ማርሽ ቀያሪው የካፒታል ገበያ፤

የካፒታል ገበያ ሲተገበር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን፤ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የተለያዩ ሀገራት የካፒታል ገበያዎች ላይ የባለሙያዎች ስልጠናና የአቅም ማጎልበቻ ድጋፍ የሚሰጠው “ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት” ገልጾ፤ ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ጋርም በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ያወሳል። የካፒታል ገበያ ማለት በአጭሩ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ተዛማች ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ግብይት የሚከናወንበት ቦታ ነው።

ባደጉት ሀገራት በስፋት የሚታወቀውን የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ወደ ሥራ ለማስገባት አዋጅ 1248/2013 ጸድቆና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል። ይሄን ተከትሎም የ’ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት’ ባለሙያ ሳንዲ ራይት፤ ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለመጀመር እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀው፤ “ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለመጀመር እያደረገች ያለችው ዝግጅት ሌሎች ልምድ ያላቸው ሀገራት ጋር እኩል ደረጃ ላይ ሊያስቀምጣት የሚችል ነው ሲሉ አሞካሽተዋል። አያይዘውም በጥንቃቄና በጥብቅ ዲሲፕሊን ከተመራ በኢኮኖሚው ላይ ማርሽ ቀያሪ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲሉ አሳስበዋል።

ለዚህ ነው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ባለፈው ሳምንት የካፒታል ገበያ መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር፣ ግልጽነትን ለማጎልበት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅምን ለማዳበር የሚረዱ ሁለት ስምምነቶችን ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ጋር በዚያ ሰሞን ነው የተፈራረመው። የመጀመሪያው ስምምነት “የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ተአማኒነት ግብረ ኃይል” ስምምነት ሲሆን፤ ስምምነቱም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ እንዲሁም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መካከል የተደረገ ነው።

የስምምነቱ ዓላማ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ህጋዊ እና ከወንጀል ድርጊቶች የጸዳ ለማድረግ በተቋማቱ መካከል ቋሚና ቀልጣፋ ቅንጅታዊ የአሰራር ሥርዓት ለመዘርጋት፤ እንዲሁም ውጤታማ የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመፍጠር የካፒታል ገበያውን ተአማኒነት ማረጋገጥ ነው። በስምምነቱ መሰረትም ግብረ ኃይሉ ማጭበርበር ባለበት ሁኔታ እና በሕገወጥ የአክሲዮን አቅርቦት ላይ የተሰማሩ፣ እና በርካታ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን እንዲያጡ ምክንያት የሆኑ አከስዮን ሻጮችን በመለየት ለፍርድ የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ተመላክቷል።

ሁለተኛው ስምምነት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተደረገ የትብብር መግባቢያ ስምምነት መሆኑን የገለጸው ባለስልጣኑ፤ ስምምነቱ በየኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አጄንሲ፣ የአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት መካከል የተደረገ ነው። ከሳይበር ደህንነት ጋር የተያያዙ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ያካተተው ስምምነቱ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን የገበያ መቆጣጠር እና የኢንቨስተሮችን ደህንነት የመጠበቅ አቅሙን ለማሳደግ ያለመ ነው።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በንቃት ለመከታተል እና ለመቅረፍ እንዲሁም አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፉን ለማሳደግ ባለሥልጣኑ አበክሮ እየሰራ መሆኑን ያመለክታል። እነዚህ ስምምነቶች የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት መካከል አንደኛው እና ዋነኛ የሆነውን የካፒታል ገበያው ተአማኒ እንዲሆን ማድረግ እና መዋቅራዊ የአደጋ ስጋቶችን የመቀነስ አላማ በቀጥታ ከመደገፍም ባለፈ ለኢንቨስተሮች ተገቢውን ጥበቃ ወይም ከለላ ለመስጠት ይረዳሉ።

የካፒታል ገበያ በተለይም በቅርቡ የሚተገበረው  የኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ጋር ተዳምሮ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ከውጭ የሚመጣ የገንዘብ አቅምን በማጠናከርና ቁጠባን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው ሳንዲ ገልጸዋል።በመሆኑም የካፒታል ገበያ ወደ ሥራ ሲገባ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናስ መምህርና የካፒታል ገበያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ታምራት መንገሻ፤ የካፒታል ገበያ በኢኮኖሚው በቂ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር እንደሚያስችል ገልጸዋል። የካፒታል ገበያው ተአማኒነትን፣ ግልፅነትን፣ ብቃትና ቅልጥፍናን ስለሚፈልግ ለዚህም ጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፍ፣ ገበያውን የሚያሳልጥ ብቁ የሰው ኃይል፣ ቴክኖሎጂና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እንደሚያስፈልግ ምሁራኑ ያሳስባሉ።

ስለ ካፒታል ገብያ ከተነሳ አይቀር የ”አዲስ ዘመኑ” ክብረአብ በላቸው፤”የካፒታል ገበያ ምን ተስፋና ስጋት ይዞ መጥቷል?” በሚል ያጠናቀረው ቆየት ያለ ማለፊያ ትንትኔ ብዙ ቁምነገሮችን አስጨብጦኛል። እናንተስ ለምን ይቅርባችሁ። የአክሲዮን ገበያ ማለት ይለናል ክብረአብ፣ አክሲዮኖች የሚሸጡበት እና የሚገዙበት ገበያ ማለት ነው። ሰፋ ብሎ ሲተረጐም ደግሞ “የካፒታል ገበያ” ይባላል። ምክንያቱም የሚሸጡት አክሲዮኖች የካፒታል ምንጭ ስለሚሆኑ ነው።

አክሲዮን የሚሸጠው ለሻጩ ኩባንያ ካፒታል ለማመንጨት ታስቦ ነው። የካፒታል ገበያ ከአክሲዮኖች በተጨማሪ ሌሎች ባለቤትነትንና ባለዕዳነትን የሚገልጹ ሰነዶች የሚሸጡበትና የሚገዙበት ገበያ ነው። በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት የሚያጠናክር የካፒታል ገበያ ‘በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013’ ተቋቁሟል።

በዚህ አዋጅ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ “የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን” መስሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሰነድ መዋዕለ ንዋዮችን በማውጣት የግብይት ሥርዓቱን ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የተሟላ የካፒታል ገበያ ስነ- ምህዳር የመፍጠር ስልጣን ተሰጥቶታል። ኢንቨስተሮችን በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የካፒታል ገበያው ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት።

በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያው መኖሩ የበለጠ ግልጽነት እንዲሰፍንና የኢትዮጵያን የተፋጠነ ዕድገት የበለጠ ለማቀጣጠል የሚያስችል ተጨማሪ ካፒታል እንዲመደብ እንደሚያስችል ብዙዎች ያናሳሉ። ኢትዮጵያ መደበኛ የአክሲዮን ገበያ ሳይኖራት እንኳን፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከአፍሪካ ሀገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ ስለመቀመጧ በማሳያነት በመጥቀስ። ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚያራምዱ ሀገሮች ሁሉ የፋይናንስ መሠረተ ልማትን በአግባቡ ማሟላት ግድ የሚላቸው ሲሆን፣ የአክሲዮን ገበያዎችም የፋይናንስ መሠረተ ልማት ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ መደበኛ የአክሲዮን ገበያ ሳይኖራት እንኳን እጅግ ሰፊ፣ ነገር ግን ብዙ ችግሮች ያሉበት ኢመደበኛ የአክሲዮን ግብይት የደራባት ሀገር እንደሆነች ይገለፃል። የአክሲዮን ገበያው ከመንግሥት የቁጥጥር ማዕቀፍ በእጅጉ ርቆ ወደፊት ቢጓዝም፣ አካሄዱ ግን አደገኛና አግባብነት የሌለው እንደሆነ ይነሳበታል። ከላይ የተዘረዘሩ የተለያዩ ምክንያቶች የኢትዮጵያን የአክሲዮን ገበያ ማቋቋም አስገዳጅና የማያደራድር ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ያደርጉታል። መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ እንዲጀመር መወሰኑ በጣም የሚደገፍ ስለመሆኑ የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለማክሮም ሆነ ለማይክሮ ኢኮኖሚው ብዙ ጥቅም ይዞ የሚመጣ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያግዝ ነው። የአክሲዮን ገበያ ወይም ግብይትን ማቋቋም ግን ጥያቄ የማይነሳበትና ወቅቱ የሚጠይቀው ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ስለመሆኑም እንዲሁ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የምጣኔ ሀብት እና ኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና እናደሚናገሩት፤ ካፒታል ገበያ ማለት አንድ ግለሰብ ገበያ ወጥቶ እንደሚገበያየው ሁሉ የአክሲዮን ገበያ ውስጥ የሼር ባለቤቶች ሼር የሚለዋወጡበት ቦታ ነው። አቶ ክቡር ገና ለአብነት ሲያነሱም የካፒታል ገበያ ሲቋቋም ባንኮች በእጃቸው ያለውን አክስዮን ይሸጣሉ፤ የገንዘብ ልውውጥ የሚካሄደውም ሼር በያዘው ግለሰብ ወይም ድርጅት አማካኝነት ነው። አንድ ሰው የአንድ ባንክ ድርሻ ቢኖረው በፈለገው ጊዜ ሄዶ አትርፎ ይሸጠዋል። እዚህ ጋር ግን መሰመር ያለበት ባንኩ ከመጀመሪያው አክስዮኑን ለባለአክሲዮኖች ስለሸጠው፤ የሽያጭ ሂደቱ በምንም መልኩ ባንኩ ጋር አይደርስም።

ስለዚህ የካፒታል ገበያ ሲቋቋም ሁለት ገበያ ይኖራል ይላሉ። አንደኛው ገበያ መጀመሪያ ድርጅቶች ሼር የሚያወጡት እና የሚሸጡት በአብዛኛው ለኢንቨስትመንት ባንክ እና ትልልቅ ገንዘብ በእጃቸው ያለ የመጀመሪያውን ድርሻ ይይዛሉ። ከድርጅቱ ሼር የገዙት ደግሞ ወደ ሁለተኛው ገበያ ይሄዱና በዚህ ገበያ ለማንኛውም ግለሰብም ሆነ ድርጅት አትርፈው ለመሸጥ በማሰብ ገበያ ላይ ያቀርቡታል።

በአጠቃላይ መታወቅ ያለበት ጉዳይ በሁለተኛ ደረጃ የሚካሄደው የሼር ልውውጥ የተሻለ ነገር ሊያስገኝ ይችላል ወይም ከነጭራሹ ሊታጣ ይችላል። ስለዚህ በጥንቃቄ መካሄድ ያለበት ጉዳይ ነው። በርካታ የሀገር ውስጥ ባንክ እና ኢንሹራንሶች ሲመሠረቱ እና ከምሥረታቸውም በኋላ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ መቆየታቸውን በማስታወስ፤ የካፒታል ገበያን ከዚህ የተለየ የሚያደርገው፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቶ ቁጥጥር እየተደረገበት በግልጽ መገበያየት ማስቻሉ ነው ይላሉ ባለሙያው።

ለሀገሪቱ ምን ይበጃል የሚለውን አቶ ክቡር ገና ሲናገሩ፤ በአብዛኛው አክሲዮን የሚገዛ ሰው አቅም ያለው ነው። በዚህም ሥርዓቱ ገንዘብ ያለውን ነው የሚጠቅመው ይላሉ። ሃሳቡም ገንዘብ ያለው በእጁ ሼር ይዞ ለኢንቨስትመንት ወይም ለንግድ ሥራ በአንድ ነገር ላይ ገንዘቡን ለማዋል በሚፈልግበት ጊዜ በተለይ በእጁ ጥሬ ገንዘብ ከሌለው ድርሻውን አውጥቶ በመሸጥ ገንዘብ እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው። በሚያገኘው ገንዘብም ድርጅቱን ያስፋፋል ወይም ያሰበውን ኢንቨስትመንት ያደርጋል ማለት ነው። የካፒታል ገበያ ሳይንሱም ይሄ ነው። በአብዛኛው ግን ይህ ይሆናል የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው ይላሉ።

ስለዚህ ሂደቱ የራሱ የሆነ አካሄድ አለው። በአንድ በኩል ከውጭ ያሉ ድርጅቶች ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያቋቁሙበት ጊዜ ወደ ሁለተኛው ገበያ ይሄዱ እና ሼር መለዋወጥ ይጀምራሉ። በዚህ ሂደት ሕዝብ ገንዘብን ወደ አክሲዮን በመለወጥ የንግድ እንቅስቃሴው ተሳታፊ ይሆናል። በውጭ ሀገራት አሁን ትልልቅ ድርጅቶች የሚባሉት በተለያዩ ኢንቨስመንቶች ላይ የራሳቸውን ሼር ይገዛሉ። ምክንያቱም ሼራቸው እያደገ ወይም ዋጋው ከፍ እያለ በሄደ ቁጥር ጥቅማቸው እያደገ መሄዱን ስለሚያውቁ ሼር መግዛት ላይ ያተኩራሉ።

በዚህ ሂደት የድርጅቶች አቅም ከፍ እያለ ይሄዳል ብለዋል። ባለሙያው እንደ ስጋት የሚያነሱት፤ የሼር ዋጋው ከፍ እና ዝቅ ሊል የሚችለው በመረጃ ነው። ለአብነት ሲያነሱ አንድ በካፒታል ገበያ የሚገባ ድርጅት ማሟላት ያለበት እና ግዴታዎች አሉ። እነዚህ ግዴታዎችና መመሪያዎች ከሀገር ሀገር የሚለያዩ የተለያዩ መስፈርቶች አሏቸው። እነዚህን ደንቦች እና መመሪያዎች የሚያወጣ፤ የሚያስተዳድር እና የሚቆጣጠር አካል አለ። ግብይቱም በሕዝብ መካከል የሚካሄድ ስለሆነ ከማጭበርበር የጸዳ እንዲሆን ጠንካራ ቁጥጥር ያስፈልገዋል ብለዋል።

ለአብነት ብንወስድ መረጃ ያለው ባለአክሲዮን ድርጅቱ መክሰሩን እያወቀ ሼሩን አሳልፎ ሊሸጠው ይችላል። ይህ እንግዲህ በገዢው ላይ የሚያስከትለው ኪሳራ ስለሚኖር ይህ ከመሆኑ በፊት የሚከለክሉ ሕጎች እና ደንቦች ስላሉ በደንብና መመሪያዎቹ መሰረት ሰዎችን ከኪሳራ መታደግ ይገባል። ሆኖም ወደ ሥራ ከመገባቱ በፊት መጀመሪያ በሥነ ሥርዓት ለሕዝቡ ግልፅ በሆነ መንገድ መቀመጥና ሕዝቡም ዝርዝር መመሪያና ደንቦቹን ሊያውቃቸው ይገባል።

በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ሞላ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ አሁን ባለው ዘመናዊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ የካፒታል ገበያ መምጣት ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። ቴክኖሎጂ ለማሳለጥ እና ኢኮኖሚው በታሰበው ልክ በፍጥነት እንዲያድግ የዚህ ገበያ ሥርዓት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው። ነገር ግን አካሄዱ በደንብ ካልተያዘ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጫና ይዞ ሊመጣ ይችላል ይላሉ። የካፒታል ገበያው መጀመር የካፒታል ፍሰቱ በደንብ እንዲንሸራሸር ያደርጋል።

በተለይ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የካፒታል ፍሰት ያሳልጣል። ይህ ከሆነ ደግሞ ካፒታል የሚፈልጉ የኢኮኖሚ ዘርፎች አስፈላጊውን ግብዓት ያገኛሉ ማለት ነው። በዚህም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አይነተኛ ሚና ይጫወታል። ይህ ሲሆን ደግሞ የተሻለ ዕድገት እና ብልጽግና ይመጣል።ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ የካፒታል እጥረት በመኖሩ የካፒታል ገበያ መፈጠሩ ያለውን የካፒታል ማነቆ ለመቅረፍ በር ይከፍታል። የካፒታል ገበያው መረጃን መሰረት በማድረግ እና በገበያው ውስጥ ያለውን የፍላጎት እና የአቅርቦት እንቅስቃሴ በማየት የካፒታል ዋጋውን ይታመናል፤ የሚቋቋሙ አክሲዮኖች ሁሉ የዛን ጊዜ ዋጋቸው ተመን ይወጣለታል። በእያንዳንዱ ጊዜ ከፍ እና ዝቅ ሊል ስለሚችልም ይህንን ሁሉ የሚቆጣጠር የገበያ ሥርዓት ይኖረዋል ይላሉ።

በየትኛውም የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ መረጃ በጣም ወሳኝ ነው። ብዙ ሀገሮች እድገታቸው የተመሰረተው በካፒታል ገበያ ላይ ነው። ዛሬ አደጉ የምንላቸው አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት የእድገታቸው መሠራት ይህ ነው። ካፒታል አላገኝም ብሎ የተቀመጠ ሰው ሁሉ ወደ ኢንቨስትመንት ስለሚገባ በዚህ ሥርዓት የሚንቀሳቀሰው ካፒታል መጠኑ እጅግ ከፍተኛ ነው። ለማንኛውም ግለሰብ ግልጽ በሆነ መልኩ በምን ያህል ዋጋ/ወለድ እንደሚያገኝ እና ትርፍ እንዲሚሰላለት መረጃው በየደቂቃው ስለሚወጣ ሁሉም በካፒታል ማርኬቱ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት ያድርበታል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You