሕጻንነት ዕድሜው ልጃቸው የሆነው መሐሙድ ቤተሰቡን ሲቀላቀል የተሰጠው መታሰቢያ የባለቤታቸው ስም ነበር ። ‹‹አንተነህ ሳህሉ›› ብለው ይጠሩታል። አንተነህ ወይም መሐሙድ ወይንሸትን የሚያውቃቸው ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። ዛሬ ባለትዳር ነው። ሙያቸውን ተምሮም የጋራዥ ባለቤት ሆኗል። ኤፍሬም የተባለው ያሳደጉት ልጅም ጋራዥ ከፍቶ በተመሳሳይ ታሪክ ላይ ይገኛል።

ወይንሸት ከሁሉም ስለ ጃክሰን ሲያወሩ ልባቸው ይነካል። እሱ አብሯቸው የኖረ ‹‹እኩያዬ›› የሚሉትና ከልጆቻቸው በፊት ያገኙት ልጃቸው ነው። ስለእሱ ብዙ ትውስታ አላቸው። ልጆች ቢወልድ እንደ እናት ሆነዋል። ሚስቱ ብትሞት እንደእህት ከጎኑ ተገኝተዋል። ስለኑሮው ብዙ የታገለው ጃክሰን ዛሬ በሕይወት የለም። ስለእሱ ያላቸው ኃዘንና ትዝታ ግን ዛሬም ከእሳቸው ጋር ዘልቋል።

ወይዘሮዋ የወንዶች ልጆች እናት ናቸው። በአጋጣሚ ሴት ልጅ አልወለዱም። ሴት ልጆችን አሳድገው ግን ለቁምነገር አድርሰዋል። ከነዚህ መሐል አንደኛዋ በፋርማሲስት ሙያ ተመርቃለች። ሱቅ ከፍተውላትም ራሷን ስታስተዳድር ነበር። በአሁኑ ግዜ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከፍለው በሥልጠና ላይ ትገኛለች። ወይንሸት ስለዚች ልጅ ያላቸው ስሜት ከፍቅር በላይ ነው። ደረቅ ጡታቸውን እያጠቡ አሳድገዋታል። ይህ ልዩ ቅርበት በቃል ብቻ አይቋጭም። የግል ሀብታቸውን ከልጆቻቸው እኩል እንድትውርሰ መብቱን ጭምር ሰጥተዋታል።

የወይንሸት አጋጣሚዎች…

ወይንሸት በአንድ ወቅት ዓይናቸው ከአንዲት እናት ላይ አረፈ። ሕጻን ልጇን ከሌሊቱ አስራአንድ ሰዓት ጀምሮ እየጎተተች ስታንገላታው ሲታዘቧት ቆይተዋል። ጠጋ ብለው ‹‹ልጁ ከሚሰቃይ ስጭኝ፣ ላሳድገው›› አሏት። ዓይኗን አላሸችም። ሳታንገራግር ከእጃቸው ላይ አኖረችው።

ሕፃኑን ተቀብለው ቤታቸው ወሰዱ። ልብስ አልብሰው አስገርዘው፣ በወጉ አሳደጉት። አሁን ሦስተኛ ክፍል ደርሷል። በጥሩ ክፍያ ከሚማርበት ትምህርት ቤት ዕውቀት እየቀሰመ ነው።

እንደዚህ ሕጻን ሁሉ በተመሳሳይ ታሪክ ያለፉ የወይንሸት ልጆች ጥቂት አይደሉም። ሁሉንም ከችግራቸው እያነሱ አሳድገዋል፣ አስተምረዋል። በቤታቸው ሳይኖሩ በውጭ የሚረዷቸውም ብዙ ናቸው። ከወይንሸት ቤት ደርሶ ተከፍቶ የሚመለስ የለም። በአቅማቸው ሁሉም በልቶ እንዲያድር፣ ከፍላጎቱ እንዲገናኝ ይተጋሉ።

ወይንሸት ወደ ኋላ መለስ ሲሉ ከራሳቸው አሳዛኝ ታሪክ ጋር ይገናኛሉ። ደጋግመው እንደሚሉት ለዛሬው ማንነት ያበቃቸው ያለፉበት ፈታኝ የሕይወት መንገድ ነው። የዛኔ በጋራዥ መካኒክነት ለአስራ ሰባት ዓመታት ቆይተዋል። ዕድሜያቸው ሲጨምር፣ ሰውነታቸው ሲገዝፍ ደግሞ ጋራዡን ትተው ሆቴል ከፈቱ። የእሳቸው ሆቴል ዋና ዓላማ ችግረኞችን ለመታደግ ነበር። ብዙዎች ከሆቴሉ ሞሰብ ታድመዋል፣ የራባቸው በልተው ጠግበዋል።

የወይንሸት ቀና ዓይኖች ከጎዳና ልጆች ላይ ተነስቶ አያውቅም። ሁሌም ልጆቹን ሲያዩ ውስጣቸው እንደተረበሸ ነው። ከእነሱ በቀረቡ ግዜ የማይታመኑ አሳዛኝ ታሪኮችን ሰምተዋል። ያለዕድሜያቸው የልጅ እናት የሆኑ፣ በሱስ ልማድ የተጎዱ፣ በርሀብ የሚንገላቱ ወገኖች ከልብ ያሳዝኗቸዋል። ለሁሉም ልብስና ምግብ አይነሱም። የተደፈሩትን ለይተው ለሕክምና ያበቃሉ፣ የሕግ ድጋፍ የሚያሻቸውን ለፍትሕ አካል ያደርሳሉ።

ወይዘሮ ወይንሸት ላሳደጓቸው ልጆች ዋስ ጠበቃ ናቸው። ማንም ቢከሰስ፣ በሕግ ቢጠየቅ ፈጥኖ ለመድረሰ የሚቀድማቸው የለም። ለተበዳይ በሽምግልና ካሣ ቢያስፈልግ ገንዘባቸውን አይሰስቱም። አንድ ሁለት ብለው ቆጥረው ይክሳሉ። ልጆቻቸውን መክረው አስታርቀው ይመልሳሉ። በመንገድ የሚያልፉ፣ የተቸገሩ ሰዎች ‹‹እርዱኝ›› እስኪሏቸው አይጠብቁም። ፊታቸውን አይተው ፈጥነው ከቦርሳቸው ይገባሉ። ይህ አጋጣሚ ለታመሙ ሰዎች ከሞት መትረፍ ምክንያት ሆኖ ስማቸውን በምስጋና ያስጠራል።

ወይንሸት የማንኛቸውም ልጆች ቤተሰቦች ሲታመሙ ሰምተው ዝም አይሉም። በታወቁ ሆስፒታሎች ከፍተኛ ወጪ ከፍለው ያሳክማሉ። ቢሞቱ የሚያስቀብሩት እሳቸው ናቸው። ማስተዛዘኑ፣ እንግዳ መሸኘቱ አይጠፋቸውም። ያሳደጓቸው ልጆችና ልጆቻቸው ተጎሳቁለው ቢያዩ አይወዱም። ልብስ ጫማቸውን ይገዛሉ፤ የሚስቶቻቸውን ማጀት ይሞላሉ፡

ሌሎች ስለእሳቸው …

ብዙዎች የዕለት ሥራቸውን ባዩ ቁጥር ያመሰግኗቸዋል፤ ይመርቋቸዋል፤ አንዳንዶች ደግሞ የበዛ ደግነታቸውን አይተው ከሞኝ ይቆጥሯቸዋል። ሌሎች ስለምን ሲሉ ይወቅሷቸዋል። እሳቸው ግን ከእጃቸው አይሰስቱም። በመስጠት ያምናሉ ። በጎ ባደረጉ ቁጥር ጎድሎባቸው አያውቅም። ሁሌም ቤታቸው በበረከት የሞላ፣ የተትረፈረፈ ነው።

በክፉ ቀናት .

በዘመነ ኮሮና ግዜ ወይዘሮ ወይንሸት ለብዙኃን በመድረስ ይታወቃሉ። የዛኔ ጎዳና ላይ የነበሩ ወገኖች ሕይወታቸው ፈተና ላይ ነበር። ወይዘሮዋ ግን ስለእነሱ ዕንቅልፍ አልነበራቸውም። ሌሊቱን ሙሉ ምግብ ሲያዘጋጁ ያድራሉ። ማለዳውን በመኪናቸው ጭነው ለሚገባቸው ሁሉ ያድላሉ። ይህ የክፉ ቀን ውለታ በበርካቶች ዘንድ አይረሴ ትዝታ ነው።

ወይዘሮ ወይንሸት ዕድሜያቸው ለገፋ፣ አቅማቸው ለደከመ ሰዎች ኃዘኔታቸው ይለያል። ሲራቡ ሲታረዙ ማየት ያስከፋቸዋል። ይህ ስሜት ስለነሱ መኖር አብዝተው እንዲጨነቁ አድርጓል። በዘንድሮ ዓመት ለችግረኛ እናቶችና ለአካል ጉዳተኞች በራሳቸው ወጪና ከሌሎች በመለመን የመኖሪያ ቤቶችን ገንብተዋል።

ተመሳሳይ ችግሮች ላለባቸው ቤተሰቦችም ግንባታውን ለመከወን የመሠረት ድንጋይ አስጥለዋል። ከየቦታው ለተፈናቀሉ ወገኖች የወይንሸት እጆች አይሰስቱም። መኪና ሙሉ አልባሳትና ደረቅ ምግቦች አሰባስበው ‹‹ይድረስ›› ሲሉ ለግሰዋል። ለዚህ በጎ ምግባራቸው ከሚመለከታቸው አካላት ዕውቅናን ከምስጋና ተችረዋል።

በወይዘሮዋ ቤት ማንኛውም ድግስ ቢኖር የሚጠራው ሰው አይለይም። ዓውደ ዓመት ቢደርስ ዕለቱ የሁሉም ነው። ማንም በእኩል ተገኝቶ ያለውን ይካፈላል። አንድ ቀን ወይንሸት የልጃቸው ልጅ ልደት ላይ በርካታ የጎዳና ሕጻናትን እንዲታደሙ ጋበዙ።

ኬክ በሚቆረስ ግዜ ብዙዎቹ ሕጻናት ለመብላት ጓጉ፣ ተጣደፉ። የጎዳናዎቹ ልጆች ግን እንደሌሎች አልሆኑም። ኬኩን በግርምታ እያዩ ስለምንነቱ ደጋግመው ጠየቁ። ወይንሸት በሁኔታው አዘኑ። ሁሉም ከዚህ ቀድሞ ኬክ ይሉትን ነገር አይተውት አያውቁም። ይህን መሰል ሐቆች ለወይዘሮዋ ልብ የሚነኩ የየዕለት አጋጣሚዎች ናቸው።

ልጆች እንደ እናታቸው…

የወይዘሮ ወይንሸት ልጆች በእናታቸው ባሕርይ ተቀርፀዋል። ስስትን አያውቁም፣ ለድሀ መስጠትና ማብላት የየእለት ተግባራቸው ነው። የመጀመሪያ ልጃቸው ከእሳቸው ጥግ አልራቀም። በአራት ተሳቢ መኪኖቹ ይተዳደራል። አድርግ ያሉትን ሁሉ ይፈጽማል፣ ሁለተኛው ልጃቸውም የአባቱን ሙያ ተረክቦ ለእሳቸው ዓላማ የተገዛ ነው። ሦስተኛ ልጃቸው ታዛዥና ትሑት ሆኖ ቀኝ እጃቸው ሆኗል።

ሁሉም ዕለተ ዓውደ ዓመትን ቤታቸው አይውሉም። ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ የደንቡን አዘጋጅተው በያሉበት ያደርሳሉ። ወይንሸት በልጆቻቸው ደግነት ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ።

የአስራ ሰባት ልጆች እናት

እጀ ሰፊዋ፣ ልበቀናዋ ወይንሸት ያገዟቸው፣ የረዷቸው ሰዎች በርካቶች ናቸው። ከወደቁበት አንስተው፣ በወጉ አሳድገው ለቁምነገር ያበቋቸው ግን በትንሹ አስራ ሰባት ይሆናሉ። ሁሉም በቤታቸው እያደጉ ራሳቸውን ችለው የወጡ ናቸው። አመጣጣቸው ከየቦታው ቢሆንም የሁሉም እናት ግን ወይዘሮ ወይንሸት ከበደ ናቸው።

በእሳቸው ማንነት ሥር አንድ ሆነዋል። በእሳቸው ፍቅርን ተምረዋል። ቸርነት ደግነትን አውቀዋል። በክፉ ደግ ቀናት ወይዘሮዋ መሰባሰቢያ ታዛቸው ናቸው። ልጆቹም ስለእናታቸው ልዩ ፍቅርና ክብር ይሰጣሉ። ወይንሸት በሀሳብ የሚያግዛቸው ቢኖር ዕቅዳቸው ብዙ ነው። ማንም ተቸግሮ ማየትን አይሹም። ስለበጎነት ያላቸውን ሊሰጡ ዝግጁ ናቸው። በሕይወት ሳሉ እጀ ሰፊው እጃቸው እንዲታጠፍ አይፈቅዱምና።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You