የፀጥታ ችግር ያልበገረው የክልሉ ግብርና ሥራ

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ አለመረጋጋቶችና የፀጥታ ችግሮች ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል። በተለይም ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የኑሮ መሰረት የሆነው ግብርና ከሰላም ውጭ የሚታሰብ አይሆንም። ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አገሩና ቀየው ሠላም ሊሆን የግድ ነው። በዚህ ረገድ በተለያዩ ምክንያቶች በአገሪቱ የተፈጠረውና እየተፈጠረ ያለው የሰላምና ጸጥታ ችግር አርሶአደሩን ጨምሮ መላውን ሕዝብ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆን አድርጎታል። የሰላምና ፀጥታ ችግር ፈተና ከሆነባቸው ክልሎች አማራ ክልል አንዱ ነው። በክልሉ አብዛኛው ማኅበረሰብ አርሶአደርና በግብርና ላይ የተመሰረተ ሕይወት ያለው እንደመሆኑ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የችግሩ ተቋዳሽ እንደነበረ ታይቷል።

የሰላምና ፀጥታ ችግር የልማቱ ማነቆ ሆኖ እንዳይቀጥል ክልሉ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም በዘንድሮ የበልግ ወቅት የእርሻ ሥራው እንዳይስተጓጎል ብርቱ ጥረት መደረጉ ነው የተገለጸው። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የግብርና ሥራውን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ማናቸውንም ችግሮች ለመፍታት ብርቱ ጥረት እየተደረገ ነው፤ በዚህም አበረታች የሚባል ውጤት እየተመዘገበ ነው የሚገኘው። በክልሉ በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 22 ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮች፣ በሁሉም ወረዳ በሚባል ደረጃ እንዲሁም በሁለት መስኖ ፕሮጀክቶች የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተከናወነ ይገኛል። ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ 140 ሺ 700 ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ተሸፍኗል። 193 ሺ 611 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል። ከ429 ሺ በላይ አርሶአደሮች በበጋ ስንዴ ልማት ተሳታፊ ሆነዋል።

በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት ከሰላም እጦትና ከተለያዩ ችግሮች ጋር በተገናኘ በተፈጠረው የማዳበሪያ ግዢ መዘግየቱ ይታወሳል። ይህ ችግር ደግሞ ከምርትና ምርታማነት መስተጓጎል ባሻገር ለመልካም አስተዳደር እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። የፌዴራል መንግስት ካለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት የማዳበሪያ ግዢን ቀድሞ በመፈፀም ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ሲያደርግ እንደነበርም ይታወቃል።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ማዳበሪያን በወቅቱ ለተጠቃሚው አርሶአደር ለማድረስ ችግሮች አጋጥመውት እንደነበርም ታይቷል። የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ እንደሚያመላክተውም፤ የክልሉ መንግስት ዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦቱ ከወትሮው በተለየ ፍጥነት ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል። ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበርም ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ ወደ ሃገር ውስጥ መግባት የጀመረውን ማዳበሪያ በፍትሃዊነት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንዲሰራጩ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል።

እንደመረጃው ከሆነ በዚህ ዓመት የተፈፀመ የማዳበሪያ ግዢም ባለፈው ዓመት ከተፈፀመው ግዢ የሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው። አሁን የክልሉ ድርሻ የሆነው አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ኩንታል ማዳበሪያ ወደብ ላይ ሲገኝ በቀጣዮቹ ጊዜያት ከወደብ ወደ ማዕከል ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ረገድም በክልሉ የማዳበሪያ አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ ከወደብ ወደ ማዕከላት የሚያጓጉዙ 14 የትራንስፖርት ማኅበራት አሉ።

የክልሉ ግብርና ቢሮ የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጎባው በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ክልሉ ካለፈው ዓመት ተሞክሮ በመነሳት የግብርና ሥራው ማነቆ የሆነ የፀጥታና ከዚያ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል። በዋናነትም የማዳበሪያና የዘር አቅርቦቱ በተሳለጠ መልኩ ለሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

ለአርሶ አደር በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ሳይዘናጋ የበልግ ልማቱን እንዲያከናውን አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ። በዋናነትም ከዚህ ቀደም ቅሬታ ይነሳበት የነበረውን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመፍታትና ለአርሶአደሩ ተደራሽ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስትና ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ስለመሆኑ ያስረዳሉ። ‹‹በክልላችን በ2016/17 የምርት ዘመን ከአምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር ለመሸፈንና 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እቅድና ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው›› ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ በ2016/17 የመኸር እርሻ ሥራ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር ተገዝቶ ከወደብ ላይም እየደረሰ መሆኑን ያስረዳሉ። በቀጣዮቹ ቀናት ለአርሶአደሩ ተጨማሪ ማዳበሪያ ተደራሽ ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ከወደብም ወደ ክልል በመጓጓዝ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በክልሉ በሚገኙ የአርሶአደር ዩኒየኖችና ማኅበራት ደርሶ ለአርሶአደሩም እየተሰራጨ ሲሆን ይህም በበጋ መስኖ ልማት ሥራው ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ እንደሆነ ነው ያብራሩት።

‹‹ዘንድሮ የመስኖ ልማታችንን በተመለከተ ደግሞ ከ333 ሺ ሄክታር መሬት በላይ አምርተን 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅደን እየሰራን ነው›› የሚሉት ኃላፊው፤ ከዚህም ውስጥ ደግሞ 250 ሺ የበጋ መስኖ ልማት መሆኑን ነው ያመለከቱት። በተያያዘም ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት የማዳበሪያ ችግር በክልሉም ተከስቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ክልሉ ይህንን ችግር መሻገር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉን ይጠቅሳሉ። ‹‹ከዚህ በፊት የአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚፈፀመው የካቲት፤ መጋቢትና ሚያዚያ ወር ላይ ነበር፤ አሁን ግን ከጥቅምት ጀምሮ ግዢ በፌዴራል ደረጃ መፈፀሙ ከምርት ወቅቱ ቀደም ብሎ ሥራዎችን በማከናወን ምርታማነትን በተጨባጭ ለማረጋገጥ እያገዘን ነው›› በማለት ይናገራሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ማዳበሪያ ወደ ሃገር ከገባም በኋላ በቀጥታ ለአርሶአደሩ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ሰፊ ርብርብ እየተደረገበት እንደሆነ ይጠቁማሉ። በተለይም የፌዴራል ግብርና ሚኒስቴር ከፀጥታው አካል ጋር በመነጋገር ካለው የፀጥታ መናጋት ችግር ጋር ተያይዞ ማጓጓዝ የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር በትብብር ሥራው እየተሰራ ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ። ‹‹በፀጥታ ምክንያት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ባይስተካከል ኖሮ ከዚህ በፊት ፈጥኖ ይገባ ነበር። ግን የፀጥታው ጉዳይ የራሱ አሉታዊ ሚና ነበረው። ቢሆንም ግን አሁን በምርት ዘመኑ ሥራ ተጀምሯል። ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው›› ሲሉም ያክላሉ።

እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ክልሉ በመስኖና በበልግ የምርት ወቅት ያለውን አቅም አሟጦ በመጠቀም በምርት ዘመኑ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ እየሰራ ነው። በዋናነትም የክልሉ ግብርና ቢሮ እንደአጠቃላይ ሁሉንም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ የሚያደርጉ የድጋፍ ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል። የማዳበሪያ ስርጭቱ በአሁኑ ወቅት በምስራቅ አማራ፤ ወልዲያ፣ በደሴ፣ ጎንደር፣ እንዲሁም ወደ ጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች መሄድ በሚገባው ልክ ባይሄድም በተቻለ መጠን ከፀጥታ አካል ጋር በመናበብ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ያለነው።

ይሁንና ማዳበሪያም ሆነ የዘር አቅርቦቱ በፍትሃዊነት ተደራሽ የማድረጉ ሥራ የሁሉም አካላት ብርቱ ትብብር ይፈልጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ኃላፊው ይናገራሉ። ‹‹ምክንያቱም ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ አርሶአደር ነው። የኑሮ መሰረቱም ግብርና ነው፤ ግብርና ለገበሬው ሕይወቱ፤ ሥራው ነው። በመሆኑም የሁልም አካላት ያልተቋረጠ ርብርብ ይፈልጋል›› ይላሉ። በዚህ ረገድም አርሶአደሩ ትኩረቱን የግብርና ሥራው ላይ ብቻ በማተኮር ለምርታማነትና ውጤታማነት እንዲተጋ ቢሮው የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ግብርና ወቅት ጠብቆ የሚሰራ አንደመሆኑም ወቅቱ ካለፈ አርሶአደሩ ብቻ ሳይሆን ሌላው ሕዝብ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። በመሆኑም አርሶአደሩ ሰላማዊ ምኅዳር ተፈጥሮለት በተረጋጋ መንፈስ ልማቱን አንዲከውን የክልሉ መንግስትም ሆነ የፀጥታ አካሉን የበኩላቸውን ድጋፍ እያደረጉ ስለመሆናቸው ያስረዳሉ። ‹‹የግብርና ሥራ የጊዜ ጥገኛ በመሆኑ ያንን ስራ የሚያስተጓጉል ማንኛም አካል ከዚህ ተግባሩ ሊታቀብ ይገባል። የሚጎዳው ደግሞ ከማንም በላይ አርሶአደሩን ነው። ይህን ማስረፅና ከእኛ የሚጠበቅ ሥራ ነው›› ሲሉም ያስገነዝባሉ።

ቢሮው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ ታሳቢ አድርጎ በሚሰራባቸው አካባቢዎች የማይናቅ ውጤት እያገኘ መሆኑን ይጠቁማሉ። የማዳበሪያ ፍላጎት መፍጠር፤ የባለሙ ያዎችን ዝግጁነት ማረጋገጥ፤ የሙያና ቴክኒክ ስልጠና መስጠት ማቀድ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፤ በዚህም የተሻለ ውጤት እያገኘን ነው ያለነው›› ይላሉ። ይሁን እንጂ የፀጥታ ጉዳይ የቢሮው ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ከባለድርሻ አካላትን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የሚሻ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በሌላ በኩልም የክልሉ መንግስት በድርቅ የተጎዱና ውሃ አጠር አካባቢዎች ላይ በፌዴራል መንግስት ከሚሰራው የድጋፍ ሥራ ጎን ለጎን ቢሮው ድርቅ መቋቋም የሚቻልባቸውን ማካካሽ እቅድ በማቀድ ራሱን የቻለ ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ። ‹‹የተጎዱ አካባቢዎች ወደነበረበት ለመመለስ ቢሮው የበኩሉን ስራ እየሰራ ነው። ይህም ቢሆን ክልሉ በመደበኛ በጀት የሚያከናውነው ሥራ አይደለም፤ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ ጥረት የሚጠይቅ ነው፤ በዚህም የተገኘው ውጤት አበረታች ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።

አክለውም ‹‹እርግጥ የፀጥታ ችግር ፈታኝ እንደነበር ይታወቃል፤ ግን አርሶአደሩ ባኅል አድርጎ ስለያዘው ዘንድሮ ሰፊ ንቅናቄ ተፈጥሮ ነው እየተሰራ ያለው›› ይላሉ። ዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ሥራው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩና ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት በተገኙበት በደቡብ ወሎ በሰፊ ንቅናቄ መጀመሩንና ወደ ሌሎች አካባቢዎችም በማስፋት ከእርሻ ስራው ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑን ይጠቁማሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው ጊዜ ሁከትና ግጭት በሚኖርበት ወቅት የለሙ ተፋሰሶች መቃጠል፤ መቆረጥ፤ መውደም ያጋጥም እንደነበር አስታውሰው፤ ‹‹አሁን ግን በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አለመረጋጋቱ ቢኖርም በአንፃሪያዊ ሁኔታ ተፋሰሶች ተጠብቀው ነው ያሉት›› በማለት ያስረዳሉ።

በተመሳሳይ የግብርና ኤክስቴንሽን ስራም ለችግሩ ሳይበገር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹በዚህም ከዚህ ቀደም ማዳበሪያ አልፈልግም ይል የነበረው አርሶአደር ዛሬ ላይ አምጡ እያለ እኛኑ ማፋጠጥ ይዟል፤ ይህም የመጣው በተሰራው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ። ያም ቢሆን ግን በየትኛውም አካባቢ በታቀደው ልክ ተንቀሳቅሰን ሰርተናል ማለት አይደለም፤ ከእቅዳችን አንፃር ብዙ ይቀረናል፤ ለዚህ ደግሞ የሁሉም የክልሉ ነዋሪና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል በማለት አስገንዝበዋል።

ከሁሉ በላይ ግን በቀጣዮቹ የምርት ጊዜያት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦቱ በፍትሓዊነት ተደራሽ እንዲሆን ከፍትሕ፤ ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ መስራት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ የሚዲያ ተቋማትም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኃላፊው አስገንዝበዋል። ‹‹ምክንያቱም የአርሶአደሩ ጉዳት ዞሮ ዞሮ የማይነካው አካል የለም፤ ጦርነት ከጨረሰው በላይ ረሃብ የሚጨርሰው ስለሚበልጥ ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። አማራ ክልል ሰላም ሳይኖር ኢትዮጵያ ሰላም ናት ሊባል አይችልም፤ በመሆኑም እንደሃገር በሁሉም አካበቢዎች ላይ ሰላም እንዲሰፍንና ገበሬው እርሻው በተሳካ ሁኔታ እንዲያካሂድ ስለሰላም መስበክ ሁላችን የድርሻችን ልንወጣ ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You