13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ከነገ በስቲያ በጋና አክራ መካሄድ ይጀምራል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ከሚሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም በዘጠኝ የስፖርት ዓይነቶች እንደምትሳተፍ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ትልቁ የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ከመካሄዱ አስቀድሞ በርካታ አህጉር አቀፍ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ ይህም ስፖርተኞች ወደ ኦሊምፒክ ከማቅናታቸው አስቀድሞ አቅማቸውን ለመፈተሽ የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ በተወሰኑ ስፖርቶች ደግሞ እንደጣሪያ ውድድርም ያገለግላል፡፡ ይህንን ዓላማው ያደረገው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎችም ከነገ በስቲያ በጋና ዋና ከተማ አክራ እንዲሁም ኩማሲ እና ኬፕ ኮስት አዘጋጅነት ይከናወናል፡፡
እአአ ከ1965 አንስቶ የሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄደው ካለፈው ዓመት ተዘዋውሮ ነው።ውድድሩ በመደበኛ በመርሀ ግብሩ መሰረት ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም ጋና ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ በገጠማት ችግር ተራዝሞ የፓሪሱ ኦሊምፒክ ጥቂት ወራት ብቻ ሲቀሩት የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ 53 ሀገራት ተካፋይ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ የኦሊምፒክ ደረጃን ጠብቆ በሚካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይም በ23 ስፖርቶች የተለያዩ ፉክክሮች የሚደረጉ ይሆናል፡፡ ከተካፋይ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም በ9 የስፖርት ዓይነቶች ልኡካን ወደ ስፍራው ልካለች፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በበርካታ ስፖርቶች እንዲሁም በርካታ አትሌቶችን ያካተተም ነው፡፡ በአጠቃላይ 149 አትሌቶችን የሚያቅፈው የኢትዮጵያ ቡድን በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች የሚፎካከር ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ በውድድሩ ለመሳተፍ ዝግጅት ስታደርግባቸው የቆዩት የስፖርት አይነቶች አሁን ከምትሳተፍባቸውም በላይ የነበሩ ቢሆንም፤ በውድድሩ ውጤታማ የመሆን እድል ተመዝኖ እንዲሁም በአቅም ውስንነት እንዲቀነሱ መደረጉ ታውቋል፡፡
ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም በሚደረገው በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በተለይ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት ውጤታማ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡ የዘንድሮውን ውድድር ለየት የሚያደርገው በዚህ ስፖርት ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት ሩጫ፣ በእርምጃ፣ በዝላይና ውርወራ የምትሳተፍ ሲሆን፤ በዚህም ለአትሌቶች የውድድር እድል ከመፍጠር ባለፈ አቅማቸውን የሚፈትሹበት መድረክም ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ዘንድሮ በሴቶች እግር ኳስ ተሳታፊ ትሆናለች፡፡ ይህም በሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አማካኝነት ነው፡፡ የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ረጅም ርቀት ቢጓዝም የመጨረሻውን ማጣሪያ ማለፍ እንዳልቻለ ይታወሳል፡፡ በዚህም ውጤቱ ምክንያት በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የመሳተፍ እድል ማግኘት ችሏል፡፡
በብስክሌት፣ ቦክስ እና ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርቶችም ጥሩ ተፎካካሪነት ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ውድድሩን ተከትሎ ዝግጅቱ ፌዴሬሽኖች በራሳቸው መንገድ ሲያከናውኑ የቆዩ ቢሆንም በበላይነት ሲያስተባብር የቆየው ግን ስፖርቱን የሚመራው መንግሥታዊ አካል ነው፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ብሄራዊ የስፖርት ማህበራት ጋር በመሆን ባቋቋመው አብይ ኮሚቴ አጠቃላይ ዝግጅቱ ሲመራ እንደቆየ በሚኒስቴሩ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አስታውቀዋል፡፡
ከአዘጋጇ ሀገር የቀረበው የተሳትፎ ጥሪ የዘገየ መሆኑን ተከትሎ ሀብት ለማሰባሰብ የነበረው ጊዜ ጠባብ በመሆኑ ዝግጅቱና የተሳትፎ ሁኔታው ውስን ሊሆን ችሏል፡፡ ከዚህ አንጻር አስቀድሞ የታቀደው በርካታ ስፖርቶች ተሳትፎ እንዲሁም ኦሊምፒክን ታሳቢ ያደረገ ተሳትፎ እንደሚኖርም አብራርተዋል፡፡
የስፖርት ማህበራቱ ውድድሩን ታሳቢ በማድረግ በራሳቸው መንገድ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተከትሎ ሆቴል ያልገቡና አስፈላጊው ድጋፍ ያልተደረገላቸው አሉ። ከዚህም ጋር በተያያዘ በቴክኒክ ኮሚቴው ታይቶ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለውድድሩ የተቀመጠው ዋነኛው ግብ ተሳትፎ ቢሆንም እንደ አትሌቲክስ ባሉ ስፖርቶች ግን ሜዳሊያዎች ይጠበቃሉ፡፡ ተሳትፎውን በሚመለከትም በመሰል መድረኮች ልምድ ማግኘት ቀዳሚው ዓላማ በመሆኑ በውድድሩ ላይ ተካፋይ ከሚሆኑት ስፖርተኞች መካከል አብዛኛዎቹ ተተኪ እንደሚሆኑ የሚታሰቡ ታዳጊና ወጣቶች ናቸው፡፡ ዝግጅቱ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን ያካተተ ሲሆን፤ ሁሉም የልኡክ አባል ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑም ተረጋግጧል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም