“ፈተና ሁልጊዜ የሚጥል ሳይሆን፤ የሚያጠነክር ነው”ሲስተር መቅደስ ብርሃኑ

ገና ልጅ እያለች ጀምራ ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት ሰዎችን ለመታደግ ትጥራለች፡፡ ይህ የውስጥ ፍላጎቷም አደጋ በበዛበት ቦታ ሁሉ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ ከትምህርት ቤት ጀምራ ለጓደኞቿ ደራሽ በመሆን ሰዎችን ለመታደግ ታደርግ የነበረው ጥረት ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባልደረባ አድርጓታል፡፡

መነሻዋ ተማሪዎች ችግር ሲያጋጥማቸው ፈጥና በመድረስ የመጀመሪያ ደረጃ ርዳታ መስጠት ነው። አደጋው ከፍ ካለና በእርሷ አቅም የሚፈታ ካልሆነ ደግሞ ለመምህራንና በትምህርት ቤቱ ለጉዳዩ ለሚቀርብ ሰው መናገር ይሆናል፡፡ በዚህም ብዙዎችን መታደግ በመቻሏ ደስተኛ እንደሆነች የምትገልጸው የዕለቱ እንግዳችን ሲስተር መቅደስ ብርሃኑ ናት፡፡ ሲስተር መቅደስ፤ ከፈጣሪ በታች ልትበጠስ ያለች ሕይወት እንድትቀጥል ከባዱን አደጋ ተጋፍጣ በእሳት የተቃጠለውን፣ በውሃ ሰምጦ ትንፋሽ ያጠረውንና በተለያየ ችግር ውስጥ ሆነው ለተጨነቁ በመድረስ ተስፋና ደስታ እንዲያገኙ ምክንያት ሆናለች፡፡

ልጅነት

ሲስተር መቅደስ ተወልዳ ያደገችው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሳሪስ አደይ አበባ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ ከተሞች ለአደጋ ተጋላጭነታቸው እጅግ የሰፋ ስለሆነ በርካታ አደጋዎችን በተለያየ አጋጣሚ እያየች፤ እየሰማች አድጋለች፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ለአደጋው የሚሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑን ታዝባለች። በተለይም የሕክምና ባለሙያዎች ሚናን በሚገባ የምትገነዘብበት እድል አግኝታ ነበርና ሐኪም መሆንን አጥብቃ ትሻለች፡፡ አነሳሾቿ ሁለት ነገሮች እንደሆኑም ታምናለች፡፡ የመጀመሪያው ከቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ታሞ ሆስፒታል አስታማሚ ሆና ቆይታለችና የሕክምና ባለሙያዎች እገዛ ምን እንደሚመስል መመልከቷ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አክስቷ የሕክምና ባለሙያ መሆኗን በምታደርጋቸው ተግባራት መሳቧ ነው፡፡ እናም ‹‹እኔ ሳድግና ትምህርቴን ስጨርስ መሆን የምፈልገው የሕክምና ባለሙያ ነው›› እንድትል አስችሏታል፡፡

ሲስተር መቅደስ ህልሟን እንድታሳካ እናትና አባት በእጅጉ ያግዟታል፡፡ የበኩር ልጃቸው በመሆኗም ጓደኛዋና የቅርብ አማካሪዋ ሆነውላታል። ይህ ደግሞ ለሌሎች ሰዎች ያላት ምልከታ ጭምር የተስተካከለ እንዲሆን አድርጓታል፡፡

ትምህርት

ሲስተር መቅደስ ትምህርቷን አሐዱ ያለችው በዚያው በአቅራቢያዋ በሚገኝ ሰኔ ዘጠኝ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ በዚህ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጅ ትምህርቷን እንድታጠናቅቅ ሆናለች፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ ፍሬሕይወት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ በትምህርት ቆይታዋም ባዮሎጂ ትምህርትን ከሁሉም በበለጠ ፈቅዳ የምትማረው እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ምክንያቷ ደግሞ የልጅነት ህልሟ በመሆኑና ከስኬት ያደርሰኛል የምትለው የትምህርት መስክ መሆኑ ነው፡፡

ሲስተር መቅደስ ለታሪክ ትምህርትም እንዲሁ ልዩ ፍቅር ያላት በመሆኑ የተሻለ ውጤት ታስመዘግብ ነበር፡፡ ይሁንና ሁለቱን ትምህርት በአንድነት የምታስኬድበት አጋጣሚ ባለመኖሩ የልጅነት ህልሟ የሆነውን የተፈጥሮው ሳይንስ መርጣ እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትላለች፡፡ መቅደስ በትምህርቷ መካከለኛ ከሚባሉት ተማሪዎች ተርታ የምትሰለፍ ብትሆንም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት ግን አልመጣላትም፡፡ በዚህም በቀጥታ የምትፈልገውን ትምህርት እንዳትማር ሆናለች፡፡

‹‹ፈተና ሁልጊዜ የሚጥል ሳይሆን የሚያጠነክር ነው›› የሚል ዕምነት ያላት ሲስተር መቅደስ፤ ህልሟን ልታሳካ የምትችልበትን መንገድ መርጣ ሜድኮ ባዮ ሜዲካል ኮሌጅን እንድትቀላቀል ሆናለች፡፡ በጠቅላላ የሕክምና አገልግሎት ትምህርትም በዲፕሎማ አጠናቃለች፡፡ ይህ ብቻም አይደለም የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመማር በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ገብታ የትናንቱን ውድቀት በድል አጠናቃለች፡፡ ዛሬም ቢሆን ቀጣይ ክፍለ ጊዜ እንዳለባት ታስባለች፡፡ ማለትም ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪዋን ለመማር እያኮበኮበች ትገኛለች፡፡ በእርሷ እምነት ትምህርት የሚቆም ነገር አይደለም፡፡ ከዘመኑ ጋር አብሮ መዘመንና መቀጠል አለበት፡፡

ከሕክምናው ባሻገርም የአደጋ ሥራ ስልጠናዎችን በተለያየ ጊዜ ወስዳለች፡፡ የቅርቡን እንኳን ብናነሳ የፓራ ሚሊተሪ ወታደራዊና አካል ብቃት የሥራ ላይ የሠራተኞች አቅም ግንባታ ስልጠና አንዱ ነው፡፡

የሥራ ሕይወት

የሕክምና ሥራ እረፍት የማይታወቅበት፤ በዓልና ቤተሰብ የማይባልበት እንዲሁም ማህበራዊ ሕይወትን በአግባቡ መምራት የማይቻልበት እንደሆነ ማንም ይረዳዋል፡፡ በአደጋ ሥራ ውስጥ ሲገባ ደግሞ የበለጠ ለሰው እንጂ ለራሰ የሚሉት ነገር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻርም ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ እናም መቅደስም የሥራ ሕይወቷን የምትቃኘው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ እንደ እርሷ አባባል፤ በአደጋ ሥራ ሕክምና ላይ ያለ ሠራተኛ ሁልጊዜ በተጠንቀቅ የሚንቀሳቀስ ነው። ለምሳ፤ ለቁርስ አልያም ለሌላ ተብሎ የሚቆጠብ ጊዜ የሌለበት፡፡ ሰከንድ ውድ የሆነበት፡፡ እየበሉ ትቶ መነሳት የተለመደበት፤ አለመብላት ያለበት በቁርጠኝነትና ከልብ በመነጨ የአገልጋይነት ስሜት ግድ የሚልበት ነው፡፡

አደጋ ላይ በሕክምናው መስክ መሥራት አንዳንድ ሥራዎች ለእንጀራ ተብለው ብቻ የሚከናወኑ እንዳልሆኑ የምንረዳበትም ነው ትላለች፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሠራተኞች ሦስት ተግባራትን ለይተው መከወን ግዴታቸው ነው፡፡ የመጀመሪያው ሕይወት ማዳን ሲሆን፤ ሁለተኛው የአደጋን መጠን መቀነስ ነው፡፡ ሦስተኛው የሚደርሰውን ጉዳት እንዳይባባስ በማድረግ ኪሳራውን መቀነስ ነው፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ በራሱ ቁርጠኝነትን፤ ትህትናንና ትጋትን ይፈልጋሉ፡፡ ጉዳት ላይ ያለን ሰው ለማዳን የሚያስፈልጉ መሰዋዕትነቶችንም ጭምር ይጠይቃሉ፡፡ አዛኝነትን በቅጡ ማድረግን ከምንም በላይ ያሻል፡፡ ምክንያቱም የራስ ሰዋዊነት ችግር እንዳለ ሁሉ ከአደጋው ተጠቂ እስከ ቤተሰቡ ድረስ በሀዘን የተጎዳ ሰው በዙሪያው ይገኛል፡፡ እናም ይህንን ሁሉ ቻል አድርጎ ለውጤታማነቱ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

የአደጋ ሥራ ወዲያው ውጤቱ የሚታይበት ነው። በዚህም ማዘንም መደሰትም ተከታትለው ሲመጡ ይታያል፡፡ ስለዚህም ሚዛኑን ወደ ደስታው ለማዘንበል ቀድሞ መገኘትን ከምንም በላይ ገንዘብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአደጋ ሥራ የዜጎችን ጤና ለመስጠት የሚያስችል ወርቃማ ጊዜን መግዢያ ነው፡፡ ምክንያቱም ፈጥኖ ሲደረስ መደረግ ያለበት ሁሉ በአግባቡ ይደረጋል። የሰውዬው ጤንነት መመለስ ያስችላል፡፡ በተፈለገው ቦታ ላይ ሆኖ ሆስፒታል እንዲደርስ ያግዛልም ትላለች፡፡

በርግጥም ሲስተር መቅደስ አሁን ያለችበትን የሥራ ቦታ ከመቀላቀሏ በፊት ልክ እንደተመረቀች ሥራ የገባችው በግል ክሊኒክ ውስጥ የጥርስ ሐኪም ረዳት በመሆን ነው፡፡ ለሰባት ወር ያህል በቦታው አገልግላለች። የተሻለ አቅምም ገንብታ ነው ከዚያ የለቀቀችው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ላይ ጥርስን የሚመለከቱ ጉዳዮች ቢመጡ በጥሩ መንገድ እንደምትፈታቸውም ታምናለች፡፡ ከዚያም በተጨማሪ የጠቅላላ አገልግሎት ሐኪም በመሆኗ ሌሎች ጉዳዮች ላይም ጥሩ አቅም እንደገነባች ታስባለች፡፡ በተለይም አሁን ያለችበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በብዙ መልኩ አቅሟን ያዳበረላት እንደሆነም ትናገራለች፡፡

የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ውስጥ በንፋስ ስልክ ቅርንጫፍ የምትሰራው ሲስተር መቅደስ፤ መሥሪያ ቤቱ ጊዜ ወርቅ መሆኑንና የሰውን ሕይወት እንዴት መታደግ እንደሚቻል ያወቀችበት ነው፡፡ እንደስሟ የተቀደሰ ተግባር የምተገብርበትም ቦታ ሆኖላታል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ቦታ እናትን ከልጇ አገናኝታለች፡፡ አባትንም ለልጆቹ ተስፋ እንዲሆን ዕድል ሰጥታለች። ሕፃናት አድገው የሀገራቸው ተረካቢ የሚሆኑበትን መንገድ ጠርጋለች፡፡ በዚያ ላይ ከአንጋፋ ሐኪሞች እግር ስር በመሆኗ የተሻለች ነርስ እንደትሆን ዕድል አግኝታለች፡፡ ፍቅርና ተባብሮ መሥራትንም ልምድ ያደረገችበት ቤት እንደሆነ ታነሳለች፡፡

‹‹የእኛ ሥራ የሰውን ልጆች ሕይወት ከአደጋ መከላከል ብቻ አይደለም›› የምትለው ሲስተር መቅደስ የሀገርና የሕዝብን ሀብት ከውድመት መታደግም ጭምር ነው ትላለች፡፡ ከሕዝቡ ባሻገር የአደጋ መቆጣጠር ሥራውን ለሚሰሩ ሠራተኞችም የቅድመ ሕክምና አገልግሎት መስጠት ሥራቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሃያ አራት ሰዓት በሥራ ላይ ሲሆኑ ሥራው የሚሰራው በሙሉ ፍላጎትና (ጠዋት፤ አድሮ ተቀባይና አዳር) በሚል በተከፋፈለው ጊዜ ነው፡፡

በመሥሪያ ቤቱ ስድስት ዓመታትን ብታስቆጥርም እርሷ ግን ገና መጀመሯ እንደሆነ ነው የምታምነው። ምክንያቱም የሠራተኛው ፍቅር፤ መተባበርና መተጋገዙ እንዲሁም ለሥራ ያለው ትጋት የሚበረታ በመሆኑ ነው፡፡ ሥራው አድካሚ ቢሆንም በአዲስ ጉልበት እንደምታከናውነው የገለጸችው ሲስተር መቅደስ፤ በተለይም ሰዎች ከአሰቃቂው ሕመማቸው ነቅተው ስታይ አምላኳን ከማመስገን ባሻገር የሥራዋን ውጤታማነት ስለምትለካበት ሁልጊዜ ፍስሃ እንዲሰማት እንደሚያደርጋትም ነው ያጫወተችን፡፡

ሲስተር መቅደስ በዚህ የሥራ ጉዞ ሌላም የተገነዘበችው ነገር መኖሩን ትገልጻለች፡፡ ይህም ሴት ልጅ ነርስ መሆኗ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚያሳይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ርህራሄን ከውጤታማ ሥራ ጋር ማከናወን ሲሆን፤ ሴት ልጅ በተፈጥሮ ብልህና ጠቢብ ስለሆነች ነገሮችን አርቆ ማየት ትችላለች፡፡ እናም አደጋ በተከሰተበት ቦታ ላይ ስትደርስ ውሳኔዋን ፍጥነት ባልተጓደለበት

ሁኔታ አሰላስላ ነው ወደ ተግባሩ የምትገባው፡፡ ይህ ደግሞ ውጤቱን የበለጠ ስኬታማ ያደርገዋል፡፡

ለአደጋ ሥራ ሴቶችን መምረጥ እንደ ሀገር የተለመደ አይደለም፡፡ ሥራው በወንዶች ብቻ እንዲሸፈን ይፈለጋል፡፡ በዚህም አብዛኛው ቦታ ላይ ወንዶች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ የምትለው ሲስተር መቅደስ፤ ሴቶች ዕድሉን ካገኙ የማያሳኩት ነገር እንደሌለ የእኛ መሥሪያ ቤት ምስክር ነው ትላለች። በእነርሱ መሥሪያ ቤት ወንድ ሴት ተብሎ የተለየ ሥራ እንደሌለም ታነሳለች፡፡ ሁሉም በተሰማሩበትና በተሰጣቸው የሥራ ድርሻ ላይ ውጤታማ ናቸውም ባይ ናት፡፡ እኔ በሕይወቴ አልችልም የምለው ሥራ የለም። እስከ አሁን የገጠሙኝ የሥራ ጓደኞቼም የሚያበረታቱ መንገድ የሚያሳዩ ለችግሮቼ መፍትሔ የሚፈልጉ ብዙ የተማርኩባቸው ናቸው፡፡ አሁን ለደረስኩበት ደረጃም ትልቁን ምስጋና የሚወስዱት ተቋሙና የሥራ ባልደረቦቼ ናቸውም ትላለች።

«ሥራው በጣም ከባድ ነው። በተለይ አንዳንድ አደጋዎች ከውስጥ የሚጠፉ አይደሉም፡፡ ግን ደግሞ ሥራው የብዙዎችን ሕይወት መታደግ ነውና አንድም ቀን በቃኝ የሚባልበት አይደለም፡፡ ልንተወውና ሌላ ሥራ ልንሰራ የምንችልበትም ዓይነት አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእኛን እጆች የሚሹ ብዙ ሰዎች አሉ። ስለዚህም ምንም እንኳን እረፍት አልባ ቢሆንም ወደነው ልንሰራው ያስፈልጋል፡፡ እኔም ይህንኑ እያደረኩ ነው ያለሁት፡፡ እረፍቴን ሳይቀር ከተማው እንዴት ዋለ? አደጋ የት ነበር? ምን ዓይነት አደጋ ነው የተከሰተው? ሰው ተጎዳ ወይ፤ እገዛው ምን ይመስል ነበርና መሰል ጥያቄዎችን ስጠይቅ እና መገናኛ ብዙኃንን ስከታተል ነው የምውለው» በማለት ለሥራዋ ያላትን ፍቅር ትገልጻለች።

መቅደስ በሥራ ጥንካሬዋና ታዛዥነቷ ከተለያዩ አካላት ሽልማቶች የተበረከተላት ሲሆን፤ እነዚህም ምስክር ወረቀትና ገንዘብ ናቸው፡፡ ከሽልማቶቿ መካከል ዛሬ ድረስ የማይረሷት በመሥሪያ ቤቷ በኩል በ2011 ዓ.ም በምትሰራበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ቅርንጫፍ ከሠራተኞች በአፈጻጸም አንደኛ በመውጣት የተሸለመችው ነው፡፡ የቦሌ ቅርንጫፍ በ2015 ዓ.ም እንዲሁ ሸልሟታልና ትደሰትበታለች፡፡

የተለዩ አጋጣሚዎች

የሲስተር መቅደስ የሥራ ላይ ገጠመኞች በርካታ ናቸው፡፡ ይሁንና ለዛሬ የተወሰኑትንና የተለዩትን አጋጣሚዎች እናንሳቸው፡፡ ከጅማሮዋም እንነሳ። «ከልጅነቴ ጀምሮ የአደጋ ሥራ ላይ መሳተፍ ያስደስተኛል፡፡ እንደምፈታውም አምናለሁ። በዚህም ከተደላደለው የመጀመሪያው ሥራዬ ለቅቄ አሁን ያለሁበትን የተቀላቀልኩት ከባዱን ነገር መጋፈጥ ስለምፈልግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከስሙ አንጻር እንዴት እንደምሰራው ፍራቻ ውስጤ ተፈጥሮ ነበር›› የምትለው ሲስተር መቅደስ፤ ማንኛውም ሰው በሠለጠነበት ሙያ ግዳጁን ይወጣ ዘንድ ግድ ነውና ሲስተር መቅደስም የሠለጠነችውን አደጋን የመከላከል ትምህርት በተግባር የምትቀይርበት ጊዜ ደረሰ፡፡ እሷም የጓጓችለት ቀን ነበርና ስምሪቱ ሲመጣ ከመቅጽበት ተነስታ ሄደች። ይህም የመጀመሪያ ገጠመኟ የሚጀምርበት ሲሆን፤ የማዋለድ አገልግሎት የሚሰጥበት ነው፡፡

ብቻዋን ስትላክ ይህ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ እናት በእርግዝና ወቅት ላይ ሆና የሚያጋጥማት ችግር ካለ መፍትሄ የመስጠቱ ሥራ የእነርሱ እንደሆነ ታውቃለች፡፡ ይህም በመጀመሪያ ስምሪቷ የገጠማትና ሁልጊዜ የምታስታውሰው ነው፡፡ አንድ እናት የመተንፈስ ችግር ያጋጠማት በመሆኑ አምቡላንሳቸው ውስጥ ገብተው የተባለበት ቤት ሲደርሱ የገጠማቸው ከአቅማቸው በላይ እንደነበር ተረዳች፡፡ ጉዳዩ እናትን ወይም ልጅን ማትረፍ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ማትረፍ ግዴታቸው እንደሆነ ወሰኑ፡፡ ፈጥነው መድረሳቸው ደግሞ ለዚህ እንደሚያግዛቸው አምነዋል፡፡ ስለዚህም ያንን ምርጫ በማድረግ ወደ ሕክምና አገልግሎቱ ገቡ። እንዳሰቡትም ሆስፒታል ሳይደርሱ ከአምቡላንሱ ላይ እያሉ የእናትን ትንፋሽ መልሰው ልጇን በሰላም ከእቅፏ አስገቡላት፡፡

ሌላኛው ገጠመኟ ደግሞ በንፋስ ስልክ ላፍቶ አካባቢ አንድ ሰው ውሃ ውስጥ ገብቶ ከላይ ልብሱ ይታያል፡፡ ሆኖም ይቆይ አይቆይ የሚታወቀው ነገር የለም፡፡ በዚያ ላይ ቦታው አይደለም ልምዱ ለሌለው ልምዱ ላላቸው ሰዎች አስቸጋሪ ነበር፡፡ የውሃው ኃይል ተወርዋሪና የሚያስፈራ ነው፡፡ በዚያው ልክ ያንን ሰው እየታየ አለማውጣት ደግሞ ሥራን እንዳለመሥራት ይቆጠራል፡፡ በዚህም ሁሉም ወደ ውሃው እንዲጠጉ አደረጋቸው፡፡ ጠላቂዎች ቢገቡም ሕክምናውን የሚሰጡትም ሊያርፉ አልቻሉም። የሰውዬውን ነብስ ለማትረፍ እንዲህ አድርገው እያሉ አስተያየት መስጠቱን ተያይዘውታል፡፡ ይህ ቅጽበት ግን የእነርሱን ሕይወት ጭምር ሊቀጥፍ ተቃርቦ ነበር፡፡ ሳያስቡት የማይወጡት ውሃ ውስጥ ሊከታቸው ሲል ጠላቂው ሠራተኛ አንቅቷቸው ተረፉ፡፡ ሰውዬው ግን አልተረፈም፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ የአደጋው ክብደት አዕምሯችንን ስለሚቆጣጠረው እሳትም ሆነ ውሃ ውስጥ አለያም ሌሎች አደጋዎች ውስጥ ጠልቀን መግባታችን አይቀሬ ነው፡፡ ከአደጋው መካከል ሆነን ጭምር አገልግሎት መስጠት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ስለሚፈጠሩም ከእነዚህ ነገሮች ይሸሻል ተብሎ መገመት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ዋና ሥራችን ስላልሆነና እኛ የምንሄድበት ምክንያት ስላለው ብዙ ጊዜ ወደ አደጋው እንድንገባ አይፈቀድልንም። ከባሰ ግን መሆኑ አይቀርም፡፡›› የምትለው ሲስተር መቅደስ፤ እዚሁ ንፋስ ስልክ ላፍቶ አካባቢ የገጠማትን ሌላኛውን ታሪክ እንዲህ ስትል አጫውታናለች፡፡

ከፍተኛ ዝናብ ጥሎ አካባቢው ተጥለቅልቋል። መኪና ጭምር የላይ ኮፈኑ ካልሆነ በስተቀር አይታይም፡፡ ስለዚህም እርሷና መሰል አጋሮቿ ፈጥነው የሚደርሱበትን ጥሪ ተቀብለው በመፋጠን ላይ ናቸው፡፡ እናም መድረሻ ጊዜ እንኳን ተመድቦላቸው ስለሚንቀሳቀሱ የውሃውን ሁኔታ በሚገባ አላስተዋሉትም፡፡ ከእኔ ሌላው ሰው ይቀድማል የሚል መርህ አላቸውና በቀጥታ ቦታው ላይ ሲደርሱ የሚችሉትን ነገር ለማድረግ ነበር ዘለው የገቡት፡፡ እንዳሰቡትም ሁሉም የየድርሻቸው ሥራ ነበረና ውሃ ጠላቂው ገብቶ ሲያወጣ እነርሱ ደግሞ አየር መስጠቱን ተያያዙት፡፡ በርካታ ስለነበሩ በጊዜው ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ተቸግረዋል። ከጸሎት ጋር ሥራቸውን በፍጥነትና ባለቻቸው ደቂቃ መጠቀም ጀመሩ፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር ተጨምሮበት ማንም ሰው ምንም ሳይሆን መታደግ ችለዋል፡፡ ይህም በሕይወቷ እስካሁን የህሊና እርካታ አገኘሁበት የምትለው ጊዜ እንደነበር ታወሳለች፡፡

ሲስተር መቅደስ ሥራዋ ሁሉ በአዕምሮዋ የተቀመጠና የዘወትር እንቅስቃሴዋ እንደሆነ የምታስታውስበትም ሌላ ገጠመኝ አላት፡፡ ይህም አንድ ቀን ከከተማ ወጣ ብላ ባለችበት ያደረገችው ትዝታ ነው፤ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከጓደኞቿ ጋር እየተዝናናች ነበር፡፡ ጥሩ ተመስጦ ላይ ናቸውም፡፡ ሆኖም ድንገት የአምቡላንስ ድምጽ ከሩቅ ሰማች፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የእሳት አደጋ መኪና ሲጮህ ከጆሮዋ ድምጹ ገባ፡፡ ወዲያው ነበር ሁሉንም በሚያስደነግጥ መልኩ ከመቀመጫዋ የተነሳችው፡፡ ጓደኞቿ ባይዟትና ባያስቀምጧት ኖሮ ሩጫዋን ልትነካው ነበር፡፡ ሆኖም ሁሉም መሥሪያ ቤት አይደለሽም ሲሉና ሲስቁ እንዲሁም ከጎኗ ያለችው እንቅ አድርጋ ስታስቀምጣት ነው ነገሩን ያረጋገጠችው፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በተደጋጋሚ ይገጥሟት እንደነበረም አጫውታናለች፡፡

መልዕክት

ማንም ሰው በተፈጥሮው ጎዶሎ አይደለም። እኩል ማሰብና ማመዛዘን ይችላል፡፡ ከዚህ አንጻርም ሴቶች ማሰብ ያለባቸው ጾታቸውን ሳይሆን በተሰጣቸው ዕድል ምን ያህል ተጠቅሜበታለሁን ነው፡፡ ተፈጥሮ የቸረችኝን ዕድል በምን ያህል ተረድቼዋለሁም ማለት አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ሁልጊዜ ራሳቸውን ከዘመኑ ጋር ለማወዳጀት መሞከር ይገባቸዋል፡፡ ያንን ሲያደርጉ ማህበረሰቡን መጋፈጥ ይችላሉ፤ አይችሉም የሚሏቸውን አካላት ይችላሉ ወደሚለው እሳቤ ያስገባሉ፡፡ ለአብነት የአደጋ ሥራ ለወንዶች ብቻ የሚተው ቢሆንም አሁን አሁን ሴቶችም ውጤታማ የሚሆኑበት ተግባር እንደሆነ እየታመነ መጥቷል፡፡ በተለይም በእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ውስጥ፡፡ ሁልጊዜ የምመክረው ሴቶች በምንም መልኩ ራሳቸውን ዝቅ አያድርጉ፤ እንደሚችሉ ለማሳየት ይጣሩ፤ ራሳቸውንም ያብቁ የሚለውን ነው ትላለች፡፡

‹‹አደጋ በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ውስጥ ታዝሎ የሚጓዙት ድንገተኛ ክስተት ነው፡፡ በሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ፤ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቶችና መሰል ተግባራት ድንገት ሊፈጠር የሚችል ነው። በዚህ ደግሞ ብዙዎችን ልናጣቸው እንችላለን፡፡ እናም ይህ እንዳይሆን አፋጣኝ ሕክምናን የሚሰጡ ሰዎችን ማፍራት ያስፈልገናል፡፡ ሥራውን ወደውት የሚሰሩትን ባለሙያዎችም ማብዛት ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት አደጋ በስፋት የሚከሰትባቸው ናቸው። ሆኖም በድንገተኛ አደጋ የሰለጠነ ባለሙያ እጅግ አናሳ ነው፡፡ በድንገተኛ አደጋና በሰብዓዊ ርዳታ በኩልም የምንሰራቸው ተግባራት በብዙ መልኩ ሕዝቡ ላይ የሚደርሱ አይደሉም፡፡ ስለሆነም በትኩረት ሊሰራባቸው ያስፈልጋል›› የሚለው ደግሞ ሌላው መልዕክቷ ነው፡፡

በእሷ የሥራ ሕይወት ውስጥ ልዩ ነገር ነበር ብላ የምትወስደውና ሊተኩርበት ይገባል የምትለው ሌላኛው ነገር ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ የሥራ መደራረቡን ጉዳይ ነው፡፡ ማለትም አንድን ሥራ ሠርተው ሌላኛው የሚመጣው በቆሙበት ቅጽበት ነው፡፡ ፋታ የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስረዳው አደጋ በሁላችንም እጅ ላይ ያለ መሆኑን ነው፡፡ እናም አደጋን ማጥፋት ባይቻልም መቀነስ ላይ መሥራት የግድ ነው የምትለው ሲስተር መቅደስ፤ በተለይም እንደ እኛ ቦታው ላይ ያለ ሰው በቻለው ልክ ቅድመ መከላከል ላይ መሥራት አለበት፡፡ ስለአደጋ ምንነት የሰለጠነውም ያየነውም ተቀራራቢ በመሆኑ ከቅርባችን ጀምረን ዜጎቻችንን በአደጋ መከላከል ተግባር ማሰልጠንና ግንዛቤ መፍጠር ይኖርብናል፡፡

አደጋ አማክሮ የማይመጣ ከመሆኑ አንጻር እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሀገር ብዙ ግንዛቤን ሊጨምሩ የሚችሉ ተግባራት መሠራት ያለባቸው ይኖርባቸዋል የሚለውም ሌላው መልዕክቷ ነው፡፡ በመጨረሻም ከተማችን አድጋለች፤ ግንባታው ጨምሯል። ነገር ግን ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። የምትለው ሲስተር መቅደስ፤ ከሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ጀምሮ ተቋሙ ሀገርን እንዲሸፍን ከማድረግ አንጻር ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ እናም እንደ ሌላው ዓለም በዘመናዊ መሣሪያ የተደራጀ ተቋም ማፍራት ላይ ቢሰራ መልካም ነው፡፡ ኅብረተሰቡም የእሳት አደጋ መኪና እየጮኸ ሲመጣ ከመከተል ይልቅ ቅድሚያ ለመስጠት ቢሞክር መልካም እንደሆነም መክራለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You