ጎረቤታሞቹ ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ በጉርብትና ረጅም ጊዜ በመቆየታቸው አንዳቸው የሌላኛቸውን ገመና እስከመሸፈን ደርሰዋል። መኝታ ብቻ ነው የሚለያቸው። አንዷ ቤት ቁርስ ከተበላ፣ ሌላኛዋ ጋር ደግሞ ምሳ ይበላል። እራቱም እንደሁኔታው በአንደኛው ቤት ይሆናል። ጓዳዪ ጓዳሽ መሶብሽ መሶቤ፤ አንች ትብሽ እኔ እብስ ተባብለው ነው ተሳስበው በጋራ የሚኖሩት። የሁለቱ መተሳሰብ ለልጆቻቸውና ባለቤቶቻቸውንም አቀራርቧል።
ሁለቱም ለፍቶ አዳሪ ናቸው። የቀን ገቢያቸው የእለት ኑሮአቸውን ስለሚሸፍንላቸው ኑሮን አማረው አያውቁም። የተትረፈረፈ ኑሮ እየኖሩ ባይሆንም ባላቻው ፈጣሪያቸውን አመስግነው አንዳቸው የሌላኛዋን ጓዳ ሸፍነው በፍቅር ነው የሚኖሩት። ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ጎረቤታሞች ይሁኑ እንጂ አኗኗራቸው የአንድ ቤተሰብ ያህል ነው።
ጎረቤታሞቹ ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ጉርብትናቸው ዛሬ ላይ እንደትናንቱ እየሆነ አይደለም። የነበራቸው ደስታ እየራቃቸው ነው። የየእለት ጨዋታቸውም በምሬት የተሞላ ሆኗል። ይህ የሆነው በመካከላቸው ፀብ ተፈጥሮ አይደለም። የኑሮው ሁኔታ ነው። ቡና ለመጠራራት እንኳን አቅም እያጡ ነው። ለፍቶ ማደሩም እየሆነላቸው አይደለም። የሚሰራው ስራና የሚገኘው ገቢ አልመጣጠን ብሏቸው ነው ይሄ ሁሉ ምሬት።
በቀን ስራ የሚያገኙት ገንዘብ እንደበፊቱ ቁርስ፣ ምሳ እራት በጋራ ሊያቋድሳቸው ቀርቶ የራሳቸውንም ጓዳ እየሞላላቸው ባለመሆኑ ነው መሬታቸው የጨመረው። መሽቶ ሲነጋ ነጋዴውን ማማረር ሆኗል ስራቸው። ከጥንቱም ቢሆን ለነጋዴው ጥሩ አመለካከት የላቸውም። እንዳሁኑ ኑሮ ሸክም ሆኖባቸው አያውቅም። ሌላ ነገር ለማሰብ እንኳን አላስቻላቸውም። በልቶ ለማደር እየተጨነቁ ነው። ይህን ሁሉ እየፈጠረባቸው ያለው ነጋዴው ነው ብለው ያስባሉ።
ጎረቤታሞቹ ባይሉም ነጋዴውና ሸማቹ አይንና ናጫ ከሆነ ከራርሟል። ከጥንቱም ፍቅር ባይሆኑም የአሁኑ ብሷል የሚሉ ጥቂት አይደሉም። ጊዜው ጥንት ለመባል ገና ነው። ግን ዓመታት ተቆጥሯል። በአንድ የአገልግሎት እቃ ላይ ነጋዴው አንድ ብር የማይሞላ ጭማሪ ነበር የሚያደርገው። ጭማሪውም እንደዛሬው መሽቶ ሲነጋ አይደለም። ኸረ እንደውም አንዳንዴ መሽቶም አይነጋም በሰዓታት ልዩነት ነው የዋጋ ጭማሪው። ታዲያ በያኔው በዓመታት ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ በሸማቹ በኩል የሚሰማው ሮሮ አይጣል ነው። አለፍ ሲልም ነጋዴው ይረገማል።
በያኔው መንግስትም በነጋዴው ላይ ይወስድ የነበረው እርምጃ ቆንጠጥ ያለ ነው ይባላል። እርምጃው እግር ተወርች እስከማሰር የደረሰ ነው አሉ። መንግስት ዋጋ እንደፈለገኝ እጨምራለሁ ላለ ነጋዴ ውርድ ከራሴ ስላለ በአንድ እቃ ላይ የሳንቲም ጭማሪ ለማድረግ እንኳን ዛር ወጥቶ ዛር ተንቀጥቅጦ ነው። ታዲያ የዚህ ዘመን ነጋዴ የሸማች ዐይን እየበላው አፍጥጦና አግጦ የሸማች ጫንቃ የማይሸከመውን ዋጋ መቆለሉ ከምን የመጣ ነው? ነገሩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ የሶስትና አራት እጥፍ ጭማሪ መደረጉ ነው፡፡
ነገሩ ሁሉ ያበቃው አንድ ኪሎ ሽንኩርት መቶ ሃምሳ ብር ማውጣቱ፣ የአንድ ኪሎ ጤፍ ዋጋ ከ120 ብር ሲዘል፣ እንደው ምንም የሌለው የነጣ ደሀ የሚመገበው የበሰለ ሽሮ ወጥ በአንድ እንጀራ 100 ብርና ከዚያ በላይ ሲሸጥ ነው። አንድ ጫማ ሰፊ በአንድ ጅማት አንድ ጫማ ዙሪያውን ሰፍቶ 50 ብር ሲቀበል ነው እጅዎን በአፍዎ ላይ ለማድረግ የሚገደዱት።
ጫማ ሰፊው ያስከፈለው ለጅማቱ ላወጣው ወጪ፣ ወይንም ለጉልበቱ አይደለም። በአንድ እንጀራ ሽሮ ፈሰስ ለሚጠየቀው ዋጋ ነው። ለዚያውም ሁለት ጫማ ሰፍቶ ከሆነ ነው መብላት የሚችለው። ለነገሩ ድሮ በአምስት ሳንቲምና አስር ሳንቲም ይሸጥ የነበረው የጫማ መስፊያ ጅማት አንዱ አምስት ብር ገብቷል። አሁን እኮ የሳንቲም ዘሮችን ካየን ቆየን። አምስትና አስር ሳንቲም ያለው ሰው ሳይሸለም ይቀራል። አስር ብር አንድ ዳቦ እንኳን ለመግዛት ባለመቻሉ አይደል የኔ ቢጤ ሳንቲም ለመቀበል ቅር የሚሰኘው።
የዋጋ ነገር ስንቱ ተነስቶ ስንቱ ይቀራል። የሰው ልጅ ለፍቶ የሚፈጥረው ገንዘብ የተገላቢጦሽ እራሱን ዋጋ እያሳጣው ነው የመጣው። የሰው ልጅና ገንዘብ ሚዛን ላይ ቢወጡ ሚዛኑ ፍታዊ ከመሆን ይልቅ ወደ ገንዘቡ ነው የሚያደላው።
የኑሮ ውደነቱ ጎረቤታሞቹ ወይዘሮ ፋጤና ወይዘሮ ይመናሹ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የብዙዎችን የእርስበርስ ግንኙነት ነው ያሻከረው። ጎረቤታሞች አንዱ መገናኛቸው ቡና ጠጡ ነው። ቀደም ሲል የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ አንድ ቤት በቀን ሶስቴ ነው የሚፈላው። ቡና ቁርሱም ቢሆን አይሰሰትም። ማኅበራዊ ትስስሩ፣ አንድነቱ፣ አብሮነቱ፣ መተሳሰቡ የሚመጣው በቡና ጠጡ ነው። ፖለቲካውም ቢሆን፣ ስለሚነሳ ሰዎች በዚህ አጋጣሚ የተለያየ አመለካከት ይኖራቸዋል። የኑሮ ውድነቱ ይሄን ሁሉ ነው እንደ ፈንጂ እየበተነ ያለው።
በተለይም ኀብረተሰቡ በዕለት ተዕለት በሚጠቀምባቸው መሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜጎችን ሕይወት እጅግ እየተፈታተነው ይገኛል። በእህል፣ በጥራጥሬ፤ በአትክልት ምርቶች፤ በግንባታ ዕቃዎች እና በቤት ኪራይ ላይ የዋጋ ጭማሪው አሳሳቢ ሆኗል። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው። ትራንስፖርት፣ የትምህር ቤት ክፍያና የመሳሰሉት ሲጨመሩበት የሕዝቡን ኑሮ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው ነው፡፡
በየቀኑና በየሰዓቱ የሚጨምረው የሸቀጦች ዋጋ በተለይም ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ኑሮ እንደምርጊት እንዲከብደው ምክንያት ሆኗል። መሽቶ በነጋ ቁጥር ‹‹ከገበያ ጠፍተዋል››፤ ‹‹ዋጋ ጨምሯል›› የሚሉት አገላለጾች ኅብረተሰቡን በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖር እያደረጉት ነው፡፡
የኑሮ ውድነቱ እንቆቅልሽ አልፈታ ያለው በምን አይነት ገመድ ቢተበተብ ነው። ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል አሉ። እጃቸውን ታጥበው፣ ያማራቸውን እየበሉ፣ በውስኪ እየተራጩ፣ አማርጠው እየለበሱ ሽሮ እንኳን እሮባቸው እጃቸውን ለልመና በዘረጉ በራሳቸው ወገን ላይ የሚጨክኑ መኖራቸው ለሰሚም ግራ ያጋባል። እንዲህ ያለውን ሚና የሚጫወቱት ደግሞ ደላሎች ናቸው የሚለው ወቀሳ የበዛ ነው።
እነዚህ ደላሎች እውቅና የተሰጣቸው እስኪመስል ድረስ በመካከል ላይ ሆነው የሚደልሉ ሕገወጦች ስለመኖራቸውና ለኑሮ ውድነቱም ምክንያት እንደሆኑ በመንግስት ስልጣን በያዙ ሰዎች ሳይቀር በየጊዜው ሲነገር ይሰማል። የሰው ጆሮም እየለመደው በመምጣቱ ሕገወጥነታቸው ቀርቶ ሕጋዊነታቸውን የሚያረጋግጥ እየመሰለ ነው። ይህን ስሜት የፈጠረው መደጋገሙ ነው።
ደላላ እስከሚታወቀው ድረስ አገናኝ ነው። ሥራውም ባገናኛቸው ሰዎች መካከል ሆኖ ተግባብተውና ተስማምተው እንዲገበያዩ ወይንም የተገናኙበትን ጉዳይ እንዲፈጽሙ ማስቻል ነው። ለስራውም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ክፍያ ያገኛል። አሁን የሚባለው ደላላ ግን አገናኝ ሳይሆን፣ ወሳኝ ነው። ማረሻና መሬት ማገናኘት ምን ማለት እንደሆነ እንኳን በቅጡ ሳያውቅ ነው ማሳ ላይ ያለውን ምርት ዋጋ ወስኖ ገበያ ላይ እንዲውል የሚያደርገው። ገበሬው የእርሱና የልጁ ጉልበት አያሳስበውም። የማምረቻ መሳሪያ ዋጋ መጨመር፣ የማዳበሪያ ወጪ፣ የከብት መኖ፣ የውሃ አቅርቦት ነው ትልቁ ጥያቄና ፈተናው።
የተፈጥሮ ዝናብ ለማግኘትም አንገቱን ወደፈጣሪው አንጋጦ የሚለምነው ይኸው ገበሬ ነው። በዚህ ሁሉ ልፋት ውስጥ ሆኖ ያመረተውን ምርት ሸጦ የድካሙን ለማግኘት በራሱ አይወስንም። በነዚህ ደላላ ተብዬዎች እጅ ይወድቃል። የእለት ጉርሱም፣ የዓመት ልብሱም ባመረተው ምርት ላይ የሚወሰን በመሆኑ መሸጡ ግድ ነው። የገበሬውን የውስጥ ገመና በማወቅ የተካኑት ደላሎች ያለምንም ርህራሄ በድካሙ ገብተው እነሱ ይከብሩበታል።
ደላሎቹ በቅድሚያ በወሬ አምራቹን የሚያዳክም ስራ ነው የሚሰሩት። በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ የዋጋ ማጣጣል ብቻ ሳይሆን የሚሰሩት፤ ምርቱንም ካቆየው ገበያ እንደማያስገኝለት ጭምር በመሆኑ አምራቹ ለመሸጥ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል። እነዚህ ደላሎች ሀገርንም ነው ፈተና ውስጥ የከተቱት። የብር የመግዛት አቅምን ብቻ ሳይሆን እያዳከሙ ያሉት የፖለቲካ ኪሳራም እያስከተሉ ነው። ዛሬ ገበያው የሚመራው በመንግስት አቅም ሳይሆን በደላላ ነው የሚለው ትችት እየበረታ የመጣውም ይኸው ሰው ያወቀው፣ ፀሀይ የሞቀው የደላሎች እንደልብ መፈንጨት ነው።
የደላሎች ጉዳይ ሕዝብንም ጥርጣሬ ውስጥ እየከተተው ነው። አይዟችሁ በርቱ የሚሉ የመንግስት ሹመኞች ይኖሩ ይሆን? መቼም በጎን ከነርሱ ጎን ቆመው፤ ለሕዝቡ እነዚህን ያለፉበትን ያልደከሙበትን ቁጭ ብለው የሚበሉ ሕገወጥ ደላሎች ከገበያው መካከል እናወጣቸዋለን ብለው ለሕዝብ በግልጽ አይናገሩም። ደግሞ እነርሱን ለማዳከም የእሁድ ገበያ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በአራት አቅጣጫ ገበያ ተከፍቷል። እነርሱም ገበያውን እንዲያረጋጉ በቁጥጥርና በክትትል የሚሰሩበት የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል። ነገሩ አንዱን ቀዳዳ ሲደፍኑ ሌላው እያፈሰሰ ነው እንደሚባለው ይሆን? ወይንስ እውነቱ ገና አልተገለጠልንም፡፡
ለመሆኑ እነዚህ ደላሎች ሀይ ባይ ያጡት ለምንድነው? መንግስትም አማራጮችን ለሸማቹ ከማቅረብ በዘለለ ሕዝብን የሚያስደስትና እፎይ የሚያስብል ደላሎቹን የሚያዳክም ሁነኛ እርምጃ ሲወስድ አይስተዋልም። ነገሩ ግራ ያጋባል። ሰፊ መሬት፣ ተስማሚ የአየር ጸባይና ስነ ምህዳር፣ ርካሽ ጉልበት አላት በምትባል ሀገር የተትረፈረፈ ምርት አምርቶ ዜጋውን አጥግቦ ለሌላው መትረፍ ያልተቻለው ለምን ይሆን? በደላላ የሚዘወር ኢኮኖሚ እስከመቼ ነው የሚዘልቀው የሁላችንም ጥያቄ ነው?
ከሰሞኑ አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ150 ብር ወደ 80 ብር በመውረዱ ሸማቹ ፈጣሪውን እያመሰገነ ነው። ምስጋናው ውሎ አያድርም። ለመገናኛ ብዙሀን ፍጆታ ከዋለ በኋላ ወደነበረበት ይመለሳል። ይህ እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ምርት በደረሰ ጊዜም ሆነ ምርት በሌለበት ወቅት የመሸጫ ዋጋ ልዩነት ሳይፈጥር ዓመታት ተቆጥሯል። ዛሬም ይኸው ነው የሚታየው። እናስ በዚህ ሁኔታ የምንቀጥለው እስከ መቼ ነው?
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም