የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው አብዛኛው ዜጋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚያደርገው ፍልሰት ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ ነው፡፡ ለፍልሰቱ የራሱ የሆነ ገፊ ምክንያት ቢኖረውም የከተማ ነዋሪው ቁጥር ግን ከፍ እያለ ስለመሔዱ አጠራጣሪ አይደለም፡፡ የከተሜው ቁጥር ከማሻቀቡ ጋር ተያይዞ ለኑሮ ውድነቱ ጫና እየፈጠረ ይገኛል፡፡
የከተማ ነዋሪዎችን የድህነት ሁኔታ ለማሻሻል ያግዝ ዘንድ መንግሥት የከተማ ግብርናን እንደ አንድ አማራጭ በመያዝ ወደሥራ ገብቷል፡፡ ይህ የከተማ ግብርና በሁሉም አካባቢ ተግባራዊ መሆን ከቻለ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖር ከማድረግ ባሻገር የምግብ ዋስትናንም ለማረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ አሁን አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ሕዝቡን የተጫነው የኑሮ ውድነት ከመቀነስ አኳያም ሚናው ላቅ ያለ ነው፡፡
ከሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ጅማ በማቅናት የጅማ ከተማ ግብርና ጽሕፈት ቤትን መዳረሻው አድርጓል፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ ጀማል እንደሚናገሩት፤ የከተማ ግብርና ከዚህ ቀደም ትኩረት አልተሰጠውም ነበር። ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በተለይም ላለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ለከተማ ግብርና ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡
የከተማ ግብርና የከተማውንና በዙሪያዋ ያሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከተማው የሚታወቀው በንግድ ማዕከልነቱ ነበር፡፡ የግብርና ምርት የሚያገኘው በዙሪያው ካሉ ቀበሌዎችና አጎራባች ወረዳዎች ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከተማ የንግድ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ተመርቶ የሚሸጥበትም ሆኗል፡፡ በተለይም ከለውጡ በኋላ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እያንዳንዱ ከተማ የራሱን ምርት ለማምረት እንቅስቃሴ በማ ድረግ ላይ ይገኛል ፡፡
ዘንድሮ እንደ ሀገር፣ እንደክልልም ሆነ እንደከተማም አስተዳደር ሰፊ እቅድ የታቀደ ሲሆን፣ ያንን እቅድ ለማከናወን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጥምረት በመሥራት ላይ ነው፡፡ እቅዱ ተግባራዊ እንዲሆን የከተማ ነዋሪውና በከተማው የታቀፉ በከተማው ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በዚህ ረገድ እኛም እንደ ግብርና ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎቻችን በማደራጀት አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ቅስቀሳ አድርገን አጠናክረናል የሚሉት አቶ አብዱላዚዝ፣ በጅማ ከተማ አስተዳደር የሚተዳደሩ 17 ቀበሌዎች እንዳሉም ይናገራሉ። በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ የከተማ ነዋሪዎችና አርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ አግኝተው እንዲሠማሩ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። የቀበሌዎቹ ነዋሪዎች በግብርና ሥራ እንዲሳተፉ ከፍተኛ ቅስቀሳ ተደርጎ በመሥራት ላይ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በዚህ ዙሪያ ዘንድሮ ልዩ እቅድ ተደርጎ እየተሠራ ነው፡፡ ከተማ ሰፊ ሕዝብ፣ አነስተኛ መሬት ያለው እንደመሆኑ፤ አነስተኛ መሬት ምርታማ ይሆን ዘንድ ቴክኖሎጂን መጠቀም የግድ የሚል ነው፡፡ ይህን በማድረግ ጠባቂነቱን በመተው ለራሱ ብቁ መሆን እንዲችል እየተሠራ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እንደ ጅማ ከተማ ሰፋፊ መሬት ያላቸው አራት ቀበሌዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች በፊት የከተማ ግብርና ትኩረት ባላገኘበት ጊዜ ሙያዊ ድጋፍ አያገኙም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉንም የግብርና ግብዓት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
በገጠር ያሉትም ባላቸው ሰፋ ያለ መሬት፣ በከተማ ያሉ ባላቸው አነስተኛ መሬት ጓሯቸውንም ሆነ ግድግዳቸውንም ተጠቅመው “ምግቤን ከጓሮዬ” በሚለው መርሕ እንዲያመርቱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ ይህ ተነሳሽነት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በአቅጣጫ መልክ የተቀመጠው አምና ሲሆን፣ እኛም እንደ ከተማችን አቅጣጫውን በመቀበል ወደተግባር የመቀየር እንቅስቃሴ ጀምረናል›› ይላሉ፡፡ በተለይ ሰፋፊ መሬት ያላቸው በመስኖም ሆነ በክረምቱ ወቅት እንዲያመርቱና ለራሳቸውም ለገበያም በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡
በከተማ ግብርና የሚሠራው በጋ ላይ በመስኖ፤ ክረምት ላይ በዝናብ ማምረት ብቻ ሳይሆን በእንስሳት ማርባት ዙሪያም ጭምር ነው፡፡ በከብት፣ በዶሮና በንብ ማነብ ላይ የተለያዩ ሥራ አጥ ወጣቶችም በመሳተፋቸው የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ጅማ ከተማ አስተዳደር ሰፊ ሥራ መሠራቱን ኃላፊው ይናገራሉ። ሼዶችን በክላስተር በመሥራት ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲጠቀሙበት ተደርጓል፡፡
ለአብነት ለዶሮ፣ ወተት ከብት እርባታ፣ ለከብት ማድለብ እና ለንብ ማነብ ሥራ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ሼዶች ተገንብተዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በራሱ በጀት ከሚሠራው ሥራ አልፎ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች፣ ማኅበራትና ባለሀብቶች በዚህ ሥራ ገብተው አምርተው የከተማውን ማኅበረሰብ ፍላጎት እንዲያሟሉ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡
እንደኃላፊው ማብራሪያ፤ የከተማው ግብርና ሥራ የከተማውንና በከተማው ዙሪያ ያሉ ቀበሌዎችን የወተት፣ ዶሮና እንቁላል ፍላጎት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በማሟላት ላይ ነው፡፡ ለሥራ አጥ ወጣቶችም የሥራ እድል በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ ሌላው በከተማ ግብርና ከሚሠራው ውስጥ ተጠቃሹ ንብ ማነብ ነው። ቀደም ሲል የማር ምርት ለከተማው ነዋሪ ይመጣ የነበረው ከገጠር ቀበሌዎች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን በከተማ ውስጥም ንብ ማነብ ይቻላል የሚለውን መርሕ በመከተል ማምረት ተጀምሯል፡፡
በጅማ አካባቢ በዓመት ሦስት ጊዜ አበባ ሊሆኑ የሚችሉ ዛፎች በመኖራቸው ለማር ማምረት ምቹ ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም ራሳቸው አምራቾቹም ሆኑ የከተማው ነዋሪ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከተወሰኑ ወራት በኋላ ማር የሚቆርጡ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ደግሞ በዘርፉ በመደራጀት ላይ ያሉ ወጣቶች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡
‹‹በሁሉም ዘርፎች ሙያዊ ድጋፍ በሚያስፈልግበት ሰዓት ቀን ከሌት በመሥራት ላይ እንገኛለን›› የሚሉት አቶ አብዱላዚዝ፣ ለአብነት ያህል ንብ ወደቀፎው የሚገባው ምሸት ላይ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በቦታው ተገኝተው ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ይናገራሉ፡፡ በዶሮና በከብቶቹም ዙሪያ ከእርባታ ሒደታቸውና ጤናቸውን ከመጠበቅ አኳያ እንዲሁ ሙያዊ ድጋፋቸው እንደማይለይ ያስረዳሉ፡፡
የከተማው ማኅበረሰብ ከአጎራባች ቀበሌና ወረዳ የግብርና ምርት ከመጠበቅ አልፎ የራሱን ምግብ ራሱ እንዲያመርት በሰፊው እየተበረታታ ይገኛል፡፡ ራሱም ተጠቃሚ ሆኖ ለገበያም እንዲያቀርብ በመሠራት ላይ ነው፡፡ ግብርና ጽሕፈት ቤት- ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ያልተቋረጠ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠትም እየሠሩ ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በከተማዋ ዙሪያ ባሉ የእርሻ መሬት ላይ የመስኖ ሥራ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ጅማ ከተማን አቋርጠው የሚሔዱ በዙሪያው የሚያልፉ ወንዞች አሉ። 12 ኪሎ ሜትር አካባቢ በሚሆን ርዝማኔ ከተማዋን አቋርጦ የሚሔደው የአዌይቱ ወንዝ ለከተማዋ ውበት ከመሆን ባሻገር ብዙ ቀበሌዎች ላይ የግብርና ልማቱን የሚያሳልጥ ነው፡፡ በየቀበሌዎቹ ቲማቲም፣ ጎመን፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ አናናስና ሌሎቹም ፍራፍሬዎችና የጓሮ አትክልቶች ይመረትባቸዋል፡፡ ሌላው ኪቶ የሚባል ወንዝ ሲሆን፣ አርሶ አደሩ በወንዙ እንዲጠቀም ሙያዊ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚህም ራሱን በመጥቀም ለከተማው ነዋሪም ምርት በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በኦሮሚያ ግብርና ጽሕፈት ቤትና በኦሮሚያ ከተማ ልማት በጥምረት ለዶሮ እርባታ 300 ሼዶችን ለመሥራት አቅደዋል፡፡ እነዚህን ሼዶች የከተማ አስተዳደሩ፣ ባለሀብቱ እንዲሁም ማኅበራቱ የሚሠሯቸው ሲሆን በአሁኑ ወቅት 194 ሼዶች ተሠርተዋል፤ ከእነሱም መካከል 115 የሚሆኑቱ ሥራ የጀመሩ ናቸው፡፡
የወተት ላሞችን በተመለከተ 100 ሼዶች እንዲሠሩ ታቅዶ በእስካሁኑ ሒደት 82 ሼዶች ተሠርተው 50ዎቹ ወደሥራ መግባት ችለዋል፡፡ የንብ እርባታን በተመለከተ ደግሞ 50 ሼዶችን በማቀድ አምስት ሺ የማር ቀፎዎችን ለማስገባት የታሰበ ሲሆን፣ እስካሁን ወደ 22 የሚሆኑ የተጠናቀቁ ሲሆን 45 ያህሉ ደግሞ ግንባታ ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ከእቅድ በላይ ከፍ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የሚያመላክት ነው ባይ ናቸው፡፡
ከእነዚህ ውስጥም 18ቱ ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅሰው፤ በዙሪያው ካሉ አርሶ አደሮች ጭምር እስካሁን ወደ ሁለት ሺ 400 የሚሆን የማር ቀፎ በመግባቱ ወደማር ቆረጣው የገቡ አሉ፤ በዚህ አያያዝ ከአምስት ሺ በላይ የማር ቀፎ ማድረስ እንደሚቻልም ግንዛቤ ተይዞበታል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ኃላፊው እንደሚሉት፤ በዶሮዎች በኩል ታቅዶ የነበረው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶሮ ለማስገባት ነበር፤ ከዚህ ውስጥ ከስድስት ሺ በላይ ዶሮ ቤት ለቤትም ሆነ በሼዶቹ በማስገባታቸው በአሁኑ ወቅት እንቁላል መጣል የጀመሩ መኖራቸውን ያመለክታሉ። ከዚህ የተነሳ በቅርቡ በጅማ ከተማ በቂ የእንቁላል ምርት ከመኖር ባለፈ ለሌላም አካባቢ የሚተርፍ እንዲሆን አቅደው እየሠሩ ይገኛል፡፡
አቶ አብዱላዚዝ እንደሚሉት፤ የከተማ ግብርናን ለማሳለጥ ጅማ ምቹ ናት፡፡ የትኛውም ቤት ያለው የከተማዋ ነዋሪ፣ ምግቡን ከደጁ ለማግኘት የሚጠበቅበት ተነሳሽነት ብቻ ነው፡፡ ቦታ እንኳን ባይኖረው በሃይላንድ፣ በተለያየ እቃና በአጥሩ ላይ ጭምር ጎመን፣ ካሮት፣ ቀይ ስርና ሌላውንም የጓሮ አትክልት ማልማትና መጠቀም ይችላል፡፡ ይህ የኑሮ ውድነቱን ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
በቅርቡ ወደከተማ አስተዳደሩ የታቀፉ የተወሰነ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ አብዱላዚዝ፣ ለእነዚህ ቀበሌዎች የከተማ ግብርናው የበለጠ ምቹ መሆኑን ያስታውቃሉ። ‹‹የከተማ ግብርና አንዱ ጥሩነቱ ገበያ ፍለጋ ችግር አለመኖሩ ነው፡፡ ስለዚህ በትንሽ ቦታ ላይ ማምረት የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪ ገበያ ፍለጋም ሩቅ አለመሄዱ ተመራጭ ያደርገዋል›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ከጠቀሜታው አኳያ ሲመዘንም ለመሥራት ተነሳሽነት ያለው ነዋሪው ለአትክልትና ፍራፍሬም ገበያ መሄድ አይጠበቅበትም ይላሉ፡፡ በከተማ ግብርና ለመጠቀም የእርሻ ትራክተር ወይም በሬ መጥመድ አይጠበቅብንም የሚሉት አቶ አብዱላዚዝ፣ በቀላል መሣሪያ አምርቶ መጠቀም እንደሚቻል ይጠቅሳሉ፡፡
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ከተጠቃሚነትና ከዋጋ አንጻር ሲታይ ፍላጎትና አቅርቦት ካልተጣጣመ የገበያ መናር ይከሰታልና ሁለቱን ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት እየተሠራ ባለው የከተማ ግብርና አቅርቦትና ፍላጎት ስለሚጣጣም ገበያው ይረጋጋል ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ለአብነት የዶሮም፣ የወተት ላሞችንም እርባታ መውሰድ ቢቻል የሁለቱም መኖ በጣም ውድ ነው፡፡ አንድ ኩንታል የዶሮ መኖ ከአራት ሺ ብር በላይ ነው፡፡ አንድ ኩንታል የከብቶች ፉርሽካም ከሁለት ሺ ብር በላይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሲታይ የግብርና ምርት ይረክሳል ለማለት ይቸግራል፡፡
‹‹ሆኖም ሰው እንቁላልና ዶሮ አሊያም ወተት ፍለጋ ትራንስፖርት አውጥቶ አይሔድም፤ ከዚህ አንጻር በተወሰነ መልኩ ቅናሽ ያሳያል ማለት ይቻላል›› ይላሉ። ከዚህ ጎን ለጎን ሰው ዶሮን አርዶ ለመብላት የበዓላት ቀንን መጠበቅ አቁሟል፡፡ ምክንያቱም በየሰው ቤት ቢያንስ አስርና አስራ አምስት ዶሮ እንዲረባ በመደረግ ላይ ነውና ሲሉ ኃላፊው ይናገራሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በመንግሥት በተሰጠ አቅጣጫ የሌማት ትሩፋት በ2015 በጀት ዓመት ተግባራዊ ሆኗል። እንደ ጅማ ከተማ የተሰጠውን አቅጣጫ በመተግበር ላይ ነን ሲሉ ኃላፊው ያመለክታሉ። ነዋሪው ወተቱን፣ ሥጋውን፣ ማሩን፣ አትክልቱን እንዲያገኝ በማድረግ የሌማት ትሩፋት ተጠቃሚ እንዲሆን እየሠሩ መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡
እንዲያም ሆኖ የከተማ ግብርና ትኩረት የሚሻው ነገር እንዳለው አቶ አብዱላዚዝ አልሸሸጉም፡፡ እንደ ዞንና ወረዳ ሁኔታዎች የተመቻቹ አይደሉም። የኤክስቴንሽን ሥርዓቱ ተጠንቶ እንዳልተዘረጋም ይጠቁማሉ፡፡ በእርሳቸው እይታ የኤክስቴንሽን ሥርዓቱ እንደከተማ ሊዘረጋ ይገባዋል፡፡ የከተማ መሬት በጣም አነስተኛ እንደመሆኑ በቴክኖሎጂ ተደግፎ ብዙ ምርት እንዲሰጥ ማድረግ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የኤክስቴንሽን ሥርዓቱ በትንሽ መሬት ላይ መሥራት የሚያስችል እንዲሆን ተደርጎ መዘርጋት እንዳለበት ይጠቅሳሉ፡፡ በተጨማሪም ሙያዊ ድጋፍ አሰጣጡ የገጠርና የከተማ አሠራሩ በራሱ ለየቅል በመሆኑ በዚህ ላይም ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ፡፡
በመሆኑም የኤክስቴንሽን ሥርዓቱ ተጠንቶ መዘርጋት፣ የከተማ ግብርናን በፖሊሲ መደገፍና የጽሕፈት ቤቱ አደረጃጀትም ምቹና አስፈላጊዎቹን ባለሙያዎች ያሟላ ሆኖ መደራጀት ይጠበቅበታል ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ እስካሁኑ እየተሠራ ያለው በነባሩ አደረጃጀት በመሆኑ በዚህ ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም ሠርቶ ማሳያዎችና በጀት እንዲሁም በሎጀስቲክም የከተማን ግብርና መደገፍ የሚያስፈልግ ነው፡፡ ሁሉን ነገር ከተማ አስተዳደሩ ሊወጣው አይችልም፡፡ ስለዚህም የከተማ ግብርና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ለውጥ እያመጣ ያለ ስለሆነ ሥራው መንግሥትን ጨምሮ የተለያዩ የባለድርሻ አካላትን ድጋፍ ይሻል፡፡ ይህ ሲሆን ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣና ነዋሪውንም ሆነ ሀገርን ይጠቅማል ይላሉ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም