የኢትዮጵያ እግር ካስ ከሚታሙበት ነገሮች አንዱ የሥነ ምግባር (ዲሲፕሊን) ጉዳይ ዋነኛው ነው፡፡ ከሀገሪቱ ትልቁ የውድድር እርከን ፕሪሚየር ሊግ አንስቶ እስከታችኛው ድረስ ከስፖርቱ ሥነምግባር ያፈነገጡ ብዙ ነገሮች ይታያሉ፣ ይሰማሉ፡፡
በእግር ካሱ በተለይም ትልቅ በሚባለው ፕሪሚየር ሊግ ትልልቅ የዲሲፕሊን ችግሮች መፈጠራቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ሀገርን በትልልቅ መድረኮች የሚወክሉ ተጫዋቾች በሚመረጡበት ሊግ ላይ ዛሬም ድረስ መቀጠላቸው ግን ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ በተለይም ሊጉ የዲ ኤስ ቲቪ ቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እያገኘና ብዙ መሻሻሎች እየታዩበት በሚገኝበት በዚህ ወቅት የሥነምግባር ጉዳይ ትኩረት አለማግኘቱ አስገራሚ ነው፡፡
በተደጋጋሚ ከዲሲፕሊን ግድፈት ጋር በተያያዘ ችግሮችን ሲፈጥሩ የሚስተዋሉት ተጫዋቾች ብቻ አይደሉም፣ ለተጫዋቾች አርዓያ መሆን የሚገባቸው አሠልጣኞችና የቡድን መሪዎች ጭምር ዋና ተዋናይ ሆነው የሚታዩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። የዲሲፕሊን ጉዳይ በፕሪሚየር ሊጉ ምን ያህል አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ የሊግ ካምፓኒው በዘንድሮው የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ዙር ከቅጣት ያገኘው ገቢ መመልከት በቂ ማሳያ ነው፡፡
ሊግ ካምፓኒው በመጀመሪያው ዙር 837 ሺ ብር የቅጣት ገቢ መሰብሰቡን በቅርቡ ባደረገው ግምገማ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ከፍተኛ የቅጣት ገቢ በማስገባት አንደኛ ደረጃን የያዘው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሲሆን፣ ከተከታዩ አዳማ ከተማ በእጥፍ የሚበልጥ ሲሆን ያስገባው ገቢም 259,500 ብር ሆኗል።
በሊጉ እስካሁን ምንም አይነት የገንዘብ ቅጣት ያልተቀጣው ብቸኛው ክለብ ፋሲል ከነማ ነው። ከጥፋት አይነቶች ከፍተኛ ገቢ በማምጣት “መሳደብ” የአንበሳውን ድርሻ ሲወስድ 569 ሺ ብር ማስገኘት ችሏል። በአንድ ጨዋታ ላይ ከአንድ ቡድን “ከ3 በላይ ተጫዋቾች ካርድ በማየት” በሚለው የጥፋት አይነትም እስከ 120 ሺ ብር ቀላል የማይባል ገቢ ማስገባት ተችሏል። በተጨማሪም በመሳደብ ብቻ አወዳዳሪው አካል ከሊጉ ክለቦች 569 ሺ ብር ማግኘት ችሏል፡፡
ይህ የዲሲፕሊን ጉዳይ በሁለተኛው ዙር ፕሪሚየር ሊግም እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ እንደማይገኝ በ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች የተላለፉ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ማሳያ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በ17ኛ ሳምንት የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ያሳለፋው ውሳኔዎች ትናንት ይፋ ተደርገዋል፡፡
በሳምንቱ መርሐ ግብር በተደረጉ ጨዋታዎች አምስቱ በመሸናነፍ ቀሪ ሦስቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 16 ጎሎች በ13 ተጫዋቾች መቆጠራቸውን ያስታወሰው ሪፖርት፣ 46 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ ሦስት ቀይ ካርድ መመዝገቡን ጠቁሟል፡፡ በሳምንቱ በአምስት ተጫዋቾች እና አንድ አሠልጣኝ ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ መተላለፉም ታውቋል፡፡ አቤል አሰበ (ድሬዳዋ ከተማ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያሰጥ ጥፋት በመፈፀሙ በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ሲሆን አንድ ጨዋታ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡ አድናን ረሻድ(አዳማ ከተማ) እና ቢንያም ፍቅሩ(ወላይታ ዲቻ) የተጋጣሚን ተጫዋች በመማታት በቀይ ካርድ ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ሲሆን ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት አራት ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የሦስት ሺ ብር ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል። አስቻለው ታመነ(መቻል) እና ያሬድ ካሳዬ(ኢትዮጵያ መድን) በተለያዩ አምስት ጨዋታዎች የቢጫ ካርድ ማስጠንቀቂያ የተመለከቱ ሲሆን ተጫዋቾቹ ለፈፀሙት ጥፋት አንድ ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ 1500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ እንዲሁም አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ/መቻል/ ክለቡ ከከባሕር ዳር ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ በተጋጣሚ ቡድን አሠልጣኝ ላይ ለፀብ የሚያነሳሳ የሥነምግባር ድርጊት ስለመፈፀማቸው ሪፖርት ቀርቦ አሠልጣኙ አራት ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪም አምስት ሺ ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በሦስት ክለቦች ላይም የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፏል። ከወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች ሄኖክ ኢሳያስ፣ ጌቱ ኃ/ማርያም፣ ዳንኤል ደምሴ፣ አዳነ በላይነህ እና መሳይ ጳውሎስ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች በረከት ግዛው፣ ዮናስ ለገሰ፣ ሐብታሙ ሸዋለም፣ ሱሌማን ሀሚድ እና ኪቲካ ጅማ እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ ሔኖክ አንጃው፣ አቤል አሰበ፣ ሄኖክ ሐሰን እና መሐመድ አብዱላጢፍ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ ሦስቱ ክለቦች በመመሪያው መሠረት አምስት ሺ ብር እንዲከፍሉ ሲወሰን በተጨማሪም ድሬዳዋ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች ድንጋይ ወደ ሜዳ ስለመወርወራቸው ሪፖርት ቀርቦ ክለቡ ሃያ አምስት ሺ ብር እንዲከፍል ተወስኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2016 ዓ.ም