
ዛሬ ከ”ቆጭቆጫ“ው አገር ወላይታ እንግባና እንደ ቆጭቆጫ በሚያቃጥለው የባህል ፍቅር ውስጥ እንቦርቅ። ቆጭቆጫ የወላይታዎች ልዩ ባህላዊ የምግብ ማባያ ነው። በወላይታ ባህል ማንኛውንም ሰው ምግብ ከመብላቱ በፊት የምግብ ፍላጎት (አፒታይት) እንዲቀሰቀስ ለማድረግ ቆጭቆጫ ከዳቦ ጋር በገበታ ይቀርብለታል። እያቃጠለ የሚወደድ፤ ከገበታ የማይነጥፍ ይሄ የምግብ ማባያ ታዲያ ምግብን በደንብ ለመመገብ በር ከፋች በመሆኑ ተወዳጅ ነው።
እኛም ስለዚህ ውብ ብሔረሰብ ባህል ስናነሳ ቆጭቆጫን መግቢያችን አደረግን እንጂ ዋናው ጉዳያችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ዓለምን እያስደመመ ስላለው ባህላዊ አልባሳቱ ነው።
ከወንዱ አለባበስ እንጀምር። በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት የባህሉ አዋቂዎችን አነጋግረናል። ሁለቱም በሙዚቃው ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ናቸው። እናም አለባበሱ ምን እንደሚመስል በሚገባ አስረድተውናል። በመጀመሪያ ያነጋገርነው በዞኑ የባህልና ዘመናዊ ኪነት ቡድን አስተባባሪ እንዲሁም ሙዚቀኛና የማስታወቂያ ባለሙያው አክሊሉ አዶላይ ናቸው።
አቶ አክሊሉን በሕገወጥ የሕፃናት ዝውውር ዙሪያ «አሳዋላማይቶስ» በሚል 2006 ዓ.ም የለቀቀው ነጠላ ዜማው ከሕዝብ ጋር አስተዋውቆታል። ለወላይታ ድቻ በተለያየ ጊዜ በሚለቃቸው ነጠላ ዜማዎችም ይታወቃል። እናም በአለባበሱ ዙሪያም ብዙ ነገር ያውቃል። ስለዚህ በጠየቅነው መሠረት ስለ ወላይታ ባህላዊ አልባሳት እንዲህ ሲል ነግሮናል። በወላይታዎች ዘንድ ወንዶች የሚለብሱት አልባሳት የተለያየ ሲሆን፤ ስሙም ሃድያ በመባል ይጠራል። «ያ» ላልታ ትነበባለችም ብሎናል።
እርሱ እንደሚናገረው፤ ሃድያ የተባለው የወንዶች ልብስ ዓይነት ያለው ሲሆን፤ የሚለየውም በቀለም አጠቃቀሙ ነው። ድንጉዛ ሃድያ፣ ሴሪያ ሃድያ፣ ጉቱማ ሃድያ፣ ጉመራ ሃድያ እየተባለም ይጠራል። የቀለምና የስም አሰጣጡ ሁኔታ ሰማያዊ፤ ጥቁር፤ ደብዛዛ ቢጫ፣ ደብዛዛ ጥቁር እየተባለ ይለያል። ልብሱም የትኛው እንደሆነ የሚታወቀው በክሩ ልዩነት ነው።
በወላይታ ሻንካ ገደዋ (አዳኞች) የሚለብሱት አለባበስ በራሱ የተለየ ሲሆን፤ ነብር ሲገድሉ ጆሯቸው ላይ ሎቲ መሰል ከብር የተሰራ ጌጥ ያደርጉና ለባህላዊ ልብሱ ልዩ ውበት ያጎናጽፉታል። ከልብሳቸው ላይ ቆዳውን ሲደርቡ ደግሞ ይበልጥ ጀግንነታቸው ይገለጻል።
«ወንዶች ልብሱን ብቻ ለብሰው አይደለም የሚንቀሳቀሱት ሙሉ ለመሆን በእጃቸው የሚይዟቸው ቁሳ ቁሶችም አሉ» የሚለው አቶ አክሊሉ፤ ከእነዚህ መካከል «ገሳ ጉንቧ» የሚባል አንዱ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ቁስ ንጉሥ የሚይዘው በትር ሲሆን፤ ከጫፉ ላይ ከብር የተሰራ ክብ መሳይ ጌጥ ይደረግበታል። ዛሬ ዛሬ ይህንን የአለባበስ ሥርዓት ትልልቅ አባቶች ይከተሉታል።
የወላይታ ወንዶች በአዘቦት ቀናት ብልኮ ይለብሳሉ። እንስቶች ደግሞ ይህንኑ ብልኮ ከወገባቸው በታች ያገለድሙታል። ከላይ ደግሞ ጥብቆ የምትባለውን በባህሉ ያጌጠች ከታችኛው ብልኮ ጋር የምትመሳሰል ያጠልቃሉ። ሻሽ ማሰርም በባህሉ ዘንድ ግድ ነው። አስተሳሰራቸውም ከሌሎች ብሔረሰብ ባህል ይለያል። ይህም ቢሆን ከተለበሰው ልብስ ጋር የሚመሳሰል መሆን እንዳለበት ይናገራል።
በወላይታ ሴቶችን በተመለከተ «ግሟ» የሚባል ሥርዓት አለ። ይህ ሥርዓት የሚደረግላት ሴት ባሏን አጠንክራ ምርታማና ባለሀብት ያደረገች ነች። በእርሷ ጥንካሬ ለዚህ በቅተሃል ሲባል ለእርሷ ክብር ለመስጠት የሚፈጸም ነው። በተለይም ከመቶ በላይ ከብት የቆጠረ ባል ያላት እንስት ይህ እንዲፈጸምላት ይፈቀዳል። በባህሉ ደግሞ «ዳላ» በመባል ይጠራል። እናም ይህንን ሥርዓት የፈጸመች እንስት ከሌሎች ሴቶች የተለየ አለባበስ ትለብሳለች።
ግሟ የሚባለውን ሥርዓት የፈጸመች ሴት «ጉፌ ጉንቧ» የሚባል በትር የምትይዝ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ይህ በትር የሚፈቀደው ለንጉሥ ነው። ሆኖም እርሷ ክብሩ ስላላት እንድትይዝ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ «ጎዶልአ ሞንጋ» እየተባለ የሚጠራውን የአንገት ጌጥ ታደርጋለች። ምግዷ በመባልም የሚጠራውን ቀለበት በጣቷ ላይ ታጠልቃለች። ጆሮዋ ላይ ደግሞ በለጫ ዱንዳ የሚባል የጆሮ ጉትቻ እንደምታደርግ አቶ አክሊሉ ነግሮናል።
የጋሞ ባህላዊ ሙዚቃ ተጫዋችና ተወዛዋዡ አቶ መላኩ ጉቾ ስለ አልባሳቶቹ እንዲህ ይላሉ። የወላይታዎች አለባበስ ከጋሞዎች ጋር ቀረቤታ ያለው ነው። በተለይም ወንዶቹ የሚለብሱት ብዙው ይመሳሰላል። ጋሞች ከአንበሳና ከነብር ቆዳ የሚሰራውን ልብስ በመደበኛው የባህል ልብስ ላይ የሚደርቡት በወላይታዎችም ዘንድ አዳኝና ጀግና ይለብሰዋል። ይህ ደግሞ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው አንዱ ማሳያ ነው ይላሉ።
እንደ ባህላዊ ሙዚቃ ተጫዋቹ ገለጻ፤ ጋሞና ወላይታዎች የሚለብሱት ልብስ ቀለምም ተመሳሳይ ነው። ለዚህም የጥንት አባቶች የልፋት ውጤት ነው። ከእንጨት ቢጫ ቀለምን፤ ከገል ቀይ ቀለምንና ከጥላሸት ደግሞ ጥቁር ቀለምን በመፍጠር ውብ ልብስ ይሰራሉ። ይህም ዘመን ተሻገረና ዛሬ ላይ የሚያመሳስለው ነገር ተፈጠረ።
በጋሞዎች ዘንድ «ጎንደሌ» እየተባለ የሚጠራው ከጉማሬ ቆዳ የሚሰራው ጋሻም በወላይታዎችም ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውልና ባህላዊ አልባሳት የሚዋብበት ነው። በእርግጥ አገልግሎቱ ለመከላከል ነው። ሆኖም ዛሬ አልባሳቱን ለማድመቅ እየዋለ ይገኛል። ሌላው «ጸንበሮ» ወይም «ሆሮርሳ» የሚባለው ሲሆን፤ በአማርኛው ጦር ማለት ነው። ይህም ቢሆን እንደ ጋሻ ሁሉ ለአደን በሁለቱም ቦታ የሚውል ነው። ለልብስ ማድመቂያ ይሆን ዘንድ ትልልቅ አባቶችም ይይዙታል።
ባህል ተወራራሽ ነው። ድንበር አይወስነውም። የወላይታ አልባሳትም ከጋሞ ጋር የመመሳሰላቸው ምስጢር ይኸው ነው የሚሉት ድምጻዊው፤ በጋሞኛ «ለለሼ» ወይም ብልኮ ተብሎ የሚጠራው በሁለቱም ቦታ ብርድን ለመቋቋም ሲባል በአዘቦት እንደሚለበስ ያነሳሉ።
«በአንድ የኢትዮጵያ ገጠራማ ቦታ ላይ ያለን ሸማኔ ከሸገሩ ወይም ከውጪ ዲዛይነሩ ጋር ስናወዳድረው ልብስን በጥሬ ዕቃው ሳይሆን በአለባበስ ምቹነቱ ማገናኘትን እንድንመለከት ያስገድደናል» የምትለው ደግሞ ዓለም አቀፍ ዲዛይነርና ሞዴሊስት ሰናይት ማሪዮ ናት።
እንደእርሷ ማብራሪያ፤ ባህል በዚህ መልኩ ካልታየ ዘመናዊነትና ባህል ለየቅል እንዲጓዙ ያደርጋቸዋል። ባህላዊ አልባሳትን ለሀገሬውም ለውጪውም ተደራሽ ለማድረግም አይቻልም። በዚህም ምርታማነትን ከፍ ማድረግ ሳይቻል ይቀራል። ተጠቃሚነት ከሌለ ደግሞ አምራቹ ይጠፋና ባህልም አብሮ ይቀበራል። እናም ሁለቱን አጣጥሞ መጓዝ ግድ ይሆናል ትላለች።
«ዘመናዊ አልባሳትን ለማስለመድ ጊዜ ይወስዳል፤ ነገር ግን ከምናውቀው ባህል ጋር እንዲተሳሰር ማድረጉ ይበልጥ ተጠቃሚነትን ያመጣልና መሞከር ያስፈልጋል» የምትለው ዲዛይነር ሰናይት፤ ባህል ለከተሜም ለገጠሬውም ውብ መሆኛ መንገድ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ባህላዊ አልባሳት በዋናነት ይነሳሉ። በዲዛይን እንዲመቹና የዘወትር እንዲሆኑ ማድረግ ከተቻለ ሁሉም ይመርጣቸዋል። ለዚህም ማሳያው የወላይታ ልብሶች በዓለም ደረጃ መለበስ መጀመራቸው እንደሆነ ታነሳለች።
የኢትዮጵያውያን ባህላዊ አልባሳት ለሥራ ምቹ ባለመሆናቸው የክት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ስለዚህም ይህንን ልምድ ወደ ዘወትር ለመቀየር የአልባሳቱን ዲዛይን የቀን ተቀን ማድረግ ይጠበቃል። ባህሉ የተጠነሰሰባቸው አካባቢዎች እንዲወዱት ማድረግ ላይ መሰራት ከተቻለም ብዙዎች ይወዱታል ትላለች። የወላይታ አልባሳት በየትኛውም ዕድሜ ላይ ያለ ሰው በፈለገው ዓይነት እያሰራ እንዲለብሰውና እንዲወደው የሆነው ዘመኑን የዋጀ እንዲሆኑ ተደርገው በመሰራታቸው ነው። ይህ ደግሞ ከአገር አልፎ የውጪ ዜጎችም ጭምር እንዲምነሸነሹበት አድርጓቸዋል። እናም ለትንሽ፣ ለትልቅ የሚባለውን ባህሉን ሳይለቅ መስራት ለአልባሳቱ እውቅና ላቅ ያለ ዋጋ እንዳለው ትገልጻለች።
ባህል ዘመናዊነት ከነካው ለምርምር ያግዛል። የኢትዮጵያ ባህል ደግሞ ቢዝቁት የማያልቅ በመሆኑ አንዱን ከአንዱ በመቀላቀል ጥበብ የፈለቀባት መሆኗን ማሳየት ቀላል ነው። እናም አብዛኛው ባህላዊ አልባሳት በአግባቡ እየተዋወቀ አይደለምና በወላይታ አልባሳት የተጀመረው የማስተዋወቅ ሥራ በሌሎችም ጠንከር አድርጎ መሰራት ይገባል። የባህል አልባሳትን ፈትሾ ማውጣት «አልባሳት እኛን ወክለው እንዲለበሱ ማድረግ» ነው።
ከአህጉረ አፍሪካ ከተውጣጡ 40 ሞዴሊስቶች ጋር ተወዳድራ ለሽልማት የበቃችው በወላይታ አልባሳት እንደሆነ የምትናገረው ሰናይት፤ «ዓለም ላይ አፍሪካዊት የባህል አስተዋዋቂ» የሚለው ስያሜ ከየትም አልመጣም፤ የወላይታን ባህል በዘመንኛ ሰርቼ ጣሊያኖችን በማልበስ ለእይታ ስላቀረብኩ ነው ብላለች።
በሕይወታችን አዲስ ነገር ሲባል ደስ የሚለንን ያህል ለመቀበልም ዝግጁ ያልሆንን ብዙዎች አለን የምትለው ዲዛይነር ሰናይት፤ ባህሉን ሳይነኩ ለእነርሱ በሚመች መልኩ የሚቀርቡትንም መጥላት እንደማይገባ ትናገራለች። በተለይ የያዝነውን አሮጌ ነገራችንን የሚያስለቅቅ አዲስ ነገር ስጋት ሊሆንብን እንደማይገባ ታስረዳለች።
እኛም ጊዜው በአዲስነቱ ሲቀጥል እኛ በድሮ ማንነታችን እንዳንጓዝ ዘመኑን በዋጀው ባህል ልንታደስ ይገባል። የወላይታው ባህል በዚህ መልኩ እየተጓዘ ነውና ሌሎችም ይህንን ያድርጉ በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው