ሀገር የዜጎቿ ውጤት ናት፡፡ ዜጎች ደግሞ በትውልድ ጅረት ውስጥ የሚፈራረቁ አላፊ ፍጡራን ናቸው። ይሁን እንጂ በሚያልፈው የኑረት ዘመናቸው ውስጥ የማያልፍ ታሪክ ጽፈው፤ የማታልፍ ሀገር መስርተው ያልፋሉ፡፡ ነገ የተባለው ጊዜ ዛሬ ሲሆን፤ ዛሬ የተባለውም ወደ ትናትን ሲቀየር፤ ሰዎችም ከነበር ዘመን ጋር አብረው ከዛሬ ወደ ትናንት፤ ከትናንትም ወደ ሩቅ ዘመን ነዋሪነት ይሸጋገራሉ፡፡
ይሄ የትውልድ ፍርርቆሽ፤ ሀገርን ሲያጸና፣ ታሪክን ሲሰራ የሚራመድበት የራሱ አካሄድና መንገድ አለው፡፡ የትኛውም ይሁን የቱ መንገድ ግን የመጨረሻ ግቡ ሀገርን ማጽናት፤ የዜጎችን ክብርና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ አያሌ ጦርነቶችን አድርገዋል፡፡ እነዚህ ጦርነቶች አንድም ከውጪ በሚመጣ ወራሪ፤ ሁለትም ከውስጥ በሚነሳ ሀገር አፍራሽ ኃይል ገፊነት የተደረጉ ናቸው፡፡
የጦርነቶቹ መካሄድ ምክንያትም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የውጪ ወራሪን ሀገር ላለማስደፈር፤ በውስጥ ባንዳም ሀገር ላለማስበተን ነው፡፡ በዚህም ጦር ተማዝዘው የአካልም፣ የሕይወትም ዋጋ ከፍለው ኢትዮጵያን እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያዊነትንም እንደ ክብር ለትውልዶች እያሳለፉ ዛሬ ላይ ተደርሷል፡፡
የዓድዋ ድል ደግሞ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ እንዴት ቢሉ፣ ወቅቱ ምዕራባውያን አፍሪካን ለመቀራመት እጣ ተጣጥለው ለወረራ እና ምዝበራ የተሰማሩበት ነበር፡፡ በዚህ መልኩም አፍሪካ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ስር ለመግባት ተገደዱ፤ ኢትዮጵያም ለጣሊያን ደርሳ ኖሮ፣ ጣሊያን የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቃ ትገባለች፡፡
ይሁን እንጂ ጣሊያን በኢትዮጵያ ጉዳይ እድለኛ አልነበረችም፤ እንደ ሌሎቹ ቅኝ ገዢዎችም ሆነ፤ እርሷም በሌሎቹ ሀገራት ላይ እንዳደረገችው ሀገራቱን ተቆጣጥሮ የመግዛት ስኬት፤ ኢትዮጵያ ላይ አልተሳካላትም።ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ የተሰነዘሩባቸውን ጥቃቶች ሲያከሽፉ የኖሩ፤ ለክብርና ሉዓላዊነታቸውም የማይበገሩ አናብስት ነበሩና ነው፡፡
ይሄ የዘመናት የሕዝብና መሪ ተግባር፣ ኢትዮጵያን አጽንቶ፤ የሕዝብን ክብር አስጠበቆ ኖሯል፡፡ በዘመነ ቅኝ ግዛት ዘመንም ጣሊያንን በዓድዋ ተራሮች መካከል አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ወደመጣችበት ሲመልሳት፤ ይሄው የሀገር ሉዓላዊነት ስሜት፣ የሕዝብ ክብር ጉዳይ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያን በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች ምድር፤ ኢትዮጵያውያንንም ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከኩ ነጻ ሕዝቦች ሆነው ዓለም ያለ ልዩነት እንዲዘክራቸው የታሪክ ሐውልት ተክለዋል፡፡
ይሄ የትናንት ታላቅነት፤ የወቅቱ አይበገሬነት ልዕልና፤ ለዛሬው ኢትዮጵያውያን ትምህርትም፣ አቅምም የሚሆን ነው፡፡ ምክንያቱም የትናንቶቹ ቴክኖሎጂ ባልዳበረበት በዛ ዘመን ሀገርና ፍቅር በሚባሉ የመናበቢያና የመተሳሰሪያ አቅሞች አኩሪ ታሪክ ለመጻፍ በቅተዋል፡፡ ትናንትን አሻግረው ዛሬን አሳይተዋል፡፡ የዛሬዎቹ ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥራን ባቀለለበት፤ ሀገርን ለማሻገርም የሕይወት መስዋእትነትን ሳይሆን የሞራልና የልብ መነሳሳትን ብቻ በሚጠይቅበት በዚህ ዘመን ከዓድዋ ባለታሪኮች ብዙ ሊማር ይገባዋል፡፡
ከትናንት አባቶቹ ወኔን፣ አልበለጥ ባይነትን፣ ሕብረትን፣ ፍቅርና መተባበርን፣ መተማመንና በዓላማ መተሳሰርን፣ ከታሪክ ነጋሪነት ባሻገር ታሪክ ሰሪነትን፣ ከጊዜና ሁኔታ ጋር ራስን አስማምቶ ልቆ መገኘትን፣… ሊማር ይገባዋል፡፡ እነዚህን የሚያደርገው እንደ ትናንቶቹ ለመሆን አይደለም፡፡ ይልቁንም ከእነርሱ ታላቅነት ልቆ ለመገኘት፤ ከእነሱ ሀገር አሻጋሪነት ተሽሎ፤ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን ራስን ማስገዛትን ገንዘቡ ሊያደርግ እንጂ፡፡
የዛሬው ሀገርን የማጽናት፣ የሕዝብን ክብርና ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ጉዞ፤ እንደ ትናንቱ ጦር የሚያጠማዝዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም በእውቀት መላቅን፤ በቴክኖሎጂ መታገዝን፤ ለዓላማ መገዛትን፤ ለሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ቅድሚያ መስጠትን፤ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝቦ መራመድን፤ ወንድማማችነትና አብሮነትን ማጽናትን፤ በችግሮች ላይ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ መግባባትን፤ ከቂምና ቁርሾ ወጥቶ ለፍቅርና ይቅርታ ቅድሚያ መስጠትን፤… በእጅጉ ይሻል፡፡
ከትናንቱ የላቀ ዛሬን መገንባት፤ ከዛሬው የተሻለ ነገርን እውን ማድረግ የሚቻለው በዚህ መንገድ መስራትና መራመድ ሲቻል ነው፡፡ የትናንት አባቶቹን ታሪክና መንገድ ያወቀና ያከበረ ትውልድ ደግሞ ከታሪኩ ተምሮ፣ ከመንገዳቸው የራሱን መንገድ ተልሞ ይራመዳል፡፡ የእነርሱን ስህተት አርሞ፣ ጥንካሬያቸውንም በላቀ መልኩ ተላብሶ አቅሙን ያደረጃል፡፡ የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ በነጻነት የቆየችን ሀገር፤ ነጻነቷን ወደ ሙላት ለማሸጋገር፣ ወደ ብልጽግናዋ ማማ ለማውጣት ሳይታክት ይሰራል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2016