ኢትዮጵያዊቷ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ንግስት

የእንግሊዟ በርሚንግሃም አስተናጋጅ የነበረ ችበት እአአ የ2003ቱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው ውድድሮች በሴቶች 3ሺ ሜትር የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች፡፡ በወቅቱ በአትሌቲክስ ልምድ ያላት አትሌት ብርሃኔ አደሬ የወርቅ ሜዳሊያውን ስታጠልቅ በአዋቂዎች ምድብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሯን የወከለችው ወጣቷ አትሌት መሠረት ደፋር ደግሞ የነሃስ ሜዳሊያውን ወሰደች፡፡ ይህም በርቀቱ መሠረት የጣለ ድል ነበር፡፡ እስካሁን ከተደረጉት 19 የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናዎች ግማሹ ሜዳሊያ ባለቤቶች ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው፡፡

ቻምፒዮናው የሚካሄድበት ዓመት ወደ ሙሉ ቁጥር መቀየሩን ተከትሎ በቀጣዩ ዓመት (2004) በሃንጋሪ ቡዳፔስት ሲካሄድም እንደቀድሞው ሁለቱ አትሌቶች በድጋሚ ኢትዮጵያን ወክለው ተገኙ፡፡ የአሸናፊነት ግምቱም ከአውሮፓዊያኑ ይልቅ ለኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ያደላ ነበር፡ ፡ አንጋፋዋ አትሌት ብርሃኔ አደሬ ደግሞ በድጋሚ ለድል የታጨች ኮከብ ነበረች፡፡ በውድድሩ ዕለትም የርቀቱ የመጨረሻው ደወል ከመሰማቱ የ20 ዓመቷ ወጣት አትሌት በአስደናቂ ብቃት ተፈትልካ በመውጣት ርቀቱን በበላይነት ልታጠናቅቅ ቻለች፡ ፡ ኢትዮጵያም በቤት ውስጥ የውድድር መድረክ 3ሺ ሜትር ርቀት በአውሮፓዊያን ተይዞ የቆየውን ታሪክ ፍቃ ባንዲራዋን ልትተክል በቃች፡፡ ይህ ወርቃማ ድልም ለመሠረት እና ለኢትዮጵያ ከተመዘገበ እነሆ ባለፈው ሐሙስ የካቲት 8/2016 ዓ.ም 20ኛ ዓመቱን አስቆጠሯል፡፡

ይህ ድል በኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮናዋ መሠረት ደፋር የአትሌቲክስ ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ሊባል የሚችልም ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከወራት በኋላ ይካሄድ በነበረው ትልቁ ስፖርታዊ ውድድር ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድኑን እንድትቀላቀል ያስቻለ በመሆኑ ነው፡፡ በአቴንስ ኦሊምፒክ የሮጠችው 5ሺ ሜትር ሲሆን በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ በማስመዝገብ ተተኪነቷን ማረጋገጥ ችላለች፡፡

በመም ውድድሮች ከ1ሺ500 ሜትር እስከ 10ሺ ውጤታማ ዓመታትን ማሳለፍ ብትችልም ተከታታይ ድል በማግኘት የደመቀችበት ግን የ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ነው፡፡ በዓለም የመድረኩ ታሪክም በርካታ ተከታታይ ድሎችን ማጣጣም ከቻሉ ጥቂት አትሌቶች መካከል አንዷ ልትሆን ችላለች፡፡

እአአ 2006 ሞስኮ አዘጋጅ በነበረችበት የቤት ውስጥ ዓለም ቻምፒዮናም መሠረት የሩሲያ እና ፖላንድ አትሌቶችን አስከትላ በመግባት አሸናፊ ነበረች፡፡ ይህ ዓመት ለአትሌቷ የስኬታማነት ማሳያ ሲሆን፤ ኒውዮርክ ላይ በ5ሺ ሜትር ርቀት 14:24.53 በመግባት የዓለም ክብረወሰንን በእጇ ልታስገባ ችላለች፡፡ በቀጣዩ የቫሌንሺያ የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይም በተመሳሳይ የሀገሯን ልጅ መሰለች መልካሙን ቀድማ በመግባት በድጋሚ የርቀቱ ንግስት ሆናለች፡፡

መሠረት በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ዶሃ ላይ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅም የስፖርት ቤተሰቡን አስደምማለች፡፡ ቀጣዩ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና መዳረሻዋ የቱርኳ ኢስታምቡል ስትሆን፤ አምስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅም የተለመደ ውጥኗ ነበር፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት ጋዜጠኞችና ባለሙያዎችም የመሠረትን አስደማሚ ገድል ለመጻፍ ጓጉተው ሲጠብቁ በኬንያዊቷ አትሌት ሄለን ኦቤሪ የአንድ ሰከንድ ብልጫ የበላይነቷን አሳልፋ ሰጥታለች።፡ የመሠረት የ3ሺ ሜትር የሜዳሊያ ጉዞ በዚህ ቢደመደምም አርቃ የሰቀለችውን ክብረወሰን ግን እስካሁንም አላስደፈረችም፡፡ በአንድ የውድድር መድረክ 4 የወርቅ፣ 1 የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 6 ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በኢትዮጵያ ብቸኛዋ አትሌት ናት፡፡ በዓለም ደግሞ በአንድ ሜዳሊያ ብቻ የምትበልጣትን ሞዛምቢካዊት አትሌት ማሪያ ሞቶላን ተከትላ ትቀመጣለች፡፡ በምትታወቅበት ርቀት ግን መሰል ገድል መፈጸም የቻለ አትሌት አልተገኘም፡፡

ከዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያውን አሳልፋ ለጎረቤት ሀገር ትስጥ እንጂ ቀጣዮቹ ድሎች ግን በተተኪዋ አትሌት ገንዘቤ ዲባባ አማካኝነት የተያዙ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ እአአ በ2014 ገንዘቤ ሁለተኛ ድል ለማጣጣም ተዘጋጅታ የነበረችውን ኬንያዊት አትሌት ረታ በመግባት አሸናፊ ስትሆን፤ ተከታዮቹን ዓመታት (2016 እና 2018) የበላይነቱን ማስመዝገብ ችላለች፡፡ ይህንን ታሪክም ከሮማኒያዋ አትሌት ጋር የምትጋራ ሲሆን፤ ጋብሬላ ዛቦ እአአ ከ1995 እስከ 1999 ባሉት ተከታታይ ቻምፒዮናዎች ባለድል ነበረች፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You