በሕዝቦች መካከል የሚኖር መልካም ግንኙነት ለሰላም፤ ጠንካራ የሥራ ባህል ደግሞ ለልማት ጉልህ አስተዋጽዖ አለው። እነዚህ በአብሮነት ሰላምን፣ በትብብር ልማትን የሚያመጣ የዜጎች መስተጋብር ደግሞ፣ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና የማይተካ ሚና አለው። ምክንያቱም፣ ልማት ከትጋት፤ ሰላምም ከፍቅርና መተሳሰብ ይወለዳሉና።
ዛሬም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ይሄንኑ አብዝተው ይሻሉ። ኢትዮጵያ የልጆቿን አብሮነት ትሻለች። ከአብሮነታቸው ደግሞ በፍቅርና መተሳሰብ የሚገነባ ሰላምን፤ ከትብብርና በትጋት የሚሳለጥ ልማትን፤ እነዚህ አብሮነትና ትጋት የሚወልዷቸውን ሰላምና ልማት ለሁለንተናዊ የሕዝብም፣ የሀገርም ብልጽግና አቅም አድርጎ መጠቀምን ትናፍቃለች።
በዚህ ረገድ፣ አንድ ሀገርና ሕዝብ ትናንት አለው። ዛሬ ደግሞ በእጁ ነው፤ ነገም የተስፋ መንገዱ ነው። እነዚህን ትናንቶች፣ ዛሬውንና ነገውን አሰናስሎ በመልካም ገጻቸው ጥቅም እንዲሰጡ ከተደረገ ያማረ ውጤት አላቸው። ካልሆነ ግን በተቃራኒው የንትርክ፣ የግጭትና የመነጣጠል ዕጣ ፈንታን ይደቅናሉ።
እኛ ኢትዮጵያውያንም ትናንቶቻችን በመልካምም፣ መልካም ባልሆኑም ሁነቶች የተሞሉ ናቸው። እነዚህ ሁነቶች ታዲያ ለዛሬው ማንነታችንና ለነገው ጉዟችን አቅምም፣ ሸክምም ሊሆኑም የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ፣ ላለፉት ሦስትና አራት አስርት ዓመታት፣ የእነዚህን የታሪክ ሁነቶች ክፉ ገጾች ብቻ በማስተጋባት በሕዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር፤ ቂምና ቁርሾ ሥር እንዲሰድድ የሚያደርጉ አካሄዶች ነበሩ።
በዚህም ኢትዮጵያውያን በበዳይነትና በተበዳይነት ስሜት ውስጥ እንዲገቡ፤ ይሄ ስሜት ደግሞ ለቂምና በቀል እንዲያዘጋጃቸው፤ በሂደትም እርስ በእርስ ወደ ግጭትና መነጣጠል እንዲገቡ የሚያደርጉ በርካታ አካሄዶች ነበሩ። ችግሩ በታሰበው ልክ ባይሆንም፣ መጠራጠርና መገፋፋቱ፤ መጋጨትና ለበቀል መነሳሳቱ ግን አልፎ አልፎ ታይቷል።
ዛሬም ድረስ ያልተሻገርነው ብሔርን፣ ሃይማኖትና ሌላም ማንነትን ማዕከል ያደረጉ ግጭትና መገፋፋቶች የዚህ አብነቶች ናቸው። እነዚህ ክስተቶች ደግሞ ሕዝቦች በጠንካራ መተማመን ላይ የተመሠረተ አብሮነታቸው እንዲፈተን፤ በፍቅርና ወንድማማችነት ስሜት ለይቅርታ የተገዛ ልባቸው እንዲሻክር፤ ብሎም ለጋራ ሀገራቸውና አብሮነታቸው የሚበጅ ትብብር ፈጥረው ልማታቸው ላይ እንዳያተኩሩ፤ አቅማቸውንም ከልማት ይልቅ ለግጭትና ጦርነት እንዲያውሉ የሚያስገድዱ ሁነቶችና ሁኔታዎችም ተፈጥረዋል።
እነዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በኅብር ደምቀው የሚገለጡባቸው የአብሮነት አውዶቻቸው እንዲደበዝዙ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ፤ ሰላም እንዲርቃቸው፣ ልማታቸው እንዲደናቀፍና የታሰበው ብልጽግና እውን እንዳይሆን ታስቦ በውስጥም በውጪም እኩያን የሚፈጸም ተግባር ነው። በመሆኑም ይሄን ሁኔታ መቀየር እና ኢትዮጵያውያን መተማመን ላይ የተመሠረተ አብሮነታቸው፤ በአብሮነት በጠነከረ ክንዳቸው እውን ለሚሆን ልማታቸው፤ በፍቅርና ይቅርታ ለሚጸናው ሰላማቸው እንዲተጉ፤ በዚህም ሁለንተናዊ ብልጽግናቸውን እውን እንዲያደርጉ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ መሥራት ይጠበቃል።
በዚህ ረገድ ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ ተግባራት መልካም የሚባሉ ናቸው። ምክንያቱም ከለውጡ ማግስት አንስቶ መንግሥት በሕዝቦች መካከል መተማመን፣ በኅብር የደመቀ አብሮነት፣ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ነድፎ እየሠራ ይገኛል።
ለምሳሌ፣ ለዜጎች ጥያቄ ምላሽ የመስጠት አካሄዱ ለዓመታት ተነፍጎ የቆየውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መልሷል። በዚህም አዳዲስ የክልል፣ የዞንና ወረዳዎች ጭምር አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል። የማንነት ጥያቄዎችና የወሰን ይገባኛል ቅሬታዎችም በውይይትና በምክክር ታግዘው በሕግ አግባብ እልባት እንዲያገኙም እየተሠራ ነው።
ከግንዛቤ ክፍተትም ይሁን ከራስ ፍላጎት አንጻር ብቻ ታይተው የተፈጠሩ ግጭቶች፣ እየታዩ ያሉ አለመረጋጋቶችም በውይይት እንዲፈቱ ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል። ዜጎች ያለፈ ታሪክ የግጭት ምክንያት እንዳይሆኗቸው ለማድረግም ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲያደርጉና ችግሮችን በይቅርታ ተሻግረው ነጋቸውን አብረው እንዲራመዱ ለማድረግም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል።
ከዚህ በተጓዳኝ እዚህም እዚያም የሚታዩ አለመረጋጋቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማዕከል ያደረጉ ችግሮችን ለመፍታት፤ በየክልል ከተሞች የሕዝብ ውይይቶች ተካሂደዋል፤ እየተካሄዱም ይገኛል። ይሄ ደግሞ ሕዝቡ ምን ይፈልጋል፤ ምንስ ሊደረግለት ይገባል፤ በምን አግባብስ ኃላፊነቱን ሊወጣ ያስፈልጋል፤… የሚሉ አንኳር ነጥቦችን ለመለየት አስችሏል።
ከሰሞኑም ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ዜጎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት ውይይት ሲያደርጉ እየታየ ነው። በዚህ ረገድ የአማራ ክልል ተወካዮች እና የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ከሁሉም ዞኖች ተውጣጥተው መምከራቸው ይታወሳል። ይሄ ደግሞ መንግሥት በየደረጃው የሕዝቡን ጥያቄ አድምጦ ለመመለስ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ጅምሩም ሕዝቦች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸው እና መጠራጠሮቻቸው እንዲጠሩላቸው የሚያደርግ ነው።
በዚህ መልኩ የሕዝቦችን ቅሬታ አድምጦ መፍታት ሲቻል ደግሞ፤ መተማመን የተሞላበት ትብብር ይፈጠራል። በመተማመን ውስጥ የሚፈጠር ትብብር ደግሞ በጋራ ሠርቶ መልማትን፤ በፍቅር ተሳስሮ ለሰላም መቆምን ያጎለብታል። በዚህ መልኩ የሕዝቦች በመተማመን አብሮ መቆም፤ አብሮ በመቆም ልማትና ሰላምን እውን ማድረግ ሲቻል፤ ሀገር እንደ ሀገር የታሰበውን ሁለንተናዊ ልማትና ብልጽግና እውን ማድረግ ይቻላል። በመሆኑም ለሀገር ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን መሆን መሠረት ለሆኑን ሰላም፣ ልማትና የሕዝቦች አብሮነት ያለ እረፍት መሥራት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም