ዓለም በትግል የተሞላች ናት፡፡ እርግጥ ያለትግል ሕይወት አይሰምርም፡፡ ትግል ሲኖርም ነው ሕይወት የሚጣፍጠው፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ የሕይወት ትግል በአንዳንዱ ላይ ክፉኛ ይበረታል፡፡ መራር ይሆናል፡፡ መንገዱ ሁሉ አመኬላ ይበዛበታል፡፡ ሰው ሆኖ መፈጠሩን እንዲጠራጠርና ራሱን እንዲጠላ ያደርገዋል፡፡ ተስፋ ያስቆርጠዋል፡፡ የቆረጠ እለት ደግሞ በምሬት ሕይወቱን እንዲያጠፋም ጭምር ይጋብዘዋል፡፡ አዎ! ሕይወት እንደዚህ ነው፡፡ አንዳንዴ ግን በሞተ ተስፋ ውስጥ ዳግም መታደስ አለ፡፡ አንዳንዴ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ባለድል መሆን አለ፡፡ አንዳንዴ በመጨረሻ ሰአታት ውስጥ ወደ ሕይወት የመመለስ እድል አለ፡፡
ወይዘሮ መሠረት በሻዳ ትባላለች፡፡ የምትኖረው እዚሁ አዲስ አበባ ጠመንጃ ያዥ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት ነበረች፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ ባሏ መጠጥ ጠጥቶ እየመጣ ይደበድባት ጀመር፡፡ ለልጆቿ ስትል ሁሉን ችላ ኖረች፡፡ በዘመድ ጎረቤት አስመከረች፡፡ በሏ ግን ሊለወጥ አልቻለም፡፡ እንደውም ባሰበት፡፡
ድብደባውና ስድቡ ቢመራት በመጨረሻ ከባሏ ለመፋታት ቆርጣ ተነሳች፡፡ አደረገችው፡፡ ከፍቺ በኋላ ግን ሕይወት እንዳሰበችው አልሰመረላትም፡፡ ለእርሷ ኑሮ በጣም ከባድ ነበር፡፡ ልጆቿን ለማሳደግ በብርቱ ተቸግራለች፡፡ ባሏ ለተወሰነ ጊዜ ለልጆቿ ገንዘብ ተቆራጭ ቢያደርግም አልዘለቀበትም፡፡ ልጇን አዝላ እንጀራ እየጋገረች ገቢ ለማግኘት ሞክራለች፡፡ በየኮንዲሚኒም ቤቱ እየተዟዟረች ልብስ በማጠብ ልጆቿን ለማሳደግ ጥረት አድርጋለች፡፡ በመጨረሻ ተስፋ ቆርጣ ልጇን ይዛ ጎዳና ወጥታ በልመና ሕይወቷን ለመምራት ተገዳለች፡፡
አንድ ቀን የወረዳ ሰዎች መንገድ ላይ ስትለምን አዩዋት፡፡ ‹‹ላይፍ ሴንተር›› ከተሰኘና ባሎቻቸው የሞቱባቸው ወይም የተፋቱ ሴቶችን እንዲሁም ወላጅ አልባ ህፃናትን ከሚረዳ ድርጅት ጋር አገናኟት። የመጨረሻ ልጇ እዚህ ድርጅት ውስጥ ከገባች ሰባት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ በዚህ ድርጅትም የተለያዩ የትምህርት መሣሪያዎችና የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላታል፡፡ እርሷም በድርጀቱ የልብስ ስፌት ሥልጠና ተሰጥቷታል። ከድርጅቱ ፈሳሽ ሳሙና በቅናሽ እየወሰደች አትርፋ የምትሸጥበት እድልም ተመቻችቶላታል፡፡
አሁን ደግሞ የ 13 ሺ ብር ብድር ተመቻችቶላትት የልብስ ማጠቢያ ማሽን ገዝታ ልብስ እያጠበች ገቢዋን በማሳደግ ልጆቿን እያሳደገች ነው፡፡ ብድሯን መልሳ በድጋሚ 20 ሺ ብር ተበድራ 100 ኪሎ ጤፍ፣ ዘይትና ስኳርና ፍሩኖ ዱቄት ገዝታ ኩኪሶችን እያዘጋጀች በየትምህርት ቤቱ ትሸጣለች፡፡ እንጀራ ጋግራ ታከፋፍላለች፡፡ በዚህም በፊት ከነበረው ሁኔታ አንፃር ዛሬ ላይ ሕይወቷ በብዙ መልኩ ተለውጧል፡፡ ከመጨረሻ ልጇ በተጨማሪ ድርጅቱ ለሶስቱ ልጆቿ በድርጅቱ ቤተመፅሃፍት እንዲጠቀሙ እድል ተመቻችቶላቸዋል። ዛሬ ላይ ለወይዘሮ መሠረት በላይፍ ሴንተር ተስፋዋ ለምልሟል፡፡
ወይዘሮ ሙሉ ግርማይ የላይፍ ሴንተር መስራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ዘመን የሽግግሩ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ ታምራት ላይኔ ባለቤት የነበሩ ሲሆን ደርግን ለመጣል በተደረገው ጥረትም በታጋይነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። በአዲስ አበባ የድርጅት ፅህፈት ቤት አመራር ሆነውም አገልግለዋል፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት ላይፍ ሴንተር የተመሰረተው የዛሬ አስራ አንድ ዓመት ሶስት ወላጅ አልባ ህፃናትን በመደገፍ ነበር፡፡ ድርጅቱ የተመሠረተውም ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ በመንግሥት ከታሰሩ በኋላ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከገጠማቸው ችግር በመነሳት ነው፡፡ ያ የችግር ጊዜም ስለሌሎች እናቶችና ህፃናት እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡ ለዛም ነው ወላጅ አልባ ልጆችንና ያለአባት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶችን ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት ለማቋቋም ያነሳሳቸው፡፡
ድርጅቱ በዋናነት የሚያገለግላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ወላጅ አልባ ልጆችና ከባሎቻቸው የተፋቱና ባለቤቶቻውን በሞት ያጡ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜም 300 የሚሆኑ መበለቶች በድርጅቱ በኩል መሠረታዊ የንግድ ክህሎት ሥልጠና፣ የልብስ ስፌት ሥልጠና፣ የብድር አገልግሎት፣ የክትትል፣ ድጋፍና ምክር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
275 የሚሆኑ ወላጅ አልባ ልጆች ደግሞ በሚሰጣቸው ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ መሠረታዊ ትምህርት መሣሪያዎችና የምግብ አቅርቦት፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠናዎች፣ አስተማሪና አዝናኝ ትምህርታዊ ጉዞዎችየልብስ ስፌት፣ የእጅ ሥራና የኮምፒዩተር ክህሎት ሥልጠናዎች፣ የሥነ ልቦናና የምክር አገልግሎት፣ የቤተ- መፅሃፍት አገልግሎትና የማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት ያገኛሉ፡፡
ወይዘሮ ሙሉ እንደሚናገሩት ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ቂርቆስ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ልደታ ክፍለከተሞች ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከአዲስ አበባ ውጪ በአማራ ክልል በዋግኽምራ ሰቆጣ ከተማ እንዲሁም በኦሮሚያ ሞጆ ከተማ ይህንኑ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ተረጂዎች ወደ ድርጅቱ የሚመጡት ድርጅቱ በሚያስቀምጣቸው መስፈርት ሲሆን መስፈርቱም ልጆቹ ወላጅ አልባ መሆናቸውና እናቶቹ ደግሞ ባል የሌላቸውና ኑሯቸውን በራሳቸው አቅም መደገፍ አለመቻል ናቸው፡፡ ምልመላው የሚካሄደውም ከወረዳዎቹ ጋር በመነጋገርና በመተጋገዝ ነው፡፡
ድርጅቱ አገልግሎቱን የሚሰጠው በአብዛኛው ውጪ ሀገር ካሉ ረጂ ድርጅቶች ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ግን በነዚህ ድርጅቶች ላይ ተንጠልጥሎ መቆየት የማያዛልቅና አስተማማኝ ባለመሆኑ በራሱ ገቢ ለመተዳደር የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ መጋቢት 5 ቀን 2016 ዓ.ም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ለማዘጋጀትና አቅድ ይዟል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጠው በተከራየው የግለሰብ ቤት በመሆኑ ከመንግሥት ቦታ ቢያገኝ ሥራውን አስፍቶ የማስቀጠል ፍላጎትም አለው፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 28/2016 ዓ.ም