ሕክምና ከመስጠት ባሻገር ሰብዓዊነት የጎላበት የባለሙያዎች ስብስብ

ለአንድ ተቋም መመስረት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ምክንያቶች የአንድን ሰው ሀሳብ እና ጊዜ ከመውሰድ፣ ለብቻ ከመብሰልሰል አልፎ ምናልባትም በሌሎች ልብ ውስጥ ጭምር ያሉ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁንና ሀሳቡን አንድ ሰው ደፍሮ ወደፊት ያምጣው እንጂ ብዙዎች ይጋሩታል። ብዙ ወደፊት የመጡ ሀሳቦችም ደግሞ ብዙዎች ተጋርተውት መፍትሄ ሲሆን መመልከት የተለመደ ነው፡፡

የዛሬው የ‹‹ሀገርኛ›› አምዳችንም ትኩረቱን በዚሁ ሀሳብ ላይ አድርጓል፡፡ ሃሳቡ በተመሳሳይ የሙያ ዘርፍ ላይ በተሰማሩ ባለሙያዎች ልብ ተጠንስሶ በርካታ ቁጥር ላላቸው ሴቶች መፍትሔ መሆን ችሏል። በጤናው ዘርፍ የራሱን ድርሻ በመወጣት ሴቶችን እያገዘ ያለው ‹‹የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት›› ነው፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የሕጻናት ሕክምና፣ የአዋቂዎች ሕክምና፣ የውስጥ ደዌ፣ የካንሰር ሕክምናዎች ይሰጣሉ፡፡ የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ክፍል ከሆስፒታሉ የሕክምና ዘርፎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሆስፒታሉ የተቋቋመው ‹‹የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት›› በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ ባሉ የማህጸን እና ጽንስ የሕክምና ክፍል ዶክተሮች፣ ስፔሻሊስቶች፣ የስፔሻላይዝድ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች በሕብረት የተቋቋመ ሲሆን፤ ትኩረቱን የካንሰር ታማሚዎችን ለማገዝ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

ዶክተር ወንድሙ ጉዱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የማህጸን እና ጽንስ ሀኪም እና የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ክፍል ኃላፊ እንዲሁም ‹‹የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት›› ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ ይህንን በሴቶች ጤና ላይ ያተኮረ የበጎ አድራጎት ድርጅት ለማቋቋም ምክንያት የሆናቸው በየዕለቱ በሆስፒታሉ ውስጥ የሚያስተናግዷቸው ታካሚዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ታካሚዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገኙ የካንሰር ሕክምና ላይ ያሉ ሲሆኑ ለሕክምና በሚመጡበት ወቅት ያልታሰበ የሕክምና ወጪ ይገጥማቸውና የሕክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን ይቸገራሉ፡፡ የስነተዋልዶ ጤና ቅድመ ምርመራ ለማድረግ ግንዛቤ እና ወጪ የመሸፈን አቅም የሌላቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች መኖራቸው እንዲሁም ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የስነ ተዋልዶ ጤና ምርመራ ማድረግ የማይችሉ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸው ይህንን ተቋም ለመመስረት እንደምክንያትነት ተቀምጧል፡፡

ወደ ሆስፒታሉ ይዘውት የመጡትን ታካሚ ለማስታመም እና ወደሚያስፈልገው የምርመራ ክፍል ለመውሰድ የታዘዘለትን መድሀኒት ለማምጣት የሚሯሯጡ አስታማሚዎች፣ በየሕክምና ክፍሉ ኮሪደር ላይ በደከመ መንፈስ ቆመው ተራቸውን የሚጠብቁ ታካሚዎች፣ በሁሉም የአገልግሎት መስኮች ላይ ትንሽ የማይባሉ ሰልፎች በሆስፒታሉ ውስጥ የተለመዱ ናቸው።

ታዲያ በዚህ ልባቸው የተጨነቁ እና እርዳታ የሚፈልጉ ታካሚዎችና የታካሚው ቤተሰቦች መሀል በትልቅ አክብሮት የሚታዩ የችግሩ መፍትሄ ሰጪ ተደርገው የሚወሰዱት የጤና ባለሙያዎች ይገኛሉ። ዶክተሮችም ቢሆኑ ስራቸው ሰውን ማከም ነውና የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ታካሚዎቻቸውን ያስተናግዳሉ፡፡ አንድ ሀኪም እና ታካሚ ያላቸው ግንኙነት በአንድ ሆስፒታል ውስጥ አልያም በአንድ ጠባብ ቢሮ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለይም ደግሞ ተከታታይ የሆነ የሕክም ክትትል የሚያደርጉ ታካሚዎች ከሐኪሞቻቸው ጋር የቤተሰብ ያክል ቅርርብ ይኖራቸዋል፡፡ በመሆኑም የአንድ ሐኪም እፎይታ በየዕለቱ ታካሚዎቹ ላይ በሚያየው ፈገግታ ይወሰናል፡፡

ሆስፒታሎች የሰው ልጅ ወደ ምድር የሚመጣበትንና የምድር ቆይታ ማብቂያንም የሚያስተናግዱ ሲሆን አንዳንዶች በሆስፒታል ውስጥ የሚከሰት ሞት ለጤና ባለሙያዎች የተለመደ ስሜት አድርገው ይወስዱታል። ነገር ግን የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት፣ አንድን ታካሚ ማዳን ሳይቻል ቀርቶ ሕይወቱ ሲያልፍ እንደማየት ልብ የሚሰብር ነገር ለጤና ባለሙያ የለም፡፡ አንድ ታካሚ በሆስፒታሉ ውስጥ በሚያደርገው ሕክምና የሚጠየቀውን የአገልግሎት ክፍያ መክፈል ሳይችል ሲቀር፣ የታዘዘለትን መድሀኒት ለመግዛት እጅ ሲያጥረው፣ ከፋ ሲል ደግሞ ያላሰበው የበሽታ አይነት ተነግሮት ከፍተኛ ገንዘብ ሲጠየቁ አስታማሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የጤና ባለሙያዎችም እኩል ያዝናሉ፡፡ ባለሙያዎቹ ታዲያ አዝነው ብቻ አይቀሩም ኪሳቸውን ፈተሽ ፈተሽ አድርገው የስራ ባልደረባቸውን አስተባብረው የታካሚዎችን ችግር መጋራት የሁሉም የጤና ባለሙያዎች የሚጋሩት የእለት ተዕለት ክስተት ነው፡፡

በሆስፒታል ውስጥ አንድ አስታማሚ የታካሚውን ሕክምና ለማድረግ የሚጠየቁ እቃዎችን መድሀኒቶችን እየገዛ ባለበት ወቅት በእጁ ያለ ገንዘብ ሊያልቅበት ይችላል፡፡ አልያም ደግሞ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚመጡ ታካሚዎች በቂ ገንዘብ ሳይኖራቸው ነገር ግን ሕይወታቸው ይቀጥል ዘንድ መታከማቸው የግድ ሆኖ ባዶ እጃቸውን በሆስፒታሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ታዲያ ለእነዚህ የተጨነቁ ሰዎች በቅድሚያ የሚደርሱላቸው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጧቸው የጤና ባለሙያዎች ናቸው።

ከሙያቸው ባሻገር ከኪሳቸው አውጥተው ይህንን ታካሚ በቻሉት መጠን ያግዙታል፡፡ በዙሪያቸው ያሉ የሙያ አጋሮቻቸውን እንዲሁ አስተባብረው ገንዘብ በማሰባሰብ የቻሉትን ያደርጋሉ፡፡ ይህ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ የተለመደ ተግባር እንደሆነ የጤና ባሙያዎቹ ያነሳሉ፡፡ እነዚህ የጤና ባለመያዎች ታዲያ ከኪሳቸው አውጥተው የሚሰጡት ገንዘብም ሆነ በሰዓቱ የሚያደርጉት ድጋፍ በዘላቂነት ችግሩን የማይፈታው በመሆኑ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ በልባቸው ሲያብሰለስሉት ቆይተዋል፡፡ ሀሳቡ በሁሉም ልብ ውስጥ የነበረ ነውና በየግላቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ ወደ አንድ የተሻለ ተቋማዊ መልክ መስጠት የሚለውን ሀሳብ በቀላሉ ሊያግባባቸው ችሏል፡፡

በመሆኑም የጤና ባለሙያዎቹ ድጋፋቸውን በዘላቂነት ለማስቀጠል አስቀድመው እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ተደራሽ የሚሆን ቋሚ የሆነ የመዋጮ ስርዓት (Patient Fund Commit­tee) በመዘርጋት ከወር ደሞዛቸው ላይ ተቆራጭ የሚያደርጉበትን መንገድ ጀምረዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ብቻም ሳያበቃ ከወርሀዊ መዋጮው ባሻገር ተጨማሪ ገንዘብ ከኪሳቸው የሚያወጡ ባለሙያዎች ነበሩ፡፡

በሆስፒታሉ ውስጥ የማህጸን እና ጽንስ ሕክምና ክፍል ውስጥ ያሉ ዶክተሮች ይህንን ሀሳብ ሲያመጡ ስፔሻላይዜሽን ትምህርት የሚማሩ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁ በየግላቸው የሚያደርጉት ድጋፍ አቅም ኖሮት ተቋማዊ ስርዓት እንዲኖረው ሀሳባቸው ይዘው ወደ ባልደረቦቻቸው መጡ፡፡ ይህ ሀሳብም በሁሉም ዘንድ ስምምነት ላይ ደርሶ ማኅበር ለማቋቋም የመጀመሪያ ስብሰባቸውን አድርገዋል፡፡ የማህጸን እና ጽንስ ሀኪም ክፍል ሐኪሞች እንደመሆናቸውም በየእለቱ በሕክምና ክፍል ውስጥ የሚያስተናግዷቸው ሴት ታካሚዎች ጤና በእጅጉ አሳስቧቸው ነበርና ‹‹የሴቶች ጤና ድጋፍ በጎ አድራጎት ድርጅት›› የሚል ስያሜ ሰጡት፡፡ አስፈላጊ ሰነዶችን በማዘጋጀት ሕጋዊ እውቅና እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጥያቄያቸውን አቀረቡ፡፡

እንደ ዶክተር ወንድሙ ገለጻ፣ ድርጅቱ ከመቋቋሙ በፊት ከወር ደመወዝ ተቆራጭ ከሚደረግ እገዛ ውጪ በአቅራቢያቸው ካሉ ፈቃደኛ ሰዎች በሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ 70 ለሚደርሱ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት መስጠት የቻሉ ሲሆን፤ ይህም በገንዘብ ሲተመን 150 ሺህ ብር የሚደርስ እርዳታ ማድረግ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡

ምንም እንኳን መነሻው ሕክምናቸውን እየተከታተሉ የገንዘብ እጥረት የገጠማቸው ሰዎችን በመርዳት ተጀመረ እንጂ ከሆስፒታሉ ውጪ የሚገኙ ሴቶችን ተደራሽ ለማድረግ፣ አስቀድሞ የመከላከል ስራንም ያካተተ እንደሚሆን በምርቃት ቀኑ ላይ ተጠቅሷል፡፡ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እድሎችን ማመቻቸት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት፣ ወደ ሆስፒታሉ መጥተው መታከም ላልቻሉ ሴቶች ያሉበት ድረስ በመሄድ የቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን በማድረግ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ከጤና ተቋማት ውጪ ከቀያቸው ተፈናቅለው በማቆያ ቦታዎች፣ በጎዳና ላይ ያሉ ሴቶችን ተደራሽ በማድረግ የሴቶችን ጤና ለመጠበቅ እና ግንዛቤያቸውን ከፍ ለማድረግ ይሰራል፡፡

ይህ በአንድ ክፍል ውስጥ የተጀመረ ሀሳብ አድጎ ራሱን የቻለ ተቋም ለመሆን ሲታሰብ በቅድሚያ የኮሌጁ አስተዳደር አካላት ተቋማዊ አሰራር እንዲኖረው ከሀሳብ ጀምሮ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የድርጅቱ ዓላማም በሕክምና ላይ የሚገኙ የገንዘብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች እገዛ ማድረግ፣ ወደ ማኅበረሰቡ በመዝለቅ ካንሰር ከመከሰቱ በፊት ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ካንሰር ምርመራዎችን ማመቻቸት እና በተለያዩ ተቋማት በመገኘት የሴቶች ጤናን የተመለከቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ሴቶች ግንዛቤው እንዲኖራቸው በማድረግ የበሽታ ስርጭቱን መግታት ይቻል ዘንድ ይሰራል። ከዚህም ባሻገር በሀገር ደረጃ የሚወጡ ጤና ተኮር ፖሊሲዎች ሴቶችን ያማከሉ ይሆን ዘንድ ተጽዕኖ መፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችን መስራት በእቅዱ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡

እነዚህን ዓላማዎች የያዘው ‹‹የሴቶች ጤና ድጋፍ የበጎ አድራገጎት ድርጅት›› በ10 መስራች አባላት እና በስምንት የቦርድ አባላት በታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ ተመስርቷል፡፡ በምርቃት ስነ- ስርዓቱ ላይም በሆስፒታሉ ውስጥ የሚገኙ የሌላ የሕክምና ክፍል ባለሙዎች እና የአስተዳደር ኃላፊዎች የኮሌጅ ዲኖች የተገኙ ሲሆን ሀሳቡ ብዙዎች የሚጋሩት እና መልካም ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑ ተገልጿል፡፡ በሆስፒታሉ ከሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥም ድርጅቱ ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ 500 አባላት ይኖሩታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ማኅበሩ እውቅና የተሰጠው ተቋም በመሆኑ ዓላማውም በአንድ የሕክምና ተቋም ውስጥ ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም እና በጎ ሀሳቡን ለሚደግፉ ሁሉ ክፍት ሆኗል።

ድርጅቱ ለታካሚዎች እገዛ ከማድረግም ባሻገር በሆስፒታሉ ውስጥ ሊገኙ የማይችሉ መመርመሪያ መሳሪያዎችን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመነጋገር እና ግንኙነት በመፍጠር እንዲኖሩ የማስቻል እቅድም አለው፡፡ ሴቶች ሕይወትን የሚሰጡ ናቸውና የሴቶች ጤና ማለት የአንድ ሰው ጤና፤ የአንድ ቤተሰብ ጤና ሳይሆን የኅብረተሰብ ጤና አለፍ ሲል ደግሞ የሀገር ጤናም ጭምር ነው፡፡ ‹‹ሴት ጤና ስትሆን ሀገር ጤና ትሆናለች›› በሚል ሀሳብ ተቋቁሟል፡፡

ማኅበሩ ለሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ የተለያዩ አባላትን ባለሀብቶችን በመደገፍ እና የገቢ ማሰባበሲያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ይሰራል፡፡ የድርጅቱን መመስረት በማብሰሪያው እለትም የደም ልገሳ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን ይህ መልካም ሀሳብ በሌሎች የሕክምናና የትምህርት ክፍሎችም መልካም ተሞክሮ መሆኑ ተነስቷል፡፡ በሀገራችን ብሂል ‹‹ችግር በቅቤ ያስበላል›› እንደሚባለው ባለሙያዎች የተመለከቱት ችግር ከሆስፒታሉ ማኅበረሰብ አልፎ ለሌሎች መድረስ የሚችልበት መንገድ መፈጠሩም እንደ መልካም የሚጠቀስ ነው፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን የካቲት 22 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You