የተተኪ ስፖርተኛ ምንጭ ከሆኑ ስፍራዎች መካከል የትምህርት ተቋማት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚዘልቁ የስፖርት ውድድር መድረኮች በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ሀገርን መወከል የቻሉ በርካታ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚቻል ይታመናል፡፡ ይሁንና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የሚካሄደው ዓመታዊ ውድድር እየተቀዛቀዘ ሄዶ እስከ መቋረጥ ደርሷል፡፡
በርካታ ስፖርተኞችን በማፍራትና ደማቅ ፉክክሮችን በማስተናገድ ከሚታወቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አንጋፋው የትምህርት ተቋም ከመማር ማስተማር ባለፈ በስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍሉ በርካታ ባለሙያዎችን በተለያዩ ዘርፎች በማፍራት በኢትዮጵያ ስፖርት ጥናትና ምርምርን ጨምሮ በርካታ ተግባራት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ተማሪዎች በአካልና በአእምሮ ብቁ እንዲሆኑም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በማሳተፍ ደማቅ ውድድሮችን እንደሚያከናውን ይታወሳል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተማሪዎቹ ውጪ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹን ለሌሎች ስፖርተኞች ልምምድ በመፍቀድም ምስጉን ነው፡፡ ይሁንና ለዓመታት ይህ ሁኔታ ተቋርጦ የስፖርት ሜዳዎቹም ጭር ብለው ከርመዋል፡፡
አሁን ግን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ ተቋርጠው የቆዩ የተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተመለሱ ሲሆን፤ በተማሪዎች መካከል የሚካሄደው የስፖርት ውድድርና ፌስቲቫልም ከቀናት በኋላ በአዲስ መልክ የሚጀመር ይሆናል፡፡
ከየካቲት 29/2016 ዓ.ም አንስቶ ለ15 ቀናት ይዘልቃል የተባለው ይህ ውድድር በ5 የስፖርት ዓይነቶች ማለትም በፓራሊምፒክ፣ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቅርጫት ኳስ እና ቮሊቦል ውድድሮችን እንዲሁም የተለያዩ ፌስቲቫሎችን ያከናወናል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ስር ባሉት ኮሌጆች መካከል የሚከናወነው ውድድሩ በወንዶች እግር ኳስ 12 ኮሌጆች በአራት ምድብ ተከፍለው የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ በሴቶች ደግሞ አራት ኮሌጆች የእግር ኳስ ውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ፡፡ በአትሌቲክስ 10 የወንድና 6 የሴት ቡድኖች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በቮሊቦል ደግሞ 9 የወንድ እና 3 የሴት ቡድኖች ተመዝግበዋል፡፡ በፓራሊምፒክ 3 የወንድና 2 የሴት ቡድኖች እንዲሁም 7 የቅርጫት ኳስ ቡድኖች ውድድሩን የሚያደምቁት ይሆናል፡፡ ውድድሮቹ የሚከናወንባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ምቹ በሆነ ሁኔታ ተጠግነው መዘጋጀታቸውም ተገልጿል፡፡
ውድድሩን በሚመለከት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶክተር)፤ መርሀ ግብሩ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ ከተደረጉ ለውጦች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያ ስፖርት ተተኪ ስፖርተኞችን በማውጣት ያላቸው ሚና ይታወቃል፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ባለፉት 73 ዓመታት የራሱን አበርክቶ አድርጓል፡፡ ባለፉት ዓመታት ሜዳዎች የስፖርት እንቅስቃሴ ስላልነበረባቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነበሩ ነገር ግን ከተለያዩ አጋር ተቋማት በተደረገው ድጋፍ ፌስቲቫሉ ተዘጋጅቷል፡፡
ተማሪዎች ሁለንተናዊ ስብዕናቸው አእምሯቸው፣ ጤናቸው እና የአካል ብቃታቸው የዳበረና የተሟላ ሁሉ አቀፍ ሆነው በቀጣይ የሀገር መሪዎች፣ ተመራማሪዎችና የተስተካከለ ስብዕና እንዲኖራቸው ስፖርት መሰረት በመሆኑ ይህ ፌስቲቫል ሊዘጋጅ እንደቻለም ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ዓመት በተወሰኑ ስፖርቶች ብቻ ውድድሮች የሚደረጉ ሲሆን፤ በቀጣይ ግን በየካምፓሶቹ ያሉ የስፖርት ሜዳቸውን በማስፋፋት፣ በመጠገንና ደረጃቸውን በማሻሻል ተማሪዎች በፌስቲቫል ብቻም ሳይሆን በስፖርት ተሳትፈው ጤናቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም ስፖርት የዩኒቨርሲቲው ባህል እንዲሆን እንሰራለን፡፡ ለዚህም ስፖርቱን የሚመሩት መንግሥታዊ ተቋማት እና የስፖርት ማህበራት አብረዋቸው እንዲሆኑም ጠይቀዋል፡፡
የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፣ አንጋፋውና በኢትዮጵያ ታሪክ የማይሻር አሻራ ያለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደቀደመ ከፍታው ለመመለስ በሚያደርገው ጉዞ ስፖርትን ማካተቱ የሚያስመሰግነው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስፖርት ከሚያድግባቸው ስፍራዎች ቀዳሚው ትምህርት ቤት ነው፤ በመሆኑም ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ከዚህ ትምህርት መውሰድ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲም ንቁ፣ ተወዳዳሪና አሸናፊ ዜጋ መፍጠር አለበት የሚል አቅጣጫ ያስቀምጣል፤ የከፍተኛ ተቋማት ስፖርት ፌስቲቫልም ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በመሆኑም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ይካሄድ የነበረው የስፖርት ውድድር በቀጣዩ ዓመት እንዲካሄድ በእቅድ መያዙንም አመላክተዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም