ጄሲ ኦውንስ- ጥቁሮችን ያስከበረ ኮከብ

የካቲት ወር ለኢትዮጵያውያን ልዩ ወር ነው። ከዓድዋ እስከ ካራማራ ታሪካዊ ድሎች በዚሁ ወር የተከሰቱ ናቸው። ኢትዮጵያውያን የመላውን ዓለም ጥቁር ሕዝቦች አንገት ቀና ያደረጉበትን የዓድዋ ድልን የሚያከብሩበት ወርሀ የካቲት በመላው ዓለምም የጥቁር ሕዝቦች ወር ሆኖ ይከበራል። በሰሜን አሜሪካ፤ ካናዳና ሌሎች ሀገራት በየዓመቱ ከሚከበረው የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ወር ሲዘከር በስፖርቱ ዓለምም ከጥቁር ሕዝብ የፈለቁ ጀግኖች ይታወሳሉ።

ጥቁር ስፖርተኞች በዘመናችን በዓለም ታላላቅ ውድድሮች የገዘፈ ተፅእኖ ቢኖራቸውም እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሳቸው አያሌ ጥቁር ከዋክብት በቆዳ ቀለማቸው መጥቆር ተንቀዋል፣ አይችሉም ተብለው ተገፍተዋል፣ እኩልነታቸውን ለማንፀባረቅም ብዙ መስዋእትነት ከፍለዋል።

በአትሌቲክስ አበበ ቢቂላ፣ በእግር ኳስ ፔሌ፤ በቦክስ መሐመድ አሊን የመሳሰሉ ከዋክብት በዓለም ገናና የስፖርት መድረኮች የጥቁር ስፖርተኞችን እኩልነት ማሳየት የቻሉ ፋና ወጊዎች ናቸው።

የጥቁር ሕዝቦች ወርን ከዚያም የዓድዋ ድልን ስናከብር በስፖርት ውስጥ ለጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ለመሆን ከበቁ ኮከቦች አንዱ የሆነውን ጄሲ ኦውንስን በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን መለስ ብለን እናስታውስ።

1913 በአላባማ የተወለደው ጄሲ ትክክለኛ ስሙ ጄምስ ክሊቭላንድ ኦውንስ ሲሆን በልጅነቱ “JC” ተብሎ ይጠራ ነበር። ወደ ኦሃዮ ከመጣ ወዲህ ግን መምህሩ ስሙን “እሴይ” ሲል ተሳስቶ በዚህ ስም ታወቀ።

ጄሲ አትሌቲክስን የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል በነበረበት ወቅት ነው። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባደረገው የመጀመሪያ ውድድር የዓለም ክብረወሰን ካስመዘገበ በኋላም ወደ ኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ገባ። በአትሌቲክሱም ትልቅ ስኬት ማስመዝገቡን ቀጠለ።

እኤአ በ1935 በሚቺጋን በተካሄደው ቢግ 10 በተሰኘ ቻምፒዮና ጄሲ በ45 ደቂቃ ውስጥ አራት የዓለም ክብረ ወሰኖችን ሰበረ። እነዚህም 100 ያርድ (9.4 ሰከንድ)፣ ረጅም ዝላይ (8.13 ሜትር)፣ 220 ያርድ (20.3 ሰከንድ) እና 220 ያርድ መሰናክሎች (22.6 ሰከንድ) ነበሩ። ይህም አስደናቂ ብቃቱ አሜሪካን በኦሊምፒክ ለመወከል አበቃው።

ጊዜው እኤአ 1936 ነው፣ ውድድሩ ደግሞ ታላቁ ኦሊምፒክ። ወቅቱ የኦሊምፒኩ አዘጋጅ የሆነችው ጀርመን ብቻ ሳትሆን አብዛኛው የዓለም ሀገራት በናዚ ሥርዓት አራማጁ አዶልፍ ሂትለር የብረት መዳፍ የሚታሹበት ነበር።

ጄሲ አሜሪካንን ወክሎ በሂትለር ገዢነት በናዚ የተዘጋጀው የበርሊን ኦሊምፒክ ከመሄዱ በፊት በአሜሪካ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ሂትለር የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚቃወሙ ኃይሎች የአፍሪካን አሜሪካውያን አክቲቪስቶች ውድድሩን እንዳይሳተፍ ይወሰውሱት ነበር። እናም አንድ ቀን ለነጭ አሰልጣኙ ወደ በርሊን ለመሄድ ማመንታቱን ተናግሮ ነበር።

ኦሊምፒኩ በአዶልፍ ሂትለር ናዚ ጀርመን ሲካሄድ “የላቀ የጀርመን ዘር” ወይም የአርያን ሕዝብ የበላይነት ማሳያ እንዲሆን የታቀደ ዝግጅት ነበር።

ሆኖም ጥቁሩ አሜሪካዊ አትሌት ጄሲ ኦውንስ በአስደናቂ ድሎቹ እነዚህን እቅዶች በማክሸፍ በኦሊምፒኩ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አጥልቆ ናዚዎች የሚተናነቃቸውን ድል ማጣጣም ችሏል። እነዚህ የወርቅ ሜዳሊያዎች፡- በ100 ሜትር (10.3 ሰከንድ)፣ በ200 ሜትር (20.7 ሰከንድ)፣ በርዝመት ዝላይ (8.06 ሜትር) እና 4×100 ሜትር ዱላ ቅብብል (39.8 ሰከንድ) ያስመዘገባቸው ነበሩ።

በእነዚህ ስኬቶች ጄሲ ኦውንስ የጥቁር ሕዝቦች እና የአሜሪካውያን ኩራት ሆነ። አሜሪካ በዚያ ኦሊምፒክ ካገኘቻቸው 11 ሜዳሊያዎች ስድስቱ በጥቁር አፍሮ አሜሪካዊያን አትሌቶች፣ በተለይም አራቱ የወርቅ ሜዳሊያዎች በጄሲ ኦውንስ የተገኙ ናቸው፡፡

የድሉ ሜዳሊያ መሰጠት ሲጀመርም አንድ ልብን የሚነካ ነገር ይሆናል፡፡ በዘረኝነት ልቡ የደነደነው አዶልፍ ሂትለር ስቴዲየሙን ለቆ ወጣ፡፡ የጥቁር ሰው እጅ አልጨብጥም፣ የድሉን ሜዳሊያም ከጥቁር ሰው አንገት አላጠልቅም ነበር ምክንያቱ፡፡

ጄሲ ከታሪካዊ ድሉ በኋላም ወደ ሀገሩ አሜሪካ ሲመለስ በኋይት ሃውስ አቀባበል ቢደረግለትም የወቅቱ ፕሬዚዳንት ሮዝቤልት እንደ ሂትለር ሁሉ ሊጨብጡት እጃቸውን አልዘረጉለትም። ከኦሊምፒክ ድሉ መልስ ሌላው ቢቀር ዝነኝነቱ እንኳን ሥራ አላስገኘለትም። ነደጅ ማደያ ውስጥ ሥራ ያገኘው ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ነው። የእንዲህ አይነቱ አበሳ መብዛት ምክንያቱ ዘረኝነት በአሜሪካ ምድር ያለ ቅጥ መስፋፋቱ ነበር።

አፍሪካ አሜሪካዊው ኦውንስ ከ32 ዓመቱ ጀምሮ ለ35 ዓመታት ያህል ሲጋራ ያለማቋረጥ አጭሷል። ይህም በደረሰበት በደል የብስጭቱ ውጤት እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ተናግረዋል። ይህ ግን የጎዳው ራሱን ነበርና በመጨረሻም በሳንባ ካንሰር ሲሰቃይ ቆይቶ እኤአ በ1980 ይህችን ዓለም ተሰናብቷል። ከዓመታት በኋላም የጀግና ሃውልት ቆሞለታል።

ጄሲ እንደ ሠራው ታሪክ የሚመጥነውን ህይወት ሳይኖር ቢሞትም በስፖርቱ ዓለም የሠራው ታሪክ ህያው ሆኖ ዛሬም ድረስ ይወደሳል።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You