በቀጣይ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ጤናማ ሕብረተሰብን በመፍጠር የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን የኢንዳስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ታምርት የአስር ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ሚያዚያ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በመግለጫው ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ በ2014 ዓ.ም በይፋ የተጀመረ ሲሆን የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆ የመፍታት እና ዘላቂ የንግድ ትስስር የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው፡፡ ይህንንም ለማጠናከር የ2016 የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ እና የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የሚካሄድ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሩጫ እንደምትታወቀው ሁሉ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚ እንድትሆን የዘርፉ ተዋናዮች አሻራቸውን የሚያስቀምጡበት ዝግጅት ነው ብለዋል፡፡ ውድድሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤታማ ለማድረግ እና ጤናማ ሕብረተሰብን በመፍጠር የአምራች ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑንም አቶ ታረቀኝ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሩጫ ስፖርት ከማሳደግ ባሻገር ፕሮፌሽናል አትሌቶችን በማሳተፍ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የስፖርት ትጥቆችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነታቸውን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት፣ በአምራቾችና በሸማቾች መካከል የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳም አስረድተዋል፡፡
አቶ ታረቀኝ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ የኢትዮጵያ ታምርት 10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በአጠቃላይ ከ10 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ይካፈላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎችም በሁለቱም ፆታ በቅደም ተከተል የ250 ሺህ ብር፣ 150 ሺህ ብር፣ 100 ሺህ ብር፣ 50 ሺህ ብር እና የ25ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትም አስታውቀዋል።
በክለብ ደረጃም ከ1 እስከ 3 የሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ100 ሺህ ብር፣ የ75 ሺህ ብር እና የ50 ሺህ ብር ሽልማት ያገኛሉ ብለዋል። የኢትዮጵያ ታምርት የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ ሁሉም ማኅበረሰብ በመሳተፍ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደረግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተሳትፎና የውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት የሩጫ ውድድር ስኬታማ እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮም የተሻለ ውድድር በተሻለ ሽልማት ለማካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት የጎዳና ላይ ሩጫ ከነበረበት የ5 ኪሎ ሜትር ወደ 10 ኪሎ ሜትር ሲያድግ በተመሳሳይ ሽልማቱም በሁለቱም ጾታዎች ከ100 ሺ ብር ወደ 250 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡
በውድድሩ ዕለትም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተዋናዮች ድርጅታቸውን በመወከል፤ አጋር ድርጅቶች እና ከ 40 በላይ የአትሌቲክስ ክለቦችና መላው የአትሌቲክሱ ቤተሰቦች የሚሳተፉበት መሆኑን አቶ አስፋው አስታውቀው፤ ሩጫው መነሻውን እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ውድድር ከዚህ ቀደም በ2015 ዓ.ም በ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ በእንጦጦ ፓርክ መደረጉ ይታወሳል።
ማህሌት ብዙነህ
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም