የኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት አባት ያልተነገረ ታሪክ

ከገብረዝጊ (ማከ) ቤተሰብ መካከል በስፖርት ጎልቶ ስማቸው የሚጠቀሰው የኦሊምፒክ ተሳታፊ የነበሩት ሻምበል አርአያ ገብረዝጊ ናቸው፡፡ እርሳቸው፣ በሰፊው የኢትዮጵያ የቦክስ ስፖርት አባት ተብለው የሚታወቁ ሲሆን፤ ይህ ስም ቢያንሳቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም፡፡ እኚህ ታላቅ ሰው የቦክስ ስፖርትን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተዋወቁ እና እንዲለመድ ያደረጉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም እኤአ በ1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ የቦክስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ እና መሪ ሆነው ተሳትፈዋል፡፡

ሻምበል አርአያ ህይወታቸው በበርካታ የክብር ዘመናት የተንቆጠቆጠ ቢሆንም፣ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ግን ብርቱ ሀዘንና መከራን አሳልፈዋል፡፡ ከእርሳቸው ጋር በመጨረሻ የተገናኘሁት እኤአ በ1997 መጀመሪያ አካባቢ በደቡብ ኤርትራ መፋንሶ በሚባል መንደር ልጎበኛቸው በሄድኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ሪፖርት የተጠናቀረው እርሳቸው ከነገሩኝ፣ ከሰጡኝ ሠነዶች፣ ከቦክስ ፌዴሬሽን ያገኘኋቸው መረጃዎች እንዲሁም ቀደም ሲል በአዲስ አበባ እኤአ 2019 ከቦክስ ስፖርት ባልደረቦቻቸው ጋር (በተለይ ከበቀለ አለሙ -ጋንቺ እና ኢንስፔክተር ታደሰ ኃይሌ ጋር) ካደረግኳቸው ቃለ መጠይቆች ነው፡፡

አርአያ ገብረዝጊ የተወለዱት እኤአ በ1923 በኤርትራ መፋልሶ ሰራዬ አካባቢ፣ ከመንደፈራ 7 ኪሎ ሜትር ከዋናው ከተማ አስመራ ደግሞ በስተደቡብ 60 ኪሎ ሜትር ላይ በሚገኘው ቦታ ነው፡፡ እድሜያቸው 18 ዓመት እስኪሞላ ድረስ በግብርና ሥራ ላይ የቆዩ ሲሆን፣ በመቀጠል ወደ አስመራ በመጓዝ በጣሊያኖች ቡና ቤት እና በሽያጭና በመሳሰሉት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡

መካከለኛ ቁመት እና መጠነኛ የሰውነት አቋም ቢኖራቸውም በተቃራኒው ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ጥንካሬ እና ብርታት ነበራቸው፡፡ (ሁኔታቸው ማይክ ታይሰንን ያስታውሰናል)፡፡ እሳቸው ይህ ችሎታ እንዳላቸው የተገነዘቡት ከጓደኞቻቸው ጋር በተለያዩ ጊዜያት የቡጢ ፍልሚያ በሚያደርጉበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ለቦክስ ልዩ ፍላጎት አደረባቸው፡፡ በወቅቱ የቦክስ ስፖርት ልክ እንደ እግር ኳስ፣ብስክሌት እና መኪና እሽቅድምድም ሁሉ በአስመራ በሚገኙ ጣልያኖች ዘንድ እጅግ ዝነኛ ነበር፡፡

ሻምበል አርአያ ጠንካራ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ መሆን በሕዝብ ዘንድ እውቅናና ክብርን እንደሚያስገኝ አስቀድመው በመረዳት፣ ፕሮፌሽናል ቦክሰኛ ለመሆን በወር 5 ሊሬ ለፈረንጆች እየከፈሉ ይሰለጥኑ ነበር፡፡ በኋላ ላይ በአዲስ አበባ ለቦክስ ስፖርት ባልደረቦቻቸው እንደተናገሩት፣ የቦክስ ስፖርት በአስመራ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በስፖርቱ ዝነኛ ለመሆን መጀመሪያ ከጣሊያኖች በኋላ ደግሞ ከእንግሊዞች ጋር መወዳደር እና ማሸነፍ ግድ ነበር፡፡ ነገር ግን ነጮቹ እንደ ሻምበል አርአያ ካሉ ጥቁሮች ጋር ለመፋለም ብዙም ፍላጎት ያልነበራቸው ከመሆኑም በተጨማሪ የተወሰኑት ከነጭራሹ ለመፋለም ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ በተለይ በጥቁር በቦክስ ተመትተው ፊታቸው ደም በደም ሆኖ በጓደኞቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው መታየት አይፈልጉም ነበር፡፡

ሻምበል አርአያ እና ጓደኞቹ የቦክስ ክህሎታቸውን በደንብ ካዳበሩ በኋላ፣ ይፋዊ ላልሆነ የወዳጅነት ፍልሚያ ነጮችን ጋብዘው የቦክስ ግጥሚያ ያደርጉ ነበር፡፡ ነጮቹም እንደፈሩት በቦክስ ድብደባ ምክንያት ፊታቸው ደም በደም ሆኖ ሲታይ ይመራቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የሀገሬው ነዋሪ ቦክሰኞች በጊዜው የነበረውን የዘረኝነት ሰንሰለት መበጠስ ያልቻሉ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያት ለትጋታቸው ምንም ዓይነት እውቅናም ሆነ የገንዘብ ሸልማት ያገኙም ነበር፡፡ እነዚህ የሀገሬው ነዋሪ የሆኑ ቦክሰኞች በየጊዜው ቅሬታቸውን እና አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ቅሉ ምንም ዓይነት ለውጥ አልነበረም፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ፣ አርአያን ጨምሮ ቢያንስ የተወሰኑ ቦክሰኞች መከራቸውን እና ችግራቸውን ሊፈታ የሚችል አማራጭ መፈለግ ጀመሩ።

ማግኘት የቻልኳቸው ሰነዶች እንደሚያሳዩት፣ አርአያ የሀገር ፍቅር ማህበርን እኤአ በ1942 በመቀላቀል በአባልነት እስከ 1952 ቆይተዋል፡፡ በ1940ዎቹ መጨረሸ አካባቢ አርአያ ከኤርትራ ለቀው በመውጣት የተሻለ ዕድል ይኖረኛል ብለው ወደገመቱበት ኢትዮጵያ ሀገራቸው ኑሯቸውን አደረጉ፡፡ መጀመሪያ ከአስመራ ወደ ደቀምሐረ በአውቶቡስ ተጉዘው፣ ከዛም ወደ አዲግራት በእግራቸው ተጓዙ፡፡ ወደ አዲስ አበባም ከትግራይ በመኪና ተጉዘዋል፡፡ በነበራቸው የቦክስ ችሎታ እና የሀገር ፍቅር ማህበር አባልነታቸው (ይህ ጊዜ ኤርትራ በእንግሊዞች አስተዳደር ሥር የነበረችበት እና ንጉሠ ነገሥቱ የኤርትራን ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ጉጉት ያደረባቸው ጊዜ ነበር፡፡) በዚህ ምክንያት አርአያ በቃኘው ሻለቃ የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ዘብ ውስጥ በቀላሉ የሚሊተሪ ፖሊስ አባል ለመሆን ቻሉ፡፡ በወቅቱ የዚህ ክብር ዘበኛ አባል መሆን ታላቅ ክብር ነበር፡፡ በሚሊተሪ የፖሊስ አባልነት ከነበራቸው መደበኛ ሥራ በተጨማሪ፣ ለፖሊስ ኃይሉ የቦክስ አሰልጣኝ ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡

እኤአ ከ1960 እስከ 1963 ድረስ በተካሄደው የኮሪያ ጦርነት ወቅት፣ ከቃኘው ሻለቃ ጋር ወደ ሩቅ ምስራቅ በመጓዝ የሚሊተሪ ፖሊስ መኮንን በመሆን አገልግለዋል፡፡ በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ጀግንነት ያሳዩ በመሆናቸው በወቅቱ የዘመቻው አዛዥ ከነበረው የአሜሪካ የጦር አዛዥ የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሻምበል አርአያ በቦክስ ስፖርት የላቀ የሙያ ህይወት የጀመሩት ከኮሪያ ዘመቻ ከተመለሱ በኋላ ነበር፡፡ በወቅቱ ከክቡር ዘበኛ ለቀው በመውጣት፣ ፖሊስ ሠራዊትን ተቀላቀሉ፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ የራሳቸውን የቦክስ ስፖርት ክለብን በአዲስ አበባ መመሥረት ችለው ነበር፡፡ ክለቡንም “ሳምሶን የቦክስ ክለብ” ብለው ሰየሙት፡፡ በወቅቱ ከፖሊስ ሠራዊትና ከክቡር ዘበኛ የሚመጡትን እንዲሁም ሌሎች ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ጨምሮ ያሰለጥኑ ነበር፡፡ በተለያዩ የቲያትር እና የሲኒማ አዳራሾችም ውድድር ያዘጋጁ ነበር፡፡ የቦክስ ስፖርት በእሳቸው ተነሳሽነት ምክንያት በተጀመረው እንቅስቃሴ ተወዳጅ እየሆነ መምጣት ችሎ ነበር፡፡ እንዲያውም ከዚህ ባለፈ “ በለው የቦክስ ክለብ ” እና “ የአዲስ አበባ ወጣቶች ክለብ” የተሰኙ ሁለት ተጨማሪ የቦክስ ክለቦች ተቋቁመው ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ክለብ በእስጢፋኖስ መንግሥቱ ባለቤትነት የተያዘ ነበር፡፡ እነዚህ 3 ክለቦች ቦክሰኞቻቸውን በመምረጥ በተለያዩ መድረኮች እንዲፋለሙ ያደርጉ ነበር፡፡ ሻምበል አርአያ እኤአ በ1964 ወደ ጃፓን ቶኪዮ ኦሊምፒክ የተጓዙት ብሔራዊ የቦክስ ቡድን መሪ እና ዋና አሠልጣኝ ሆነው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ደግሞ በኮንጎ በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በዚሁ ኃላፊነት ተሹመው ነበር፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላሳዩት ውጤታማ ሥራም የኢትዮጵያ መንግሥት የምስጋና ደብዳቤ አበርክቶላቸዋል፡፡

ሻምበል አርአያ ኦሊምፒክና መላ አፍሪካ ጨዋታዎችን ጨምሮ በበርካታ ውድድሮች መሳተፍ የቻሉ ቦክሰኞችን በሰልጣኝነት ዘመናቸው ማፍራት ችለዋል፡፡ ከነዚህ መካከል፡-

ከአዲስ አበባ ጥላሁን እሸቴ፣ አሰፋ አግነው ፣ ንጉሤ ኃይለጊዮርጊስ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአስመራ ደግሞ ተስፋሚካኤል፣ አደም ፋላ፣ ማሞ በየነ ይታወሳሉ፡፡ ሻምበል አርአያ አሰልጣኝና ቡድን መሪ ሆነው ወደ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ከዚያም ከአንድ ዓመት በኋላ እኤአ በ1965 መላ አፍሪካ ጨዋታ ላይ ካሳተፋቸው ቦክሰኞች መካከል አበበ መኮንንና ታደሰ ገብረጊዮርጊስ ከአዲስ አበባ፣ ታደሰ ገብረጊዮርጊስ፣ ንጉሤ ሀብተጊዮርጊስ፣ በቀለ አለሙ- ጋንቺ ከአስመራ ይገኙበታል፡፡

ሻምበል አርአያ ባገኙት ሰፊ ዝና እና ችሎታ ምክንያት፣ በእሳቸው እና በጣሊያን ታዋቂ በነበረው ቦክሰኛ ፍሬዝጊ ገብረሥላሴ መካከል በአስመራ ከተማ በ1960ዎቹ የቦክስ ውድድር ተካሂዶ ነበር፡፡ ፍሬዝጊ ወደ አስመራ ለውድድር ሲመጣ አርአያም ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ በመሄድ በውድድሩ ተገናኝተዋል፡፡ ውድድሩም በአቻ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው፡፡

ሻምበል አርአያ ከአሰልጣኝነት እና ከተወዳዳሪነት ባሻገር የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ኢንተርናሽናል የቦክስ የሪንግ ዳኛ እና ከሪንግ ውጭ ዳኛ ሆነው የሰሩበት ታሪክም አላቸው፡፡

ሻምበል አርአያ እና የኢትዮጵያ ቦክስ ቡድን በ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ላይም ተሳትፈዋል፡፡ ከሜክሲኮ በኋላ ግን፣ በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ይመራ በነበረው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሸን ከቦክስ ውድድር ወደ ማራቶን እና ሌሎች ሩጫ ስፖርቶች ትኩረቱን አዙሮ ነበር፡፡ ቦክስ ከሩጫ ውድድር ይልቅ ከፍተኛ አካላዊ ዝግጅት የሚያስፈልገው እና ከፍተኛ በጀት የሚፈልግ በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን የአካል ቁመና የተመቸ ስፖርት ላይሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም የቦክስ ስፖርት በኢትዮጵያ ያለው ተፈላጊነቱ እየቀነሰ ሄደ፡፡ የቦክስ ቡድኖች በከፍተኛ ድካም የሚገነቡ እና ከባድ ሥራን የሚጠይቁ በመሆኑ፣ ከመንግሥት በቂ ክትትል እና ድጋፍ ስላልተገኘ፣ የቦክስ የቡድን አባላቶች በየፊናቸው ተበታተኑ፡፡ ሻምበል አርአያም ከቦክስ ስፖርት በጡረታ በመገለል፣ በፖሊስ መኮንንነት ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ ሙያቸው በሐረር በመቀጠል ደግሞ ደሴ ተመድበው ነበር፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮ-ሶማሌ ጦርነትም ተሳትፈዋል፡፡ በመቀጠልም ወደ ሸዋ ፖሊስ ከዛም አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት በፖሊስ ሻምበልነት ተመደቡ፡፡ ከዚያ በኋላ ነውም ነው በጡረታ የተገለሉት፡፡

ሻምበል አርአያ ዮሴፍ የሚባል ልጅ ነበራቸው፡፡ ልጃቸው ጎበዝ እና ታታሪ የነበረ በመሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ሆኖም ይሰራ ነበር፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ወታደራዊው ደርግ ወደ ሥልጣን በመምጣት ተቃዋሚዎችን በተለይም ኢህአፓን ለማጥፋት የቀይ ሽብር ዘመቻ በመጀመሩ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያንን ለእስር እና ለሞት ተዳረጉ፡፡ ዮሴፍም የኢህአፓ አባል ነህ በሚል ተጠርጥሮ በአዲስ አበባ ከርቸሌ ወደሚባለው እስር ቤት ተወረወረ፡፡ የስኳር ህመምተኛ የነበረ በመሆኑ እና ደርግም መድኃኒቱን እንዳይወስድ የከለከለው በመሆኑ በሽታው በፈጠረበት የጤና መወሳሰብ ህይወቱ አልፋል፡፡ እስከሬኑ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ በ1982 በአራዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ ተፈፅሟል፡፡ ይህ ለሻምበል አርአያ እጅግ ልብ የሚሰብር ክስተት ነበር፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ ሕይወት ለሻምበል አርአያ ጥሩ አልነበረችም፡፡

በዚህ ምክንያት ሻምበል አርአያ ከእውነታው ውጪ በሆነ አስተሳሰብ በመያዝ፣ አብዝተው የአልኮል መጠጥ ይጎነጩ ስለነበር የአካልም ሆነ የአእምሮ ጤናቸው እያሽቆለቆለ ሄደ፡፡ ይከፈላቸው የነበረው ጡረታ በቂ ባለመሆኑም በአዲስ አበባ ከሚገኙት እጅግ ከተጎሳቆሉ መንደሮች መካከል በ4 ኪሎ በሚገኘው መኖሪያ ሰፈር ለመኖር ተገደው ነበር፡፡ በዚህም ቤተሰባቸው በተለይም እናታቸው ለተንስኤ ትተውለት ባለፉት እና በመፋልሶ በሚገኘው ቤታቸው እንዲኖሩ ወስደዋቸው ነበር፡፡ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ሻምበል አርአያ ወጣት የሆነች ሚስት ያመጡላቸው ሲሆን፣ ለተወሰኑ ዓመታትም አብራቸው ኖራለች፡፡ ነገር ግን በሚከፈላቸው ጡረታ ማነስ እና ምናልባትም ዕድሜያቸው በመግፋቱ ምክንያት በድንገት ጥላቸው ልትሄድ ችላለች፡፡

በህይወቱ ከፍተኛ ቦታ ለመድረስ የቻለው ታላቁ የቦክስ ስፖርት ሰው፣ ከኮሪያና ከጃፓን ርቆ በሚገኘው አንድ የአፍሪቃ መንደር ተወስኖ፣ ከአንድ ውብ የነበረች የዮኮሃማ፣ (ጃፓን) ፍቅረኛው በቶኪዮ ከተማ የተነሱት ፎቶግራፍ እያየ በስተ እርጅናው ብቻውን ይኖር ነበር፡፡ እንደበፊቱም ራሱን መሆን አልቻለም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ይህ በሕይወቱ ለሀገር ታላቅ ሥራ የሠራው ባለውለታ መሆኑን ሳያውቁና እርሱ ባልፈጠረው ከልጁ ጋር በተያያዘ ቀውስ ለዚህ ዕጣፋንታ መዳረጉን ሳይገነዘቡ፣ መጥፎ ነገር ሲናገሩትና ሲያጣጥሉት“እኔኮ ጀግና ወታደር ነኝ!!!” ብሎ ይመልስላቸው ነበር፡፡ ይህን መስማት ታሪኩን ለሚያውቁ ሰዎች እጅግ ልብ የሚሰብር ነበር፡፡ ቀደም ሲል ያገኘው ዝና፣ በዓለም ደረጃ ተሳታፊነቱና የሀገር ባለውለታ መሆኑን ዘንግቶት ነበር፡፡ ወጣትነቱን የሰዋለትና ያን ያህል የደከመበት ሙያ የሚገባውን አልከፈለውም፡፡

ሰለሞን ገብረጊዮርጊስ (ዶ/ር)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You