‹‹እንሶስላ›› ወይም ‹‹ሂና›› በመባል የሚታወቀው መዋቢያ እንደየአካባቢ መጠሪያው ይለያያል። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ‹‹እንሶስላ›› በመባል የሚጠራ ሲሆን፤ በተለያዩ አካባቢዎች ደግሞ ‹‹ሂና›› በሚል መጠሪያ ይታወቃል። ‹‹እንሶስላ›› በተለይ በሰሜኑ የሀገራችንን ክፍል የሚበቅል ተክል ሲሆን፤ ለመዋቢያነት የሚያገለግለው ስሩ ነው።
የዚህ ተክል ስሩ ተፈቅፍቆ ሞቅ ያለ ውሃ ውስጥ ይዘፈዘፍ እና ሴቶች እጃቸውን ውስጡ በመክተት እንሶስላው ቆዳቸው ላይ እስከሚታይ ድረስ እግራቸውን ሆነ እጃቸውን ይሞቁታል። ይህም በተለምዶውም ‹‹ እንሶስላ መሞቅ›› በመባል ይታወቃል። ‹‹እንሶስላ›› ለሠርግ፣ ለተለያዩ ፕሮግራሞች እና ለበዓላት ወቅት ልጃገረድ እና እናቶች የሚጠቀሙትና እንደ አንድ መዋቢያ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው።
በአሁን ላይ ደግሞ ‹‹እንሶስላ›› ወይም ‹‹ሂና›› በባህላዊ ሆነ በዘመናዊ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል። በተለይ አሁን ላይ ሴቶች እንደአንድ መዋቢያ የሚጠቀሙት የሚያጌጡበት ነው። ‹‹እንሶስላ››ወይም ‹‹ሂና›› በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ሴቶች የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ በኢድ ፣ በኒካህ ወቅት እጅና እግራቸውን ለማስዋብ ይጠቀሙበታል። ይህ ቀደም ባሉት ጊዜያት መዋቢያው በእጅ እና በእግር ላይ ሲሰራ እምብዛም ዲዛይን ባይታይባቸውም፤ አሁን ላይ ግን ዘመናዊ በሆነ መልኩ ‹‹ሂናን›› በተለያየ ዲዛይን የሚሰሩ ባለሙያዎች ብቅ እያሉ ነው።
በሂና ዲዛይን ሥራ ብቅ እያሉ ካሉ ባለሙያዎች መካከል ወጣት ሀያት እሸቱ አንዷ ናት። ሀያት ሙያውን ያገኘችው በስልጠና እንደሆነ ትናገራለች። በቤት ውስጥ ጓደኞቿን ከመስራት ጀምራ በአሁኑ ሰዓት በግሏ የሜክአፕ፣ የሂና እና የጥፍር ስራ ባለሙያ በመሆን ትሰራለች። ሙያውን ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎችም ስልጠና ትሰጣለች፡፡
‹‹ሂና የተሰራች ሴት የተለየ እና ተጨማሪ ውበትን ትላብሳለች›› የምትለው ሀያት፤ ደንበኞቿ ያሉበት ድረስ ወይም ቤት ለቤት በመሄድ የምትሠራ መሆኑን ትናገራለች። በይበልጥ ደግሞ በአሁኑ ሰዓት ያለውን የማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ስራዎቿን በግል ማህበራዊ ገጿ ላይ በማስተዋወቅ ደንበኞች ማፍራት ችላለች።
ሀያት እንደምትለው፤ ‹‹ሂና›› ቀደም ሲል በአብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ሴቶች በኢድ፣ በኒካህ ወቅት ለእጅና እግራቸውን ለማስዋብ ይጠቀሙበታል። ይህ ለሴቶች ብዙም አዲስ ባይሆንም የተለያየ ዲዛይኖችን በመጠቀም እጅ ላይ የሚሳለው የሂና መዋቢያ ግን በአሁኑ ጊዜ በብዙዎች ዘንድ ተለምዶ ሴቶች ለተለያየ ፕሮግራም ለመሰራት የሚመርጡት ነው። ፕሮግራም ባይኖርባቸውም አንዳንድ ሴቶች በአዘቦት ቀንም ይሰራሉ።
በእጅ ላይ የሚሳለው ዲዛይን በአብዛኛው የአበባ ቅርጽ ያለው ሲሆን፤ እጃቸው ወፈር ያለ ከሆነ ሞላ ያለ ዲዛይን፤ ቀጠን ያለ ከሆነ ደግሞ ቀጠን ያለ ዲዛይን መጠቀም ተመራጭ ነው የምትለው ሀያት፤ ‹‹ሂናውን ለመስራት እጅ ላይ የሚሰራ በመሆኑ የሂናው ዱቄት ተበጥብጦ በፕላስቲክ ላይ ከተደረገ በኋላ በተፈለገው ዲዛይን እጅ ላይ ለመስራት ያስችል ዘንድ በጠባቡ ቀዳዳ ይበጅለታል። ከዚያም በምትሰራዋ እንስት ላይ ባለሙያዋ የመረጠችውን ዲዛይን መስራት ትጀምራለች። ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለመደ የመጣ ሲሆን፤ እንደሰዎች ፍላጎት እና ምርጫ አይናቸው ውስጥ የገባውን ዲዛይን ለመሰራት ይመርጣሉ›› ትላለች ።
ሂናው ለመስራት የሚያገለግሉት ግብዓቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚመጣጡ እንደሆኑ የምትገልጸው ሀያት፤ ከስዊድን እና ከሱዳን የሚመጣና በአረብ ሀገራት በስፋት የተለመደ መሆኑን አንስታለች። ሂና የተለያየ ቀለም ያለው ሲሆን፤ አልፎ አልፎም ሴቶች ለጸጉራቸው ይጠቀሙበታል። ጸጉራቸውም ጥቁር፣ ቀይ እና አብረቅራቂ እንዲሆን በማድረግ ተጨማሪ ውበት ይኖረዋል፡፡
የሂናው ቀለም እና ዲዛይን የሚወሰነው የደንበኛዋን ምርጫ መሰረት በማድረግ ነው። የምትለው ሀያት፤ ይሁንና እሷም ከልምዷ በመነሳት የተለያየ አማራጭ ያላቸውን የራሷን ዲዛይን መፍጠር እንደቻለች ነው ያጫወተችን። ዲዛይኑም ቀለል ያለ የሂና ዲዛይን መሆኑን ጠቅሳ፤ አንዲት ሙሽራ ደግሞ ለሠርጓ የምትሰራው የተለየ እንደሆነ ገልጻለች።
‹‹ሂናን›› በእጇ ላይ የተሰራች እንስት ለምትፈልገው ፕሮግራም ከተጠቀመችበት በኋላ እንደልቧ ውሃ መንካት የምትችል ሲሆን፤ ከአምስት ቀን በኋላ በራሱ ጊዜ እየደበዘዘ እና እየለቀቀም ይሄዳል። የሂናን ሥራ በእጅ ላይ መስራት ከግብዓቱ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው ሲሆን፤ አለርጂክ እንዳይኖርባቸው መጀመሪያ ሙከራ ከተደረገ በኋላ ወደ መስራት ይገባል። የእጁን ዲዛይን ሰርቶ ለመጨረስም 30 ደቂቃ ያክል የሚወስድ መሆኑን ነው ሀያት የገለጸችው።
በሥራው ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን፤ አሁንም እየሰራች እንደሆነና ለስራዋ የምትጠይቀው ክፍያም እንደምትሰራው ዲዛይን የሚወሰን መሆኑን ትናገራለች። የምትሰራው ዲዛይን የሚበዛ ከሆነ ዋጋውም ጨምሯል። በተጨማሪም የሚጠየቀው ዋጋ እንደየቦታው እና የውበት ሳሎኑ የሚለያይ ሲሆን፤ እጇን ብቻ የምትሰራ እንስት ከሆነች 250 ብር ብዙ ከሆነ ደግሞ 500 ብር ድረስ የሚጠይቅ እንደሆነም ገልጻለች።
ሙያውን ለመልመድ ሰዎች እስከፈለጉት እና ትኩረት ሰጥተው ከተለማመዱት ለመልመድ ያን ያክል ከባድ እንዳልሆነ የገለጸችው ሀያት፤ በአሁኑ ወቅት የሂና ተጠቃሚ እንስቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው እንደሆኑና ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚመርጡት እንደሆነም ትናገራለች። እሷ እንዳለችው፤ የሂና ሥራ ለብዙ እንስቶች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ቢሆንም የሂና ባህል የአረብ ሀገራት ባህል እንጂ የኢትዮጵያውያን እንዳልሆነ አመላክታለች፡፡
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን መጋቢት 2/2016 ዓ.ም