የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ካለፈው እሁድ ጀምሮ በባቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል። ለተከታታይ አስር ቀናት በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ከመላው ኦሮሚያ የተውጣጡ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ይህ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በክልል ደረጃ ሲካሄድ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን በበርካታ የስፖርት አይነቶች ፉክክር እንደሚያስተናግድ ተጠቁሟል።
የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር በክልሉ ረጅም ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ ቆይቷል። ዘንድሮ ይህ ውድድር በአዲስ መልክ ዳግም መካሄድ እንደጀመረ የኦሮሚያ ክልል የስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ በውድድሩ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።
ውድድሩ በትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና የትምህርት ቤቶችን ስፖርት ለማሳደግ እንደሚካሄድ የተናገሩት ዶክተር ቶላ፣ በዚህም ክልሉን በአገር አቀፍ ውድድሮች ከመወከል ባለፈ አገርን በታላላቅ የስፖርት መድረኮች የሚያስጠሩ ጠንካራ ስፖርተኞች ማፍራትን ዓላማው እንዳደረገ አስረድተዋል።
ኦሊምፒክን ጨምሮ በተለያዩ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ውጤታማ ያደረጉ በርካታ አትሌቶች መፍለቂያቸው ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተር ቶላ፣ የትምህርት ቤቶች ስፖርትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል። የኦሮሚያ ክልል በአፍሪካ ደረጃ በሚካሄዱ የትምህርት ቤቶች የስፖርት ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን በማስታወስም ይህን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው፣ አገራችን የበርካታ ወጣቶች አገር መሆኗን ጠቁመው ትምህርት ቤቶች ወጣቶች እውቀት ብቻ የሚሸምቱባቸው ሳይሆኑ ጠንካራ ስፖርተኞች የሚፈሩባቸው ጭምር መሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም በትምህርት ቤቶች ስፖርት ተጠናክሮ መቀጠሉ ለጤናማ አካልና ለብሩህ አእምሮ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክት በመሆኑ ወጣቶች በትምህርታቸው ጠንክረው እንዲወጡ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዘዳንትነት ማእረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ፣ የትምህርት ቤቶች ስፖርት መጎልበት አንድነት፣ ወዳጅነትና አብሮ መኖርን ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። እንደ ኦሮሚያ ክልል በትምህርት ቤቶች ስፖርትን በማጠናከር አገርን በታላላቅ ውድድሮች የሚወክሉ ጠንካራ ስፖርተኞችን ለማፍራት የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የውድድሩ አስተናጋጅ የሆነችው የባቱ ከተማ ከንቲባ አመዲን ኢስማኤል በበኩላቸው፣ ለዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የትምህርት ቤቶች ውድድር ዘንድሮ እንደ አዲስ መጀመሩ እንደ አገር ለትምህርት ቤቶችም ጥቅሙ ብዙ መሆኑን አንስተዋል።
የውድድሩ ባለቤት በዋናነት የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሲሆን የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በተባባሪነት የቴክኒክ ድጋፎችን ይሰጣል። ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለጋዜጠኞች ባደረገው ገለፃ፣ የውድድሩ ዓላማ በዋናነት ሁሉም ትምህርት ቤቶች ስፖርት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ለማነቃቃት መሆኑ ተጠቁሟል። ከዚህ ባሻገር የክልሉን ስፖርት ለማነቃቃትና ለማጠናከር እንደሚረዳም ታምኖበታል።
ከክልሉ ባሻገር ወደፊት ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም መድረኮች የሚያስጠሩ ጠንካራ ስፖርተኞች መፍለቂያቸው ትምህርት ቤቶች እንደሆኑ በማመን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተጠቁሟል። ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስ ስፖርት በስተቀር በሌሎች ስፖርቶች እንደ አፍሪካም እንደ ዓለምም ተፎካካሪ መሆን እየቻለች አይደለም። ይህን ለመለወጥ የአገሪቱ ስፖርት ተስፋ ያለው በትምህርት ቤቶች ውስጥ መሆኑ ተገልጿል።
ውድድሩ በአስተናጋጁ ባቱ ከተማ እና በአርሲ ዞን መካከል በተደረገ የእግር ኳስ የመክፈቻ ጨዋታ የተጀመረ ሲሆን በአትሌቲክስ የወንዶች አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ፉክክርም ተከናውኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም