ከጎንደር – ሸገር ከዱባይ – እስከ ኢተያ

ልጅነትን በትዝታ…

ገጠር ተወልዳ አድጋለች። ጎንደር አካባቢ ከምትገኝ አንዲት አነስተኛ ቀበሌ። ቤተሰቦቿ መልካም ምግባር አላቸው። ልጆች በሥርዓት እንዲያድጉ፣ በበጎ እንዲቀረጹ ይሻሉ። ይህ መሻታቸው ሀብታም ገዝሙን በጨዋነት እንድትቀረጽ አስችሏታል።

ሀብታም ለቤተሰቡ ሁለተኛ ልጅ ነች። በቤቱ እንደማንኛውም የገጠር ልጆች የራሷ ድርሻ አላት። የታዘዘችውን ትሠራለች። የተባለችውን ትፈጽማለች። ወላጅ አባቷ በአካባቢው መልካም የሚባሉ ሰው ናቸው። ይህ እውነት በልጆቻቸው ማንነት ላይ አርፏል። ሁሉም ልጆች በትምህርት አልፈው ለሀገር እንዲበጁ፣ ለራሳቸው እንዲ ጠቅሙ ይ ሻሉና ያ ስተምሯቸዋል።

ሀብታም ከተወለደችበት ገጠር ወጥታ ለጥቂት ጊዜያት ጎንደር ከተማ ኖራለች። ዕድሜዋ አስራ ሶስት ዓመት ሲሞላ ግን ሁኔታዎች ምቹ አልሆኑም። ቦታውን ልትለቅ ተገደደች። ሀገሯን ለቃ፣ አካባቢውን ትታ አዲስ አበባ ገባች።

አዲስ አበባ

ሀብታም በወቅቱ ያጋጣማት ጉዳይ የራሷ ምስጢር ነው። ዛሬ ላይ ‹‹እንዲህ ሆነብኝ›› ብላ ማስታወስን አትሻም። በአስራ ሶስት ዓመቷ አዲስ አበባ ስለመምጣቷ ግን ትናገራለች። የዛኔ በዕድሜ ትንሽ ልጅ ነበረች። ይህ ጊዜ ከእናት ጉያ የማይርቁበት፣ እንክብካቤን የሚሹበት ነው። ክፉ ደግን መለየት ቢቻልም በልጅነት፣ ከቤተሰብ ሲራቅ ናፍቆት ትዝታው ሊያስከፋ፣ ሆድ ሊያስብስ ይችላል።

ሀብታም በዚህ ዕድሜዋ ከወላጆቿ፣ ከእህት ወንድሞቿ ካደገችበት ሰፈር ራቀች። አዲስ አበባ ስትገባ የቅርብ ቤተሰቦች ተቀበሏት ። ልጅነቷ ቀጠለ። እንደማንኛውም የአዲስ አበባ ልጅ ጨዋታውን ቡረቃውን አላጣችውም። ዕድሜዋ ከፍ ማለት ሲይዝ ራሷን ለመቻል ሞከረች።

በንግዱ ዘርፍ፣ በግሏ እየሮጠች የሥራን ክቡርነት፣ ገንዘብ የማግኘትን ጥቅም አወቀች። ከዚህ በኋላ ሀብታምን ከፍጥነቷ የሚገታት አልተገኘም። ርቃ እያሰበች፣ ነገዋን አቀደች። ይህ ትልሟ በአዲስ አበባ ብቻ አልወሰናትም። ትዳር ይዛ ጎጆ እንደወጣች ስለወደፊት ሕይወትና ኑሮ ከትዳር አጋሯ መከረች።

የጥንዶቹ ምክር በአንድ ሃሳብ ተቋጨ። ከአዲስ አበባ ርቀው አርሲ ‹‹ኢተያ›› ከተማ ላይ ሊኖሩ ተስማሙ። ኢተያ የባለቤቷ የትውልድ ሥፍራ ነው። እንዲህ መሆኑ ሀብታምን ‹‹ለሀገሩ እንግዳ ፣ ለሰዉ ባዳ›› እንዳትሆን አገዛት። ልጅነቷን፣ ወጣትነቷን ያሳለፈችበትን አዲስ አበባ ለቃ ወደ አርሲ ስትጓዝ በሙሉ ልብና ፈቃደኝነት ሆነ።

ኢተያ

ኢተያ ላይ የጸናው ትዳር በመልካም አብሮነት በልጆች በረከት ሰምሯል። ሀብታም አሁንም ስለነገው መልካምነት ታስባለች። በጥሩ መሠረት ልጆች እንዲያድጉ አቅም መፍጠር፣ ጥሪት መያዝ ፍላጎቷ ነው። ይህ ዕውን እንዲሆን ዛሬን በትጋት ማለፍ ግድ ይላል።

ቆራጥ ልብ ፣ ብርቱ ክንዶች ያላት ሀብታም ያሰበችውን ለማሳካት ባህር ተሻግራ ፣ በጉልበቷ ማደር ግድ ብሏታል። ይህን ለማድረግ የወሰነችው ሴት ያሰበችውን ልትከውን አልዘገየችም። ለሃሳቧ ግብ፣ ለዓላማዋ ስኬት ወደ አረብ ሀገር ለመጓዝ ትኬቷን ቆረጠች።

ሀብታም ቀኑ ሲደርስ ሻንጣዋን ሸክፋ ፣ ባሏን ልጆቿን ተሰናበተች። እንዲህ ለማድረግ የዓላማን ጽናት ያሻል። ቆራጥነት ይጠይቃል ። ቤቷን ትታ ሀገሯን ርቃ ስትሄድ ይህ ማንነት ከእሷ አልጠፋም። የምትወዳቸውን የምትሳሳላቸውን ልጆቿን በተሻለ ለማኖር እንዲህ ማድረግ አለባት። የእናትነት አንጀቷ ቢፈትናትም መንገዷን አልተወችም ። ለተሻለ ነገ ጉዟዋ ወደ አረብ ሀገር ‹‹ዱባይ›› ሆነ።

2012 ዓ.ም ለሀብታም የአዲስ ሕይወት ጅማሬ ነው። አሁን በማታውቀው ሀገር፣ በማታውቃቸው ባዕዳን ፊት ሥራ ጀምራለች። በዚህ ሥፍራ ከምታውቀው ባህልና ቋንቋ ውጭ እየኖረች ነው። ቀድሞ ያልቀመሰችውን ምግብ ትቀምሳለች፣ አካሏ የሚያውቀው አይነት አየር አይጠብቃትም።

እንዲያም ቢሆን ሀብታም ሁሉን እንዳመጣጡ ልትቀበል ዝግጁ ናት። ይህ አይነቱ እውነት ገና ከሀገሯ ስትወጣ ሊገጥማት እንደሚችል ታውቃለች። ደግነቱ ለሥራ የገባችበት ቤት መልካም ሆነላት። ቀጣሪዎቿ ልክ እንደእሷ ሥራ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ናቸው። በሌሎች የምትሰማው ጭካኔና ክፋት የላቸውም።

አሠሪዎቿ ሀብታምን እንዳገኟት በፍቅር ተቀበሏት። ቤቱ የልጆች ቤት ነው። ህጻናት ይሮጡበታል፣ ከወዲያ ወዲህ ይቦሩቁበታል። ይህ አጋጣሚ ልጆቿን ትታ ለመጣችው ሀብታም መልካም የሚባል ሆነ። ከእናትነት የተረፈ ማንነቷ ሞግዚት ሆኖ ለመቀጠል አላገዳትም። ሥራውን ወዳና ፈቅዳ ተቀበለችው።

ውሎ ሲያድር ሀብታምና አሠሪዎቿ በወጉ ተግባቡ። ልጆቹ ከልብ ወደው ቀረቧት። እናት ሀብታም ይህኔ ፈገግታዋ ተመለሰ። ስጋት ጭንቀቷ ራቀ። በጊዜው ባገር ቤት ሁለት ልጆቿን ትታ ነበር ። ሁለቱም ህጻናት ናቸው። ሁሌም ሞግዚት የሆነችላቸውን ልጆች ባየች ቁጥር ልጇቿ ውል ይሏታል፣ ይናፍቋታል።

ናፍቆትና ትዝታ

አንዳንዴ ደግሞ የሀገሯ ትዝታ ከአቅሟ በላይ ይሆናል። የጎረቤት፣ የጓደኝነት ፍቅር ፣ የአውደ ዓመቱ፣ የገበያው ግርግር በዓይኗ ይዞራል ። ይህ ሁሉ ሀብታምን ቢፈትናትም አንገዳግዶ አልጣላትም። እሷ ካገር የወጣችበትን እውነት ለአፍታ አትዘነጋም። ቢከፋትም፣ ትስቃለች፣ ብትናፍቅም ትችለዋለች።

የሀብታምና የአሠሪ ቤተሰቦቿ ቅርበት ከሌሎች ይለያል። አራቱ ልጆች ስለእሷ ያላቸው ፍቅር የጠበቀ ነው። አአፍታ እንድትለያቸው አይሹም። ይህን የሚያውቁት ባለቤቶች ያከብሯታል፣ ይወዷታል። በእሷ ዕምነት እንዲህ ለመሆን የራስ ጥንካሬ የግድ ይላል። ዓላማን ስራ ላይ ብቻ ካደረጉ መንገድ ሁሉ ቀና ነው።

ሀብታም አረብ ሀገርን ሕይወት ሥራ በጀመረች ጊዜ የነበረው እውነት ከዚህ አልተለየም። ልጆቹን ወዳ፣ አሠሪዎቿን አክብራ፣ ሥራዋን አውቃ መቀጠሏ ያጎደለባት የለም። ሰዎቹ ስለእሷ መልካም ሆነው እንዲኖሩ አግዟታል። አንዳንዴ ሀብታም የሰው ሀገርን ከራሷ ጋር ታወዳድርና ትገረማለች።

ስለኢትዮጵያ የነበራት ስሜት ይበልጥ የገነነው በባዕዳን መሀል በሆነች ጊዜ ነው። በወቅቱ ይህ አይነቱን እውነትት ሁሉም የሀገሯ ልጆች እንዲጋሩት ትሻ ነበር። የዛኔ በእሷ ውስጠት የተመላለሰው ሀቅ ሀገር ማለት ክብር የሁሉም ዜጎች መሠረት እንደሆነች ነው።

ሀገር ምንም ድሃ ብትሆን ለልጆቿ አስትንፋስና ዋስትና ስለመሆኗ በራሷ ደርሶባት አረጋግጣለች። ለእሷ ከሀገሯ በላይ ምንም የለም ። ደጋግማ እንደምትለውም ስለሀገር ገና ያልተከፈለ ብዙ ዋጋ አለ። ይህን መክፈል እንደሚገባ የሚታወቀው ደግሞ ከሀገር ሲርቁ ፣ ከወገን ሲነጠሉ ነው።

መልካምነት ለራስ

ወይዘሮዋ በአረብ ሀገር ሕይወት እንደብዘዎቹ በደል አላገኛትም። እንደውም ዝምድና በሚመስል ቅርበት መልካምነትን አትርፋለች። ባልና ሚስት አሰሪዎቿ፣ ያፈሯቸው አራት ልጆች ስለእሷ ያላቸው ፍቅር የተለየ ነበር። ዛሬም ቢሆን የዋህነታቸውን ታነሳለች። ልጆቹ የሚፈልጉትን ካገኙ በራስ ባህርይ መቅረጽ ቀላል ነው። እናትነቷ ከልጅነታቸው ተዳምሮ አብራቸው ጥሩ ጊዜ አሳልፋለች።

አሠሪዎቿ የእሷን መብትና ክብር አይጥሱም። አውደዓመት በመጣ ጊዜ ከሀገሯ ልጆች ጋር በዓሉን እንድታሳልፍ ይፈቅዳሉ። እሷም ብትሆን ስለእነሱ ባህልና ዕምነት ልዩ ክብር ትሰጣለች። ይህ አይነቱ ግንኙነት የሶስት ዓመታት ቆይታዋን በመልካም ጊዜ አሳልፏል።

ሀብታም ከልጆቹ እናት ጋር የጓደኛ ያህል ትቀርባለች። በሁለቱ መሀል የሥራ ግኑኝነት ቢኖርም የዋህነቷ ያመዝናል። እንደባህርይዋ፣ እንደ ሃሳቧ ታድራለችና ባለመግባባት ተጋጭተው አያውቁም። ሁሉንም ልጆች በእኩል ቀርባ የምትወደው ሀብታም፤ በተለይ የመጨረሻዋ ልጅ እሷ ከሄደች በኋላ የተወለደች በመሆኑ የተለየ ፍቅር አላት።

መብትና ግዴታዋን ጠንቅቃ የምታውቀው ሴት የነገ ዓላማዋን እያሰበች ለቤቱ ወግና ሥርዓት ተገዝታ ታድራለች። እንዲህ መሆኑ በመላው ቤተሰብ ዘንድ ፍቅርና አክብሮት አትርፎላታል።

ሰርቶ ለመውጥ አግኝቶ ለማረፍ ስደት የሄደችው ወይዘሮ ካሰበችው ለመድረስ እየጣረች እየደከመች ነው። እስካሁን ማንነቷን የሚጋፋ እንቅፋት አልገጠማትም። ልጆቿ እየናፈቋት ሀገሯ እየታወሳት ጥርሷን ነክሳ በስራ መትጋት ቀጥላለች።

ሀገር ቤት የሚገኘው ባለቤቷ ልጆቹን በማሳደግ ቤቱን በመምራት ቀኝ እጅ ሆኗታል። ሀብታም ወደ ጎጇዋ ተመልሳ የምትሠራውን ታስባለች። ርቃ የሄደችው ለዓላማ ነውና ለአፍታ መዘናጋትን አታውቅም። የላቧን የድካሟን ፍሬ ከዳር ለማድረሰ ሁሌም በሥራ ላይ ትታያለች።

ሀብታም በዱባይ ኑሮዋ የአንዳንድ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለመታዘብ ችላለች። አብዛኞቹ በደላላ ተታለው ከቤታቸው የወጡ ህጻናት ናቸው። ጥቂት የማይባሉትም ከአሰሪዎቻቸው በሚደርስባቸው ጥቃት የአካል ጉዳት የገጠማቸው፣ የአእምሮ ህመም ያስጨነቃቸው ናቸው።

ህገወጥ ደላሎች በነዚህ ልጆች ሕይወት ለመጫወት ጥቅማቸውን ያስቀድማሉ። ወገኖቿ በሰልፍ ተደርድረው እንደ ዕቃ የሚመረጡበትን አጋጣሚ ባየች ጊዜ ወስጧ ያነባል። አእምሮዋ ይጨነቃል። ይህን የማያውቁ ቤተሰቦች ከእነሱ የተለየ ጥቅም መፈለጋቸው ደግሞ ሌለው አስከፊ ጉዳይ ነው።

ሀብታም በዚህ ላይ ያላት አቋም ይለያል። ወላጆች በዕድሜያቸው ያልበሰሉ ልጆቻቸውን ከመላክ አልፈው ጥቅም መሻታቸውን እንደ ከፋ ጥፋት ትቆጥረዋለች። እሷን የሚያውቁ የሀገርቤት ቤተሰቦች ስለልጆቻቸው መረጃ ሲጠይቋት ቆይተዋል። በወቅቱ ሄዳ ካየቻቸው አብዛኞቹ ጉዳት ያጋጠማቸውና ያልተረጋጉ ናቸው። ከነዚህ መሀል በርካቶቹ ልጆች በመሆናቸው የሚባሉትን የሚሰሙ አልነበሩም። ይህን ሁኔታ ዛሬ ላይ ሆና ስታስበው ሁኔታቸው ከልብ ያሳዝናታል።

አሁን ሀብታም ወደሀገሯ ለመመለስ እያሰበች ነው። ልጆቿ፣ ባለቤቷ ናፍቃዋታል። ሀገሯ፣ ኑሮዋ ውል ብሏታል። ጊዜዋን ለማጠናቀቅ ቀሪ ጊዜ እንዳላት ታውቃለች። አስካሁን የሠራችውን በወጉ ከተጠቀመች ግን ይበቃታል። ውስጧ ከዓመታት በፊት ከሀገር ስትወጣ ያሰበችውን ለማሳካት ጊዜው መድረሱን እያሳወቃት ነው። ከምንም በላይ ልታያቸው የናፈቀቻቸው ቤተሰቦቿ ጉዳይ ያሳስባታል።

ሀብታም ከሶስት ዓመታት የአረብ ሀገር ቆይታ በኋላ ጉዞዋ ወደሀገር ቤት ሆነ። ይህ ውሳኔዋ አሠሪዎቿን ማስደንገጡ አልቀረም። ድንገቴ ሃሳቧን አላመኑትምና በዋዛ ሊለቋት አልፈለጉም። ተመልሳ እንደምትመጣ ባወቁ ጊዜ ግን ተረጋግተዋል።

ሀብታም ሀገር ቤት ከመጣች በኋላ የልጆቿ ፍቅር መልሶ አጓጓት። ትዳር ጎጆዋን አስባ ወደነበረችበት ልትመለስ ከበዳት። እንደቀድሞው ከባለቤቷ መክራ የመሄዱን ጉዳይ ሰረዘች። የቆረጠችውን ትኬት ፣ መለሰች ። መምጣቷን የሚናፍቁ ያሳደገቸቻው ልጆች ተስፋ አልቆረጡም ። ከዛሬ ነገ መመለሷን ናፍቀው ደጅ ደጁን ጠበቁ። በተለይ ትንሽዬዋ ልጅ አልቻለችም፣ በናፍቆቷ ተሰቃየች። ሀብታም ተመልሳ አልሄደችም።

ይህ ስሜት የቀረው በልጆቹና በቤተሰቦቻቸው ላይ ብቻ አልሆነም። እሷም እነሱን ባሰበች ቁጥር ውስጧ ይላወሳል። አብራቸው ያሳለፈችውን መልካም ጊዜ እያሰበች ትተክዛለች። እንዲያም ሆኖ ውሳኔዋን አልሸረፈችም። ዛሬም ባቀደችው መንገድ ለመጓዝ ጅማሬዋን ልታሳካ ታስባለች።

አንዳንዴ ከአረብ ሀገሮቹ ቤተሰቦች ጋር በስልክ ቴክኖሎጂ ታወጋለች። ሴትየዋ እንደእህቷ ታያታለች። ልክ እንደትናንቱ ሆና ታናግራታለች። ልጆቹ እሷን ሲያዩ ደስ ይላቸዋል። ስለመምጣቷ ተስፋ አይቆርጡምና ሊያገኝዋት ይናፍቃሉ። ይህ አይነቱ ግንኙነት ግን እያደር ጉዳቱ አመዘነ።

ትንሸዬዋ ልጅ ከመደሰት ይልቅ በናፍቆቷ ተጎዳች፣ ተሳቀቀች። ሀብታም ይህኔ መቁረጥ እንዳለባት ገባት። አልዘገየችም። ፈጥና አደረገችው። ዳግም ቤተሰቦቹን ላለማግኘት ወስና ወደራሷ ሕይወት ተመለሰች። አሁንም ድረስ የምትደውልላት አሠሪዋ አዲስ አበባ መምጣት እንደምትፈልግ ትነግራታለች።

ሕይወት እንደገና

ወይዘሮዋ ትናንትና ጥላት ወደ ሄደችው ኢተያ ከተማ ተመልሳለች። ኢተያን ልክ ተወልዳ እንዳደገችበት ሀገር ትወዳታለች። ስለነዋሪው ያላት ክብርና ፍቅር የተለየ ነው። በዚህ ስፍራ ሁሉም እንዳሻው ሰርቶ ያድራል። አንዱ ለሌላው ያለው መልካምነት ያሰደንቃታል። የባለቤቷ የትውልድ ከተማ በሆነችው ኢተያ ኑሮን ከመሠረተች ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል።

አሁን ሀብታም የቀደመ ዕቅዷን የምትከውንበት ፣ የላብ ድካሟን ዋጋ ዳር የምታስይዝበት ጊዜ ደርሷል። ቆፍጣናዋ ሀብታም ዓላማዋን አልሳተችም። የጎደላትን ለመሙላት መኖሪያ ቤቷን ሰርታ ጨርሳለች። ከመጣች በኋላ ሌላ ልጅ ብትወልድም ይህ ምክንያት ሆኖ ከሃሳቧ አልታቀበችም። ሶስት ልጆቿን እያሳደገች፣ ትደሯን በወጉ ትመራለች።

ያሰቡት ሲሳካ…

ሀብታም ካለችበት አንዲት ጠባብ ቤት በደረስኩ ጊዜ በርካታ የሚመገቡ እንግዶችን በማስተናገድ ሩጫ ላይ ነበረች። የምሳ ሰአት ነውና ወጪ ገቢው በርክቷል። የምትሠራበት ምግብ ቤት ጠባብ የምትባል ነች። ቤት ደጁ ግን በሰው አጀብ ተጨናንቋል።

ሀብታም ሁሉንም እንደዓመሉ እንደፍላጎቱ ትታዘዘለች። በእሷ ዘንድ ‹‹እከሌ ይቅደም፣ እከሊት ትቆይ›› ይሉት ልማድ የለም። ሁሉንም በእኩል እያስተናገደች ትባትላለች። በእንግዶቿ ፊት የተለየ ርካታ ያስተዋልኩ መሰለኝ። እውነቴን ነበር። ሰዎቹ እሷን መርጠው በሳሎኗ መታደማቸው ይህ አይነቱ መልካምነት ስቧቸው መሆኑን ለማወቅ አያዳግትም።

ሀብታም ዛሬ የልቧ ሞልቷል፣ የሃሳቧ ደርሷል። ትናንት በሰው ሀገር ላይ ሆና ሲሰማት የነበረው ኀዘን ዛሬ በጉልበቷ ድካም በላቧ ወዝ መታበሱን አውቃለች። አሁን ከሷ መሰል ወገኖች ጋር ተደራጅታ የፈጠረችው ራስን የመቻል ተግባር ከምንም በላይ ደስታዋን አሳምሮታል። ሀብታም ዛሬ በሀገሯ ላይ መሥራቷ ብቻ ልክ እንደ ስሟ የደስታዋ ፣ የፍላጎቷ ሀብታም አድርጓታል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You