ሀገራችን የቀይ ባህር ተጋሪ የነበረችና አሁንም ቢሆን በቅርብ ርቀት የምትገኝ ወሳኝ ሀገር ናት። ለዓባይ ተፋሰስም ከፍተኛውን ድርሻ የምታበረክት ቁልፍ ሀገር ናት። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያን ከቀይ ባህርና ከዓባይ ፖለቲካ አውጥቶ ማሰብ የሚቻል አይደለም። ከዚህም ባለፈ ከነዚህ የውሃ አካላት ጋር የተያያዘ ዘላቂ ፍላጎት አላት። የውሃ አካላቱ ከሀገሪቱ ደኅንነትና ህልውና ጋር ያላቸው ቁርኝትም ከፍ ያለ ነው።
አሁን ካለችበት ኋላቀርነት እና ድህነት በልማት ወደ ብልጽግና ለመጓዝ ለጀመረችው ሀገራዊ የልማት ንቅናቄ ስኬትም ፣ የእነዚህ የውሃ አካላት አስፈላጊነት መተኪያ የሌለው ነው። ለበለጸገች ሀገር ግንባታ ዋነኛ አቅሞች መሆናቸውም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።
አሁንም ላይ ወደ ባህር ተጋሪነት ማማተራችን፤ በቀይ ባህር ቀጣና ላይ የነበረንን ሥፍራ ለመመለስ ሆነ በአዲስ መልክ በቀጣናው ቁልፍ ተዋንያን በመሆን የሀገራችንን ደኅንነት በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ እንደሚረዳን ይታመናል። ወደ ዓባይ ተፋሰስ ከሚገባው ውሃ የተወሰነውን መጠቀም ካልቻልንም አሁን ላይ እየተፈታተነን ያለው ድህነት እየከፋ ሊሄድና ወደ ቀውስ ሊያመራ እንደሚችል እንዲሁ ።
እየጨመረ ያለው የሕዝብ ቁጥር፣ የከተሜነት መስፋፋት፣ የግብርና ምርቶች ፍላጎት መጨመርና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን የውሃ ሀብቶቻችንን በይበልጥ እንድንጠቀም ያስገድዱናል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የኃይል ፍላጎትም ሊሟላ የሚችለው ወደ ዓባይ ተፋሰስ የሚቀላቀሉ የውሃ ሀብቶቻችንን ባግባቡ መጠቀም ስንችል ነው ።
እነዚህ የውሃ አካላትን ለመጠቀም የምናደርጋቸው ጥረቶች ተጨማሪ የስጋት ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል ።እስካሁን የመጣንባቸው መንገዶችና ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ የሚያመላክቱ ናቸው።በቀጣይም ተመሳሳይ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙን ብዙም አጠያያቂ አይሆንም።
ከጥንት ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ህልውናም ሆነ ደኅንነት ከሁለት የውሃ አካላት / ከቀይ ባህር እና ከዓባይ ተፋሰስ / ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። የውሃ አካላቱ ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል ከቀደሙት ዘመናት ጀምሮ ዛሬም የቀጠለ ነው፡ እነዚህን የውሃ አካላት መቆጣጠር የሚፈልግ የትኛውም የውሃው ተጋሪ ሀገርም ሆነ ሌላ በየወቅቱ የሚነሳ ሉዓላዊና ቀጣናዊ ኃያል ሀገር በአንድም ሆነ በሌላ በኢትዮጵያ ላይ የደኅንነት ጫና ማሳደሩ የማይቀር ነው።
የውሃ አካላቱ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል ለሌሎች የውሃ ተጋሪዎችም ሆነ ሌላ ፍላጎት ላላቸው ሀገራት ጠቃሚ የውሃ አካላት ናቸው። ቀይ ባህር በዓለም ላይ የንግድ ኮሪደር ከሆኑ የውሃ አካላት መካከል አንዱ ነው፤ ለውሃው ተጋሪ ሀገራት ደግሞ ከኢኮኖሚ በዘለለ በርካታ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች አሉት።
የዓባይ ተፋሰስን ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ያህል ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት በእጅጉ ይፈልጉታል። ከውሃ አካላቱ የሚገኘው ጥቅም በርካታ ከመሆኑ የተነሣ ተዋናዮችም በርከት ያሉና የተለያየ የኃይል አቅም ያላቸው ናቸው። የውሃ አካላቱ ተጋሪ ሆነውም ሆነ በርቀት ላይ የሚገኙ ሀገራት መብዛታቸው ለተጠቃሚነት የሚደረገውን ትግል ከባድና ውስብስብ ያደርገዋል። በታሪክ እንደታየውም እነዚህ የውሃ አካላት የግጭትና የትግል መንስኤ ሆነው አገልግለዋል።
ሀገራችን በእነዚህ የውሃ አካላት ምክንያት ከጥንት ጀምሮ ሥጋት እያስተናገድን ነበር ፤ አሁንም በተመሳሳይ ሥጋት ውስጥ ነች ፤ወደፊትም ውሃዎቹን ታሳቢ ያደረጉ ስጋቶች ከፊታችን ይጠብቁናል፣ ይህንን ሀገራዊ ተጨባጭ እውነታ በስኬት ለመሻገር ሥጋታችንን እየቀነስንና ጥቅማችንን እያሳካን መሄድ የሚያስችል ስትራቴጂክ እይታ ያስፈልገናል።
አሁን ያለንበት ተጨባጭ እውነታ ሆነ ወደ ፊት ሊያጋጥሙን ከሚችሉ ችግሮች አንጻር ያለን አማራጭ እጆቻችንን አጣጥፎ አርፎ መቀመጥ ሳይሆን፣ የትኛውንም አይነት ችግር እንደየባህሪው እየተጋፈጥን ጥቅሞቻችንን እያስከበርን መሄድ ብቻ ነው ።ለዚህ ደግሞ እንደ ሀገር ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያስፈልገናል።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር ትናንት ለህትመት የበቃው የሁለት ውሃዎች አብይ ስትራቴጂ ሰነድ፤ ከውሃ አካላት ጋር በተያያዘ ሀገራችንን እየገጠማት ያለውን ዘላቂ የህልውና እና የደኅንነት ሥጋት በማመላከት ጥቅሞቿን ልታሳካ የምትችልባቸውን የመፍትሔ መንገዶች ማመላከት የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም