የአፍሪካ የነፃነት ምልክት ነው፤ አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች በአንድ ድምፅ ከፍ አድርገው የሚናገሩት ደግሞም የሚኮሩበት ድል ነው፤ ዓድዋ! ። 1888 ዓ.ም ሰውን በቆዳ ቀለም ለይቶ፤ ደካማና ኃያል፤ ገዢና ተገዢ፤ ባሪያና ጌታን ታሳቢ አድርጎ የመጣን ወራሪ ኃይል ያነገበውን የነጭ የበላይነት እሳቤን ከመሠረቱ የቀየረ ድል ነው። የድሉ ባለቤት የሆኑ የአባቶቻችን ልጆች እንደሃገር በዓለም አቀፍ መድረክ ባሉን ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ውስጥ የተሰጠን የአቻነት መንፈስ ባለፈ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ሥምረትና ቅቡልነት የዓድዋ ድል ዋነኛ ማዕከልና ማጠንጠኛ ስለመሆኑ ይነሳል።
ምንግዜም ኢትዮጵያውያንና መላው ጭቁን ሕዝብ የሚኮሩበት ፤ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ለተጎናፀፈችውና ለሚሰጣት ክብር ሁነኛ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ እንደሆነም ይነገራል። የዲፕሎማሲ ኩራታችን ምንጭ ሆኖ ሁላችንም በየደረስንበት ከአንገታችን ቀና ብለን እንድንሄድ ቀንዲል ሆኖ እያበራ ያለ ድል እንደሆነም አጠያያቂ አይደለም።
በዛሬው ልዩ እትማችንም የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከፍታ የነበረውን አበርክቶ እንዲሁም ድሉን መነሻ በማድረግ በዲፕሎማሲው መስክ መሠራት በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ጋር ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ጣሊያን ድል ከመንሳቷ በፊት በዓለም ላይ የነበራት ገፅታ ምን ይመስል ነበር ?
አምባሳደር እሸቴ፡- እንደሚታወቀው ከዓድዋ በፊት የነበረው ጊዜ የዘመነ መሳፍንት ማብቂያና ከዓለም ጋር በተወሰነ መልኩ ግንኙነት የጀመርንበት ወቅት ነበር። ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት ደግሞ በአካባቢና በጦር መሪዎች ማዕከላዊ መንግሥቱ ተዳክሞ የነበረበት፤ መልክ ያለው የውጭ ግንኙነት ያልነበረበት ጊዜ ነበር። ታላላቆቹ የአውሮፓ መንግሥታት አፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ወይም ደግሞ ባላቸው ቅኝ የመግዛትና የማንበርከክ ፍላጎት የየአካባቢ መሳፍንቶችን እየደገፉ የሚሠሩበት፤ የተበታተነ አይነት ሁኔታ ነበር። ወደኋላ ዘመን ገፋ አድርገን ስንሄድም ከውጭ ዓለም ጋር በተወሰነ መልኩ ራስን የማግለል ሁኔታ ነበር የሚታየው። በእርግጥ በአክሱም ዘመን መንግሥት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአዋሳኝ የዓለም ሀገራት ጭምር ተፅዕኖ የምትፈጥርና ገናና ሥም ያላት ሀገር ነበረች።
ከዓድዋ ወዲህ ያለውን ዲፕሎማሲ ስናነሳ ደግሞ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካ ላይ ተዘርግቶ የነበረውን ፅኑ ፍላጎት መረዳት ተገቢ ነው። በቅኝ ግዛት ቦታ ለመያዝ በነበረው የቅርምቱ ፉክክርና ውድድር እርስበርሳቸው እስከመጋጨት የደረሰቡት ጊዜ ነበር። ያንን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከተጠቀሙባቸው ስልቶች አንዱ መሬት ላይ ሆኖ ግዛቱን መቆጣጠር ነው። ሌላው በተፈፀሙ ውሎች ወይም በተፈረሙ ውሎች መሠረት የመቆጣጠር መብት እንዲኖራቸው (ሌጂትመሲ) በአንድ ሀገር ላይ የማድረግ አካሄድ ነበር። ጣሊያኖቹም የተከተሉት ይሄኛውን መንገድ ነው። ከዓድዋ በፊት መሬት ለመውረርና ለመስፋፋት ሲሞክሩ በገጠማቸው ተግዳሮት ምክንያት የውጫሌን ስምምነት መፈረም ነበረባቸው።
እንግዲህ በዚያ ገና ለጋ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ማዕከላዊ መንግሥት እና የውጭ ጉዳይ የውጭ ግንኙነት አያቶቻችን ስምምነቱን ዓላማ ተረድተው መግባባት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል። ይህም ሲባል ኢትዮጵያ በጣሊያን ቁጥጥር ስር አለመሆንዋንና ራሷን የቻለች ነፃ ሀገርና መንግሥት መሆንዋን በገሃድ ማሳወቅ ችላለች። ያንን ደግሞ ጣሊያኖቹ ባለመቀበላቸውና ትልቁ ዓላማቸው ባለመሳካቱ ሁለተኛ አማራጭ መከተል መረጡ። በመሣሪያ ኃይል ኢትዮጵያውያንን አምበርክከው ሰብረው የኢትዮጵያ ግዛትን ለመቆጣጠር የሞከሩት ሙከራ ሳይሳካ ቀረና ዓድዋ ላይ በተከፈለ መስዋዕትነት እኛም የዛሬው ነፃነታችንን ይዘን ቆየን።
አዲስ ዘመን፡- ጀግኖቻችን በዓድዋ ላይ ጣሊያንን ድል መንሳታቸው ለዲፕሎማሲው የነበረው አበርክቶ እንዴት ይታያል?
አምባሳደር እሸቴ፡- ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን ድል መንሳታቸው በዓለም ላይ መነቃቃት ፈጥሯል። ቀድሞ የነበረው እኩልነትን ወይም ሚዛኑን ያልጠበቀ፤ የራስን ፍላጎት ሌላ ላይ የመጫን የምዕራባውያኑ እሳቤ እንዲመክን በማድረግ ረገድ የላቀ አበርክቶ ነበረው። ምክንያቱም ደግሞ አፍሪካውያን ከአውሮፓ ጋር እኩል አይደሉም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል። ዓድዋ ነፃ ያወጣው እኛን ጥቁር ሕዝቦችን ብቻ ሳይሆን መላውን ጭቁን የዓለም ሕዝብን ጭምር ነው።
በቅኝ ገዢዎች ስር የነበሩ ሌሎች ሀገራት እኩል ነፃ ሕዝቦች ነን፤ ነፃ መንግሥት ነን የሚል እሳቤ እንዲኖራቸውና በዲፕሎማሲው ዘርፍ እኩል የመደራደር ብቃት እንዲኖራቸው ያደረገ ግዙፍ ድል ነው። እናም በከፍተኛ ደረጃ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ለውጦታል። በዓለም ላይ ኢትዮጵያ ምንአይነት ሀገር እንደሆነች፤ ምን አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ሕዝብ እንዳላት፤ የነፃነት ፣ የእኩልነት ፣ የሀገርነት መርሆችን ለዓለም ማሳየት የቻለ ድል ነው።
እንዳውም በቁንፅል ደረጃ ብቻ የሚታይ አይደለም። ይህ ድል በሌሎች ትርክቱን በደንብ በሚሠሩት ተመሳሳይ የተገፉ ሕዝቦች ለምሳሌ በዓረቦች ወይም በእስያውያን የተገኘ ድል ቢሆን እኛ ባልኮሰኮስነው መልክ አይሆንም ነበር። የፈጣሪ ፈቃድ ሆኖ አሁን ላይ ግልፅና ጎልቶ በሚታይ ሁኔታ ስለዓድዋ የምንናገርበት ዘመኑ ደርሷል። የዓድዋ ድል መታሰቢያ ማዕከል መገንባቱ በራሱ ለዚህ አመላካች ነው። በአጠቃላይ ድሉ ለዲፕሎማሲያችን ከፍታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ነበረው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነት እንዲኖራት በማድረግ ረገድስ የድሉ ሚና እንዴት ይገለፃል?
አምባሳደር እሸቴ፡– ዓድዋ ሌላው ይቅርና በሥነ- ልቦናችን ውስጥም እንዲገነባ ያበረከተው አስተዋፅዖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ኢትዮጵያውያን ከማንኛው ሃገር ጋር እኩል ነን የሚለውን ሥነ-ልቦና የገነባነው በዓድዋ ምክንያት ነው። ያም በመሆኑ ነው እኮ ልክ ከዓድዋ ጦርነት በኋላ ተከትሎ የመጣው የአውሮፓ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥታት ጋር ቁጭ ብለው እየተደራደሩ እኮ ነው እንደአቻ መንግሥታት አብረን እንሥራ፤ በንግድና በመሳሰሉ የኢኮኖሚ ጥቅሞች እንተባበር የሚለው ነገር ቅቡልነት እያገኘ የመጣው። የዲፕሎማቲክ ልዑኩንና ተልዕኮ ይዞ የመጣው ዓድዋ ነው።
ዓድዋ እኩልነትን ፈጥሯል ከሚባለውም በላይ የሚታይ ነው። ምክንያቱም ደግሞ ኢትዮጵያውያን እኩልነታቸውን አረጋግጠው ብቻ አይደለም የቀረው፤ ሌሎች እንዲማሩበትም ነው ያደረገው። በወቅቱ ቅኝ ግዛት ገና እየተንሰራፋ ነበረ። የነፃነት ትግልና እና ፓንአፍሪካኒዝምን ማቀንቀን ተጀመረ። ስለዚህ እኛ የእኩልነት መንፈስን፤ ኢትዮጵያ በወቅቱ እንደበለፀጉ ሀገራት ነፃነትና መብቷን የምታስጠብቅ፤ ተደራድራ የምታገኝ መሆንዋን ከማሳወቅ አልፎ ለሌሎች ትምህርት ሆኗል።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሊግ ኦፍ ኔሽን ምሥረታ የራሷን በጎ አሻራ እንድታሳርፍና አባል ሆና ከሌሎቹ ታላላቅ ሃገራት እኩል ቁጭ ብላ ስለሠላም ለመደራደር አስችሏታል። ግልፅ በሆነ መንገድ የእኩልነት ሥነ- ልቦናችን ከፍ እንዲል ያደረገ ነው።
አሁን ላይ ማንኛውም የሰው ዘር በቀለሙ፤ ወይም በኢኮኖሚ ደረጃው የማይለያይ መሆኑን መረዳት የሚቸግራቸው አልያም መቀበል ያልቻሉ፤ ቅኝ መገዛታቸው በፈጠረባቸው ተፅዕኖ ምክንያት የበታችንነት መንፈስ የሚሰማቸው አሉ። ወደ እኛ ሲመጣ ግን ይህ ስሜት የለም። አሁን ላይ ቀርቶ በወቅቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን የነበራቸው የእኩልነት ሥነልቦና አስገራሚ ነበር።
እኔ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በ1985 ዓ.ም ላይ የናሚቢያ ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያውያን ከነበራቸው በራስ የመተማመንና የእኩልነት ጠንካራ ሥነልቦና ይደነቁ ስለነበር ከኢትዮጵያ የተለያዩ ባለሙያዎችን በመውሰድ ከቅኝ ግዛት ስሜት መውጣት ያልቻለውን ሕዝባቸውን ይህንን የእኩልነት መንፈስ እንዲረዱ ለማስቻል የሄዱበት መንገድ እንደነበር አስታውሳለሁ።
በወቅቱ ሕዝባቸው ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎቹ ጋር እኩል የመሆን ስሜትን በራሱ መማር ተቸግሮ እንደነበር ነው የነገሩኝ። ይህ ምንያህል የሥነልቦና ጫና አሳድረውባቸው የሚያስረዳ ነው። ይህ የበታችነት መንፈስ አሁንም በአንዳንድ ሀገራት ሕዝቡ አዕምሮ ተሰንቅሮ ይስተዋላል፤ ወደ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሲመጣ ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው፤ በየጊዜው በሚገጥሙን ነገሮች ተፅዕኖ ሲደረግብን፤ ሁኔታው ከመንገድ የወጣ ብሔራዊ ክብርን የሚነካ ሲሆን ቅድመ ሁኔታዎችን አንቀበልም።
በተለይም ነፃነትንና እኩልነትን የሚጋፋ ከሆነ ሁሉም የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ቀድሞ ከነበሩት ዲፕሎማቶች ጀምሮ ዛሬ የሚገቡ አታሼዎች ድረስ የሀገርን ክብር የሚነካ ነገር ላይ እንደነብር የሚያስቆጣ ስሜት ነው በውስጣችን ያለው። ይሄ ዓድዋ የሰጠን በረከት ነው ብዬ አምናለሁ። ከዚያ በፊት ደግሞ ለውጭ ተፅዕኖ የተጋለጥንበት ሁኔታ ስለሌለ ይህንን የተገዢነት ስሜት አናውቀውም። ደግሞም መሠረት ባይኖረው ኖሮ ዓድዋም ሊመጣ አይችልም ባይ ነኝ።
ዓድዋ ዋናው ነገር ኢትዮጵያ መንግሥት ያላት ሉዓላዊ ሀገር መሆንዋን እንዲቀበሉ ማድረጉ ነው። በወቅቱ ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ቅኝ ገዢዎቹ ከፋፍለው በያዙት ሀገሮች ስያሜ ያላቸው ነበሩ። የሉዓላዊነት መገለጫ ሀገሩም መንግሥቱም ነው። ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በቴክኖሎጂ የተስፋ ጫማ ባናደርግም፤ በባዶ እግራችንም ብንሆን፤ ነፃነታችንን ለማስከበር ወደኋላ አንልም።
በሊግ ሆፍ ኔሽን ተደራድረን እንደማናቸውም ነፃ ሀገራት ድምፃችንን አሰምተን ነው አባል የሆነው። ያንን በራስ የመተማመን ብቃት የጎለበትነው አባቶቻችን ዓድዋ ላይ ባጎናፀፉን ድል ነው። ያንን እኩልነት ስሜት ብቻ ሳይሆን በሚጨበጥ፤ በሚዳሰስና መለካት በሚቻል መልኩ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አካል መሆን ችላለች። በአጠቃላይ ዓድዋ እንደሕዝብ ወይም እንደሰብዓዊ መብት ብቻ ሳይሆን እንደሀገር ያንን እንድናገኝ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መጎልበትስ የዓድዋ ሚና ምን ነበር?
አምባሳደር እሸቴ፡– የቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖ እየበረታ ሲመጣ የዓድዋ ድል ደግሞ ጭቁኖች ያንን የቅኝ ግዛት ቀንበር ከላያቸው ላይ የማራገፍ ፍላጎቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል። በአውሮፓም፤ በሰሜን አሜሪካም ንቅናቄዎች ነበሩ። የባሪያ ንግድ ከተወገደ በኋላ የሉዓላዊነት ጥያቄና የቀለም እኩልነት ጥያቄዎችና ቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ የማለት ስያሜዎች የተጠነሰሱበት ዘመን ነበር። ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ይህንን ድል በሚያገኙበት ጊዜ በጣም ከፍተኛ ጉልበት ነው የሰጡት። ለፓን አፍሪካኒዝምና ለጥቁሮች የነፃነት ንቅናቄ ስሜት ዝም ብሎ ከመብላላት ወደ አደባባይ እንዲወጣና የነፃነት ማረጋገጫ መሠረት ሆኖ ጎልቶ እንዲወጣ፤ መደፋፈር እንዲፈጠር አድርጓል፤ የይቻላል ስሜት ፈጥሯል።
ራስን ነፃ ማውጣትና ጥቁር ሕዝቦች እንደማንኛውም ሌላ ሕዝብ እኩል ናቸው የሚለውን ስሜት በጣም አጠናክሮታል፤ የማይቆራረጥ እንዲሆን አድርጎታል። ተቋማዊ እንዲሆን አድርጎታል። የተለያዩ የነፃነት ንቅናቄዎች በተደራጀ መልኩ እንዲጀመሩ አድርጓል። በዚያው መንፈስ እየቀጠለ ሄዶ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ የሚወጡባቸውን ተቋማት ፤ አቋሞች፤ አደረጃጀቶች እየፈጠሩ ወደ ነፃነት እንዲጓዙ መበረታታት ፈጥሯል።
ግን ደግሞ ያንን ብቻ አድርጎ አይደለም የቀረው፤ ኢትዮጵያን እንደምሳሌ እያዩ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከመቼው ጊዜ በላይ እንዲጎለብት አድርጓል። ሰውን ለነፃነት የሚቀሰቅስ፤ የሚያነቃቃ መንፈስ ፈጥሯል። ያ መንፈስ ደግሞ መሠረት እንዲኖረው ያደረግነው እኛ ነን። በእ.ኤ.አ 1963 ነፃ የወጡትን የአፍሪካ ሀገራት የተለያየ የመከፋፋል ዝንባሌ ነበር ፤ያንን አልፈው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት የፓንአፍሪካኒዝም አስተሳሰብና መንፈስ ማዕከል እንዲኖረው አድርጓል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አፍሪካ አሁንም ቢሆን በእጅ አዙር የሚደረጉ የቅኝ አገዛዝ ዝንባሌዎችና ጫናዎች እንዳሉባት እሙን ነው፤ ይህንን ጫና በመከላከል ረገድ ምን ሊሠራ ይገባል ይላሉ?
አምባሳደር እሸቴ፡- እንግዲህ የፖለቲካ ቅኝ አገዛዝ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እየከሰመ መጥቷል። ትልቁ መከራና ፈተና ሆኖ የቀጠለው የባሕልና የኢኮኖሚ ቅኝ አገዛዙ ነው። ታዳጊ ሀገራት በተለይ የአፍሪካ አህጉር ያለምዕራባውያኑና ቀድመው ከበለፀጉት ሀገሮች ድጋፍና ትብብር ውጪ የማደግ ተስፋ የለውም ፤ ጨለማውና ተስፋቢሱ አህጉር እያሉ የቀጠሉት ተፅዕኖ ነው ትልቁ ፈተና። በማዕድናት፤ በንግድ የሚያደርጉት ብዝበዛ አለ።
የየሀገራቱ ሕዝቦች ተጠቃሚ ሳይሆኑ ለራሳቸው እየወሰዱ የሚበለፅጉበት ሁኔታ ነው ያለው። ሌላው እንደካንሰር የሚታየውና አንዴ ከተተከለ ለማውጣት አስቸጋሪ የሚሆነው የውጭ እርዳታ የሚባለው ነገር ነው። በውስጡ የሰብዓዊ ድጋፍ፤ የልማት ድጋፍ አለው፤ የወታደራዊ ድጋፍና የመሳሰሉትን ልንጠቅስ እንችላለን። እነዚህ በሙሉ የእጅአዙር ቅኝ አስተሳሰብ ወይም የጥገኝነት አስተሳሰብና ሥነልቦና እንዲጠናውት አድርገዋል። ነፃ የወጡ ሀገራት ውስጥ ያሉት ተቋማት ራሳቸው ጠንክረው እንዳይቆሙ የሚያደርግ ነው። ይህም ለኒዮ ኮሎናሊዝም በር ይከፍታል ማለት ነው።
ስለዚህ ይህንን ለመቋቋም ልንሠራቸው የሚገባቸው ሥራዎች አሉ። በዓድዋ ጦርነት ላይ ሕዝቡ እንዲሳተፍ ጥሪ ሲቀርብለት ወታደራዊ ሥልጠና አልወሰደም፤ ጠመንጃ ሁሉም የለውም፤ ስንቅ የለውም፤ ቤተሰብ አለው፤ ሀገርን፣ ምድርን ፣ ምሽትህን ሊነጥቅህ ጠላት መጥቷል፤ ተነስ ሲባል ምንም ሳያቅማማ ነው የተመመው። አሁን ደግሞ እንዲህ አይነት የረቀቀ ተፅዕኖ መውጣት የምንችለው በሥራ ነው። መሥራት፤ መመራመር ፤ ማወቅና በተለይ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ክብርን የሚነካና የሚያዋርድ፤ የበታች የሚያደርግ ነገር መሆኑን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል።
እርግጥ እርዳታ ሕይወት ያቆያል፤ ትክክል ነው፤ ሆኖም የተወሰነ ጊዜ ተቸግረን ከዚያ ውስጥ መውጣትና ራስን መቻል ያስፈልጋል። ለአሁኑ ትውልድ ይሄ እንደከባድ መስዋዕትነት ሊቆጠር ይችላል ግን ወላጆች ተቋማት እና መገናኛ ብዙኃን ይህንን ለመለወጥ ሰፊ ሥራ ሊሠሩ ይገባል። የሰውን ልጅ ነፃነት ሊረጋገጥ የሚችለው በመሥራት እንዲሁም በኢኮኖሚ ተወዳዳሪ መሆን ሲቻል ነው። በዚህ መልክ ክብርና ነፃነት ማስጠበቅ ያስፈልጋል።
የዓድዋ አባቶቻችን ገድል እና በጦርነቱ ያገኙት ውጤትም ከሕሊና ወቀሳ ድነን እነሱን እንድንዘክር የሚረዳን ከጥገኝነት ስንላቀቅ ነው። እናም የኒዮ ኮሎናሊዝም ሆነ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ብዙ መንገዶችን የማስከፈትና አስቀድሞ ያደገውን የዓለም ክፍል የበለጠ ለማበልፀግ የሚደረገውን ሩጫ መቋቋም የሚቻለው በመንቃት፤ በመሥራት፤ በመማርና በመመራመር ነው የሚለው መልዕክት ተገቢ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ዓድዋ ጥሎት ካለፈው አበርክቶ አኳያ በዓለም ላይ ድሉን ማስተዋወቅ አለመቻሉ ይነሳል፤ እርሶ በዚህ ላይ ያሎት ምልከታ ምንድን ነው? ምንስ ሊሠራ ይገባል ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር እሸቴ፡– ልክ ነው፤ በዓድዋ ከተከፈለልን ዋጋ አኳያ የሚገባውን ያህል አሳውቀነዋል ብዬ አላምንም። እንደሚታወሰውም፤ ቀደም ባሉት ዓመታት እንዲሁ በተለሳለሰ መንገድ እያከበርነው እንሄድ ነበር። ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ ደግሞ ጨርሶ የመፋዘዝ እና የመደብዘዝ ነገር ነበር። በየመሐሉ ደግሞ በጣም አውርደነው ድሉ የእኛ እስከማይመስል ድረስ የተገኘንበት ሁኔታም የማይካድ ነው።
ይህንን የሚያክል የዓለም ሕዝቦችን እኩልነትና ነፃነት ያረጋገጠ መስዋዕትነትና ድል አራክሰነው፤ የአካባቢ ጉዳይ አድርገነው በጣም በሚያሳንስ ሁኔታ ውስጥ ገብተን ነበር። በነገራችን ላይ እኛ የድሉ ባለቤት የሆንን ሕዝቦች ይህንን ሁሉ ስናደርግ ሌሎቹ ጋር ግን ይከበር ነበር።
ደቡብ አፍሪካ ያከብሩታል፤ ጎረቤታችን ኬኒያም ይዘክሩታል፤ በጽሑፎቻቸው ያወጡታል፤ አረሱትም ነበር። ካሪቢያንና ጥቁር አሜሪካውያን በደንብ በደመቀ ሁኔታ ነው የሚያከብሩት። በተቃራኒው ደግሞ እኛ የድሉ ባለቤት የሆንን ሕዝቦች በራሳችን ላይ ይሄ አይነት ጥፋት ነው አድርሰን የነበረው።
በእርግጥ ይህም አይነቱ የተሳሳተ ምልከታ የሚመጣው የተወሰነ ፍላጎት ባላቸው ኃይሎች እንደነበር ይታወቃል። ይህ ቡድን ታዲያ በሕዝቡ ዘንድ በድሉ ዙሪያ የጋራ መግባባት እንዳይኖር፤ የአመለካከት ችግር እንዲፈጠር በማድረግ ትልቁን ድላችንን አሳንሰን እንድናይ በመደረጉ ነው። ያ የብዙዎች ቅሬታ የነበረው ጉዳይ አሁን ላይ ምላሽ እያገኘ ነው፤ የዓድዋ ድል የአርበኞቹ የአያቶቻችን ገድል ቋሚ ማስታወሻ ቆሞለታል፤ ማዕከል፤ ጥናት ምርምር ለማድረግ የተሻለ እድል አለ። ይሄ ማለት ዲፕሎማቶቻችን ውጪ ወስደው የሚሠሩበት፤ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ግብዓት ይወጣል ማለት ነው።
አንዱ ቱሪስት የመሳቢያ መሣሪያም ነው። ሌሎቹ ሃገራት እኮ አደባባይ የተደረጉ ሰልፎች እንደቱሪስት መሳቢያ አድርገው ያስተዋውቋቸዋል። ለምሳሌ ሙባረክን የጣለው የታሃሪር ስኩዌር ሰልፍ የተካሄደበትን አደባባይ ግብፆች አሁን ላይ እንደአንድ የቱሪዝም መዳረሻ ተጠቅመው ገቢ እያገኙበት ነው። ይህ ትንሽ ለዓለም ጆሮ የሚቀርብ ነገር ሲገኝ ኢንቨስት ተደርጎበት የሚሠራ መሆኑን ያሳያል። ይህንን ያህን የተደበቀ ድል አውጥተን መሥራት ነው ያለብን።
በዚህ ረገድ ዘንድሮ ከሌላ ጊዜ በተለየ በሚሲዮኖቻችን ደመቅ ባለ ሁኔታ ይከበራል። ከዚህ በኋላ ባላ ጊዜ ግን በአግባቡ እየታቀደ ማዕከሉንም ሰዎች እየመጡ እየጎበኙት፤ ቦታው ድረስ እየሄዱ በማየት፤ እዛ የሚካሄደው ዩኒቨርስቲና ምርምር እያደገ ዓድዋ የነፃነት መሠረት የተጣለበት ቦታ መሆንዋን ዓድዋና የጦርነቱ አካባቢዎች የምናሳውቅበት ሊሆን ይገባል። በነገራችን ላይ ይህንን ማድረጋችን የኢኮኖሚ ጥቅምም ያመጣል። የክብር፤ የታሪክ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ቱሪዝምን በማስፋፋት የኢኮኖሚ ጥቅምም ጭምር የሚያመጣ ስለሆነ ብዙ ሥራ ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ግን ዲፕሎማቶች ለሚሠሩት ሥራ ዋና መሠረት የሚሆነው ሀገር ውስጥ የሚሠራው ሥራ ነው። አስቀድሜ እንደገለፅኩልሽ በጥናት በምርምርም በሌሎችም ጉዳዮች የምንሠራው ሥራ ለአባቶቻችን ድል ያለንን ክብርና የሃገራችን አንድነትና ነፃነት አስጠብቀን በመቆየት ነው ዲፕሎማሲያችንንም ማሳደግ የምንችለው። ደግሞም ይህ ሥራ የዲፕሎማቶች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ለሀገሩ አምሳደር ሆኖ የየበኩሉን አስተዋፅዖ ሲያበረክት ነው። ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አባቶቻችን ስለሠሩት ድል ማንሳትና ሃገራችንን ማስተዋወቅ የሁላችን የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አምባሳደር እሸቴ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2016 ዓ.ም