የብሄር በሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርብና አብሮነትን ለማጠናከር እንደሚረዳ በዓሉን አስመልክቶ በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ኢግዚቢሽን ላይ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡
ኢትዮጵያውያን አሁን ላይ የታየውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ አብሮነታቸውን የሚያጠናክሩበት ወሳኝ ምእራፍ ላይ መገኘታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ የባህል አልባሳትን ይዘው የቀረቡት ወይዘሮ ኤልሳቤት ገቢሳ እንዳሉት በአሉ የሌሎችን ብሄሮች ባህልና አልባሳት ለመተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡
“ከተማ ላይ ብቻ የሚዘወተሩ ዲዛይኖችን እሰራ ነበር” ያሉት ወይዘሮ ኤልሳቤት ከዚህም በፊት በበአሉ ላይ አዘውትረው መሳተፋቸው ለስራቸው ግብአት የሚሆኑ የባህላዊ አልባሳት ዲዛይኖችን ከተለያዩ ብሄረሰቦች እንዲያገኙ እንዳስቻላቸውም ይናገራሉ።
በሃገሪቱ ላይ የሚታየው ለውጥ አብዛኛው ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ኤልሳቤት በአንዳንድ የሃገሪቱ ክፍል አብሮነትን የሚሸረሽሩ ግጭቶች አፋጣኝ እልባታ ያሻቸዋል ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን የሚያምርብን አንድነታችንና እንግዳ ተቀባይነታችን ነው፤ ሰላማችንን በመጠበቅም ለሃገራችን እድገት እንስራ” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
እንደ ኢ.ዚ.አ ዘገባ ከጅማ የቤት እቃዎችን በማቅረብ በኢግዚቢሽኑ የታደመው ወጣት ያሬድ ታደሰ የገበያ ትስስር ከማግኘቱም በላይ ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ለመተዋወቅና ለባህል ልውውጥ ይረዳል ብሏል።
“ሃገራችን በተሻለ ሁኔታ ላይ ናት፣ መንግስትም ሁሉንም ዜጋ ያማከለ ስራ በመስራት ላይ ነው፣ ወጣቱም ይህን ተረድቶ ወደ ተሻለ ጥያቄና እድገት መሄድ እንጂ በስሜት ወደ አላስፈላጊ ግጭት መግባት የለበትም” ብሏል ወጣት ያሬድ።
ሰላምንና አንድነትን አስጠብቆ እንደ ሃገር ለመቀጠል ወጣቱ “እኔ እበልጣለሁ” ከሚለው አስተሳሰብ በመላቀቅ፣ እርስ በእርስ መደማመጥና መረዳዳት ይገባል ነው ያለው።
ከገመድ በእጅ የሚሰሩ የቤት እቃዎችን ይዞ የቀረበው ሌላው ወጣት ቴዎድሮስ ታደለ በበኩሉ አብዛኛው የሃገሪቱ ህዝብ ወጣት በመሆኑ ሰላም የማስፈኑ ድርሻውም ከፍተኛ ነው ብሏል፡፡
በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የወጣቱ ትልቁ ጥያቄ የሆነውን የስራ እድል ፈጠራ ተጠናክሮ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡
ሌላው የኢግዚቢሽኑ ታዳሚ ቢኒያም ሙሉጌታ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ኢትየጵያውያን ከመላው ሃገሪቱ ተሰባስበው ባህላቸውን የሚያሳዩበትና የሚቀራረቡበት ቀን ነው ይላል፡፡
“ኢትዮጵያውያን ለጋራ ሃገራችን የሚያስፈልገን መፈቃቀር ነው፣ ሌላ ሁሉም ነገር አለን፣ ሰውን በሰውነቱ ማክበር፣ ኢትዮጵያዊያን ሰው ስቃይ ሲደርስበት ማየት ይቻለናል የሚል አስተሳሰብ የለኝም፣ መልካም ነገር ማድረግ አለብን” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡