እንባ

የትም ቦታ ምንም ነው። ሞልቶ ከፈሰሰ እልፍ ዘመናት ተቆጥረዋል። ልብ የሚወደውን ያክል መጥላትም እንደሚችል ቆይቶ ነው የገባው። አንዳንድ እድሎች አሉ፣ አንዳንድ ቀኖች አሉ፣ አንዳንድ አጋጣሚዎች አሉ የሚደገሙ መስለው ከታሪክ የሚሰወሩ። ስንስቅ..ስቀን ስንሰነብት ያሳቁንን ልቦች፣ ያሳቁንን ነፍሶች እንረሳለን። በደረቅ ፊት ላይ፣ በደብዛዛ ገጽ ላይ ሳቅን የዘሩልንን ጸጋዎቻችንን እንዘነጋለን።

አሁን ሌላ ነው..ሩታን እያሰበ የሚኖር። አሁን ሌላ ነው ከሩታ ጋር የሆኑትን፣ ያደረጉትን፣ ያወሩትን እያሰበ የሚኖር። እንደ እሷ ደስታን የሰጠችው፣ እንደ እሷ ግፍ የሰራባት ሴት የለችም። በመውደዷ ተማምኖ፣ በፍቅሯ ታብዮ በሴትነቷ ላይ እንደፈለገ ሲሆን ነበር። ብዙ ጊዜ አስቀይሟት ታርቃዋለች። ብዙ ጊዜ በድሏት ይቅርታ ብለዋለች። ብዙ ጊዜ የማይሆን ነገር ሲያደርግ በመተው አልፈዋለች። ነፍሱ ከስህተት የማትማር..አንድ አይነት ስህተትን ስትደጋግም የምትኖር ነበረች። አንድ ቀን ግን ሌላ ሆነችበት..አንድ ቀን ግን ከሚያውቃት ርቃና መጥቃ አገኛት። ያን ቀን፣ ያን ሴትነቷን አይረሳውም..

እያጨሰ ወደተቀመጠበት ቦታ እስከዛሬ ባልተራመደችው የዝግታ ርምጃ ተራምዳ አጠገቡ ቆመች። ከሚያቦነው ጭስ ጋር እየተጫወተ አላያትም ነበር። ሲያጨስ አያውቃትም። ሲጠጣ ትዝ አትለውም። እሱን መልካም ወንድ ለማድረግ የለፋችውን ልፋት ለሌላ ብትጠቀመው እሄኔ አለም ከሚያውቃቸው ስኬታማ ሴቶች ውስጥ አንዷን ሆና በቴሌቪዥን ያያት ነበር።

‹እኔ የሌለሁበት ዓለም ናፍቆሀል አይደል? ጠየቀችው።

ዝም አላት። ሲያጨስና ሲጠጣ አያውቃትም..

‹አንድ ሴት የምትጎዳው ሴት ማለት ምን ማለት እንደሆነች የማያውቅ ወንድ ላይ ስትወድቅ ነው። የአንድ ወንድ የስልጣኔ ደረጃ የሚለካው ለሴት ልጅ ባለው ክብር ልክ ነው። ሴትን ማክበር ለእናትህ፣ ለእህትህ፣ ለልጅህ የምትከፍለው ውለታ ነው። እና ደግሞ የእኚህን ሶስት ነፍሶች ጎዳና መጥረግ ነው..ይሄን መቼም እንዳትረሳ።

ዞር ብሎ አያት..እጇ ላይ አነስተኛ ሻንጣ ይዛለች።

‹የት ልትሄጂ ነው? ጠየቃት። በአፍና በአፍንጫ በሚግተለተል ጭስ በታጀበ ቃላት።

‹አንተ የሌለህበት፣ ትዝታህ..ናፍቆትህ ከማይደርስበት..ወንድነትህ ከማይከተለኝ ሩቅ ቦታ› መለሰችለት።

ወፍራም እና ነፍናፋ ሳቅ ከጉሮሮው ወጣ። ‹እኔ የሌለሁበት የትም የለም..

‹እውነት ነው አንተ የሌለህበት የትም የለም ግን ነፍሴ አንተ የሌለህበትን አንድ ቦታ ፈልጋ አግኝታልኛለች..ወደዛ እየሄድኩ ነው። እርግጠኛ ነኝ መቼም አትደርስብኝም› አለችው።

‹አንድን ሰው ስትርቂው ይበልጥ እየተከተልሽው ነው..

‹ይበልጥም ግን ትርቀዋለህ..

‹አትልፊ..

‹እመነኝ አለፋም..

‹አንቺ ከልፋት ውጪ ለምንም አልተፈጠርሽም..እንዲህ እንደ አሁኑ ሄደሽ መመለሽን ረሳሽ እንዴ? ሲል በንቀት ጠየቃት።

‹እውነት ነው ሄጄ ተመልሼ አውቃለሁ። አጠገብህ ላልደርስ ምዬ ቃሌን አፍርሼ አውቃለሁ። ያኔ ግን የመለሰኝ ፍቅር ነው። ከውስጤ እውነት ይልቅ የአንተ ፍቅር በልጦ ከሽሽቴ መልሶኛል። አሁን ግን እመነኝ..አልመለስም ልመለስ ብልም አይቻለኝም።

‹አንቺ ከኔ ውጪ ዓለም የሌለሽ ሴት ነሽ። እያፈቀርሽኝ እንድትኖሪ የተፈጠርሽ ነሽ።

‹ልብ ከማፍቀር እኩል መጥላትም እንደሚችል የማያውቅ ልብ ነው ያለህ። ለዚህ ልብህ የኔ ሄዶ መመለስ ጀግንነቱ ነበር። አሁን ግን ለዚህ ልብህ ዳግመኛ እድል አልሰጠውም። ዛሬ የምታየኝ ለመጨረሻ ጊዜ ነው። ፈልገህ ስታጣኝ፣ ጠብቀህኝ ስቀር ምን ያክል እንደራኩህ፣ ነፍሴም አንተ የሌለህበትን ስፍራ ፈልጋ እንደደረሰችበት ትረዳለህ። ለኔ የነፈከኝን ፍቅር፣ ክብር፣ መልካምነት ወደህይወትህ ለምትመጣው አዲስ ሴት እንድትሰጣት ደህና ሁን..›

ትታው ሄደች። ትታው ስትሄድ እንደምትመለስ እያወቀ ነበር። ትታው ስትሄድ እንደ እስከዛሬዋ እሱ የሌለበትን ቦታ ስታጣ ተመልሳ ወዳለበት እንደምትመለስ በማመን ነበር። ግን አልተመለሰችም ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ።

ከስምንት ዓመት በኋላ ልብ ማፍቀር ብቻ አይደለም መቁረጥም እንደሚችል ተማረ። የሚያፈቅሩን ልቦች፣ መሄድ እየፈለጉ የሚያመነቱ እግሮች በፍቅር እግር ብረት ተይዘው እንደሆነ ተረዳ። የትም ቦታ ምንም ሆኖ ራሱን አገኘው። የቆመው በእሩታ ፍቅር እንደነበር ዛሬ ነው የገባው። በዓለም ስፍራ ሩታን ያልፈለገበት ቦታ የለም..አላገኛትም። እሱ የሌለበት ስፍራ ወዴት እንደሆነ አልደረሰበትም። ነፍሷ ፈልጋ ያገኘችላት እሱ የሌለበት፣ ትዝታው የማይደርስበት፣ ናፍቆቱ የመከነበት ስፍራ ከሃሳቡ ጠፋ። ሩታ ከእሱ ሌላ ህይወት እንደሌላት ነበር የሚያውቀው። እሷ የምሞተው ከአንተ የተለየሁ ቀን ነው ብላው ነበር። ታዲያ ከእሱ ውጪ እንዴት ህይወት እንዳገኘች አልገባውም። በዚህ ሃሳብ ብዙ ጊዜ ኖሯል።

ከስምንት ዓመት በኋላ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ነበር። ሩታን እያሰበ። ግሮሰሪው ባንኮኒ ላይ የመተኛት ያክል አዝምሟል..። አንድ ጊዜ ሲጋራውን፣ አንድ ጊዜ ደግሞ ብርጭቆውን ወደ አፉ እያለ ይለፋደዳል። አጠገቡ፣ ዙሪያው ወደዚያ ወደዚህ የሚሉ ሴቶች ይታዩታል። ከፊት ለፊቱ በሚያጨሰው የሲጋራ ጭስ ውስጥ ለዓመታት የጠፋችበትን ሴት አያት። ማመን አልቻለም..የሚያየውን እውነት ተጠራጠረ። ገና አልሰከረም..ትዝታውን ገርስሶ ለመጣል እንጂ ብዙም የመጠጣት አመል የለውም። የሚያጨሰውም ያቺን እንደ ተለኮሰ ላምባዲና የህይወቱን ጨለማ ገልጣ ሰው ያደረገችውን ነፍስ ለመርሳት ነው።

አፉ ላይ እየነደደ የሚጨሰውን ጭስ ወደ መተርኮሻው ጥሎ የፊትለፊቱን ሴት አያት። ራሷ ናት..ማክዳ። የስቃዩ ማብቂያ ይቺ ሴት ናት። የሚጠይቃት እልፍ ጥያቄ አለው..

እየተንገዳገደ ወዳለችበት ተራመደ። አጠገቧ ደርሶ ማክዳ ሲል ጠራት..። አጠገቧ አብረዋት የተቀመጡ ሶስት ወንዶች በዓይናቸው ተከተሉት።

ዞራ አየችው። አላወቀችውም..

‹..አስታወሽኝ?

‹ይቅርታ አላስታወስኩህም..

በዚያ ሁኔታ ራሱን ማስተዋወቅ አልፈለገም..ስላላወቀችው ደስ ብሎታል። ስላላስታወሰችው ስለ ሩታ እንደፈለገ ሊጠይቃት ይችላል። ሩታ በጣም የምወዳት ጓደኛዬ ናት ብላ አስተዋውቃው ነበር። ሊረሳት ያልቻለውም ቤት ከሩታ ጋር አብረው የተነሱት ፎቶ ስላለ ነው።

‹የሩታ ጓደኛ ነሽ አይደል? ሲል ጠየቃት።

በዝምታ ለረጅም ጊዜ አስተዋለችው።

‹እባክሽ ስለሩታ ንገሪኝ…ምንም እንዳትዋሽኝ! ሲል ተለማመናት።

የሆነ ነገር ትዝ ያላት መሰለ። ፊቷ ላይ የሆነ ትውስታ አንጃበበ። ‹ኦኬ..ቶማስ ነህ አይደል?

‹አዎ ነኝ..ሩታ የት ናት?

‹አዝናለሁ ቶማስ..ሩታ ካረፈች ሰባት ዓመት አልፏታል። ያኔ ካንተ እንደተለየች ነበር ራሷን ማጥፋቷን የሰማሁት› ብላው ተንሰቀሰቀች።

አጠገቧ አልቆመም ትቷት ሄደ። በመንገዱ በዝምታ ውስጥ ሲነፈርቅ ነበር። ለካ እኔ የሌለሁበት ዓለም ያ ኖሯል። ለካ ያን ቀን ዳግመኛ ወደአንተ አልመለስም፣ አንተም አትደርስብኝም ያለችው ወደ ሞት እየሄደች ነበር። በሩታ ፍቅር ዘመኑን ሙሉ ያለቅሳል። ዘመኑን ሙሉ ያቀረቅራል። ፍቅሯን፣ ደግነቷን ሲያስብ አይሆኑ ይሆናል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You