አንድ ሜትር ተኩል እርዝማኔ ያለው እባብ፤ ከሰው ልጅ ሆድ ውስጥ ይቅርና በናሽናል ጂኦግራፊ ላይ እንኳን አለ እንዴ? ሊያስብለንና ሊያስደንቀን ይችላል። ይህ ታዲያ እዚሁ ሀገራችን ውስጥ በጎጃም ብቸና፤ ከአንድ ግለሰብ ሆድ ውስጥ ሲላወስ ወጥቷል ይለናል የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ። በ1951 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ብዙ ጉዳዮቹ ግርምትን የሚያጭሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። መሪዎች በአዲስ አበባ በስብሰባቸው አንበጣን ስለማጥፋት ሲመክሩ፤ የአንበጣ መንጋውም በተመሳሳይ ሰዓት ከበረሃ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ በማድረግ መውጫ መግቢያውን ወረው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፤ የእንስሳቱ ዓለም ዳራ የደረሰበት ሌላ ሆኗል። የሐረርን ጅብ ምን ነካው?…ከሰው አፍ ሥጋን ተካፍሎ እንዳልበላ፤ አሁን አጥሩን ጥሶ በመግባት የታዳጊውን ጉንጭ ቦትርፎታል። “…ወስላቶቹ ተይዘዋል” እነዚህ ወስላቶች እነማን ናቸው? ሁሉም በዛሬው “አዲስ ዘመን ድሮ” ተሰናስነው እናገኛቸዋለን።
የአንበጣ መንጋ መጣ ሲንጋጋ
ትላንት ከሰዓት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ሲያንዣብብ የነበረው የአንበጣ መንጋ የመጣበት “ግልጽ የሆነ ጉዳይ” የተሳካለት አይመስልም። በረሃውን ለቆ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የመጣበት ዋናው ጉዳይ በመናገሻ ከተማው ውስጥ የሚገኘውን የአንበጣ መከላከያ ዋና መሥሪያ ቤት ለመውረር ነበር።
የአዲስ አበባ ቤቶች ሁሉ ጣራቸው የተሸፈነው ተመሳሳይ በሆነ የሻገተ ቆርቆሮ ስለሆነ፤ መሥሪያ ቤቱን ለይቶ ሊያውቀው የቻለ አይመስልም። አንበጣው ከመጣበት ጉዳዮች ሁለተኛው፤ በአፍሪካ አዳራሽ ስለ አንበጣ መከላከያ ይደረግ የነበረውን ጉባኤ ለመቃወም ይመስላል። ዳሩ ግን አንበጣው የደረሰው ጉባኤው ከተበተነ ስለሆነ፤ በጉዞው የተደሰተ አይመስልም።
በፍልውሀ አቅራቢያ በአስፋልቱ መንገድ ላይ አርፎ የነበረውን አንበጣ መኪና ሲፈጨው በአየር ላይ ደግሞ ያንዣብብ የነበረውን፤ የሰማይ አዕዋፍ እየተከታተሉ ይለቅሙት ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙት ሰው፤ መኪናና የባሕር ዛፍ ቅጠል ይዞ በመውጣቱ፤ አገር አቋርጦ የመጣው የአንበጣ ወራሪ የዕለት ምሳውን ሳያገኝ ግራና ቀኝ ተበታትኖ የቀረ ይመስላል።
“ደጅ ያልተከላከሉት ሌባ ከማጀት ይገባ” እንደሚባለው ሁሉ እነሆ አንበጣው እስከ ዋና መሥሪያ ቤቱ ድረስ መጥቷል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 1951 ዓ.ም)
ልጁን ጅብ ነከሰው
ሐረር፤ በ26/8/1951 ዓ.ም ለ27 አጥቢያ ከሌሊቱ በግምት 6 ሰዓት ሲሆን፤ ከኤረር አውራጃ ፖሊስ ጽ/ቤት በስተምዕራብ በግምት 2 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው ዲምቱ ከተባለው ቀበሌ አመድ አብዱላ የተባለውን የኢሣ ሬር ጎሣ ዕድሜው 14 ዓመት የሆነውን ልጅ እበረት ውስጥ ከብቶች መሐል ተኝቶ ሳለ ጅብ አጥሩን ጥሶ ገብቶ በስተግራ ጉንጩ ላይ ነክሶት አንጎሉን በመፈጥፈጥ ከአጥሩ ውጭ ይዞት ሲሔድ በመከታተል በሁለት ጥይት ተኩስ ከጅቡ አፍ ያስጣሉት መሆኑን፤ በመግለጽ ወንድሙ የሆነው ቡህ አብድላ በ27/8/1951 ዓ.ም ከጠዋት በሁለት ሰዓት ላይ ቁስለኛውን በቃሬዛ ይዞ በመቅረብ ስለአመለከተ፤ በፖሊስ ክፍል አስፈላጊውን ሕክምና የተደረገለት መሆኑን የአዳልና ኢሣ አውራጃ ግዛት ፖሊስ ጽ/ቤት በአስተላለፈው ደብዳቤ አረጋግጧል።
ከሰው ሆድ ውስጥ 1 ሜትር ተኩል እባብ ወጣ
በጎጃም ጠቅላይ ግዛት በብቸና አውራጃ በይናጭ ም/ወረዳ ግዛት አራሾች ጊዮርጊስ ከተባለው አገር ውስጥ አበበ ዓለምነህ የተባለ ሰው ከ4 ዓመት ጀምሮ የሆድ ውስጥ ሕመም አድሮበት በሕክምናና በአገር ልምድ መድኃኒት ብዙ ዓመታት ሲያሳልፍ ቆይቶ ሳለ ፤ በያዝነው ወር በዚሁ አውራጃ ደብረ ወርቅ ከተባለው አገር ላይ ጠበል ሲጠጣና ሲጠመቅ ከሰነበተ በኋላ፤ በአራተኛ ቀኑ ቁጥራቸው የበዛ እንደ እንሽላሊት ወይም እንደ ዓሣ መልክ የሆኑ ነፍሳት በሠገራ ከወጡለት በኋላ፤ በመጨረሻ አንድ እባብ እስከነፍሱ ቁመቱ አንድ ሜትር ተኩል የሚሆን ስለወጣ ይህ ተዓምር በዚያው ለተሰበሰቡት በሽተኞች ታይቶ በበትር ተይዞ ከቤተ ክርስቲያን ቀርቦ በእግዚአብሔር ምሕረትና በጠበሉ ፈዋሽነት ነዋሪውና የአካባቢው ሕዝብ የተደነቀበት መሆኑን የብቸና አውራጃ ግዛት በቁጥር 2ሺ ሁለት መቶ 27 ጽፎ በላከው ማስረጃ ተረጋግጦአል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 1951ዓ.ም)
በጫካ ይኖሩ የነበሩት ሦስቱ ወስላቶች ተይዘዋል
የሠላማዊውን ሰው ነፍስ በማጥፋትና እንዲሁም ገንዘብ በመቀማት የሚኖሩት 1ኛ/እሸቴ ዓለሙ 2ኛ/ዘለቀ ባዩህ 3ኛ/ዘነበ አየለ የተባሉ ወስላቶች በአርማጭሆ ወረዳ በጋለገር ም/ወረዳ ግዛት ደዚ ቢሆን ከተባለው ቀበሌ በትውልድ ሀገራቸው ውስጥ የተጠቀሰውን ወንጀል በመፈጸም ሲኖሩ፤ የዚሁ ክፍለ አገር አጥቢያ ዳኛ አቶ ዘሪሁን ገብረየስና የሀገሩ የነጭ ለባሽ ሹማምንቶች እንዲሁም ሕዝቡም ሀሳባቸውን በመደገፍ ወስላቶቹ ሚያዚያ 27 ቀን 1951 ዓ.ም ከበረሃ የከብት እረኞችን ስንቅና እንዲሁም የተላላፊውን ሰው ልብስ እያስወለቁና ገንዘብም መቀማታቸውን ስለተሰማ፤ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ ከተሰበሰበ በኋላ፤ ይገኛሉ ከተባለበት ቦታ ሌሊቱን በዙሪያው ከቦ አድሮ ሲነጋ እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠይቃቸው አንያዝም በማለት ከጉድባ ገብተው ስለተኮሱባቸው መልሰው እሩምታ በመተኮስ አንደኛውን ዘለቀ ባዩህ የተባለውን ወንጀለኛ አቁስለው ሲያዝ፤ እንዲሁም ዘነበ አየለ የተባለውን ሳይቆስል ሁለቱም ከነመሣሪያቸው ተይዘዋል። ሦስተኛው እሸቴ ዓለሙ የተባለው ስላመለጠ አሁንም በመታደን ላይ ሲሆን፤ የተያዙትን ወስላቶች የዚሁ ቀበሌ ሕዝብ በአጥቢያው ዳኛ አማካይነት ቁስለኛውን ተሸክመው ያልቆሰለውን በገመድ ጠፍረው አምጥተው፤ ግንቦት 5 ቀን 1951 ዓ.ም ለአውራጃው ገዥ ሰጥተዋል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 2ቀን 1951ዓ.ም)
አዲስ ዘመን ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም