ሁለቱ ወርቆች

በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ የሀገርን ስም በማስጠራት ቀዳሚ በሆነው አትሌቲክስ፤ በርካታ ሜዳሊያዎች የተመዘገቡት በሴት አትሌቶች መሆኑ ይታወቃል። ይህም በተለያዩ ውድድሮች የታየ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮናም ከተገኙት አራት ሜዳሊያዎች መካከል ሶስቱን ያጠለቁት ሴቶች ናቸው፡፡ የዓለም ቻምፒዮናዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ በ3ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ስታገኝ ወጣቶቹ አትሌቶች ጽጌ ድጉማ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ በ800 ሜትር እና 1 ሺ500 ሜትር ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገራቸው አስመዝግበዋል፡፡

የስፖርት ተሳትፎዋ የሚጀምረው ከትምህርት ቤት ሲሆን፤ የወደፊት ተስፋዋን በተመለከቱ ባለሙያዎች ከዓመታት በፊት ወደ ማሠልጠኛ ማዕከል እንድትገባ ተደረገ፡፡ አሰላ በሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሠልጠኛ ገብታም ሥልጠናዋን ካጠናቀቀች በኋላ በአትሌቲክስ ስፖርት በርካታ ስመጥር አትሌቶችን ያፈራውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ ተቀላቀለች፡፡ ሩጫን ስትጀምር በኢትዮጵያ እምብዛም ባልተለመደው አጭር ርቀት ቢሆንም በሂደት ወደ መካከለኛ ርቀት በማሳደግ ስኬትን ማጣጣም ጀምራለች።

አትሌቲክስ ፈታኝ ስፖርት መሆኑን የምትጠቁመው አትሌቷ በትዕግስት ማለፍ ከተቻለ ውጤቱ እጅግ አስደሳች እንደሆነም ታመላክታለች። በእርግጥ በስፖርቱ በርካታ ስኬቶች በሴት አትሌቶች የተመዘገበ ነው፡፡ የዚህም ምስጢር ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ውድድር በሚካሄድበት ሥፍራ ባለው የአየር ሁኔታና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ካልተበገሩ በቀር ከዚህም በላይ ውጤት ይመዘገባል የሚል እምነት አላት፡፡ ቀጣይ ዕቅዷም ጉድለቷን በማሻሻልና ጠንክራ በመሥራት በፓሪስ ኦሊምፒክ ዳግም ሀገሯን በክብር ማስጠራት ነው።

በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ከሁለት ዓመት በፊት በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌቷ፤ በዚህ ቻምፒዮና ደግሞ በ1 ሺ500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዳለች፡፡ ተወልዳ ባደገችበት ማህበረሰብ ጥቂቶች ካልሆኑ እንደእሷ ለአትሌቲክስ ስፖርት ፍላጎት ያላቸውንና ጥረት የሚያደርጉ ሴቶች መበረታታታቸው ከስኬት አድርሷታል፡፡ ባደገችበት ወረዳ በሚገኝ ፕሮጀክት ውስጥ ችሎታዋን በማዳበር መስፍን ኢንጂነሪንግ ስፖርት ክለብን ለመቀላቀል ችላለች፡፡ ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው የጸጥታ ችግር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በግሏ በምታደርገው ጥረት ራሷን ለውጤታማነት ሀገሯንም ለስኬት አብቅታለች፡፡

እሷን መሰል ሴት አትሌቶች በየውድድሩ አሸንፈው ለራሳቸውና ለሀገራቸው ሜዳሊያዎችን በተደጋጋሚ የማስገኘታቸው ምስጢርም በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ እና በመመካከር በመሥራታቸው መሆኑን ትጠቁማለች፡፡ ከአሠልጣኞች የሚሰጡትን የትኛውንም የአሯሯጥ ስልትም በአግባቡ ይተገብራሉ፡፡ ይህንኑ ጠንካራ ሥራ በመድገምም በቀጣይ ለሚኖሩት የዳመይንድ ሊግ እና ኦሊምፒክ ሀገሯን መወከልም ቀጣይ እቅዷ ነው፡፡

ለወጣት ሴት አትሌቶችም ‹‹እኛ አንጋፋዎቹን እየተመለከትን አሁን ካለንበት ደርሰናል፤ ተተኪዎች ደግሞ እኛን በመመልከት የተሻለ ሆነው ይገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከለፋችሁና ጠንክራችሁ ከሰራችሁ ከምታስቡት ደረጃ ለመድረስ ትችላላችሁ›› ስትልም መልዕክቷን ታስተላልፋለች፡፡

ብርሃን ፋይሳ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

 

 

 

 

 

Recommended For You