በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የአፍሪካን ትንሳኤ ማረጋገጥ ይገባል

ፓን አፍሪካኒዝም፣ የቀደምት አፍሪካ መሪዎች (በተለይም ከዓድዋ ድል ማግስት የተቀነቀነ) እሳቤ ቢሆንም፤ የመላው ጥቁር ሕዝብ የንቅናቄ አብዮት ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ አብዮት ደግሞ፣ አንድ የሆነ አነሳሽና አቀጣጣይ ሃሳብና ትግበራ ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓድዋ ድል ተጠቃሽ ነው። እናም ንቅናቄው ከዓድዋ ድል በኋላ የተቀጣጠለ የጥቁር ሕዝቦች የንቃትና የብርታት፣ የተሃድሶና የአብሮ መቆም ደወል ነው፡፡

ይሄ የትንሳኤ ጽንስ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ከሚባሉ ሕዝቦች ምኩራብ ነፍሶ መላውን አፍሪካ የነካ የአንድ መሆን አቃፊ ሥርዓት ነው፡፡ በበረታ ሃሳብና ተጋድሎ መንጭቶ በትውልድ ብኩርና ላይ ያረፈ ጥቁርነትን ከነፃነትና ከሉአላዊነት ጋር ያስተሳሰረና ያጋመደ አፍሪካዊ ገመድ ነው፡፡

ይህ የፓን አፍሪካኒዝም (አጠር ሲል “አፍሪካኒዝም”) ንቅናቄ በአፍሪካ ምድር መሠረቱን ሲጥል የተነሳበት አላማ ነበረው። የነጭን የበላይነት እሳቤና ተግባር ተዋግቶ በማሸነፍ ለማምከንና የአፍሪካን ማንነትና አንድነት ለመመለስ ከማሰብ የተጀመረ ነው፡፡

በአፍሪካ ምድር የወደቁ እንዲነሱ፣ የተኙ እንዲነቁ፣ የተበላሹ እንዲስተካከሉ የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ የአፍሪካን አንድነት፣ ብሔራዊነት፣ ነጻነት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር፤ እንዲሁም ታሪካዊና ባህላዊ መስተጋብርን ከመፍጠር አኳያ የላቀ ዋጋ ነበረው፡፡ አፍሪካ በጥቁርነቷ የኮራችበት የመነሳት ጊዜም ነበር፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የተበረዙና የተከለሱ ታሪኮችን ከማስተካከልና ነቅሶ ከማውጣት እንዲሁም፤ አፍሪካዊ ማንነትን ከማስቀጠል አኳያ የሚነገር የታሪክ ዐሻራን አሳርፏል፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተጽዕኖው እንዳለ ሆኖ በሥነ ጽሑፍና በባህል በማናቸውም አፍሪካዊ እሴቶች ላይ መነቃቃትን የፈጠረ ቀጣዩን የትውልድ መረማመጃ መንገድ ያበጀ፣ ከሕዝባዊነት አኳያም ወጀበ ሰፊ ንቅናቄን የፈጠረ ነበር፡፡

ይህንን የጥቁሮች ንቅናቄ የነፃነትና የፍትህ ንቅናቄ /ፓን አፍሪካኒዝም / አቅም አግኝቶ ለአፍሪካውያን ተስፋ እንዲሆን የዓድዋ ድል ወሳኝ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል። ድሉ ለጥቁር ሕዝቦች ትግል የይቻላል መንፈስን በማላበስ ትልቅ አቅም ሆኗል። ጥቁሮች ኢትዮጵያ ባትኖር ፓን አፍሪካኒዝም ሆነ የአፍሪካ ህብረት ነፍስ ባልዘሩ ነበር የሚሉም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ በበረታ ሃሳብና ሚዛናዊነትን በተላበሰ አመክንዮዋ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከትላንት እስከዛሬ ለምዕራባውያን ፈተና ሆና ቆይታለች፡፡ ዛሬም እንኳን አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን እያሰቡና እሷን እያዩ የሚበረቱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መኖር ለአፍሪካ ኩራት ቢሆንም፣ ይሄን የማይሹ የምዕራቡ ዓለም አካላት መኖራቸው ግን የሚካድ አይሆንም፡፡ የአብዛኛዎቹን የአፍሪካ ሀገራት የፖለቲካ አስተሳሰብ ብናይ በምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት የቆሸሸ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምዕራባውያን አፍሪካን ለራሳቸው እንድትመች አድርገው ሊሰሯት ጥረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ፖለቲካና ኢኮኖሚውን ብናይ በነሱ ሃሳብ አፍላቂነት የሚዘወር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ አፍሪካዊ እሳቤን ይዞ አፍሪካን ለመለወጥ የሚጥር አፍሪካዊ መሪ በአህጉሪቷ ያለመበርከቱ ምስጢርም ከዚህ የራቀ አይሆንም፡፡

ሊቢያን የመሳሰሉ ጠንካራ ኢኮኖሚን ገንብተው ለዜጎቻቸው የተንደላቀቀ ኑሮን ያመቻቹ ሀገራት ሳይቀር በአሁን ባሉበት ሁኔታ ውስጥ መገኘታቸውም የዚህ ሁነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በርካቶች አፍሪካዊው ቼኮ ቬራ ይሉት የነበረው የእነ ቶማስ ሳንካራ እውነትም ከዚሁ የሚተሳሰር ነው፡፡

እነዚህ እውነቶች የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ማምከኛ ክስተቶች ተደርገውም ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ለአብነት፣ ቶማስ ሳንካራ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ ሆኖ አፍሪካን ከነጮች የበላይነት ለመጠበቅ ያልከፈለው መስዋዕት አልነበረም። ጥቅምት 15/1987 በሴራ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ለአፍሪካ በየቀኑ የሞተ አብዮተኛ ነበር፡፡

አፍሪካ ውስጥ እናት ሀገሩ ቡርኪና ፋሶ በፈረንሳይ የቅኝ ግዛት ተጽዕኖ እንደምትሰቃይ ሁሉ፣ ሌሎችም በቅኝ ገዢዎች የሚሰቃዩ የአፍሪካ ሀገራትን ለመታደግ ሲል የፈረንሳይን መንግሥት የበላይነት የሚገዳደር የፀረ ኢምፔሪያሊስት ፖሊሲን ይፋ ያደረገ መሪ ነበር፡፡ እንግዲህ ይሄ ሰው ነው በፖለቲካ ደባ የተገደለው፡፡ በዚህ መልኩም አፍሪካ ለዘመናት በተንኮልና ሴራ ውድ ልጆቿን ስትገብር ኖራለች፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም የተመሰረተውም ከዚህ መሰሉ ጫናና ሴራ ራስን ለመታደግ ሲባል ነው፡፡

አንዳንድ ኃይሎች የአፍሪካ መንግሥታት ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው መልካም ሲሰሩ ማየትም መስማትም አይፈልጉም፡፡ የእነሱ ፍላጎት አፍሪካ ኃይልና የአመራር አቅም አጥታ በፖለቲካው ምህዳር እጃቸውን አስገብተው እንዳሻቸው መዘወር ነው፡፡ የነሱ ፍላጎት አፍሪካ ለምንም ነገር ወደ እንድታንጋጥጥ አድርጎ መፍጠር ነው፡፡ የነሱ ፍላጎት ትውልዱ የውጭ ኃይል አምላኪ እንዲሆንና የራሱን ጥሎ የነሱን አንጠልጥሎ ራሱን አጥቶ ማየት ነው፡፡ ከትላንት እስከዛሬ የተራመዱባቸው ጎዳናዎች በአፍሪካ ሕዝቦች የህልውና መና የተጠረጉ ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት ስልጣኔአቸው በአፍሪካ አንጡራ ሀብት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በኢፍትሀዊነት የተጓዙበት መንገድ ዛሬ ላይ አፍሪካን አራቁቶ እነሱን ግን ፈላጭ ቆራጭ አድርጓቸዋል፡፡ ይሄ ጭቆና ነው መላውን ጥቁር ሕዝብ አነሳስቶ ፓን አፍሪካኒዝም እንዲፈጠር መሠረት የሆነው፡፡

እናም እኛ አፍሪካውያን ዛሬም በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ዳግም መንቃት፣ ዳግም መነሳት አለብን፡፡ ይሄን ስናደርግ ግን ዋጋ ለመክፈል ጭምር በመዘጋጀት ነው፡፡ ምክንያቱም እሳቤው ላቅ ያለ አፍሪካዊ ልዕልናን የሚፈጥር እንደመሆኑ ሊጥለው የሚገፋው ኃይል አያጣምና ነው፡፡

እነቶማስ ሳንካራ እኮ ለአፍሪካ ዋጋ የሌላቸው ጥቅም የለሽ ቢሆኑ ኖሮ በአጭር የመቅረት እጣ ፈንታ አይገጥማቸውም ነበር፡፡ የነዚህን ብርቱ ሰዎች የራቀ አስተሳሰብና አፍሪካዊ ራዕይ ስለሚታወቅ ነው የሴራ ሰለባ የሆኑት፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ የውጭ ኃይሎች አፍሪካን የሚያጠቁት በገዛ አፍሪካውያን መሆኑ ነው፡፡

እሳቱን አይለኩሱም ያቀብላሉ እንጂ፤ የተቀበለውን እሳት ይዞ ራሱን ለሚያቃጥለው ኃይል አቅምን ይሰጣሉ፡፡ እናም እርስ በእርሱ ሲቀጣጠል ከዳር ቆመው ያያሉ፡፡ በመጨረሻም እሳት አጥፊ ሆነው ይከሰታሉ፡፡ በዚህ መልኩ ነው በአፍሪካ ውስጥ ለአፍሪካ ሞገስ የሆኑ የነፃነት አርበኞች በአጭር የቀሩት፤ ሀገራት ወደኋላ ለመንሸራተት የተገደዱት፤ አፍሪካውያን ሀብታቸውን ተጠቅመው መልማትና መበልጸግ ሲችሉ፤ ዛሬም በድህነት ውስጥ ሆነው የበዪ ተመልካችና ተመጽዋች ሆነው የሚታዩት፡፡

በአፍሪካ ምድር ለጥቅም ሲባል ወንድምን መግደል የተለመደ ነው፡፡ ጠላቶቻችን ለዘመናት በዚህ መንገድ ነው እያጠቁን ያሉት፡፡ ቶማስ ሳንካራ የተገደለው በጓደኛው ነበር፣ መሀመድ ጋዳፊም በተመሳሳይ መልኩ ነበር ወደ መቃብር የወረደው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በውጭ ኃይሎች ቆስቋሽነት በቅርብ ሰዎቻቸው የተገደሉ በርካት የነፃነት አርበኞች እዚም እዛም አሉ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ የነጮችን የበላይነት እንደምስስ የምንለው በምክንያት ነው፡፡ ለዚህ ነው ወንድማማችነት ያሻናል የምንለው፡፡ ለዚህ ነው በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ውስጥ ተቃቅፈን በሴራ ያንቀላፋችውን አፍሪካ እናንቃ የምንለው፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም በአፍሪካ ምድር ዳግም መለምለም አለበት፡፡ በተለይ አሁን ላለችው አፍሪካ የአንድነት መንፈስ ያስፈልጋታል፡፡ እንደ ቶማስ ሳንካራ ዓይነት ለአፍሪካ ድምጽ የሆኑ፣ ስለ አፍሪካውያን የሚሟገቱ ግለሰቦች ያስፈልጉናል። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት እስከዛሬ የውጭ ተጽዕኖችን አሻፈረኝ ስትል የመጣች ሀገር ናት። አሁንም በማናቸውም የውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ ሀገራትን እድል ነስታለች፡፡ አለፍ ሲልም በአፍሪካ ጉዳይ ከአፍሪካ ሌላ ሊወስን የሚገባው ኃይል ሊኖር አይገባም የሚለው አቋሟን እንደያዘች ዘልቃ ፍሬውን እያየን እንገኛለን፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም በዚሁ የእሳቤ መልክ የምንገለጥ ነን፡፡ ለምሳሌ፣ የተለያዩ ኃይሎች በኢኮኖሚ የዳበረ ክንዳቸውን ተጠቅመው ባልተፈለገ አካሄድ የመጡብንን የውጭ ጫናዎች አልቀበልም ማለታችን ከፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ አንዱ ነው፡፡ እናም የቀድሞዋ አፍሪካ፣ የነፃነት ትንሳኤዋን ያየችው በኢትዮጵያ በኩል ነበር፡፡ አዲሷ አፍሪካም ዳግም ትንሳኤዋ በኢትዮጵያ በኩል የሚመጣ እንደሆነ ማመን ያስፈልጋል፡፡

እኚህ የለውጥና የትንሳኤ ሃሳቦች ፍሬ እንዲያፈሩ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ አፍሪካዊ የሆኑ ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ግለሰቦች ቁርጠኛ ሆነው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ለምንድነው እነቶማስ ሳንክራ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚነሱት? ለምንድነው ስለ አፍሪካ አንድነት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲመጣ ብቻ የምንጮኽው? የአፍሪካን ጉዳይ የሁልጊዜ ጉዳያችን ማድረግ ለምን አቃተን? ብለን ብንጠይቅ፤ ምላሹ ድምጾቻችን ያልተሰሙት፣ ሃሳቦቻችን ፍሬ ያላፈሩት ጊዜ እየጠበቅን ስለምንጮህና ስለምንሰባሰብ ነው የሚል ይሆናል፡፡

አፍሪካዊነት እስኪያብብ ድረስ፣ ፓን አፍሪ ካኒዝም እስኪቀጣጠል ድረስ፣ የምዕራባውያን የበላይነት እስኪከስም ድረስ በጋራ መጮህ አለብን፡፡ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ሃሳቦችን ማራመድ አለበት። አፍሪካ ወደ ፊት እንድትራመድ እነቶማስ ሳንካራ ሞት መነሳት የለባቸውም፡፡ በአፍሪካ ጉዳይ እንቅልፍ ያጡ በርካታ ቶማስ ሳንካራዎች አሉ፡፡ መጪው ጊዜ አፍሪካ ከእንቅልፏ ነቅታ ያስተኟትን የምትገዳደርበት ዘመን እንዲሆን በበላጭ ሃሳብ መትጋት ይኖርብናል፡፡

አፍሪካ ለችግሮቿ መፍትሔ ያላመጣችው ለምንድነው የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ የሚሆነው ቁርጠኝነት ማጣት ነው፡፡ በብዙ ነገር ላይ ስብሰባ ተቀምጠን ተወያይተናል፤ ለውጥ ግን አናመጣም። ተግባር ላይ ሰነፎች ነን፡፡ ቁርጠኛ ቢኮን ኖሮ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካን ችግር ለመፍታት በቂ ነበር፡፡ ግን ያ ሲሆን አይታይም፤ ካለም ሙከራ ነው፡፡ ይሄ ያልሆነው ግን ችግሮቻችን ከአቅማችን በላይ ሆነው አይደለም፡፡ ችግሮቻችን እያሰቃዩን ያሉት ለለውጥ የሚሆን ቁርጠኛ አቋም ስለሌለን ነው፡፡

አፍሪካ ሁለት መልክ አላት፤ ከፓን አፍሪካኒዝም መመሥረት በፊት ያለችውና ከተመሠረተ በኋላ የተፈጠረችው አፍሪካ፡፡ ከፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በፊት የነበረችው አፍሪካ በብዙ ፋሽስታዊና፣ አፓርታዳዊ ሥርዓት እንዲሁም በነጮች የአስተሳሰብ የበላይነት የወደቀችበት ጊዜ ነበር፡፡ ብዙዎች ያን ጊዜ ሲያስታውሱት የጨለማው ዘመን በማለት ነበር፡፡ የአሁኗን አፍሪካ የፈጠራት በኢትዮጵያ ምሳሌነት በጥቁር አፍሪካውያን የነፃነት ታጋዮች ድምጽ ነው፡፡ እርግጥ የአሁኗ አፍሪካ ልትመልሳቸው የሚገቡ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩባትም፤ በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የጠለሸ ነፃነቷን ማግኘቷ ግን የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በአንድ ቃል የአሁኗ አፍሪካ ጭቆናና የነጮች የበላይነት ባስመረራቸው ጥቁሮች የተፈጠረች ናት፡፡

አሁንም ቢሆን አፍሪካ የታደሰና ኃይል የተላበሰ አንድነት ያስፈልጋታል፡፡ እንደ ፓን አፍሪካኒዝም ያሉ የንቅናቄ መድረኮችና ሃሳቦች ያስፈልጓታል። ሞትና እንግልትን የማይፈሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ግድ ይሏታል፡፡ አንቆ ከያዛት የምዕራባውያን አስተሳሰብ እስካልተላቀቀች ድረስ አፍሪካ ሁሌም ምጽወተኛ ናት፡፡ ራሷን ችላ መቆም አትችልም። ኃይሏን፣ ነፃነቷን እንድታገኝ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ቁርጠኛ ሀገራት፣ እንደ ቶማስ ሳንካራ ዓይነት ሞትን የማይፈሩ ትውልዶች ያስፈልጋሉ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን የካቲት 27/2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You