በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ከዓለም አምስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ በመሆን ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ከትናንት በስቲያ ቡድን ወደ ሀገሩ ሲመለስ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል:: በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተዘጋጀው የዕውቅና እና ሽልማት መርሃግብር በ6ኛው የአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና የተሳተፉ አትሌቶችንም ያካተተ ነበር::
በረጅም ርቀት አትሌቲክስ የኢትዮጵያ ተፎካካሪ የሆኑ ሀገራት ጭምር እምብዛም ውጤታማ ባልሆኑበት በዚህ የውድድር መድረክ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ግን ጠንካራ ተፎካካሪዎች መሆናቸው ይታወቃል:: ይኸውም በመካከለኛ ርቀት አትሌቲክስ ኢትዮጵያ ያላትን አቅም በግልጽ ያሳየችበት ሆኗል:: በተለይም ከተገኙት የወርቅ ሜዳሊያዎች መካከል አንደኛው ለኢትዮጵያ በ800 ሜትር የመጀመሪያው ድል ነው::
የድሉ ባለቤት የሆነችው ወጣቷ አትሌት ጽጌ ድጉማ ውድድሩን በሚመለከት ‹‹ይህን በመሰለ መድረክ ስሳተፍ የመጀመሪያዬ በመሆኑ የማገኘውን እድል ላለማባከን ጥረት አድርጌያለሁ:: በእርግጥ ከነበረኝ ዝግጅት አንጻር በራስ የመተማመን ስሜት ነበር የሮጥኩት ተሳክቶልኛል›› ስትል ገልጻለች:: ከአትሌት መሀመድ አማን በስተቀር በዚህ ርቀት የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማጥለቅ የቻለ የለም:: በመሆኑም በአጭርና መካከለኛ ርቀት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተፎካካሪ ሊሆኑ አይችሉም የሚለው እሳቤ ለዓመታት በአትሌቲክሱ ውስጥ ተንሰራፍቶ ቆይቷል:: በመሆኑም የአሠልጣኞችም ሆነ አብዛኛዎች አትሌቶች ትኩረት በረጅም ርቀት ላይ የተገደበ ነበር::
ይህንን የማትቀበለው አትሌት ፅጌ ‹‹በመካከለኛ ርቀት ውጤታማነት በኢትዮጵያ ያልተለመደ ቢሆንም አቅሙ እንዳለ ግን እኔ ማሳያ ነኝ›› ትላለች:: ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በተለያዩ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት ያሉ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች በርቀቱ ተሳታፊ ቢሆኑም ለውጤታማነት የእነሱ ጥረት ብቻውን በቂ አለመሆኑን ‹‹ከአትሌቶች ጠንካራ ስራ ባለፈ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሌሎች አካላት አስፈላጊውን ነገር ማመቻቸት ቢችሉ ውጤት ይመጣል›› ስትልም ታብራራለች::
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገኘችው ጽጌ ሥፍራው በርካታ ተተኪ አትሌቶች ሊወጡ የሚችሉበት በመሆኑ ባለሙያዎች አካባቢውን ተደራሽ ማድረግ ይገባቸዋል:: በክልሉ ወምበርማ ላይ የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከል ያለ ቢሆንም እሷ በተወለደችበት የካማሽ ዞን ግን የፍላጎቱን ያህል ትኩረት በመስጠት ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን መክፈት አስፈላጊ ነው ትላለች:: የዚህ ዓመት ዋነኛው ዓላማዋም ትልቁ የስፖርት ውድድር ኦሊምፒክ ነው፤ በመሆኑም ‹‹ደካማ ጎኖቼን በማሻሻል ለሀገሬ ውጤት ብቻም ሳይሆን ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ እሠራለሁ›› ብላለች::
በውድድሩ ሌላኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሯ ያስገኘችው ደግሞ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ናት:: በቤልግሬዱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ800 ሜትር ተወዳዳሪ የነበረችው አትሌቷ የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ የሚታወስ ነው:: አትሌቷ በቤት ውስጥ ቱር ውድድር ጥሩ ተሳትፎ ማድረጓንና በቻምፒዮናው ላም ከቡድን አጋሮቿ ጋር በመሆን ውጤት ለማስመዝገብ አቅደው ወደ ግላስኮ ማቅናታቸውን ታወሳለች:: በቡድን ስራ ከወርቅ እስከ ነሃስ ያለውን ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ለማስገኘት ጥረት ቢያደርጉም አንዱን ብቻ ማስመዝገብ ተችሏል:: በመሆኑም አሁንም ያለእረፍት በመሥራት በቀጣይ ለሚኖሩት የዳይመንድ ሊግና የኦሊምፒክ ሚኒማ ማሟያ ውድድሮች መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንም ትገልጻለች::
አስቀድሞ የ400 ሜትር አትሌት የነበረችው ፍሬወይኒ በሂደት ወደ 800 ሜትር ከዚያም 1 ሺ500 ሜትር ልታሳድግ ችላለች:: ይኸውም ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት ያላትን አቅም የሚያሳይ ሲሆን፤ አሁን ላይ ጅማሬው ቢሆንም በቀጣይ እንደ ዓለም ቻምፒዮና ባሉ የውድድር መድረኮች ተፎካካሪ እንዲሁም ክብረወሰን የሆኑ ሰዓት የመመዝገብ እድሉ ሰፊ እንደሚሆን እምነቷ ነው::
በግላስኮ በነበረው ቻምፒዮና የ800 ሜትር ቡድኑን የመራው ወጣቱ አሠልጣኝ አለሙ ዋቅጅራ ነው:: የቀድሞው አትሌት በአሠልጣኝነት ከመጣ ወዲህ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ያለ ሲሆን፤ ለሀገሯ አዲስ ታሪክ የጻፈችውን አትሌት ጽጌ ድጉማን ጨምሮ ሂሩት መሸሻን የመሳሰሉ አትሌቶች በማፍራት ላይም ይገኛል:: ቡድኑ ወደ ቤት ውስጥ ቻምፒዮናው ከመጓዙ አስቀድሞ ጠንካራ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ለውጤት እንዳበቃው ይገልጻል:: ይሁንና የመካከለኛ ርቀት ሩጫ በመም ላይ የሚደረግ እንደመሆኑ በሀገሪቷ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል::
ለልምምድ ሱሉልታ በሚገኘው የቀነኒሳ በቀለ መም መሄድ የግድ ቢሆንም በጫና ምክንያት አስፈላጊውን ልምምድ ለማድረግ አዳጋች እየሆነ ነው:: የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ደግሞ በፌዴሬሽኑ በኩል ካልሆነ መግባት አይቻልም:: በዚህም ምክንያት በመካከለኛ ርቀት የሚፈለገው ውጤት ሊመዘገብ አልቻለም:: የረጅም ርቀት አትሌቶች በጎዳና እንዲሁም ኮረኮንች ባላቸው ሥፍራዎች ልምምዳቸውን ማድረግ ይችላሉ:: ይህ ርቀት ግን የግድ መም የሚፈልግ በመሆኑ መንግሥት ሊሠራበት እንደሚገባ ያሳስባል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም