የሴቶችን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማላቅ ይገባል

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ የሚከበረው የዘንድሮው የሴቶች ቀን፤ መሪ ሐሳቡ “ሴቶችን እናብቃ! ልማትንና ሠላምን እናረጋግጥ!” የሚል ነው። መሪ ሐሳቡ እንደሚያመለክተው ደግሞ፤ ልማት እና ሠላምን ለማረጋገጥ ሴቶችን ማብቃት እጅጉን የሚያስፈልግ መሆኑን ነው። ዛሬ ላይ ዓለማችን በሠላም እጦት ውስጥ ለመኖሯ አንዱ ምክንያትም ይሄው ሴቶችን አብቅቶ ያለማሳተፍ ስለመሆኑም በርካታ አመክንዮዎችን መጥቀስ ይቻላል።

እርግጥ ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙ ሴቶች ዛሬም ገና አልበቁም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየውም፤ እ.ኤ.አ. በ2023 በዓለም ላይ የሴቶች ቁጥር አራት ቢሊዮን ይገመታል። ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከዓለም ሕዝብ 49 ነጥብ 75 ይሆናል። በእርግጥ በዓለማችን ላይ ላለፉት 22 ዓመታት በተከታታይ ወንዶች ከሴቶች ይልቅ በቁጥራቸው ብልጫውን ይዘው ዘልቀው እንደነበር ይታወቃል። ዛሬ ዛሬ ግን የሴቶች ቁጥር ከወንዶች ጋር እኩል በሚያስብል ሁኔታ በመምጣት ላይ ይገኛል።

ይህ ግን ከቁጥር አንጻር ያለውን መረጃ የሚያሳይ እንጂ፤ ሴቶች በቁጥራቸው ልክ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፉ ላይ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዛው ልክ የሄደ አይደለም። ይሄ ሁኔታ ደግሞ ሴቶች ከእነዚህ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸው ብቻ ሳይሆን፤ ከውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውም ጭምር እንዲርቁ እያደረጋቸው ስለሚገኝ ይሄንን አካሄድ መቀየር የተገባ ነው።

በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ወዲህ በመጡ መሻሻሎች የሴቶች ተሳትፎን በሁሉም መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መልካም ጅምሮች ታይተዋል። ለምሳሌ፣ በሀገራችን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያለው የሴቶች ውክልና ከፍ ብሏል። ይህም የሴቶች ቁጥር ከወንዶች አንጻር በመቶኛ ሲሰላ 42 ነጥብ አምስት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል። ይህ ከፍ ያለው የሴቶች ቁጥር መታየቱ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ በካቢኔ አባልነት(ሚኒስትርነት) ደረጃ ያለው የሴቶች ተሳትፎ እስከ 50 በመቶ የደረሰበት አጋጣሚ ነበር። አሁንም ቢሆን ድርሻቸው ከፍ ያለ ነው። ኢትዮጵያ በፕሬዚዳንቷ፤ አዲስ አበባም በከንቲባዋ ሴቶችን ከፊት ማስቀደሟም የዚህ ሌላው አብነት ነው።

ነገር ግን ይሄን መሰሉ ሁነት በየደረጃ ሲታይ ከላይ ያለው ዓይነት አካሄድ በተዋረድ ሲወርድ አይታይም። በአንዳንድ ተቋማት ደግሞ የሴቶች ተሳትፎ ብርቅ የሚሆንበት ሁኔታ በሰፊው ይታያል። ሆኖም እውነታው የሴቷን ተሳትፎ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፍ ይበልጥ በማጎልበቱ ረገድ የላይኛውን ዓይነት የውሳኔ ሰጪነት ቦታው እንዲኖራቸው ማድረጉ ለልማቱም ለሠላሙም ሚናው የጎላ መሆኑን ተገንዝቦ መሥራትን ይጠይቃል።

እንደ መሪ ሀሳቡ ሁሉ ሴቶች የቁጥራቸውን ያህል የውሳኔ ሰጪነቱን ስፍራ ይዘው ቢሆን፣ ሀገራችን ዛሬ እየደረሰባት ያለው የሠላም ችግር ይሄን ያህል ገፍቶ ላይወጣ ይችል ነበር። እናም ሴቶችን ከወንዶች ባልተናነሰ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት ዛሬም ቢሆን አይረፍድም፤ አልረፈደምም። ተሳትፏቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚጠየቀው ቀናነት ብቻ ነው። ሴቶች የሚሳተፉበት የልማትም የሠላምም ሒደት ጤናማነት የተረጋገጠ ስለሚሆን ከዚህ አንጻር ሴቶችን ወደውሳኔ ሰጪነት ቦታው ማምጣቱ አዋጭ ነው።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ካሉ አምስት ሀገራት መካከል ለሴቶች የተሻለ ውክልና በመስጠቱ የምትጠቀስ ብትሆንም፤ ይህ ብቻ በራሱ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም። ዛሬም ቢሆን ውሳኔ ሰጪ የሆኑ ናቸው የሚባሉ ተቋማት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ በተፈለገው ልክ አይታይም። ሴቶችን በፖለቲካው ዘርፍ ከወንዶች እኩል ለማሳተፍ የሚደረግ ጥረት በአገራችን መሪ ዘንድ ቢኖርም ገና ብዙ የሚቀረን ነገር መኖሩ ሊዘነጋ አይገባም።

የዘንድሮው መሪ ሐሳብ፣ “ሴቶችን እናብቃ! ልማትንና ሠላምን እናረጋግጥ!” የሚል እንደመሆኑም፤ ሴቶችን ማብቃት የግድ ነው። ሴቶችን አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ከአመራር ሰጪነት ቦታ መግፋት አግባብነት የሌለው አካሄድ ነው። ደግሞም ሴቶች ተገቢ የሆነ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል ሲባል እንዲያው ለይስሙላ መሆን የለበትም። በመንግሥት ካቢኔ ውስጥም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሴቶች ተሳትፎ ከፍ ሊል ይገባል ሲባልም ለተሳትፎ ብቻ መሆን የለበትም።

ምክንያቱም ሴት ወደ አመራርነት እና ውሳኔ ሰጪነት መጣች ማለት፤ ሙስናን ከመሠረቱ ለማጥፋት መንገዱ ተጀመረ ማለት ነው። የሠላም መስፈን የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚያደርጋት እርሷን በመሆኑም፣ ሴት ወደ ውሳኔ ሰጪነት ስትመጣ ስለሠላም ቅድሚያ ሰጥታ ትሠራለች። በሀገራችን ሠላም ሰፈነ ማለት ደግሞ ልማት በሚፈለገው ልክ ይሳለጣል።

ሴቶች፣ ተገቢውን ስፍራ ሲይዙ ለሠላም መስፈንም ሆነ ለልማት መሳለጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል የሚባለውም እውነት ስለሆነ ነው። ከዚህ አኳያ ሴቶችን ማብቃት ማለት ማኅበረሰቡን ካለበት ውጣ ውረድ ማላቀቅ ነው። ሀገርን ከድህነት አረንቋ ማውጣት ነው። ወጣቱ በሠላም እጦት ሥራ ፈት ሆኖ ተስፋ እንዳይቆርጥ ሥራ እንዲፈጠርለት ማስቻል ነው።

ሴቶች ወደ አመራርነት እና ውሳኔ ሰጪነት ይምጡ ሲባል፣ ሴቶችን ተሳታፊም ተጠቃሚም የሚያደርጉ ሥራዎች ይከናወኑ ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ሴቶችን ዛሬም ቢሆን እየደረሰባቸው ካለው ጥቃት መታደግና መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው። ሴቶችም በራሳቸው የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን ለማሳደግ በየተሠማሩበት አቅማቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል። በዚህ መልኩም ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማደግ ሁሉን አቀፍ ትብብርና ሥራ ይጠይቃል።

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016  ዓ.ም

Recommended For You