በዚህ ሳምንት መጨረሻ በሚካሄደው የኒውዮርክ ግማሽ ማራቶን ጀግናው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶታል። በውድድሩ ላይ 11 የሚሆኑ ኦሊምፒያኖችን ጨምሮ በርካታ ድንቅ ችሎታ ያላቸው አትሌቶች እንደሚሳተፉ ታውቋል።
ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች በስፋት በሚፎካከሩበት በዚህ ውድድር 18 የሚሆኑት ግማሽ ማራቶንን ከ1 ሰዓት ከ02 ደቂቃ በታች ማጠናቀቅ የቻሉ ናቸው። ይህም ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የሚደረግበትና የርቀቱ ምርጥ ሰዓት የሚመዘገብበት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። በውድድሩ የሚሳተፉ አትሌቶችም ለፓሪስ ኦሊምፒክ የሚያደርጉትን ዝግጅት የሚለኩበት እንደሚሆን ተጠቁሟል።
አጓጊ በሆነው በዚህ ውድድር በተለይ ምሥራቅ አፍሪካዊያኑ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ኬንያ አትሌቶች ለአሸናፊነት ቀዳሚውን የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል። የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ በተለይ የሳበው የምንጊዜም የረጅም ርቀት ውድድሮች ጀግናው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው።
በመም የ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር ርቀቶች፣ በሀገር አቋራጭ እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች ዘመን የማይሽራቸው ታሪኮችን የሰራው ቀነኒሳ በግማሽ ማራቶን ብዙ ታሪክ የለውም። ዘንድሮ ግን የውድድር ዓመቱን ጅማሬ ኒውዮርክ ላይ በግማሽ ማራቶን በማድረግ ወደ ለንደን ማራቶን የሚሸጋገር እንደሚሆን ታውቋል።
አስደናቂው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በግማሽ ማራቶን ሩጫ ተሳትፎ ብዙም ባይታወቅም በኒውዮርክ ከተማ ሲሮጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። የአራት ጊዜ የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ፣ 16 ጊዜ የዓለም ቻምፒዮናው እንዲሁም በማራቶን ሶስተኛው ባለፈጣን ሰዓት አትሌት ከዚህ ቀደም የነበረው የኒውዮርክ ማራቶን ተሳትፎው ለሩጫው አዲስ እንዳይሆን ያግዘዋል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም እአአ በ2020 በለንደን በተካሄደ ግማሽ ማራቶን ተሳትፎው 1:00:22 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ከፈጣን አትሌቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።
በወቅቱ የለንደን ግማሽ ማራቶንን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ቀነኒሳ፤ በእንግሊዛዊው አትሌት ሞሃመድ ፋራህ ተይዞ የቆየውን ሰዓት በ1 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ ነበር ያሻሻለው። ቀነኒሳ በኒውዮርክ ግማሽ ማራቶን ላይ ከሚሳተፉት አትሌቶች መካከልም የርቀቱን አራተኛ ፈጣን ሰዓት የያዘ ሲሆን፤ ካለው አቅም አኳያ አሸናፊ የመሆን እድሉ ከፍተኛ እንደሚሆንም ይጠበቃል።
የቀነኒሳ ተሳትፎ የውድድሩን ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑን ተከትሎ ፉክክሩም በዛው ልክ ከፍ እንደሚል ተገምቷል። በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች ግን ፈታኝ የሆነ ፉክክር ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ በኩል ከቀነኒሳ ባሻገር ኑሯቸውን በአሜሪካ ያደረጉ ሌሎች አትሌቶችም በውድድሩ የሚሳተፉ ሲሆን፤ በተለመደው መረዳዳት ለውጤታማነት ሊሮጡ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ባለፈው ዓመት ርቀቱን 1:03:05 በሆነ ሰዓት መሮጥ የቻለው አትሌት የኔው አላምረው፤ በውድድሩ ከሚሳተፉት አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። ሌላኛው አትሌት ደስታ ኡቱራ ደግሞ ባለፈው ዓመት ባርሴሎና ላይ 1:04:28 ያስመዘገበና መቀመጫውንም በዚያው በኒውዮርክ ያደረገ አትሌት ነው።
ከብሩክሊን ወደ ማንሃተን በሚደረገው ውድድር ውብ የሆነችውን ከተማ እያቋረጠ መጨረሻውን በሴንትራል ፓርክ ያደርጋል። በዚህም ውድድር የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱን ያገኙት የፈጣን ሰዓት ባለቤቶች መካከል ቀዳሚው ኬንያዊው አትሌት አቤል ኪፕቹምባ ይገኝበታል። በግማሽ ማራቶን ጠንካራ ተፎካካሪነት የሚታወቀው ይህ አትሌት እአአ በ2021 ቫሌንሲያ ላይ ያስመዘገበው 58:07 ሰዓት የግሉ እና በኒውዮርክ ግማሽ ማራቶን ተሳታፊዎች ቀዳሚ ያደርገዋል። ይሁንና አትሌቱ ካለው ታሪክ አንጻር ተፎካካሪ የመሆን እንጂ የማሸነፍ እድሉን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ በርካታ ናቸው።
ሌላኛው የርቀቱ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ታንዛኒያዊው ጋብሬል ጋይ እአአ በ2020 ያስመዘገበው 59:42 የሆነ ሰዓት አለው። ያም ሆኖ አሸናፊነቱ አጠራጣሪ ነው። በዜግነት ትውልደ ኤርትራዊው የኖይዌይ አትሌት ዘሪ ክብሮምም በውድድሩ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሴቶች መካከል በሚካሄደው ውድድር አትሌት ፋንቱ ዘውዴ እና ደሚቱ ሃዋስ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2016 ዓ.ም