በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሚካሄደው የስፖርት ውድድር ከዓመታት በፊት መቋረጡን ተከትሎ በየተቋማቱ ያለው የስፖርት እንቅስቃሴ ደብዝዞ ቆይቷል፡፡ አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከዓመታት በኋላ በድጋሚ በኮሌጆቹ መካከል ውድድር በማዘጋጀት ተማሪዎቹ ወደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ በማድረግ ፈር ቀዳጅነቱን አሳይቷል፡፡
ዩኒቨርስቲው በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሉ በርካታ ባለሙያዎችን በተለያዩ ዘርፎች በማፍራት በኢትዮጵያ ስፖርት በማበርከት ላይ የሚገኘው አስተዋፅዖ ትልቅ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ስፖርተኛ ተማሪዎችንም ለማፍራት ዓላማው ያደረገ ውድድር በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል የድረ-ምረቃ አስተባባሪና በፌስቲቫሉ ዐቢይ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር አስጨናቂ ታደሰ ላለፉት 37 ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሎች መካከል ይካሄድ የነበረውን ስፖርታዊ አንቅስቃሴ ደማቅ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር አስጨናቂ፣ በዩኒቨርሲቲው የውስጥ ከውድድሮች ባለፈ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከልም በተማሪዎች በጉጉት የሚጠበቁ የስፖርት ውድድሮች ይከናወኑ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር አስጨናቂ ገለፃ፣ በ1997 ዓም የከፍተኛ ትምህርት የስፖርት ማኅበር ተመሥርቶ የመንግሥትና የግል ትምህርት ተቋማት በውድድሩ እንዲሳተፉ ቢደረግም ከዚያ በላይ መቀጠል አልቻለም፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታትም ውድድሩ በነበረበት ሁኔታ መቀጠል ባለመቻሉ ተቋረጠ፡፡ ምናልባትም በውድድሩ ወቅት በተማሪዎች መካከል ይነሳ የነበረው አለመግባባት እንዲቋረጥ ውሳኔ ላይ ለመደረሱ ምክንያት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ እንደ ሃገር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ሲካሄድ በቆየው ውድድር ላይም በትምህርት ክፍሎች መካከል የውስጥ ውድድር በማድረግ ብቻ ዩኒቨርሲቲውን የሚወክሉ ተማሪዎች ተመርጠው እንዲሳተፉ ይደረግ ነበር፡፡ ይህም ውድድር ሲቋረጥ የስፖርት ውድድሮቹን የሚመራው የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሉ ክለብ በማቋቋም አማራጭ ለመውሰድም ሞክሯል፡፡ በዚህም በእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቮሊቦል ክለቦቹ በፌዴሬሽኖች በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ ሲወዳደር ቆይቷል፡፡ በክለቡ ውስጥም የሚሳተፉት ተማሪዎች አልነበሩም፡፡ ነገር ግን ይህም ቀጣይነት ስላልነበረው የእግር ኳስ ቡድኑ ብቻ ሲቀር ሌሎቹ ፈርሰዋል፡፡
በቅርቡ የዩኒቨርሲቲው አመራር መቀየርን ተከትሎ ግን በድጋሚ የስፖርታዊ ውድድሮችና ፌስቲቫሉ እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ በዚህም ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ12 ኮሌጆች መካከል ተማሪዎችን ብቻ ማሳተፍ ዓላማው ያደረገ ውድድር በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም የእግር ኳሱን ጨምሮ የፈረሱትን የአትሌቲክስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቮሊቦል ስፖርት ክለቦችን በተማሪዎች ብቻ እንዲደራጅና ዳግም ዩኒቨርሲቲው እንዲወከል የታቀደ መሆኑን ዶክተር አስጨናቂ ያስረዳሉ፡፡ ሌላው ዩኒቨርሲቲው በርካታ ካምፓሶች ያሉት መሆኑን ተከትሎ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እስኪመረቁ ባሉት ዓመታት እርስ በእርስ አይተዋወቁም ነበር፡፡ ስፖርት የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ተከትሎም ፌስቲቫሉ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡
በዚህም በፌስቲቫሉ ላይ በጥቅሉ 642 ተማሪዎች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሲወዳደሩ ሌሎች በርካታ ተማሪዎች ደግሞ ለድጋፍ ስለሚገናኙ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ካለባቸው የትምህርት ጫና አረፍ እንዲሉ ያግዛቸዋል፡፡ ከፌስቲቫሉ መክፈቻ አንስቶ ተወዳዳሪዎች እያሳዩ ያሉት እንቅስቃሴና ተነሳሽነት አስደናቂ ሲሆን፤ 12ቱም ኮሌጆች በእግር ኳስ፣ 9 ኮሌጆች በቮሊቦል፣ 7 ኮሌጆች በቅርጫት ኳስ፣ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኮሌጆቹ በየትምህርት ክፍሎቻቸው መካከል ውድድር በማድረግ ወደዚህ ፌስቲቫል የገቡ ሲሆን፤ በነበራቸው አጭር ጊዜ ዝግጅት በማድረግ ወደ ፉክክሩ ገብተዋል፡፡ እንደአጠቃላይ ሲታይም ከሚጠበቀው በላይ አቅም ያላቸውና ዩኒቨርሲቲውን ሊወክሉ የሚችሉ ተማሪዎች እየታዩ ነው፡፡ ይኸውም በቀጣይ ዓመት ከዚህ በበለጡ የውድድር ዓይነቶች ሊሳተፉ እንደሚችሉ አመላካች ነው፡፡
የስፖርታዊ ውድድሮች መካሄድን ተከትሎ አስተናጋጅ አካል ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚያገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ውድድሩ ከሚከናወንባቸው ዋናው የ6ኪሎ ካምፓስ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ እና በቴክኖሎጂ ካምፓሶቹ ያሉት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እድሳት ስለተደረገላቸው ተማሪዎች በብዙ መልክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ተማሪዎች ዘንድ እየተለመደ ያለው ከትምህርት የተረፋቸውን ጊዜ የሚያሳልፉት በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ነው፡፡ በመሆኑም ከአካል እንቅስቃሴ ርቀው የቆዩ ተማሪዎችን ወደ ስፖርት በመመለስ በአዕምሮና በአካል ብቃት የዳበሩ እንዲሆኑ ያግዛቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ፈርቀዳጅ የሆነው ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን በመመልከት ቀድሞ የነበረው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ይካሄድ የነበረው የስፖርት ውድድር እንዲመለስና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችንም ሊያነቃቃ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም መምህሩ ይጠቁማሉ፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም