የሀረሪ ሴቶች የእጅ ጥበብ ሥራ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን

ሀረሪዎች ቤት በድንገት የገባ እንግዳ ዓይኑን ከቤቱ ግድግዳ ላይ መንቀል አይችልም። በተለያየ ቀለማት የተለያየ መጠን ያላቸው በግድግዳ ላይ የተሰቀሉ የተለያዩ የስፌት ጌጣጌጦች በእጅጉ ትኩረት ይስባሉ። ስፌቶቹ ለቤቱ ድምቀት ከመስጠታቸው በተጨማሪ ውብ በመሆናቸው አንዱን ከሌላው ለማስበለጥ ይቸግራል።

በጥንቃቄ የተሰሩ መሆናቸው የቀለም አገባባቸው፣ የሥራቸው ጥራት ምስክር ነው። እነዚህ የእጅ ጥበብ ውጤቶች የሀረሪ ሴቶችን የሚያስመሰግኑም ናቸው። የእጅ ጥበብ ውጤቶቹ ለሀረሪዎች መለያም ሆነዋል። በሀረሪ በስፌት የሚሰሩ ጌጣጌጦች ልዩ ቦታና ትርጉምም አላቸው።

እነዚህን የእጅ ሥራዎች በሀረሪዎችና ሀረሪዎች ብቻ የሚታወቁና የሚሰሩ (ዲዛይን) የተደረጉ ናቸው ሲሉም የናቢዳን ኮሌጅ ዲን ወይዘሮ ፍርዶስ ቶፊቅ ይገልጿቸዋል። እርሳቸው እንዳሉት የስፌት ዓይነቶች ወደ 27 ናቸው። ከስፌቶቹ መካከልም በሀረሪ ባህል ሀመትሙት የሚባል የስፌት ዓይነት አለ። አንዲት ያገባች ሴት በሙሽርና ጊዜዋ ለባሏ እናት (ለአማቷ) በስጦታ የምታበረክተው የስፌት ዓይነት ነው።

በሀረሪዎች ባህል ያገባች ሴት ጫጉላ ቤት የምትቆየው ለአንድ ዓመት ነው። አማቷ ዓመት ሙሉ የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው። ሙሽራዋ ደግሞ ሀመትሙት የተባለውን ስፌት በአንድ ዓመት የቆይታ ጊዜዋ ሰፍታ ጨርሻ ለአማቷ በስጦታ ታበረክታለች። እያንዳንዱ ስፌት እንዲህ ያለ ትርጉም፣ ባህላዊ፣ ሥርዓትና ወግ አለው። አገልግሎቱም ይለያያል። ስፌቶቹ በመጠንም በይዘትም ይለያያሉ።

አሁን ላይ እንደጥንቱ ባህልና ወጉን ጠብቃ በአማቷ ቤት አንድ ዓመት ተቀምጣ ሀመትሙት የተባለውን የስፌት ዓይነት ሰፍታ ለአማት በስጦታ የምታበረክት ሙሽራ ማግኘት ከባድ ሆኗል። ባህሉ እየቀረ ነው ማለት ይቻላል ። እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ሀመትሙት የተባለውን ስፌት ለአማት በስጦታ ማበርከት አልቀረም። ሙሽራዋ ሰፍታ ከመስጠት ይልቅ ከገበያ ገዝታ ነው የምታበረክተው። ይህ ሁኔታ እየተለመደ በመምጣቱ በምትኩ ገበያው ነው የደራው። ህመትሙት የተባለው የስፌት አይነት 30ሺ ብር ዋጋ እየተጠየቀ ይገኛል።

የሀረሪ ሴት ስታገባ የተለያዩ የስፌት ዓይነቶች ያስፈልጓታል። በቀደመው ጊዜ እናቶች በቤታቸው ውስጥ ይሰፉ ስለነበር ገበያው አይታወቅም። ልጆችም የእናታቸውን ስለሚከተሉ ክፍተቱ አልነበረም። አሁን ላይ ግን የመተካካቱ ነገር እየቀነሰ በመምጣቱ ስፌቶች ወደ ገበያ በመውጣታቸው በዋጋ ውድ እየሆኑ መጥተዋል።

ወንዶች ሙሽራ ሲሆኑ እንዲሁ ሙሽራነታቸውን የሚገልጽ በእጅ የተሰራ ቆብ ነው የሚያደርጉት። ቆቡ በአዘቦቱ ጊዜ ከሚደረገው በተለየ ዲዛይን ነው የሚሰራው። የእጅ ጥበብ ሥራውም ከበድ ይላል። ቀድሞ በቤት ውስጥ ሴቶች ያዘጋጁት የነበረው የወንድ ሙሽራ ቆብ አሁን ላይ ወደ ገበያ ወጥቷል።

በመሆኑም ወደ ገበያ ወጥቶ ግዥው ከፍተኛ እየሆነ ነው። የአንድ ቆብ ዋጋም እስከ 15ሺ ብር እየተሸጠ ነው። እነዚህ የሀረሪ መገለጫ የሆኑ ሀገር በቀል እሴቶች ተዳክመው እንዳይጠፉ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ለማስቻል ሥልጠና እየተሰጠ ቀጣይነት እንዲኖረው ማሰልጠኛ ኮሌጅ መክፈት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ሥልጠናው የሚሰጥበት ኮሌጅ ታሪካዊ በሆነ ቤት ውስጥ መሆኑ ደግሞ ሌላው ገጽታ ነው ። ይህም ታሪክንና ባህልን በማስተሳሰር ጠብቆ ለማቆት የተደረገውን ጥረት ያሳያል ። የቤቱ አሰራር ጥንታዊነቱን ያሳብቃል። የኮሌጁ ዲን ወይዘሮ ፍርዱስ እንደገለጹልን፤ የእቴጌ ጣይቱ ጫጉላ ቤት ነበር ። በኋላም ቆንጽላ ጽሕፈት ቤት ሆኖ አገልግሎት ሰጥቷል ። ሰዎች ለመኖሪያም ሲጠቀሙበት ነው የነበረው።

ቤቱ ለረጅም ጊዜ በመቆየቱና ለተለያየ አገልግሎትም በመዋሉ ምክንያት ተጎድቶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ከስፔን መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ጥገና ተደርጎለት በጥሩ ይዘት ላይ እንዲገኝ ማድረግ ተችሏል።

ይህ ታሪካዊ ቤት እድሳት ከተደረገለት በኋላ በሀረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ስር ሆኖ ከባህልና ታሪክ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶች እንዲሰጥባቸው ነው የተደረገው። ናያቢዳን የሚል ስያሜ የተሰጠው ሀገር በቀል እሴት ማሰልጠኛ ኮሌጅ ይገኝበታል። ናያቢዳን እናት ማለት እንደሆነና የተሰየመውም በሙያቸው በሚታወቁ እናት እንደሆነ የናያቢዳን ኮሌጅ ዲን ወይዘሮ ፍርዶስ ቶፊቅ ገልጸውልናል።

በኮሌጁ ሀገር በቀል የሆኑ እውቀቶችን ለትውልድ ለማስተላለፍ የሀረሪ መገለጫ የሆኑ ስፌቶች፣ ባህላዊ አልባሳትና ተያያዥ የሆኑ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ ነው ወይዘሮ ፍርዱስ የነገሩን። የሥልጠናው ዋና ዓላማ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣው ባህላዊ ስፌት ቀጣይነት እንዲኖረው ነው ብለዋል። እናቶች ይዘው ያቆዩት ቢሆንም በተለያየ ምክንያት የማሸጋገሩ ነገር እየቀነሰ እንደሆነም ነው የገለጹልን። ወይዘሮ ፍርዱስ ኮሌጅ መኖሩ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ያስችላልም ብለዋል። ለዚህም ሲባል ሥልጠናው በነፃ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩልም ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን አላስፈላጊ ቦታ ከሚያውሉ ሙያ የሚያገኙበትን እድል በመፍጠር፣ የሙያ ባለቤት ከሆኑ በኋላም ለገቢ ማስገኛነት እንዲጠቀሙበት፣ ተማሪዎችም ትምህርት ቤት ሲዘጋ እንደጊዜ ማሳለፊያ እንዲሆናቸው ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

ወይዘሮ ፍርዱስ እንደገለጹት፤ በኮሌጁ ውስጥ የሀረሪ የቤት ግንባታን ጨምሮ የሀረሪን ባህል፣ ታሪክና ወግ የሚያንፀባርቁ ወደ 11 የሚሆኑ ሥልጠናዎች ናቸው የሚሰጡት። ከነዚህ ውስጥም አንዱ የስፌት ሥልጠና ነው። ስፌትን ቀለል አድርጎ ማየት አያስፈልግም። ሰልጣኞች በአንድ በኩል ባህልንና ታሪክን አቆይተው ለትውልድ በማሸጋገር፣ በሌላ በኩል ደግሞ በገቢ ማስገኛነት ስለሚጠቀሙበት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።

በተለይ ደግሞ ሴቶች የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሥልጠናው የተለያየ እውቀት የሚያስጨብጥና የሙያ ክህሎትን የሚያስገኝ በመሆኑ፣ ጥቅሙ የጎላ ይሆናል። ከበድ ያለ የሥራ መሣሪያም ሆነ የመሥሪያ ቦታ አያስፈልግም። በቤት ውስጥ ሆና ገቢ ማመንጨት ትችላለች ። ኪሮሽና ክር ግብዓት ብቻ ነው የሚያስፈልገው።

ኮሌጁ እስከ ሌቭል 2 ነው አሰልጥኖ የሚያስመርቀው። ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፍ የሚያቀርቡት የሰለጠኑባቸውን በተግባር በማሳየት ነው። ኮሌጁ ከአምስት ጊዜ በላይ ያሰለጠናቸውን አስመርቋል። በቁጥርም ከአንድ መቶ በላይ ይሆናሉ።

ኮሌጁ ለሚሰጠው 11 የሥልጠና ዓይነቶች የሚያስፈልገው ግብዓት ሰፊና በዋጋም ውድ እንደሚሆን ይጠበቃል። ይሄን እንዴት እየተወጣ ነው ብለን ወይዘሮ ፍርዱስ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ ለሀገር በቀል እሴቶች ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ ተሟልቶ ሥልጠናው እንዲሰጥ እየተደረገ ነው። አንዳንዴ ወረዳዎችና የተለያዩ የሥልጠና ጥያቄ የሚያቀርቡ ሲገኙ ከነርሱ በሚገኝ መጠነኛ ገቢም ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሌጁ ስልጠና እየሰጠ ያለው ባህሉን ታሪኩን በሚያውቁና በሥራው ውስጥ ባለፉ እናቶች ነው። እናቶች ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ለተተኪው ትውልድ እያሸጋገሩ የደመወዝ ተከፋይ ሆነው ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

በኮሌጁ በስፌት ክፍል ውስጥ ሥልጠና እየሰጡ ካሉት መካከል አንዷ የሆኑትን ወይዘሮ ሰአዳ አብዶሽ አሊ እንደነገሩን፤ እየሰጡ ያለው ሥልጠና የሀረሪ የአለላ ስፌት ነው ። ኮሌጅ ተከፍቶ እንዲህ ሥልጠና ከመሰጠቱ በፊትና አሁን ያለውን ሁኔታ እንዲህ አጫውተውኛል ‹‹ቀደም ባለው ጊዜ ሴት ልጅ በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋም ተቀጥራ አትሰራም። ከወላጆችዋ ጋርና በኋላም ትዳር ስትይዝ ቤተሰቧን በመምራት ነው የምታሳልፈው። የቤት ውስጥ ሥራዋን ስትጨርስም ስፌት ትሰፋለች። ሁሉም ስፌትን ይማራል። ይሰፋል። በዚህ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ እስከዛሬ ቆይቷል››

በጊዜ ሂደት ግን ነገሮች እየተቀየሩ መምጣታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ሰአዳ፤ ሴቶች በተለያየ ሥራ ላይ ተሰማርተው ውጭ መዋል በመጀመራቸው በጊዜ ማጣትና በተለያየ ምክንያት በቤት ውስጥ ሴቶች ስፌት መስፋት እየቀነሱ እንደመጡ ነው ያስረዱት ። የእደ ጥበብ ኮሌጅ መከፈቱ በጣም ጥሩ እንደሆነም ይገልጻሉ።

እርሳቸው እንዳሉት ማሰልጠኛ ኮሌጁ ባይከፈት የባህል ስፌት እየቀነሰና ከነጭርሱም ሊጠፋ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችል ነበር። ብዙዎች ከመስፋት ይልቅ ወደ ግዥ ፊታቸውን እያዞሩ መጥተዋል ። ገበያ ላይ ደግሞ ዋጋው እየተወደደ በመሆኑ አቅምን ይፈታተናል። ይህ ሲሆን ደግሞ ወደ መተው ስለሚኬድ ባህሉ ይጠፋል። ይህ ሥጋት ሆኖባቸው አዝነው እንደነበርም ይገልጻሉ። አሁን ግን በኮሌጁ መከፈት ተስፋ አድርገዋል።

እርሳቸውም አስተማሪ ሆነው በሚከፈላቸው የወር ደመወዝ ኑሮአቸውን እየመሩ፣ እውቀታቸውንም እያሸጋገሩ በመሆኑ ደስተኛ ናቸው።

በዚሁ በስፌት ሥልጠና ክፍል ውስጥ የወንዶች ቆብ በኪሮሽ እየሰራች ያገኘናት ሰልጣኝ ወጣት ሀምዲያ ነስሩ፤ በኮሌጁ የሚሰጠውን ሥልጠና ፈልጋ እንደገባች ነው የነገረችን። በቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ( አካውንቲንግ) እየተማረች ነው። በትርፍ ጊዜዋ ደግሞ በእደ ጥበብ ሙያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ውስጥ የእጅ ሙያ ለመማር ወስና በኮሌጁ መግባትዋን ነው ያጫወተችን። እርስዋ እንዳለችው፤ በቤት ውስጥ የስፌትም ሆነ የኪሮሽ ሥራ የሚሰራ የቤተሰብ አባል ባለመኖሩ ሞክራ አታውቅም።

በኮሌጁ ከገባች ገና አጭር ጊዜ በመሆኑ ልምምድ እያደረገች ያለው የወንዶች ኮፍያ በመሥራት ነው ። ኮፊያው በኪሮሽ ነው የሚሰራው። በመቀጠል ስፌቱንም ተለማምዳ የሙያ ባለቤት ለመሆን አስባለች። ወጣት ሀምዲያ ለጊዜው እውቀቱ እንዲኖራት ነው ፍላጎትዋ ። ወደፊት ግን ገበያውን አጥንታ መነሻ ገንዘብ(ካፒታል) ፈልጋ ወደ ገቢ ምንጭነት በመለወጥ ተጠቃሚ ልትሆን እንደምትችል ነው የነገረችን።

ወጣት ሀምዲያ እንደነገረችን ስልጠናው አልከበዳትም። በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ወደተግባር የገባችው። ስልጠናው በነጻ መሰጠቱ ፍላጎትን ሊጨምር እንደሚችል ታምናለች። ወጣቶች እድሉን እንዲጠቀሙበትም መልእክቷን አስተላልፋለች ። ኮሌጁ የጀመረውን አጠናክሮ በመቀጠል የሀረሪዎች መገለጫ የሆነውን ሀገር በቀል እሴት እንደሚያስቀጥል ተስፋ ጥላበታለች።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን  የካቲት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You