የጉጂ ዞን በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ሰፋፊ ዞኖች አንዱ ነው፤ በተፈጥሮ ሃብትም የታደለ፤ በተለይም ደግሞ በሀገሪቱ ትልቅ የወርቅ ክምችት አለበት ከሚባሉ ስፍራዎች አንዱ ነው። ቡና የሚበቅልበት የአረንጓዴ ወርቅ መናኸሪያም፤ በእንስሳት ሃብት፣ በማር እና በደን ልማትም ስመ ገናና ከሆኑ አካባቢዎች መካካል ነው። ከዚህም ባሻገር የገዳ ሥርዓት በፅኑ ስር የሠደደበትና አሁንም ድረስ ሳይሸራረፍ፣ ባህል፣ እሴትና ወጉ ጭምር ሳይበረዝ የሚተገበርበት አካባቢ ነው።
በሌላ ጎኑ ሰፊ ኢንቨስትመንት የሚካሄድበትን ያክል ዕድገት ያልተመዘገበበት ዞን ነው። በተለይም በማዕድን ልማት ዙሪያ በነዋሪዎች ለዓመታት ቅሬታዎች የሚቀርቡበት አካባቢ ነወ። በዛሬ ዕትማችን በእነዚህና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ከሆኑት አቶ ነጋሽ ቡላላ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ጉጂ ዞን እና አሁናዊ ገፅታዋ እንዴት ምን ይመስላል ?
አቶ ነጋሽ፡– ጉጂ ዞን በሰፊው የሚገለፅ ነገር አላት። የሕዝቡ አኗኗር አጠቃላይ ሲታይ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል አኳያ የተፈጥሮ ሃብትና ሕዝብ በሚገባ ተጣምሮና ተዋዶ የሚኖርባት ዞን ናት። በጉጂ ዞን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አሉባት ማለት አንችላለን። ዞኑ በጠንካራ የገዳ ሥርዓትም የሚታወቅ ነው። በእርገጥ የገዳ ሥርዓት በሌላ ቦታም አለ። ነገር ግን ጉጂ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ ሥርዓቱ ሳይቋረጥ የቀጠለበት እና ያበበበት ነው።
ይህ ሥርዓት ከዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ስለመኖሩም አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህም በዞኑ የገዳ ስርዓትን ለረጅም ዘመናት ሲተገበር እንደኖረ ማሳያ ነው። በዚህም ጎን ለጎን ዞኑ በደን ልማት እና በለምነቱ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን፡- በጉጂ ያለው የደን ልማት ምን የተለየ ገጽታ አለው?
አቶ ነጋሽ፡- እዚህ አካባቢ ደን ማለት ሕይወት ነው። ደን ልማት ከገዳ ሥርዓት ጋር ይያያዛል። በጉጂ ውስጥ ደን ማለት ልክ የሰው ሕይወት ያክል ቦታ የሚጠው ነው። ደን ማንም ብድግ ብሎ አይጨፈጭፍም። የመኖር ሚስጥር እና ሕይወት ነው ተብሎ ይታሰባል። በዚህም የተነሳ ለዘመናት ሳይነካ የኖረ እና በመቶ ሺህ ሄክታር የሚቆጠር ደን አለ። በደን ሽፋን ከኦሮሚያ ዞኖች ቀዳሚው ነው። በጣም ጥቅጥቅ ያለ ደን ያለበት ነው። ሕዝብ እየተበራከተ ሲሄድ ደን ይጨፈጨፋል ብለን ስለንምንሰጋም የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀይሰንም እየሰራን ነው። ይህ ለደን ልማት ካለን ፍላጎት እና ልዩ ትኩረት የመጣ ነው።
በገዳ ሥርዓትም ደን ማለት ሕይወት በመሆኑ ደን ሲጨፈጭፍ የተያዘ አካልም ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቀዋል። ይህ በመሆኑም ነው ጉጂ ያለው ደን እና የሰው ልጅ ትስስር ጠንካራ ነው የምንለው። በዞናችን በግብርና እና በአጠቃላይ የሕዝብ የሰፈረበት ቦታ ሲደመርና በደን ከተሸፈነው ጋር ሲነፃፀር በደን የተሸፈነው ይበልጣል። ደን መጠበቅ አለብን ከሚል እሳቤ ደግሞ አዲስ ስትራቴጂ ዘይደናል።
አዲስ ዘመን፡- ምን የተለየ ስትራቴጂ አላችሁ?
አቶ ነጋሽ፡- በዞኑ ከፍተኛ የደን ሽፋን መኖሩ የሚታወቅ ነው። ይህ መጠበቅ አለበት። ነገር ግን ደግሞ ከዚህ በተለየ ሁኔታ አንዳንድ አዳዲስ ሐሳቦችን ማፍለቅ አለብን ብለን አስበናል። ከምዕራብ ጉጂ እስከ ባሌ ድረስ ጥቅጥቅ ያለ ደን ሽፋን ያለበት ነው። እኛም በጉጂ ዞን ውስጥ 29ሺ ሄክታር ደን ጥብቅ ደን እና ብሔራዊ ፓርክ እንዲሆን እየከለልን ነው። ይህን የምንከልለው ደግሞ ብዙ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ነው።
የመጀመሪያው የአካባቢ የአየር ንብረት ከቀድሞ በተለየ ሁኔታ እንዳይቀየር ነው። ይህ እንደ ሀገርም ፋይዳው የጎላ ነው። ሌላው እንደ ሀገር ግሪን ኢኮኖሚ አኳያ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያለው በመሆኑ ነው። ደን እንዳይሳሳ እና እንዳይጨፈጨፍም ጥበቃ ያገኛል። በአጠቃላይ በሀገሪቱ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መሰረቱ እንዲጠናከርና ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ በዓለም ዘንድ ያገኘችው ከፍተኛ ትኩረት የበለጠ ትርጉም እንዲኖረው በማሰብ ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዞኑ ከደን ልማት በዘለለ የሚታወቀው በማዕድን ጭምር ነው። በዚህ ላይ የሚጠበቅባችሁን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ነጋሽ፡- ዞኑ ለኢንቨስትመንት በጣም ምቹ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው። በ2016 በጀት ዓመት 143 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ገብተዋል። በቀጣይ ይህን ለማሳደግና 700 የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ለማስገባት እየሰራን ነው። እንደ ኦሮሚያ ክልል ደግሞ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያለበት ዞን ጉጂ ዞን ነው። እስከ አሁን በጥናት የተለዩ 53 የሚደርሱ ማዕድናት እንዳሉም ይታወቃል።
ከእነዚህ ውስጥ 31 የሚሆኑት ተለይተው አንዳንዶቹ እየተመረቱ ነው፤ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ገበያ ፍለጋ ላይ ነን። ይህ የሚሳያው አካባቢው በከፍተኛ ደረጃ በማዕድን የበለፀገ ስለመሆኑ ነው። በሌላ አካባቢ የሌሉ እና በጉጂ ብቻ የሚገኙ እጅግ በዋጋ ደረጃ በጣም ውድ፣ በዓለም ገበያ ደግሞ በእጅጉ ተፈላጊ የሆኑ ማዕድናትም ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- የማዕድን ሃብት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ነዋሪው ሕዝብ ከዚህ ሃብት እየተጠቀመ ነው?
አቶ ነጋሽ፡- ተጠቃሚነትን በተመለከተ የአካባቢው ሕዝብ በተለይም ወጣቶችን አደራጅተን እንደየአስፈላጊነቱ እየተጠቀሙ ነው። በተለይ በወጣቶች አደረጃጀት በተመለከተ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሴክተር አደራጅተን በትኩረት እየሰራን ነው። በመሆኑም 121ሺ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅደን እስካሁን በማዕድን ዘርፍ ላይ ብቻ 50ሺ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል። በዚህ ሴክተር የተፈጠረው የሥራ ዕድል በጣም ብዙ ነው። በዚህ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠንም በጣም ከፍተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል ብቻ ወጣቶችን አደራጅቶ ማሠማራት ተገቢ ቢሆንም፤ የማዕድን ዘርፉ ልዩ እውቀት፣ ቴክሎጂ እና ጥበብ አይፈልግም?
አቶ ነጋሽ፡- ማዕድናት ክፍፍል ወይንም ዘርፍ አላቸው። የከበሩ ማዕድናት የሚባሉ አሉ። በሌላ ጎኑ ደግሞ በዞኑ ውስጥ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚያገለግሉ ማዕድናት ብለን ከፍለን በየዘርፉ እየሰራን ነው። አንዳንዶቹ ማዕድናት በፌደራልና በክልል መንግስት ብቻ ስምሪትና ፈቃድ ሊሰጡ ይችላሉ። የሀገር ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ቅድሚያ ይሰጠዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ መደበኛው ማኅበረሰብ ሊጠቀመው የሚችለው ነው።
እኛም እነዚህን ሁኔታዎች ታሳቢ አድርገን ነው የምንሰራው። ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት ላይ ወጣቶችን አደራጅተን እየተጠቀሙ ነው። ለአብነትም ለኮንስትራክሽን እና ለተለያዩ ግንባታዎች ግብዓት የሚሆኑና ውስብስብ ዕውቀት የማይጠይቁ ማዕድናት አሉ። በአጠቃላይ ሲታይ ግን ማዕድናት ላይ ከፍተኛ አቅም ያለው የሰው ኃይል ማሰማራት እንደሚቻል ተገንዝበን ወደ ሥራ ገብተናል።
በአርብቶ አደርም ሆነ አርሶ አደር አካባቢ ይህን ተግባራዊ አድርገን ወጣቶች ተጠቃሚ ሆነዋል። እያንዳንዱን ሥራ በኃላፊነት የምንሰራው መሆኑን በሚገባ ማጤን ይገባል። በብዛት እየሰራን ያለነው ወጣቱ ከዝቅትኛ አቅም ተነስቶ ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገር አለበት በሚል እሳቤ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ በመደራጀቱ ብቻ ወደ ሌላ ደረጃ መሸጋገር ይችላል ብለው ያምናሉ?
አቶ ነጋሽ፡- እኛ ወጣቶችን አደራጅተን የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የምናደርገው በዚያው እንዲቆዩ አይደለም። ከጥቃቅን ተነስተው፣ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ እንዲያድጉ አስበን ነው። ከሥር ከሥሩ ደግሞ ሌላ ይተካል። ከመካከለኛው ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ አድገው ሀገርን እንዲጠቅሙ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ ለምርጥ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከኦሮሚያ ማዕድን ባለስልጣን ጋር በመነጋገር ማሽኖችን የሚያገኙበት ዕድል እየተፈጠረ ነው።
ወርቅ ላይ ጥሩ እየሰራን ነው። በሌሎች ማዕድናትም ላይ እየሰራን ነው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ወጣቶቹ ተደራጅተው ጥሩ ሥራ እየሰሩ እያለ የገበያ ችግር ያጋጥማቸዋል። ዞናችን ከማደራጀት ጀምሮ አቅሙ የሚችለውን ሁሉ ያግዛል። ችግሮችን ለማቃለል ከኦሮሚያ ማዕድን ባለስልጣን እና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር መፍትሄ እያበጀን ነው። በትልልቅ ድርጅቶችም ደረጃ ራሳቸውን በየጊዜው እንዲያሳድጉ ነው ድጋፍ እናደርጋለን። በአጠቃላይ ግን ማኅበረሰቡ ተጠቃሚነት እንዲሆንና የአካባቢ ሃብትም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ውስጥ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ድርጅቶች ኢንቨስትመንት እያካሄዱ ነው። ይህም ሆኖ ማዕድናት ባሉበት አካባቢ ኮንትሮባንድ ስጋት መሆኑ ይታወቃል። ስጋቱን ለመቀልበስ ምን እየሰራችሁ ነው ?
አቶ ነጋሽ፡- ትክክል ነው። ማዕድን በባህሪው በጣም ሕገ ወጥ ንግድ እና ለፈጣን የኮንትሮባንድ ዝውውር የመጋለጥ ዕድል አለው። ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እና ተፈላጊነት አኳያም በጣም ተጋላጭ የሆነ ዘርፍ መሆኑም የሚታመን ነው። እኛም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ታክስ ፎርስ›› አዘጋጅተን እየሰራን ነው። ለአብነትም እኛ ከኦሮሚያ ማዕድን ባለስልጣን እና ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የተናበበ ሥራ እየሰራን ነው። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ፈትተናል ወይንም ደግሞ የመጨረሻውን እልባት ሰጥተናል ማለት አንችልም።
ቀደም ሲል በርካታ ችግሮች ነበሩ። ማዕድን የሀገሪቱን የምጣኔ ሃብት ዕድገት ወይንም የኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ይወስናሉ ወይም በኢኮኖሚው ውስጥ ወሳኝ ናቸው ተብለው ከተመደቡ ዘርፎች መካካል እንደ አንዱ የተቆጠረው ከለውጥ ወዲህ ነው። ቀደም ሲል የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑም ለችግር የመጋለጥ ዕድል ነበረው።
ቀደም ሲል ሀብቱ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር፤ ጥቂቶችም ይጠቀመበት ነበር። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ሀገርንም የሚጎዳ ሥራ ይከናወን ነበር። አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ የማዕድን ኮንትሮባንድን ንግድ አስቀርተናል ባይባልም ቀደም ሲል ከነበረው ሕገ ወጥ አሰራርን ከማስቀረት አኳያ ግን ከፍተኛ መሻሻል ይታያል። ሀገርና ሕዝብን በመጉዳት የጥቂት ግለሰቦችን ኪስ የማጨቅ ባህሪ እና ዝንባሌ አሁን የለም።
አዲስ ዘመን፡- በጉጂ ውስጥ ማዕድን ልማት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብበት እንደነበር ይታወቃል። በተለይም ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል። አሁንስ ቅሬታዎች የሉም?
አቶ ነጋሽ፡- ከለውጡ በፊት የነበሩ ቅሬታዎች ትክክለኛ ነበሩ። እነዚህ ቅሬታዎች ቀደም ሲል የነበሩ ናቸው። ከለውጡ በኋላ ግን መፍትሄ አግኝቷል። መንግስትም ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጦ ወደ ተግባር ተገብቷል። ድርጅቶችም የነበራቸውን ብልሹ አሰራሮች እንዲያርሙ ተደርጓል። ማኅበረሰቡ ከአካባቢው ከሚገኘው ሃብት እንዴት ተጠቃሚ ይሆናል በሚለው ላይ አሰራር አለ። የሕዝቡ ተጠቃሚነት ምን መሆን አለበት የሚለው በሚለው ሕግ ወጥቷል። ይህንንም ከቀበሌ ጀምሮ በወረዳ፣ ዞን፣ ክልል እና ፌደራል ደረጃ ማን ምን ይሰራል የሚለው አሰራር ተቀምጧል።
ቀደም ሲል ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙትም ጥሩ አልነበረም፤ አሁን ይህ ተስተካክሏል። በእርግጥ ኢንዱስትሪ ሲቋቋም ከችግር ነፃ ነው ማለት አይቻልም። ይሁንና ይህን መፍታት የእኛ ድርሻ ነው። እኛም ወጣቶችን ስናደራጅ ወደ ተሻለ ቦታ እንዲደርሱ እና ኅብረተሰቡም እንዲጠቀም ነው። ሕብረተሰቡም ቀደም ሲል የነበረው ቅሬታ መፈታቱን ያምናል። ቀደም ሲል የነበረውና ለዓመታት የነበረው ችግር አሁን የለም። እኛም ለበለጠ ዝግጁነትና ጥንቃቄ ጥናቶችን እያካሄድን ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ግን፤ በዞናችን የማዕድን ጉዳይ መስመር የያዘው አሁን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን እንዳይደገሙ ቀደም ሲል የነበሩት ችግሮች ምንጫቸው ተለይቷል?
አቶ ነጋሽ፡- የማዕድን ዘርፍ ትልቁ ችግር እና ድሮም የተበላሸው ከአሰራር ነበር። ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ግልፅነት የጎደላቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ። አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ማዕድን ሰብስበው ጭነው ወደሚፈልጉበት ቦታ ይወስዱ ነበር። ጠያቂ የሌለው በመሆኑ ሃብት ይባክን ነበር። ዋነኛ የቅሬታ ምንጭ ከሆኑትም ውስጥ አንዱ ይህ ነው። በአሁኑ ወቅት ከቀበሌ ጀምሮ በእያንዳንዱ የመንግስት የስልጣን እርከን ላይ ያለ ሕጋዊ አካል ኃላፊነቱ ምንድን ነው፤ ምንስ ይሥራ የሚለው ተለይቷል።
አሁን ከሮያሊቲ ክፍያ ጀምሮ ማዕድንን በተመለከተ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው ሕጋዊ አሰራር ተቀምጦለታል። በዚህም የተነሳ ሕዝብን ችግር ውስጥ የሚከት ነገር የለም። በፊት የነበረውን አሁን እንዳለ አድርጎ መውሰድ አግባብ አይደለም። እኛ ከሕዝቡ ጋር በቅርበት እየተወያየንና መፍትሄ እየሰጠ ነው። ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን በፍጥነት ለመመለስ የሚያስችል ሕጋዊ አሰራር ዘርግተናል። ይህ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታች ድረስ የወረደ በመሆኑ አሁን ስጋት የለም።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ሀገር ኮንትሮባንድ ንግድ ካለባቸው አካባቢዎች አንዱ ጉጂ ዞን ነው። ይህን በመከላከል ላይ ምን የተሰራ ነገር አለ?
አቶ ነጋሽ፡– በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ከለውጡ በፊት እጅግ አስቸጋሪ የሆነ የኮንትሮባድ ንግድ ነበር። ሕገ ወጥነት ያለበት ዘርፍ አንዱ ማዕድን ነው። ሌላው በዚህ አካባቢ ኮንትሮባንድ የሚነሳው በኬኒያ ሞያሌ በኩል የሚገቡ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች አሉ። ይህንን ለመከላከል ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረግን ነው። ጠንካራ ሥራዎችን በመስራታችን ውጤት ተገኝቷል። ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት የኮንትሮባንድ ሸቀጦች በቁጥጥር ሥር አውለናል። ቀደም ባሉት ዓመታት ከኮንትሮባንድ ንግድ ከሁለት ሚሊዮን ብር የዘለለ አንሰበስብም ነበር።
ሕገ ወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ሰፊ ሥራ ሰርተናል። በአሁኑ ወቅትም ቢሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ እርምጃ እየወሰድን ነው። በተለይም ማዕድናት፣ አልባሳትና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች በብዛት በኮንትሮባንድ ዝውውር ውስጥ መኖራቸውን ተገንዝበናል።
አሁን የኮንትሮባንድ ንግድ ጉዳይ አሳሳቢ አይደለም። ይህን ለማስቀረት ብዙ ሰርተናል። የመጀመሪው ማዕድን ትክክለኛ ገበያ ላይ እንዲቀርብ እና ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግ ነው። ሌላኛው ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር ያለንን ጠንካራ ቁርኝት ማሳደግና ችግሮችን በውይይት መፍታት ብሎም ግንዛቤ ማሳደግ ነው። በዚህም ስኬታማ የሚባሉ ክንውኖች አሉ።
ኅብረተሰቡም አሁን ላይ ከኮንትሮባንድ ንግድ ይልቅ ሕጋዊ መሆኑን አዋጭ መሆኑን እየተገነዘበ ነው። የቁጥጥር ሥርዓታችንም ከተለመደው አካሄድ በተለየ መንገድ ስትራቴጂን እና ዕውቀትን መሰረት ያደረገ ነው። በዚህ የተነሳ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግበናል። በቀጣይም አጠናክረን የምንቀጥለው ነገር ቢኖር ኮንትሮባንድ ንግድን ለማስቆም የምናደርገው ጥረት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ጉጂ ዞን ከሠላም እና መረጋጋት አኳያ አልፎ አልፎ ጥያቄዎች ይነሱበታል። አሁንስ?
አቶ ነጋሽ፡- ሰዎች በርቀት ሆነው ጉጂ ሠላም የሌለ ይመስላቸዋል። እኔ ግን አንድ ነገር ማሳወቅ የምፈልገው ጉጂ በጣም ሠላም ነው። በዞናችን ውስጥ 13 ወረዳዎች አሉን። 11 ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ ፀጥታ ችግር የለባውቸም። ሁለቱ ወረዳዎችም ከሁለት ቀበሌ የማይበልጡ ብቻ አልፎ አልፎ የተወሰነ ችግር አለ። እነዚህም ከምስራቅ ቦረና ጋር የሚዋሰኑ ወረዳዎች ናቸው።
ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ስልታዊና ውጤታማ ኦፕሬሽኖችን እያካሄድን ጠላት የሚንቀሳቀስበት ቀጣና አሳጥተናል። ስለዚህ ጉጂ ሰላም ነው። የሠላሙ ምንጭ ደግሞ ኅብረተሰቡ ነው። ሕዝቡ ይህን የተማረው ከገዳ ሥርዓት ነው። በገዳ ሥርዓት ውስጥ ሠላም ቅድሚያ ይሰጠዋል። በመሆኑም የአባገዳዎች እና የሕዝቡ ሚና ቀላል አይደለም።
ከዚህ በተጨማሪ የፀጥታ መዋቅራችን ትልቁን ኃላፊነት እየተወጣ ነው። ሚሊሻዎች፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሠላምና መረጋጋቱ ትልቅ አበርክቶ አላቸው። በመሆኑም ሁሉም ወረዳዎች በልማት ላይ ናቸው። ልማት ማካሄድ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ወደ ዞኑ መጥቶ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚችል በዚህ አጋጣሚ መልዕክት ማስተላለፍ እወዳለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ ነጋሽ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም