በስኮትላንድ ግላስጎው ለሶስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ባልተለመደና በአዲስ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ በማስመዝገብ ፈጽማለች። በሴቶች 800 ሜትር ወጣት አትሌት ጽጌ ድጉማ እንዲሁም 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ኃይሉ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስመዝግበዋል።
ኢትዮጵያ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና በ800 ሜትር ውድድር ብቸኛው የድል ታሪካ በሞሃመድ አማን የተጻፈ ነበር ። መሃመድ አማን በ2013 የዓለም ቻምፒዮና ኢስታምቡል እና ሶፖት ላይ በቤት ውስጥ ውድድር በተከታታይ ባለድል ከሆነ በኋላ ለዓመታት ይህንን ታሪክ የሚጋራ አትሌት ሳይገኝ ቆይቷል ። በዘንድሮው ቻምፒዮና ግን ድንቅ ብቃት ላይ በምትገኘው ወጣት አትሌት ጽጌ ድጉማ የርቀቱ ሌላኛው ድል ሊመዘገብ ችሏል።
አዲሷ ኮከብ ውድድሩን ተቆጣጥራ በመሮጥ የመጨረሻውን ዙር በፈጣን አሯሯጧ ልዩነት በመፍጠር አሸናፊ ልትሆን ችላለች። የ23 ዓመቷ አትሌት ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተገኘች ሲሆን፤ የጥሩነሽ ዲባባ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ፍሬ ናት። አሁን ላይ ለንግድ ባንክ አትሌቲክስ ክለብ በመሮጥ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ተስፋዋን በማሳየት ላይ የምትገኝ ወጣት ናት።
በዚህ የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ውድድሯን በቤልጂየም አድርጋ በአሸናፊነት ስታጠናቅቅ፤ በቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር ደግሞ 1ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ66 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ፈጣን ሰዓት በመግባት አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል ።
አትሌቷ እአአ በ2017 በአልጄሪያ አዘጋጅነት በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በ200 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማጥለቅ ችላ ነበር። በ400 ሜትር ደግሞ ከ2019 እስከ 2022 በተከታታይ በኢትዮጵያ ቻምፒዮና የሜዳሊያ ባለቤት ሆና ነበር የቆየችው ። በረጅም ርቀት አትሌቲክስ ላይ በተመሰረተው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አዲሳ እንቁ አዲስ ነገር ማስመዝገቧን ቀጥላለች።
ልቃ በታየችበት በግላስጎው ዓለም ቻምፒዮናም ርቀቱን 2:01.90 በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ በቻምፒዮናው ሁለተኛውን ወርቅ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች። ከውድድሩ በኋላም ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በነበራት ቆይታ ‹‹ውድድሩ ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ የምገልጽበት ቃላት ይቸግረኛል። የተጠቀምኩት የአሯሯጥ ዘዴ ወደፊት እንድሄድ በማስፈንጠር አሸናፊ እንድሆን አድርጎኛል። ወደ ውድድሩ ስመጣ እንደማሸንፍ አውቅ ነበር፤ ምክንያቱም ጠንካራ ዝግጅት ሳደርግ ነበር። ከዚህ በኋላ ትኩረቴ ኦሊምፒክ ነው፤ የወርቅ ሜዳሊያውን በድጋሚ ወደ ሀገሬ መውሰድ እፈልጋለሁ›› በማለት ተናግራለች።
ከሁለት ዓመት በፊት ቤልግሬድ ላይ በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው ፍሬወይኒ ኃይሉ ደግሞ በ1ሺ500 ሜትር ሌላኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ማስመዝገብ ችላለች። በአሳማኝ ብቃትም የውድድሩ ፈርጥ መሆኗን አስመስክራለች። በቤት ውስጥ የዙር ውድድር ሌቪን እና ቱሪን ላይ አሸናፊ የነበረችው የ23 ዓመቷ አትሌት በቻምፒዮናው ርቀቱን ለማጠናቀቅ 4:01.46 የሆነ ሰዓት ፈጅቶባታል። ድሏን ተከትሎም አትሌቷ ‹‹ይህ ውጤት ለእኔ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል ነው። ለዚህ ያበቃኝ ደግሞ በስልጠና ቡድናችን ውስጥ በመተጋገዝ መስራታችን ነው። ጠንክረን መስራታችን ለውጤት አብቅቶኛል፤ በቀጣይ ለኦሊምፒክም ከዚህ በተሻለ ጠንክረን እንሰራለን›› ስትል አብራርታለች።
የተቀሩት ሜዳሊያዎች በሁለቱም ጾታዎች 3ሺ ሜትር የተገኙ ሲሆን፤ በርቀቱ እጅግ ትጠበቅ የነበረችው አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ የብር ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ጠንካራ ፉክክር በታየበት የወንዶች ውድድርም የርቀቱ የመጨረሻዎቹ ሜትሮች ላይ በነበረው ከባድ ፉክክር የብር ሜዳሊያው ለጥቂት ከሰለሞን ባረጋ እጅ ሊወጣ ችሏል። በዚህም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ አራት ሜዳሊያዎች በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ፈጽማለች።
ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው በ800 ሜትር፣ በ1500 ሜትር እና በ3000 ሜትር በሴትና በወንድ በአጠቃላይ በ8 ሴቶች እና በ5 ወንዶች በድምሩ 13 አትሌቶችን በመያዝ ነው የተካፈለችው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም