የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብደልአዚዝ አል-ሳዑዲ የኳታሩ ኢሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታሃኒ በሳምንቱ ማብቂያ በሪያድ በሚካሄደው የባህረ ሰላጤው አገራት ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ እንዳቀረቡላቸው የኳታር ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡ የሳዑዲ አረቢያው ንጉሥ ለኳታሩ ኢሚር ያቀረቡት ግብዣ ኳታር ከነዳጅ ላኪ አገራት ድርጅት (Organization of Petroleum Exporting Countries – OPEC) ራሷን እንደምታገልል ይፋ ካደረገች በኋላ የተላለፈ ጥሪ መሆኑ ተንታኞች ጉዳዩን ከብዙ አቅጣጫዎች እንዲመለከቱት በር ከፍቷል፡፡
ይሁን እንጂ ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታሃኒ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚሄዱና እንደማይሄዱ የኳታር ዜና አገልግሎት በዘገባው ያለው ነገር የለም፡፡ ባለፈው ዓመት በኩዌት አስተናጋጅነት በተካሄደው የባህረ ሰላጤው አገራት ትብብር ካውንስል ጉባዔ ላይ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን የተወከሉት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮቻቸውና በሚኒስትሮቻቸው ነበር፡፡
የዘንድሮውን ጉባዔ በተመለከተም የኩዌት መንግሥት ሁሉም የካውንስሉ አባል አገራት ተወካዮች እንደሚሳተፉ ያለውን ተስፋ ገልጿል፡፡ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኻሊድ አል-ጃራላህ የተሳታፊዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅና አባል አገራቱም የካውንስሉን የቆዩ መልካም ተሞክሮዎች አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የንጉሱ ግብዣ ሳዑዲ አረቢያ በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያና በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት እየደረሰባት ካለው ዓለም አቀፋዊ ጫናና ውግዘት ጋር ያያዙት ወገኖችም አሉ፡፡
እነዚህ አካላት እንደሚሉት፣ ሳዑዲ አረቢያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመሆን በየመን በንፁሃን ዜጎች ላይ የምትፈፅመው ግፍ እንዲሁም የአሜሪካ የደህንነትና ስለላ መስሪያ ቤቶች አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ ግድያ እጅቸው እንዳለበት የሚያመለክቱ መረጃዎች ይፋ ማድረጋቸው ሳዑዲ አረቢያን ለበረታ ተቃውሞና ጫና ስለዳረጋት ከኳታር ጋር የገባችበትን ውዝግብ በማብረድ የሚሰነዘርባትን ወቀሳ ማቀዝቀዝ ትፈልጋለች፡፡ ከኻሾጊ ግድያ በኋላ ባለፈው ጥቅምት ወር አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሰልማን የኳታርን ኢኮኖሚ እድገት ማድነቃቸው ከኳታር ጋር ያላቸውን ቁርሾ ለማለዘብ እንደሚፈልጉ ማሳያ ነው ተብሎ መገለፁም የሚታወስ ነው፡፡
ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ባህሬን ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠው ልዩ ልዩ ማዕቀቦችን ከጣሉባት አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ተቆጠሩ፡፡ በግንቦት 2009 ዓ.ም በአረብ ባህረ ሰላጤ ቀጠና ኃያል ናት የምትባለውን ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ግብፅ፣ ባህሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ‹‹ኳታር አሸባሪዎችን እየደገፈች ነው›› የሚል ክስ አቅርበው ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አቋርጠዋል፡፡ ሊቢያ፣ የመንና ማልዲቭስም የነሳዑዲ አረቢያን ፈለግ መከተላቸው ይታወሳል፡፡
ልዕለ ኃያላኗን አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች አገራት ሁለቱን ወገኖች ለማስማማት ያደረጓቸው ጥረቶች ይህ ነው የሚባል የረባ ፍሬ ሳያፈሩ ቀርተዋል፡፡ ኳታርም ሆነች እነ ሳዑዲ አረቢያ አባል በሆኑበት የባህረ ሰላጤው የትብብር ካውንስል (Gulf Cooperation Council – GCC) በኩል የተደረጉት ጥረቶችም አልተሳኩም፡፡ አሜሪካ የባህረ ሰላጤው አገራት ውዝግባቸውን እንዲፈቱ የፈለገችው በቀጠናው ተጨማሪ የፀጥታ ስጋት እንዳትፈጥር እንዲሁም ኳታር ከባህረ ሰላጤው ጎረቤቶቿ ከተገለለች ወዲህ ከኢራን ጋር የጀመረችው ጠንካራ ግንኙነት የትራምፕን አስተዳደር ስላሳሰበው እንደሆነ ይነገራል፡፡
እነ ሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር ለመደራደር ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎችም በኳታር በኩል ተቀባይነት በማግኘት ሳይችሉ ቀርተው የሁለቱ ወገኖች ፖለቲካዊ ሽኩቻና ፍጥጫ ያለምንም መፍትሄ እስካሁን ድረስ ዘልቋል፡፡ ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከል በተለይ የአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያና ዶሃ ውስጥ የሚገኘው የቱርክ ወታደራዊ ሰፈር እንዲዘጉ እንዲሁም ኳታር ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ የሚጠይቁት መደራደሪያዎች ለኳታር መንግሥት ፈፅሞ የማይዋጡ ሆነዋል፡፡
ውዝግቡ እነ ሳዑዲ አረቢያ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲያቋርጡ አገሪቱ ላይ ካቀረቡባት ክሶች የዘለሉ ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉትም የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመው ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፡፡ ታዲያ አገራቱ ወደዚህ ፖለቲካዊ ሽኩቻ ውስጥ ገብተው እንዲህ ረዘም ላለ ጊዜ ይቆያሉ ብለው የገመቱት ወገኖች በጣም ጥቂት ነበሩ፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሁለቱ ወገኖች አለመግባባት የከፋ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል የገመተው መንግሥታቱ ከኳታር ጋር ያላቸውን ፖለቲካዊ ግንኙነት ከማቋረጣቸውም በተጨማሪ በየአገሮቻቸው የሚገኙ የኳታር ዜጎች አገሮቹን ለቀው እንዲወጡ የጊዜ ገደብ ባስቀመጡበት ወቅት ነው፡፡ የሳዑዲ አረቢው ንጉሥ ለኳታሩ ኢሚር ያቀረቡት የሰሞኑ ግብዣ ከአንድ ዓመት በላይ ለዘለቀው የባህረ ሰላጤው ፖለቲካዊ ቀውስ የመፍትሄ መጀመሪያ መሆን የመቻሉ ነገር በውል አልለየለትም፡፡ የመረጃው ምንጮች ፡ ‹‹አልጀዚራ›› እና ‹‹ብሉምበርግ››) ናቸው፡፡
አንተነህ ቸሬ