በሀገር ፍቅር ስሜት የበጎ አድራጎት ስራን የጀመረው ድርጅት

ዓለማችን ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› ለሚለው አባባል ተገዢ የሆኑና ሰው መሆናቸውን በተግባር የሚያሳዩ በርካታ ሰዎች አሏት፡፡ እነዚህ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ ሰው ለተባለ ፍጡር ሁሉ በጎ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች የእኔ የሚሉት አይኖራቸውም፡፡ ሁሉም የእነሱ እነሱም የሁሉም ናቸው፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር የእምነት አገር ናት በምትባለው ኢትዮጵያ እዚህም እዚያም ይስተዋላል። ኢትዮጵያውያን በጋራ አብሮ የመኖር የቆየ ባህል ያላቸው በመሆኑ መረዳዳት፣ መተጋገዝና መደጋገፍ ጠንካራ ባህላቸው ነው፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መቋቋማቸውም የኢትዮጵያውያኑ አብሮ የመኖር የቆየ ባህላቸው የወለደው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም ወንድም እህቶቻቸውን፤ እናትና አባቶቻቸውን እንዲሁም ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን ጭምር ከወደቁበት አንስተው የነገ ተስፋቸውን ብሩህ ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡

የዕለቱ እንግዳችን ‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› በማለት በሀገር ፍቅር ስሜት ተነሳስቶ ወደ በጎ ሥራ በተሰማራ ቤተሰብ ነው፡፡ ቤተሰቡ ለዓመታት ይኖር ከነበረበት ሀገረ አሜሪካ ወደ ሀገሩ ጠቅልሎ በመግባት በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛሉ፡፡

ቤተሰቡ ከተሰማራባቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች መካከልም በኤች አይ ቪ ኤድስ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች የተዳረጉ ዜጎችን በመደገፍ የሚሠሩት ሥራ አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚሰራው ቤዛ የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተመሰረተ 17 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ በኤች አይ ቪ ኤድስ ሳቢያ ለተለያዩ ችግሮች በተጋለጡ ሴቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ድርጅቱ በተለይም በኤች አይ ቪ ኤድስ ሳቢያ ተስፋ ከቆረጡ ሴቶች ጎን በመሆን ‹‹አይዟችሁ፤ ሁሉም ያልፋል፤ መኖር ይቻላል፤ በርቱ ተበራቱ›› ያለ ድርጅት ስለመሆኑ የቤዛ ኢንተርናሽናል ኮሚኒቲ ዴቨሎፕመንት መስራችና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ባለራዕይ ወይዘሮ ሶፊያ አሰፋ ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ሶፊያ እንዳሉት፤ ድርጅቱ የተቋቋመው በቤተሰብ ነው፤ ሥራውን የጀመረውም በ1999 ዓ.ም ሲሆን፣ ሕጋዊ ፈቃዱን በ2000 ዓ.ም ነው የወሰደው፡፡ እሳቸው ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን አጋር አድርገው የበጎ አድራጎት ድርጅቱን በቤተሰብ ሲያቋቁሙ መነሻ ሃሳባቸው ከውስጥ የመነጨ የአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡ በትምህርት ምክንያት ከሀገር ወጥተው አራት አስርት ዓመታትን ያሳለፉት ወይዘሮ ሶፊያ፤ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አንድም ቀን አገራቸውን ዘንግተው አያውቁም፡፡

ቤተሰቡ አንዱን ቀዳዳ ደፈንን ሲል ሌላኛው ቀዳዳ እያፈሰስ 42 ዓመታትን በባዕዳን ሀገር ሊያሳልፍ ተገዷል፡፡ እሳቸውም ያኔ ስለ አገራቸው የሚሰሙት ሁሉ ያሳምማቸው ነበር፡፡ ከ42 ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ወደ እናት አገራቸው ጠቅልለው ለመምጣት ወቅታዊ ሁኔታው ያስገደዳቸው በመሆኑ ወደ አገራቸው ተመለሱ። በወቅቱ በባዕድ አገር ሆነው ሲያደምጡት የነበረውና በአገሪቱ ውስጥ ያለው ችግር ከወሬ አልፎ ስጋ ለብሶ አይኑን አፍጥጦና ጥርሱን አግጦ ተመለከቱት፡፡ ይህን ጊዜ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ወስነው ሰዎችን ለመርዳት ከውስጥ በመነጨ ፍላጎትና በአገር ፍቅር ስሜት አንድ ብለው ጉዞ ጀመሩ፡፡

ወቅቱ አንድ ትውልድን እምሽክ አድርጎ እንደጨረሰ የሚነገርለት የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የተስፋፋበትና ብዙዎችን የጨረሰበት ወቅት እንደነበር ወይዘሮ ሶፊያ ያስታውሳሉ፡፡ በሽታው በተለይም ወጣቱን ትውልድ በብርቱ የጎዳ በመሆኑ አብዛኛው ወጣት በፍርሃት የተሸበበበትና ቆፈን ውስጥ የነበረበት ጊዜ ነበር። በወቅቱም የመጀመሪያ ሥራቸው ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር መሆን አለበት ብለው በማመን በተለይም ወጣቱን ሰብስቦ ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት አድርገው መስራት ጀመሩ።

‹‹ወጣቱ ከተማረና ግንዛቤ ከተፈጠረለት የገባበትን ችግር መረዳት ይችላል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም የሚፈጠርለትን አጋጣሚ በመጠቀም ራሱን ማዳን ይችላል›› በሚል ዕምነት ወደ ሥራው የገቡት ወይዘሮ ሶፊያ፤ ወጣቶችን አሰባስበው የሚሰጡት ትምህርትም መሰረቱን በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ በማድረግ ለሕይወት አስፈላጊና ገንቢ የሆኑ ትምህርቶችን ይሰጡ እንደነበር ነው ያጫወቱን፡፡ ወጣቱን በስነ ምግባር በማነጽ የሕይወት መርሆዎችን በማስታጠቅ፤ በተለይም ታማኝ ዜጋ እንዲሆንና ለሀገሩ መጸለይ እንዲችል በማስተማር በርካታ ወጣቶችን ከገቡበት ድባቴ ማውጣት እንደቻሉ ይናገራሉ፡፡ መነሻቸውን ወጣቶች ላይ ያደረጉት ወጣቶች ለብዙ ችግር ተጋላጭ ከመሆናቸው ባለፈ የነገ ሀገር ተረካቢ እነሱ በመሆናቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ በእነሱ ላይ መስራት የግድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ ሀገራቸው የተመለሱበት ወቅት ኤች አይ ቪ ኤድስ የተስፋፋበትና አብዛኛውን ወጣት ተስፋ ቢስ ያደረገበት ወቅት እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሶፊያ፤ በወቅቱ ለኤች አይ ቪ ኤድስ የተዳረገው አብዛኛው ወጣት የሚገኘው እንጦጦ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በጊዜው እርሳቸው ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ስፍራው ባቀኑበት አጋጣሚ በርካታ ወጣቶች በፕላስቲክ ቤት ሰርተው ይመለከታሉ። በስፍራው የነበሩት አብዛኞቹ ወጣቶች ወደ ሥፍራው ያቀኑት በእምነታቸው ተስፋ በማድረግ ለመዳን ጓጉተው እና ከቤተሰብ ሸሽተው ነው፡፡ ‹‹በወቅቱ ከወጣቶቹ መረዳት የቻልኩት የመዳኛ አልያም የመሞቻ ቀናቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሶፊያ፣ በርካታ ችግሮችን እንዳሳለፉ ተናግረዋል፡፡

በኤች አይ ቪ ኤድስ የተያዘ ሊታከምበት የሚችል መድሃኒት ምንም አይነት መዳህኒት አለመኖሩም ችግሩን ይበልጥ እንዳወሳሰበው ይናገራሉ፡፡ መገለልና መድሎው ከበሽታው በላይ ወጣቱን እንደጎዳውም ነው የገለጹት። እሳቸው እንዳሉት፤ በጸበል መዳንን ተስፋ አድርገው በእንጦጦ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ደጃፍ የተጠለሉና በፕላስቲክ ቤት ሰርተው የሚኖሩ ከአራት ሺ በላይ ዜጎችን ቦታው ድረስ ሄደው ተመለከቱ፡፡ ከዛም አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው በማመን በመጀመሪያ ወደ እነሱ በመቅረብ የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው በማድረግ ማስተማርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ሰጡ፡፡

በዋናነት መኖር እንደሚቻልና ተስፋ እንዳይቆርጡ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት የጀመሩት በእንጦጦ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በተፈቀደላቸው አዳራሽ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሶፊያ፤ በቦታው ያሉትን ሰዎች በሙሉ ሰብስቦ በማስተማርና የምግብ አቅርቦት ተደራሽ በማድረግ ሥራው መጀመሩን ነው ያስረዱት። እንዲህ እያለ የተጀመረው የበጎ አድራጎት ሥራ ድርጅት በማቋቋም ከማስተማር ባለፈ የተለያዩ ስልጠናዎችን ማለትም የጌጣጌጥ፣ የስፌት፣ የቆዳ፣ የሸክላና ሌሎችም የእጅ ሥራዎችን በማሰልጠን ወጣቶቹ ሥራ መፍጠር እንዲችሉ እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በወቅቱ ሰልጠና ወስደው ወደ ሥራ የገቡት 50 ሴቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ወይዘሮ ሶፊያ፤ ሴቶቹ ድርጅቱ ያመቻቸላቸውን የተለያየ የሙያ ስልጠና እንዲሁም መጠነኛ የሆነ መነሻ ካፒታል ይዘው ወደ ሥራ እንዲገቡና የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ በማድረግ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል፡፡ ራሳቸውን ከመቻል ባለፈም ነገን ተስፋ ማድረግና መኖር እንደሚቻል ማሳያ ሆነው የነገ ተስፋቸውን ብሩህ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡ ውጤታቸው ሌሎች ተስፈኞችን እየወለደና ባለራዕዮችን እየፈጠረ እስካሁን 11 ሺ የሚደርሱ ሴቶች ከድርጅቱ ባገኙት ስልጠናና የገንዘብ ድጋፍ ራሳቸውን ችለው ወጥተዋል፡፡

በአሁን ወቅትም በቤዛ ኢንተርናሽናል የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ሕጻናትን ጨምሮ 200 የሚደርሱ ተገልጋዮች አሉ፡፡ የሚሉት ወይዘሮ ሶፊያ፤ ድርጅቱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ ከክፍለ ከተማው ጋር ይሰራል፡፡ ክፍለ ከተማው በአካባቢው የሚገኙ እገዛና ድጋፍ የሚሹ ሴቶችን መልምሎ የሚሰጣቸው ሲሆን፤ በተለይም በኤች አይ ቪ ኤድስ የተያዙ እናቶችና ሕጻናት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ሲሆን በአብዛኘው ሴቶች ተጋላጭ እንደሆኑም ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሴቶችም የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።

ከዚህ ቀደም የድርጅቱን አገልግሎት አግኝተው እራሳቸውን ችለው የወጡት ዜጎች ጭምር በድርጅቱ እያገለገሉ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሶፊያ፤ በማስተማር፣ ስልጠና በመስጠትና በተለያየ አገልግሎቶች እገዛ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ በተለይም የጌጣጌጥና የእጅ ሥራ ስልጠናዎችን የሚሰጥ እንደመሆኑ የሚመረቱ ጌጣጌጦችና የተለያዩ የእጅ ሥራዎቹ በመሸጥ ገቢ የሚያገኝ እንደሆነም ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ያቀርቡ እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ሶፊያ፤ በአሁን ወቅት ግን መንግሥት ባወጣው ሕግ መሰረት ለውጭ ገበያ አይቀርብም ነው ያሉት፡፡

በድርጅቱ ከሚመረቱት ጌጣጌጦች መካከል ከጥይት ቀለሃ የሚሰሩ የተለያዩ ጌጣጌጦች ማለትም የአንገት፣ የእጅ፣ የጆሮ፣ የእግርና ጌጣጌጦች ይገኙበታል፡፡ ከጌጣጌጥ በተጨማሪም የሸክላ ሥራዎችንና የስፌት ሥራዎችን በተለያየ ዲዛይን እየሰሩ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ የገበያ መዳረሻዎቻቸውም ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ጨምሮ በመሸጪያ ሱቆች እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

ከድርጅቱ ባገኙት የስልጠናና የማማከር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነው የተለያዩ ምርቶችን እያመረቱ በመሸጥ የገቢ ምንጨ አግኝተው ራሳቸውን የቻሉና ነገን በብዙ ተስፋ የሚጠባበቁ በርካታ ውጤታማ ሴቶች ስለመኖራቸው የገለጹት ወይዘሮ ሶፊያ፤ ለእዚህም ሽሮሜዳ አካባቢ ሱቅ ከፍተው ቡና በማፍላት፣ የሸክላ ሥራዎችን አምርተው በመሸጥና በሌሎች ሥራዎች የተሰማሩ ሴቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ሥራውን ሲጀምር ወቅቱ ኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የተስፋፋበትና ሰዎች የሚገለሉበት በመሆኑ በርካታ ችግሮችን እንዳሳለፉ ጠቅሰው፣ የእዚህ ችግር ሰለባዎች አብዛኞቹ ወጣቶች እንደነበሩና ታሪካቸው እጅጉን ልብ የሚነካ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ከዩኒቨርሲቲ የወጡና ቤተክርስቲያን ውስጥ የተሸሸጉ ነበሩ፡፡ የሚላስ የሚቀመስ ሲያጡም ተሸፋፍነው ልመና ይወጡ እንደነበሩም አጫውተውናል፡፡ በወቅቱ ለበሽታው የተሰጠው ስዕል እጅግ በጣም አስፈሪና አስከፊ በመሆኑ ብዙዎች ከድርጅቱ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት በሕይወት ተለይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች በሚገኝ የገቢ ድጋፍ አንዳንድ መድሃኒቶችን በማቅረብም ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን መታደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አሁን ላይ ማኅበረሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ከፍ ያለ በመሆኑ መድሃኒቱ በስፋት ተለምዷል የሚሉት ወይዘሮ ሶፊያ፤ አሁን ጊዜው ተሻሽሏል የሰዎች ግንዛቤ አድጎ የተሻለ ጊዜ ላይ ደርሰናል በማለት ገልጸዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ደግሞ መዘናጋት ተፈጥሯል፤ መዘናጋቱ ችግሩ ካለፈው ጊዜ ባልተናነሰ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆን እያረገው ነው ይላሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ብዙዎች እየተዘናጉ ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱን ማነቃቃትና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ኤች አይ ቪ ኤድስ ዛሬም ብዙዎችን እየጨረሰ ነው፡፡ ሰዎች እጅግ ተዘናግተዋል። መድሃኒቱ ፈዋሽ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህን በመረዳት ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም ጤና ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

በቀጣይ በተለይም ወጣቱ ላይ ሰፊ ሥራ የመሥራት ዕቅድ ያላቸው ወይዘሮ ሶፊያ፤ ድርጅቱ መገናኛ አካባቢ የማገገሚያ ማዕከል እያስገነባ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ በወጣቱ ባህሪና ስነምግባር ቀረጻ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስልጠናዎችን በተለያየ መንገድ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራ በበጎ ፈቃድ ላይ ተመስርቶ የሚሰራ ሥራና ከፍተኛ የሆነ ወጪ የሚጠይቅ እንደመሆኑ መንግሥትን ጨምሮ እያንዳንዱ ግለሰብ የበኩሉን መወጣት ከቻለ ብዙዎች ዘንድ መድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

‹‹መኖር ማለት ለኅብረተሰብ መፍትሔ መሆን ማለት ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሶፊያ፤ ድርጅቱ በሚሰራቸው የበጎ ሥራዎች በተለይም ብዙዎች ከገቡበት ድባቴ ወጥተው ዛሬን መኖር መቻላቸውና ነገን በተስፋ መጠባበቃቸው ከፍተኛ የሆነ የመንፈስ እርካታን እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፤ ይህም አንዱ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እንደሆነና በጎ ማድረግ ለራስ እርካታና ለእግዚአብሔር ብድራት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም

Recommended For You