ኀዘን ከሟች ይልቅ ቋሚን ይገዘግዛል። ነገር ግን “ሰው በኀዘን ምክንያት ተሰብሮ መቅረት የለበትም።” ወይዘሮ ቅድስት አሳልፍ ለዚህ ሃሳብ ማሳያ ናቸው። እንዴት ቢባል ተከታታይ በሆኑ ዓመታት ሁለት ወንድሞቻቸውንና አባታቸውን በድንገተኛ በሞት ያጡና ኀዘን ቅስማቸውን ብቻ ሳይሆን ልባቸውንም ሰብሮት ነበር። ነገር ግን የተሰጣቸውን ማጽናኛ ምክር ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ እርሳቸውም የሌሎች ልብ ተሰብሮ እንዳይቀር በማጽናናት አገልግሎት ተግባር ተሰማሩ።
ከዚህ የማጽናናት አገልግሎት በተጨማሪም የዓለም እርቅና ሰላም ግብረ ሠናይ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆንም በሰላምና ዕርቅ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ በመሆናቸው ወይዘሮ ቅድስት አሳልፍን በእነዚሁ ሁለት ጉዳዮች ዙሪያ በማነጋገር የዛሬ የሕይወት ገጽታ እንግዳችን አድርገናቸዋል። መልካም ንባብ፡-
ማንነት
ወይዘሮ ቅድስት አሳልፍ ትውልድና ዕድገታቸው አዲስ አበባ ነው። በእዚሁ ከተማ ትዳር መስርተው ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። በየደረጃው ትምህርታቸውን ያጠናቀቁትም እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ነው። ከንግድ ሥራ መለስተኛ ኮሌጅ በሂሳብ መዝገብ አያያዝ ሙያ ተመርቀው በኢትዮጵያ ማዕድን ሀብት ልማት ኮርፖሬሽን ሥር ሻኪሾና አዲስ አበባ በሚገኙ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች በልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነት ለ25 ዓመታት ያህል በመንግሥት ሠራተኝነት አገልግለዋል።
ከ25 ዓመታት የመንግሥት ሥራ አገልግሎት በኋላ
ወይዘሮዋ ከ25 ዓመታት የመንግሥት የሥራ አገልግሎት በኋላ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታት በሙሉ ጊዜ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሠማርተዋል። በዋናነት ታላቅ ወንድማቸውን ካጡበት ከ1995 ዓ.ም. ሰኔ ወር ጀምሮ ለፈጣሪያቸው ቃል በገቡት ኀዘንተኛን የማጽናናት አገልግሎት የተሠማሩ ሲሆን በዕርቅና ሰላም ሥራ ላይም ያገለግላሉ።
ሰኔ 16 ቀን 1995 ዓ.ም. ከድሬዳዋ ወደ አዲስ አበባ ለሥራ ወጥቶ ሲመለስ ከዚህ ዓለም የተለየው ወንድማቸው በአዲስ ሜካኒካል ኢንተርፕራይዝ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ደረጃ ላይ ነበር። በደንብ የተማረና ለሀገሩ ገና ብዙ ሊጠቅም የሚችል ሰው ነበር። የመኖርያ ሠፈራቸው አንድ ላይ በመሆኑ አብረው እየወጡና እየገቡ በየዕለቱ ይገናኙ ስለነበር በድንገተኛ የመኪና አደጋ መለያየታቸው ወይዘሮ ቅድስት መንፈሳቸውን በእጅጉ ሰብሮት ነበር።
“እኔ ታላቅ ወንድሜን በድንገት ማጣቴ ከፍተኛ የመንፈስ መታወክ አድርሶብኝ ነበር” ሲሉ የኀዘን ስሜታቸውን ክብደት ይገልጹታል። በቅጽበት ከወንድማቸው የተለዩበት አጋጣሚም በመላው ቤተሰብና ወዳጅ ዘመዶቻቸው የፈጠረው ኀዘንና ድንጋጤ እንዲህ በቀላሉ የሚፋቅና የሚጠፋም እንዳልነበረም ያስታውሳሉ።
“ይህ ክፉና ዘግናኝ አጋጣሚ መከሰቱም እንኳን ለእኛ ለቤተሰቦቹ ቀርቶ ለማያውቀው ሰው ጆሮም እጅግ የከበደና የቀፈፈ፣ ኀዘኑንም ለመቀበል ያዳገተና የማይረሳ ሰቀቀንን ትቶ ያለፈ በመሆኑ የሞት መጀመሪያ የሚመስል ገጽታም ነበረው” ይላሉ።
ያችን የቀን ጎዶሎ ፈተና በእምነት የሚያሸንፉበት አቅም በጸሎት እስኪያገኙ በምድር ላይ በዓይነ ሥጋ ለማያዩት ሟች ወንድማቸው በዕለቱ ደረት እየደቁ አንብተዋል። በሰለስቱ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው “ያዘነ ቢኖር እርሱ ይጸልይ” ባለው የመጽሐፍ ቃል መሠረት ለፈጣሪአቸው ከዚህ ጽኑ ኀዘን እንዲያወጣቸው ተንበርክከው ለምነዋል። መልሳቸውንም አገኙ።
መልስ ለሰጣቸው አምላክ ቃል ገብተው ከተንበረከኩበት ጸሎት በርትተው ተነሱ። ባገኙት መልስ ተበራተውም ቤተሰባቸውን ለማበርታትና ቃላቸውን ሊፈጽሙ በቁርጠኝነት ወሰኑ። የአገልግሎት መነሻ ቀናቸው የወንድማቸው ሰለስት የአባታቸው የሁለተኛ ዓመት ዝክር ዕለት ነበርና ይህን ቀን ሲያስታውሱ ይደነቃሉ።
በሰልስት ከመጽሐፍ ቅዱስ ያነበቡት የማጽናኛ ቃል የወይዘሮ ቅድስት የአገልግሎት መነሻ ሆነ። ወንድማቸውን ለማሰብ በቤተ ክርስቲያን ከሚደረገው ጸሎትና ጸበል ጸዲቅ ጋር ለኀዘነተኞችም የወንጌል ትምሕርትና የማጽናኛ ዝማሬ ምግበ ነፍስ ሆኖ እንዲቀርብ ማስደረጋቸው በአገልግሎቱ እንዳጠነከራቸውም ይገልጻሉ። በዚህ የምግበ ነፍስ ምክክርም ባገኙት መንፈሳዊ እውቀት በቅዱስ መጽሐፍ “ከመልካም ሽቱ መልካም ስም ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል።…” ያለውን እውነት በሚገባ መገንዘባቸውንም ያስረዳሉ።
ይህንን ግንዛቤአቸውንም ለብዙዎች ለማስረዳት ብዙ ሥነ ግጥሞችን አዘጋጅተዋል። ሰዎች በቁማቸው ሳሉ ሕይወታቸውን ካስተካከሉ ሞት ሟችንም ሆነ ቋሚን እንደማይጎዳ፤ ይልቁንም ከሞተው ሰው በመማር ብዙዎች ወደ ተሻለ ሰብዕና እንዲመለሱ ለማበረታታት ከኀዘን ያወጣቸውን አምላካቸውን በማመስገን በተከታዮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ብዙ አጽናኝ መልእክቶችን ለኅብረተሰቡ ማድረሳቸውን ይገልጻሉ።
“-አቤቱ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት፤
– የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን፤
– እኛ ራሳችን በተጽናናንበት መጽናናት ሌሎችን ደግሞ ማጽናናት እንችላለን፤
– እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፤
-እናት ልጇን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ።”
በሚሉ እና በሌሎች በርካታ መነሻ ጥቅሶች የተዘጋጁትን እነኚህን የማጽናኛ ጽሑፎች ከምቹ ቤት መልቲ ሚዲያ ጋር በመሆን በሬዲዮ ሞገድ አማካኝነት ለኀዘንተኞች ባሉበት የማድረስ ዕቅድ እንዳላቸውም ነግረውናል። ዕቅዱ ከተሳካ ማንም ሰው ሬዲዮኑን ከፍቶ እያዳመጠ ሊፅናናበት ይችላል የሚል ዕምነትና ተስፋም አላቸው።
እንግዳችን ወይዘሮ ቅድስት እንደነገሩን ይሄ ዕቅድ መተግበሩ በኀዘን ወቅት ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን ዘግቶ የማዘን ባሕላችንን አጽናኝ መልእክቶችን በማድመጥ በጎ ልምድ ይተካልናል። የማይቀረውንም ሞት በአግባቡ በመረዳትም ከኀዘን ስብራት ድነን ከሞተው ሰው በመማር የራስን ቀሪ ዘመን በቅንነትና በትሩፋት ሥራዎች ተሰማርቶ ሕይወትን ለማቃናት ያስችላልም ባይ ናቸው።
መፅናናት እና ማጽናናት
ወይዘሮ ቅድስት የደረሰባቸውን ጥልቅ ኀዘን በማዳመጥ በተለይም ወላጅ እናታቸው ያሉ በመሆናቸው ለእርሳቸውና ላዘነው ቤተሰብ በየደረጃው ያለውን ክብደት እያገናዘቡ ተጽናንተው ለማጽናናት ያስቻሉአቸውን የሃይማኖት አባቶችና ወንድሞች ያመሰግናሉ። ይህ በቤተክርስቲያን አባቶችና ወንድሞች የሚሰጥ የማጽናኛ ቃል ብርታትና ጥንካሬ እንደሰጣቸው ጠቅሰው ሌሎችም እንዲሁ በኀዘን ተጎድተው ከሰውነት ተራ ወጥተው ለጉስቁልናና ለአእምሮ መረበሽ እንዳይዳረጉ አጽንተው የሚያበረታቸውን ምክር በወቅቱ ለማግኘት በራሳቸው የማይችሉ ከሆነ የቅርብ ወዳጆቻቸው እንደ እምነታቸው ይህንን ሊያደርጉላቸው ይገባል ይላሉ።
“ሰው በኀዘን ምክንያት ተሰብሮ መቅረት የለበትም” ያሚለውን አባባል የሚያረጋግጡልን ወይዘሮ ቅድስት፤ ወደ ሕሊናቸው ተመልሰውና የራሳቸውን ተሞክሮ በማካፈል እንደራሳቸው ያዘኑ ሌሎች ሰዎችን ወደ ማጽናናት ካመሩ 21 ዓመታት አስቆጥረዋል። በተደጋጋሚ “የደረሰብኝ ኀዘን ከባድ ቢሆንም ወደ ራሴ ስመለስ ከራሴ ጋር ተማከርኩ። ሌሎች ኀዘንተኞች እኔን እያዩ መበርታት አለባቸው የሚል ድምዳሜም ላይ ደረስኩ” ብለዋል።
በእርግጥ ይህን የበጎ ፈቃድ የማጽናናት አገልግሎት በጀመሩበት ሰሞን ኀዘንተኞችን ሲያገኙ የሚነግሯቸው ገጠመኝ የእርሳቸውንም ልብ እየሰበረ ይጎዳቸው እንደነበር አልሸሸጉም። እንባ እየቀደመ በእጅጉ ሲያስቸግራቸው የቆየ ቢሆንም፤ በነበራቸው ብርቱ ቁርጠኝነት እየታገዙ የማጽናናት ተግባራቸውን ዳር ለማድረስ በወንድማቸው ሰለስት የገቡት ቃል ወደ ኋላ እንዳይመለሱ አደረጋቸው።
“የደረሰብኝን እየነገርኳቸውና መውጫውንም እያሳየኋቸው ብዙዎችን ላጽናና ሞክሬአለሁ ሰዎች ተራቸው እስከሚደርስ ድረስ ማህበረሰቡን በማገልገል የተፈጠሩበትን ዓላማ ማሳካት እንዳለባቸው ማበረታታት አለብኝ ያልኩበት ሃሳብ ከብዙ ሰዎች ጋር መልካም ግንኙነት ፈጥሮልኛል” ይላሉ። ይህንን ኀዘንተኞችን የማጽናናት ተግባር ከግለሰብ ኀዘን ቤቶች በተጨማሪ ሃሳባቸውን ከሚደግፉ ጋር በመተባበር ሀገራዊ በሆኑ ኀዘኖችም ጭምር ተሳትፈው ውጤት እንዳዩበትም ይገልጻሉ።
ለአብነት ወደ ጎንደር ከተማ ሲጓዝ በነበረ የስካይ ባስ አደጋ የ43 ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት የፈጠረውን ከፍተኛ ኀዘን ለማብረድ ከአገልጋዮች ጋር ያደረጉት ጥረት፣ ተድባበ ማርያም ለግንቦት ልደታ በዓል ሲጓዙ 18 ወገኖቻችን ለሕልፈት የተዳረጉበትና ሌሎች የቆሰሉበት አጋጣሚንም በማጽናናት መሳተፋቸው፣ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ መጋቢት አንድ ቀን ወደ ኬንያ በመጓዝ ላይ ሳለ በገጠመው የቴክኒክ ብልሽት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በደረሰው አደጋ ከ35 ሀገሮች ከተውጣጡ 157 የተለያዩ ሀገር ዜጎች መካከል 17 ያህሉ ወጣት ኢትዮጵያውያን በመሆናቸው ከመምህራንና ከአየር መንገዱ ባልደረቦች ጋር በመተባበር የሟች ቤተሰቦችን የማጽናናት ተግባር ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ። በተደጋጋሚ በተከናወነ የማጽናናት አገልግሎት ወይዘሮ ቅድስት ተሞክሮአቸውን በመከተል በርትተው ባዩአቸው ወገኖቻቸው ደስ እንደሚሰኙም ተናግረዋል።
የማጽናናት ኅብረት
እንግዳችን እንደሚሉት በኀዘን ምክንያት ብዙ ሰዎች ተሰብረው ይቀራሉ። ከኀዘን በኋላ ያለ ሕይወታቸው በእጅጉ ይወሳሰባል። በከባድ ኀዘን ይመታሉ። ትውስታው ጉልበት ያሳጣቸዋል። ቅስማቸውን ሰብሮት ያልፋል። ሊያደርጉ የሚችሉትን ሁሉ እንዳይፈጽሙ ያደርጋቸዋል። ወደ አእምሮና ወደ ሌሎች ህመሞችም የሚሄዱ አንዳንድ ሰዎች አሉ። “እኔ እግዚአብሔር ረድቶኝ እንዳልፍ የሆንኩት ይሄን ምዕራፍ ነው” ሲሉም ወይዘሮ ቅድስት ወደ ኋላ መለስ ብለው ስለራሳቸው ኀዘን ያስታውሳሉ።
“እጅግ የከበደኝን ኀዘን ያቀለሉልኝ የማጽናናት ተግባር ላይ ከተሰማሩ ካሕናት አባቶች፣ መምህራነ ወንጌል ወንድሞች የሚወጡት መንፈሳዊ ቃሎች ስለሆኑ ይህንን ተሞክሮ ሌሎች እንዲያገኙት ለማድረግ የማጽናናት ህብረትን መሥረተናል” ይላሉ።
ለምሳሌ ሰዎች ባለፉ ወገኖቻቸው ስም “የእገሌ ፋወንዴሽ” እያሉ እንደሚያቋቁሙ ሁሉ የማጽናናት ህብረታቸውን “በማኅበረ ጰራቅሊጦስ (በአጽናኝ መንፈስቅዱስ)” ስም ከካሕናትና ከመምህራነ ወንጌል ጋር በመመካከር አቋቁመው ለመቀጠል እየተሰባሰቡ መሆኑን ገልጸውልናል።
እንግዳችን “ዛሬ ኀዘን ቢሆን ነገ ደስታ ይመጣል። እጅግ ብዙ ደጋጎችን በተለያየ መንገድ በሞት አጥተናል። በምድራችን ኃጢአት ሲበዛና ሰላም ሲደፈርስ ሞት ብዙዎችን ይነጥቀናል። ይህንን በመንፈሳዊ አረዳድ ተገንዝቦ ደስታና ሰላምን ለማግኘት የማጽናኛ ህብረቱ አስፈላጊ ነው” ብለዋል። ይህ የማጽናኛ አገልግሎት ተሳታፊነት እርቅና ሰላም ላይ እንዲተጉም አድርጎአቸዋል።
የዓለም እርቅና ሰላም ግብረ ሠናይ ድርጅት
እንግዳችን ከዚህ ኀዘንተኞችን የማጽናናት ተግባር ጎን ለጎን የዓለም እርቅና ሰላም ግብረ ሠናይ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ሥራን በበጎ ፈቃደኝነት እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል። ድርጅቱ በ1992 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ከፍትህ ሚኒስቴር ሕጋዊ ፈቃድ በማውጣት ሀገራቸውን በወቅቱ በተለያየ ደረጃ ላይ በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆነ የሥራ መስክ እንዲሁም በንግዱ ዓለምና በሥነጥበቡ ዘርፍ ተሰማርተው በቅንነትና በታማኝነት ባገለገሉና በማገልገል ላይ ይገኙ በነበሩ ጥቂት ሰላምና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተቋቋመ ድርጅት ነው።
እንግዳችን እነዚህ ለአገራችን ምን እንሥራ ብለው ከተሰባሰቡ ቅን ኢትዮጵያውያን ጋር አባል ሆነው የፈቃድ አገልግሎቱን ከጀመሩ ወደ 13 ዓመት ሲሆናቸው በጽህፈት ቤቱ በኃላፊነት ሲያገለግሉም ሦስት ዓመት ተጠግተዋል። ድርጅቱን በመመስረትና እስከ አሁንም በዳይሬክተርነት በመምራት ላይ የሚገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ክሊኒክ ባለቤት የሆኑትና በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በዋና ሥራ አስኪጅነት ያገለገሉት የድርጅቱ መስራች ዶክተር ያዕቆብ በቀለ መሆናቸውን ገልጸውልናል።
ይህ የዓለም እርቅና ሰላም ግብረ ሠናይ ድርጅት ከሃይማኖት፤ ከፖለቲካ፤ ከጎሳና ከጾታ ወገንተኝነት ርቆ ለሰው ልጆች ሕይወት ከሚያስፈልጉ ዋና ግብአቶች ተርታ ሰላም ሊመደብ እንደሚገባው አምነው ድርጅቱን ያቋቋሙ ብዙዎች ናቸው። አሁንም እየተባባሰ የመጣው የሰላም መደፍረስ እያሳሰባቸው የሚመካከሩ ብዙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሀገርም በውጭም ሀገር ሆነው ይህ ድርጅት እንዲጠናከር ይመክራሉ። ድርጅቱንም በአማካሪነትና በበላይ ጠባቂነት ያገለግላሉ። እነኝህን ከመሰሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ለሀሐገር ሰላም መመካከርና ባለራዕዮች የመሠረቱትን ተቋም ለማስቀጠል በመጣር ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያውያን የሌሉበት ምድር ስለሌለ ለጊዜው ድርጅቱ የሚንቀሳቀሰው በኢትዮጵያ ቢሆንም “የዓለም እርቅና ሰላም ግብረ ሠናይ ድርጅት” የሚል ስያሜን ይዟልና ነገ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ቦታ ሁሉ የሰላምና የዕርቅ ቤተሰብ እንዲኖር ለማድረግ ጥረት መኖሩንም ገልጸውልናል።
ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በሕጋዊ ተቋማትና በማኅበረሰቡ ውስጥ የተነሱ በርካታ አለመግባባቶችን በማቀራረብ አወያይቶ መፍትሔ ሰጥቷል። በተለይም በ1997 በሀገራችን ከነበረው ምርጫ ጋር ተያይዞ በመንግሥትና በመንግሥት ተፎካካሪዎች መካከል የነበረውን ቅራኔ ለመፍታት ጥረት ካደረጉት አንጋፋ የሀገር ሽማግሌዎች የሚገኙበት ተቋም መካከል ይህ ተቋም አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኮቪድ ምክንያት አገልግሎቱ ተቀዛቅዞ ቢቆይም እንግዳችን እንደሚሉት የድርጅቱ አገልግሎት መቋረጥ የማይገባው መሆኑን በማመን እንቅስቃሴውን መቀጠሉን ያወሳሉ። “ምቹ ቤት መልቲ ሚዲያ” ከተሰኘ ተቋም ጋር ልዩ የእናቶች የሰላም ጥሪ “ልጆቼ በጡቴ፣ ልጆቼ በሞቴ፣ ልጆቼ አፈር ስሆን” በሚል የመንግሥት ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች ሀደ ስንቄዎች፣ እናቶችና አባቶች እንዲሁም ሕጻናት በተገኙበት ጦርነት ይቁም ጥያቄአቸውን በጥናት የተደገፈ ዶክመንተሪም በማቅረብ ጭምር በሰፊው አስደምጠዋል።
“በጦርነት ምክንያት አጋሮቻቸውን ልጆቻቸውንና ወንድሞቻቸውን ከማጣታቸው ባሻገር በሚደርስባቸው መደፈር እና ሌሎችም ጥቃቶች የሥነ ልቦና ጉዳት የገጠማቸውን ሴቶች ማየት በእጅጉ ልብ ይሰብራል። በዚህ ዶክመንተሪም እናቶች በተለያዩ ቋንቋዎች ባደረጉት ንግግር ጦርነት እጅግ ጎጂና ልብ ሰባሪ መሆኑን በመግለጽ በይቅርታና እርቅ ሰላም እንዲመጣ በእንባ ተማጽነዋል።”
እንግዳችን እንደገለጹልን ድርጅታቸው ከሌሎች 9 ተቋማት ጋር በመተባበር “የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ” በሚል ሐምሌ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ለሁሉም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ ለምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር፣ ለአባ ገዳዎች ለሀደ ስንቄዎችና ለበርካታ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጥሪ በማስተላለፍ ልዩ የኢትዮጵያ እናቶች የሰላም ጥሪ መርሐ ግብር በማካሄድ ጦርነት እንዲቆም ጠይቀዋል። ከዚህ መርሐ ግብር ውጤት በመነሳት ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር በመገናኘትና በመወያየት ፕሬዚዳንቷና ሌሎች ከፍተኛ ሴት ሚኒስትሮችን ጨምሮ ነሐሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በተገኙበት መድረክ ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ሁሉም ለሰላምና እርቅ እጁን በመዘርጋት ብሔራዊ የንስሃ ጥሪ እንዲደረግ የሃይማኖት አባቶች ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።
በዚህ ጉባዔ የተላለፉ ድንቅ ድንቅ መልእክቶች በየሚዲያው ባይቀርቡም በተዘዋዋሪ የእናቶች እንባ ምላሽ አግኝቶ በትግራይ ክልል የሚደረገው ጦርነት ቆሞ የሰላም ሂደቱ ለመጀመር መብቃቱን እንደ መልካም ውጤት የሚያዩት መሆኑንና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በአማራ ክልል የሚደረገው የወንድማማቾች ጦርነት እጅግ የብዙ እናቶችን ልብ እንደሰበረ ይገልጻሉ። ሁሉም ወገኖች የሰላምን መንገድ በመሻትና ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታት የእናቶችን እንባ ለማስቆም እንዲቻል መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ እንዲወስድም በእናቶች ስም አሳስበዋል። ሀገራችን በይበልጥ ዘላቂ ሠላም እንድታገኝና ሠላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከተለያዩ የሰላም ሃሳብ አራማጆች ጋር ጥረት እንደሚያደርጉም ቃላቸውን ይሰጣሉ።
የዓለም እርቅና ሠላም ግብረ ሠናይ ድርጅት ሥራውን በትጋት ይቀጥል ዘንድ አቅማቸው የፈቀደላቸውን የቀድሞ አባሎችንም ሆነ ለሀገራቸው ሰላም የሚጨነቁትን ሁሉ በማሰባሰብ አሁን ካሉት ሃምሳ ያህል አባላት ጋር አጠናክሮ ለማስኬድ ከቀድሞዎቹ አንጋፋ አባሎች ምክርና እገዛ በማግኘት በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ካሉ በውጭ ሀገር ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሰላም ፈላጊ ህብረቶች ጋር ተጣምሮ ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጅቱ ከወመዘክር ፤ ከባህልና ቱሪዝም፣ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ “ሕዝባዊ ልማትና ሰላም፣ ሚዲያና ሰላም፣ ጥበብ ለሰላም፣ ሃይማኖትና ሰላም፣ ሀገራዊ ዕሴትና ራስን ማወቅ በወጣቶች፣ ሴቶችና ሰላም፣ የዕድሮች ሁለንተናዊ የሰላምና ዕርቅ ሚና፣ ወዘተ…” የመሳሰሉ የውይይት መድረኮችን የትብብር ሰነድ በመፈራረም ሲሠራ መቆየቱን ያወሳሉ።
በተለይ የሰላም ሃሳብን የማራመድ ተግባሩን ተወካዮቹን በየክልሎች በመላክ በአርባ ምንጭና በቤኒሻንጉል ተመሳሳይ መድረኮች እንደነበሩአቸው አውስተዋል። “አባላቱ እንደ ልብ ተዘዋውረው ለመሥራት አረጋውያን በመሆናቸውና የበጀት ችግር በመኖሩ ዘግይቶ እንጂ ድርጅቱ እንደ ነበረው እቅድ በየክልሉ ቅርንጫፎች ኖሮት ቢሠራበት ዛሬ የምናየው ችግር ሁሉ አይኖርም ነበር” ይላሉ።
‹‹በኢትዮጵያ ዘላቂ የሠላም መሠረት ለመጣል አብሮ መስራት አስፈላጊ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ቅድስት “ሰላምን በማኅበረሰቡ ውስጥ ለማስፈን ዋናውን ድርሻ መንግሥት መውሰድ እንዳለበት ደጋግመው ያሳስባሉ። ከሌሎች ጋር በቅንጅት ወደ ታች ወደ ሕብረተሰቡ ወርዶ ለመሥራት ላለው ጽኑ ሃሳብ በዋናነት እንቅፋት የሆነባቸው የበጀት አለመኖርና የሚዲያ ሽፋን አለማግኘት መሆኑን በማውሳት ይህን ለመቅረፍ የሚወዱ ሁሉ ተባብረው ቢሠሩ ዘላቂ የሰላም መሠረት መጣል እንደማያዳግት ገልጸዋል።”
ሴቶችና ሠላም
እንግዳችን ሴቶች በሰላም ጉዳይ መሳተፋቸው ትልቅ ጠቀሜታም አለው ይላሉ። እንዳንፀባረቁት ሃሳብ እርሳቸውን ጨምሮ ሁሉም ሴቶች ሰላምን ይሻሉ። ሴቶች በጣምም ለሠላም ይመቻሉ። በሰላም እጦት የሚደርሰው ችግርም ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ይልቅ በእጅጉ የሚጎዳው ሴቶችን ነው። ምክንያቱም ልጅን ትዳርን፣ አባትን፣ መመኪያ ወንድምን ማጣት ከፍተኛ ስብራት የሚያደርሰው ሴቶች ላይ ነው።
ስለዚህ በከፍተኛ ደረጃ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሴቶች የበለጠ ተነቃቅተውና ምክንያታዊ ሆነው መንቀሳቀሳቸው በአሁኑ ሰዓት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱን ሲገልፁም “በምጡም፤ በመውለዱም በማሳደጉም ከፍተኛውን ልፋት የሚያደርጉትና ለሰው ልጅ ሕልውና ትልቁን ዋጋ የከፈሉት ሴቶች ከሃምሳ ዓመት በላይ አልቅሰዋል። ከእንግዲህ በኀዘን መጎዳታቸው መቀጠሉ ግፍ ነው። ይህ ግፍ እንዲቆም ሴቶች ሊነቃቁና ሰላምን በማስፈን ሂደቱ ከፍተኛውን ድርሻ ሊይዙ ይገባል።” ይላሉ።
“እንደሚታየው የፀባችን መነሻ ፤የመካረሩም፤ የጭካኔውም ተግባር በአብዛኛው የጸብ ገመድ ጉተታውም ሲከናወን የቆየውና አሁንም እየተከናወነ ያለው በወንዶች ነው” በመጽሐፍ እንደተጠቀሰው ፈጣሪ የሚጠላቸውና የሚጸየፈው ተግባር በሰፊው በምድራችን ተከናውኗል ሲሉም ያክሉበታል።
እንደ ወይዘሮ ቅድስት አባባል ሴቶች ይህ ጉዳት እንዲቀንስ በጸሎትና በጎ ሃሳብ በማፍለቅ ትውልዳቸውንና ሀገራቸውን ሊጠብቁ ይገባል። ሴቶች ሠላምን መሻታቸውን ወደፊት መጥተው በየአደባባዩ እየወጡ እየተባበሩ ሰላም ለሀገራችን፤ ሠላም ለሕዝባችን የሚለውን ዓርማ ከፍ አድርገው በማውለብለብ አላስፈላጊ የሆኑ ፀብና ክርክሮች ከሀገራችን እንዲወገዱ ማድረግ አለባቸው።
እንደእርሳቸው አባባልም ሴቶች በአሁኑ ሰዓት ትልልቅ ደረጃ ላይ መድረሳቸውና ኃላፊነትን መውሰዳቸው ይህን መልካም ሃሳብ ለማስፈጸም እድል መመቻቸቱን ያሳያል። “ትክክለኛ ሰው በትክክለኛ ኃላፊነት ቦታ በሃይማኖትም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ እየተቀመጠ ሀገራችን ያላትን ባሕላዊና ሃይማኖታዊ እሴት በመጠቀም ከሕዝቡ ጋር እነኚህ ተቋማት ተናበው ለመሥራት ቢወስኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገራችን ካላት ችግር ሁሉ ነፃ ትወጣለች” ሲሉም ሃሳባቸውን ገልጸዋል።
ሴቶች የሰላም ሃሳብ ላይ በመሳተፍ ባሉበት ተቋም፣ በቤተሰባቸውና በማህበራዊ አገልግሎት ዙሪያ የነቃ ተሳትፎ ቢያደርጉ መልካም እንደሆነም ይመክራሉ። እንደ እንግዳችን ሴቶች የበርካታ በጎ እሴቶች ተምሳሌቶችም ናቸው። አብዛኛዎቹን መልካም እሴቶች ለትውልድ በማስተላለፍም አርአያነት አላቸው። ለምሳሌም በእርስ በእርስ ግንኙነቶች መካከል ያሉና ለመከባበርና ለመግባባት የሚጠቅሙ የትህትና እሴቶችን በፍቅር ማስኬድን በተመለከተ እርሳቸው ከእናታቸው፤ እናታቸው ከአያታቸው በሰዎች መካከል ሰላምን ለማስፈን ይጠቀሙባቸው የነበሩትንና ያወጉላቸውን መልካም እሴቶች ዛሬ ላይ በ60 ዓመታቸው ድልድይ ሆነው ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በእጅጉ እንደሚመኙ ገልጸውልናል። ይህ የእሴት ቅብብልም በደንብ ከተሠራበት በቀልን አስቁሞ ተባብሮ ለመሥራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
ፋይዳ
እንግዳችን እንደሚሉት እርሳቸው ስለሰላም ተግተው የሚሠሩበት የዓለም እርቅና ሰላም ግብረ ሠናይ ድርጅት ሊያከናውናቸው ያዘጋጃቸው በርካታና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ጥናታዊ ሰነዶች አሉት። ከላይ እንደተገለጸው ከዚህ ቀደም ውይይት ከተደረገባቸው የሰላም መድረኮች በተጨማሪ “ሕዝባዊ የውይይት ባሕል ለሰላም›› በሚል የተዘጋጀ ቋሚ የውይይትና የምክክር መርሐ ግብር፣ እንዲሁም ‹‹ምክንያታዊ ትውልድ ሰላምን ለማጽናት፣” የሚሉና ሌሎች ሰላምን ለማጽናት ፋይዳ ያላቸው የምክረ ሃሳብ ሰነዶች ስላሉ ብዙ መሥራት እንደሚቻል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዜጎች እርስ በእርሳቸው ተከባብረው ተዋደውና ተባብረው በመኖር ከራሳቸው፣ ከፈጣሪያቸው፣ ከመሰሎቻቸው፤ ከአካባቢያቸውና ከተፈጥሮ ጋር ታርቀው እንዲኖሩ ማበረታታትና ተገቢውን የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ይህንን ሃሳብ በአጽንኦት ማስተማር የድርጅቱ መርህ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ከ95 በመቶ በላይ አማኝ የሆነ ሕዝብ ላላት ሀገራችን ድንቅ የሆነ አደረጃጀት ካላቸው ተቋማት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ቢሠራ ፋይዳው እንኳን ለእኛ ለጎረቤት ሀገርም ሆነ ለዓለም የሚተርፍ ነው ብለዋል።
መልዕክት
እንደ እንግዳችን መልዕክት ሴትም፤ ወንድም፤ ልጅም፤ አዋቂም ሁሉም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ያለው የማኅበረሰባችን ክፍል ለሠብዓዊ መብት መከበር አብሮ መቆም አለበት። ሠብዓዊነት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል። ይህ ደግሞ በዜግነት ሁሉን ወደ አንድነት ያመጣዋል። ፈጣሪ ‹‹እርስ በእርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትዕዛዜ ይቺ ናት›› ብሎ ለሰው ልጆች የሰጠው ትእዛዝ ለሁላችን ነውና መዋደድ አለብን። የቀደመው አንጋፋ ሰላም ወዳድ ማኅበረሰብን ያፈራ የግብረ ገብ ትምህርት አሁንም ለትውልዱ መሰጠት አለበት።
ሀገርን በቡድን ሳይሆን ሰብዓዊ መብቶችን በጠበቀ የዜግነት ስሜት ማሳደግ ይገባል። ጃፓን ዛሬ ላለችበት የዕድገት ደረጃ የደረሰችው በጃፓን ውስጥ ያሉትን ጎሳዎች በአንድነት ይዛ ነው። ቻይናም ብዙ ጎሳዎች አሏት። ብዙ የበለጸጉ ሀገሮች በእኛም ሀገር ሆነ በአፍሪካ የሚታየው አይነት ችግር አይታይባቸውም። እኛ የዓድዋን ድል ስንዘክር ለብዙ አፍሪካውያን ነጻነት ተምሳሌትና ፈር ቀዳጅ ሆነን መታየታችንን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። ይህንን ድል የተጎናጸፍነውም አንድ በመሆናችን ነው።
ድህነት በሀገራችን ሲበረታ ተባብረን ልናሸንፈው ሲገባን ክፍተት መፍጠራችንና መለያየታችን ለወራሪ ጠላት በተዘዋዋሪ በፈቃድ እጅ ሰጥቶ መሸነፍን የሚያሳይ ነውና ሁላችን ባለን ጸጋ ይህን ችግር ለመፍታት ቆም ብለን ማሰብ ይገባናል። በውይይት የሚፈታ ችግር ሆኖ ሳለ በብዙዎች ቸልተኝነትና ራስ ወዳድነት የሀገር ሀብት ሲወድም ወገን ሲጎዳ ዳር ቆሞ ማየት ነገ ራስን የሚጎዳ በታሪክም ተወቃሽ የሚያደርግ ነውና ልናስብበትና ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።
ኢትዮጵያውያን የቋንቋ፤ የሃይማኖትና ሌሎች የተለያዩ ልዩነቶቻችን ውበቶቻችን ናቸውና አንድ ሕዝብ ሆነን መቀጠል አለብን። አንጋፋዎቹ የዓለም እርቅና ሠላም ግብረ ሠናይ ድርጅት መስራቾችና አባሎቻችን ከተለያየ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡና ለአንድ ኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር ያሳዩ መሆናቸውን መመልከት በቂ ይሆናል። ይሄን የአንድነት ተሞክሮም ለሀገር ተረካቢው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል። ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን” በማለት መልእክታቸውን ጠቅልለዋል። እኛም ከእንግዳችን ጋር የነበረንን ቆይታ በዚህ አጠናቀናል። በሌላ ንባብ እስከምንገናኝ በቸር ቆዩን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም