ጥሩ ገቢ አለህ። ጥሩ ትሠራለህ። ትምህርትህን በትጋት ትማራለህ። ወይም ደግሞ ጥሩ አቅም አለህ። ግን በምትፈልገው ልክ አልተቀየርክም። ለምንድን ነው? መልሱን ታውቀዋለህ? ‹‹The magic of thinking big›› የተሰኘ መፅሃፍ የብዙ ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ቀይሯል። በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በትልቁ ማሰብ እንዴት በሕይወት ላይ ተአምር እደሚፈጥር የሚያሳይ መፅሃፍ ነው። ‹‹ትልቅ በማሰብ ሕይወትን መቀየር›› በሚል በአማርኛ ቋንቋ ተተርጉሟል።
ትልቁን ስታስብ መጀመሪያ ለራስህ የምትሰጠው ቦታ ይቀየራል። አንተ ለራስህ የምትሰጠው ቦታ ሲቀየር በራስ መተማመንህ ከፍ ይላል። በመቀጠል ሰዎች ላንተ የሚሰጡህ ቦታ ይቀየራል። ሥራ የምትሠራበት መንገድ ይቀየራል። የጊዜ አጠቃቀምህ ይለወጣል። ገንዘብ አያያዝህም እንደዛው። ከዛ ሕይወትህ እስከመጨረሻው ይቀየራል። ይህ ሁሉ ግን የምታደርገው ገና ከመነሻው ትልቁን ካሰብክ ነው።
አየህ! ትልቁን ማሰብ ስትጀምር በመጀመሪያ የሚቃወምህ ውስጣዊ ድምፅህ ነው። ‹‹ኧረ እባክህ ይቅርብህ! አንተ እንዴት አድርገህ ነው የምታሳካው ይህን ያህል ገቢ ያሳካ ዘር ማንዘርህ ውስጥ እኮ የለም፣ የት የተማርከውን ነው፣ ምን መነሻ ገንዘብ ኖሮህ ነው፣ ምን ዘመድ ኖሮህ ነው›› ይልሃል ውስጥህ። ይቃወምሃል። በፍፁም አይሆንም ይልሃል። እሱን እንደምንም አሸንፈህና ተቋቁመህ ወደ ስኬት ልትጓዝ ስትል ቀጥሎ የሚቃወሙህ ሰዎች ናቸው። ያውም በዙሪያህ ያሉ የቅርብ ሰዎች።
‹‹ኧረ እባክህ ይቅርብህ! አርፈህ ተቀመጥ!›› ይሉሃል። ትልቁን እንዳታስብ ይሰብሩሃል። ያስቆሙሃል። ታዲያ ምን ይሻልሃል? ራሴን አሸንፌ በዙሪያ ያሉ ሰዎችን ጫና ተቋቁሜ ትልቁን አስቤ ትልቁን እንዴት ነው የማሳካው? ካልክ ይሄው መፍትሄው …
የመጀመሪያው ራስን አሳንሶ አለማየት ነው። ጉድለትህን ብቻ የምታሰብ ከሆነ፣ ድክመትህን ብቻ የምታስብ ከሆነ ድክመት ራሱ ይቆጣጠርሃል። አንዳንዴ ሰዎች ጠንካራ ጎንህን ቀለል አድርገው ይነግሩሃል። ‹‹አንተ እኮ ጎበዝ ነህ! ምንም አትል!›› ይሉህና ደካማ ጎንህን ግን ጫን አድርገውና አብዝተው ይነግሩሃል። ‹‹አትችልም እኮ! እንደው ቢቀርብህ እኮ ይሻላል›› ይሉሃል። ልብህን ይሰብሩታል። ሞራልህን ያዳክሙታል። ከዛ በራስህ አትተማመንም። ራስህን አሳንሰህ ታያለህ።
አየህ! አንዳንዴ ጥፋት ስታጠፋ ራስህን በጣም ትወቅሰዋለህ። ‹‹እኔ እኮ አልረባም፣ እንዲህ ባላደርግ..›› ትላለህ። የሚገርመው ነገር ራስህን በወቀስከው ቁጥር ስተትህን እየደጋገምከው ነው የምትሄደው። መቼም አትስተካከልም። ታዲያ ምን ይሻላል? ለራስህ የምትነግረውን ነገር መቀየር አለብህ። ጥንካሬህ ላይ አተኩር። በነገራችን ላይ አንተ ማለት አእምሮህን አይደለህም። ምን ማለት መሰለህ አእምሯችን እንደ አንዱ የሰውነት ክፍላችን ነው። እንደ እግራችንና እጃችን የምናዘው ነው። አንተ በፈለከው ሰአት የምታዘው ነው።
ለምሳሌ እጅህን የሆነ እቃ አንሳ ብለህ አንተ ካላዘዝከው በራሱ ሄዶ አያነሳም። እግርህ ከመሬት ተነስቶ መንገድ ይጀምራል እንዴ? አይጀምርም። አንተ ነህ እግርህን የምታዘው። አእምሮህ እንደ እግርህ ነው። አካልህ ነው። የሚያስበውን አንተ ነህ የምትመርጥለት። ግን ብዙ ሰው ይሸወዳል። አእምሮዬ እያሰበ ተጨነኩኝ፣ ጭንቀት ብቻ ነው የማስበው ይላል። ለምን? አእምሮውን ማዘዝ አይፈልግም። አእምሮ የሚታዘዘው በቃላት ነው። በምትሰማው ነው። በምታየው ነው። ስለዚህ የምትሰማው ወይም ለራስህ የምትነግረው ነገር ጥሩ መሆን አለበት።
ራስህን መናቅ የለብህም። አየህ ራስህን በጣም አሳንሰህ የምታይ ከሆነ አእምሮህ አንተን ለማሳነስ፣ ዝቅ ለማድረግ አይቦዝንም። አንተን ዝቅ ለማድረግ እስከሚችለው ድረስ ዋጋ ይከፍላል። ከዚህ በተቀራኒ ራስህን ትልቅና ገዘፍ አድርገህ የምታየው ከሆነ አእምሮህ አንተን ከፍ ለማድረግ ዋጋ ይከፍላል። ስለዚህ በፍፁም ራስህን አሳንሰህ አትየው።
ሁለተኛው ትልቅ አሳቢ የሚያደርግህ ቃላቶችህን መጠንቀቅ ነው። ሕይወትን እንደጦርነት ነው የማስባት ካልክ ሁሉም ነገር ላንተ ውጊያ ነው። እያንዳንዱ ቀን ላንተ የውጊያና የጦርነት ሜዳ ነው። ሰዎች በሁለት ይከፈላሉ። ወይ ወዳጅ ናቸው አልያ ደግሞ ጠላት ናቸው። አንተን ካልወደዱህና ከተቃወሙህ ጠላት ናቸው። ካንተ ጋር የሚስማሙ ከሆነ ወዳጅ ናቸው። ሕይወት ከባድ ትሆናለች። ለምን? እንደጦርነት ነዋ የምታየው። አንተ ግን ሕይወትን የምትረዳት እንደ ጨዋታና እንደ መደሰቻ ሜዳ ከሆነ ሁሌም ታጣጥመዋለህ። ሰዎች ላንተ ተመሳሳይ ናቸው። ሁሉም አንተን በጥሩ መልኩ ነው የሚያስተናግዱህ። ሁሉም ይወዱኛል ብለህ ታስባለህ።
ቃላቶችን በተለይ መጠንቀቅ አለብህ። ‹‹እኔ ይሄ ኑሮ አልገፋ ብሎኛል፣ አልቻልኩም፣ አይሆንልኝም ብቻ እስቲ ልሞክረው፣ እኔ ብዙ ነገር እኮ አይሳካልኝም›› አትበል። መጥፎ ቃላቶችን ከሕይወትህ መዝገበ ቃላት ውስጥ አውጣቸው። አንተ ውስጥ መኖር የለባቸውም። አንተ ጋር መኖር ያለበት በጣም የሚያጀግንህ፣ ጥሩ ስሜት የሚፈጥርልህና ሞራልህን የሚያነሳሳ ነገር መሆን አለበት።
ዶክተር ኢሞቶ የተሰኘው ጃፓናዊ የሠራው ጥናት በአንድ ወቅት ዓለምን ጉድ አሰኝቷል። በጥናቱ መሠረት መጥፎ ንግግርና መጥፎ ቃላት የሰውን ሕይወት እንደሚያበላሽ፤ ምክንያቱ ደግሞ የሰው ልጅ 70 ከመቶ ውሃ መሆኑን አረጋግጧል። አንተም ለምትናገረው ተጠንቀቅ ወዳጄ!
ሶስተኛው ህልምህን ወይም ዓላማህን ገዘፍ ማድረግ ነው። ምን ማለት መሰለህ? ትልቁ ቦታ ለኔ ይባኛል ማለት አለብህ። የሥራህን ጫፍ ማየት አለብህ። አካውንታን እሆናለሁ አትበል። ትልቁ አካውንታንት እሆናለሁ በል። እዛ ቦታ ላይ እቀመጣለሁ ብቻ አይደለም የምትለው፤ ያ ቦታ ይገባኛል፣ ሚሊየነርነት ይገባኛል በል። የምድር በረከት ሁሉ ለኔ ይገባኛል በል። ትልቁን ስእል ማየት አለብህ። ትልቁን ዓሳ ማጥድ አለብህ።
አንድ አሳ አጥማጅ ባህር ላይ መረቡን ዘርግቶ ዓሳ የሚያጠምድ ከሆነና ትልቁን ዓሳ የሚፈልግ ከሆነ ትናንሽ ዓሳዎች ሲመጡ ማሳለፍ አለበት። ትልቁ ዓሳ መረብ ውስጥ እስኪገባ መጠበቅና መታገስ አለበት። ግን ትንንሾቹን አይቶና ጓጉቶ መረቡን ካነሳ ባህሩ ይረብሸውና መረብ ውስጥ ሊገባ የነበረውን ትልቁን ዓሳ ያሸሸዋል። አንተም በሕይወትህ በጣም ትልቁን ነገር ፈልገህ ታግሰህና ወጥረህ መሥራት ስጀምር ትናንሽ እድሎች ይመጣሉ። ‹‹አይ! እነዚህ አይመጥኑኝም›› ብለህ ማሳለፍ አለብህ። ላንተ የሚገባው ትልቁ ስለሆነ። ትልቅ አሳቢ ካልሆንክ ሕይወትህን አትቀይርም። ህልምህ ትልቅ መሆን አለበት።
አራተኛው ወሬህ፣ ውሎህም ሃሳብህ ሁሉ መቀየር አለበት። ትንንሽ ወሬዎችን ማስወገድ መቻል አለብህ። ትናንሽ ሃሳቦችን፣ ሰው ማማትን፣ ስለችግር ማውራትን፣ ማቆም አለብህ። እንደውም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ‹‹ትናንሽ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ስለ እቃ ያወራሉ። ከእነሱ የሚሻሉት ስለ ሰው ያወራሉ። ከፍ ያለ አእምሮ ያላቸው ግን ስለ ሃሳብ ያወራሉ›› ብሏል። አንዳንድ ቦታዎች ላይ ስትውል ለአእምሮህ የሚመጥን ካልሆነ ይህ ቦታ ለእኔ አይመጥንም ብለህ ራስህን ዞር ማድረግ አለብህ። ይህ ቦታና ወሬ ለእኔ አይገባኝም ብለህ ራስህን ለትልቁ ቦታ ማጨት አለብህ።
የታክሲ ሰልፍ ከሚያሳስባቸው ሰዎች ጋር የምትውል ከሆነ መቼም መኪና አትገዛም። ውሎህ እኮ በጣም ወሳኝ ነው። አእምሮህ ደጋግሞ የሚሰማውን ነገር ነው የሚያደርገው። ሕይወትህ ላይ የሚገለጠው። ስለዚህ ትናንሽ ወሬዎችና፣ ዝቅ ያሉ ሃሳቦች የሚወሩበትና የሚሰሙበት ቦታ ላይ አትዋል። ለዚህ ነው ብዙ ጊዜ ዜና አትስሙ የሚባለው። ምክንያቱም አሉታዊ ነገሮችን ትሰማለህ። ስለሀገርህና ስለ ኑሮ ውድነት ስትሰማ ‹‹አይ ያለችኝ ትበቃኛለች የእኔን ሕይወት አልቀይርም በልቼ ካደርኩ በቂዬ ነው›› ትላለህ። የምትሰማው ነገር፤ ወደ አእመሮህ የሚገባው ሃሳብ መቀየር አለበት።
አምስተኛው ሁልጊዜም ቢሆን ራስን ማሳደግ ነው። በየቀኑ በጠዋት ስትነሳ ‹‹ዛሬ ደግሞ ሕይወቴ ላይ ምንድን ነው የምጨምረው?›› ማለት አለብህ። ምንድን ነው የማሳድገው ማለት አለብህ። ፎርብስ የተሰኘው መፅሄት ስፖንሰር አድርጎ በዓለም አቀፍ ሥራ ፈጣሪዎች ላይ ባጠናው ጥናት መሠረት አምስት የሚሆኑ የሚያመሳስሏቸው ፀባዮች እንዳሏቸው ተረጋግጧል። አንዱና ግን ሁሉንም አንድ ያደረጋቸው ፀባይ በጠዋት ተነስተው ዛሬ በሕይወታቸው የሚያደርጓቸውና የሚፈቷቸው ችግሮች መኖራቸው ነው። በየቀኑ የሚያሳድጉት ነገር አላቸው ማለት ነው።
አንተም ትልቅ የምታሰብ ከሆነ ሁሌም ማደግ አለብህ። ባለህበት ቆመህ ከቀረህማ ሕይወትህ ተደጋጋሚ ነው የሚሆነው። ትልቅ የሚያስብ ሰው ራሱን ያሳድጋል። አየህ በሂደተ ለውጥ ማመን አለብህ። የሰው ልጅ የሚቀየረው በሂደት ነው። በአንድ ጊዜ ዛፍ ላይ አይወጣም። ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም ይባላል። ሕይወትን የምትቀይረው በሂደት እያደክ ከሆነ ብቻ ነው።
ስድስተኛው በዙሪያህ ያሉትን ሰዎች አድንቃቸው። አንድ ነገር አትርሳ የምታወራውን ነገር አንተም መልሰህ ትሰማዋለህ። ስለዚህ የምታወራው ነገር መልካም መሆን አለበት። ለሰዎች አድናቆት እንጂ ትችትና መጥፎ ነገር መናገር የለብህም። ለምን መሰለህ? አንደኛ እነርሱን ትጠቅማቸዋለህ። ሁለተኛ ለራስህ ጥሩ ነገር እየነገርከው ነው። ሰው ታደንቃለህ። አየህ! ሰው የሌለውን አይሰጥም። አንዳንድ ሰዎች የሰው እንከን፣ ጉድለትና መጥፎውን ብቻ የሚታያቸው ውስጣቸው መጥፎ ነገር ስላለ ነው።
የሌለህን እኮ አትሰጥም። ስለዚህ ጥሩ ነገር የምትናገር ከሆነ ውስጥህ ጥሩ ነገር ስላለ ነው። ለመፎ ነገር ብለህ አይደለም የምታደርገው። የእውነት ከልብህ ሆነህ ነው። በቅንነት ነው መሆን ያለበት። ያኔ እነርሱንም ትቀይራቸዋለህ። ስለጥንካሪያችን ባወቅን ቁጥር ድክመታችንን መቀየር በጣም ቀላል ይሆናል። ወደአእምሮህ የሚገባው ነገር በጎ ከሆነ ድክመቶችህን ሁሉ መቀየር ትችላለህ። ሰዎችን የምትወዳቸው ከሆነ አድናቆትህን ነው መግለፅ ያለብህ። ድክመታቸውን ራሳቸው ይቀይሩታል።
ሰባተኛውና የመጨረሻው ለሕይወትህ በጣም ወሳኝ ነው። በተለይ ትልቅ ለምናስብ ሰዎች። ተግባርህ በጣም ወሳኝ ነው። አየህ! ትልቁን አስበህ መሬት ላይ እንደሚወርድ፤ እንደሚሳካ ዋስትናና ማረጋገጫ የሚሆንህ የተግባር ሰው ከሆንክ ነው። ያለበለዚያ ትንሳፈፋለህ። ስለዚህ የድርጊት ሰው መሆን አለብህ። ያመንክበትንና እጅ ላይ ያለውን ነገር ማድረግ አለብህ። መቀየር አለብህ። በተለይ ስሜትህን ከፍ የሚያደርጉ ነገሮችን ማድረግ አለብህ።
ለምሳሌ ስፖርት እሠራለሁ ካልክ ሥራ። ጧት እነሳለሁ ካልክ ተነስ። ሻወር እወስዳለሁ ካልክ ውሰድ። ስራ ቦታ በጊዜ እሄዳለሁ፤ በደምብ አምሽቼ እሰራለሁ ካልክ ሥራ። ትልቁን ስታስብ ወደ ተግባር ካልመነዘርከው እውነት አይሆንም። አየህ! የሚታሰቡ ነገሮች መሬት ላይ የሚወርዱት በጥረት ነው። የተግባር ሰው መሆን አለብህ!!
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2016 ዓ.ም