የአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከአራት ዓመት በኋላ ነገ ይካሄዳል

የአፍሪካ ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ነገ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ አዘጋጅነት ይካሄዳል፡፡ ከአራት ዓመታት መቋረጥ በኋላ ዘንድሮ ለ6ኛ ጊዜ ለሚደረገው ውድድር ቱኒዝያ መሰናዶዋን አጠናቃ ባለፉት ቀናት እንግዶቿን ተቀብላለች፡፡ በዚህ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚካፈሉ ሲሆን፤ በመጪው ወር መጨረሻ ለሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ከወዲሁ ራሳቸውን የሚፈትሹበት ፉክክር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን ውድድር ጨምሮ ለዓለም አቀፉ የሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና የሚወክሏትን አትሌቶች ባለፈው ጥር/2016 ዓም በተካሄደው የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ኢንተርናሽናል ውድድር ላይ መርጣለች፡፡ በዚህም መሠረት በ14 ሴቶች በ14 ወንዶች በአጠቃላይ በ28 አትሌቶች ትወከላለች ። በዚህ ውድድር ላይም ከ20 ዓመት በታች በሴቶች 6ኪሎ ሜትር እና በወንዶች 8ኪሎ ሜትር፣ በአዋቂዎች 10ኪሎ ሜትር ወንድና ሴት እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ አትሌቶቿን የምታሳትፍ ይሆናል፡፡

ለዚህም ቡድኑ ዝግጅቱን ከየካቲት 8 ቀን 2016 ዓም አንስቶ ለገጣፎ ለገዳዲ በሚገኘው ስለሺ ስኅን ሆቴል ተሰባስቦ ሲያካሂድ ቆይቶ ከትናንት በስቲያ ሌሊት ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አቅንቷል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በለገጣፎ እንዲሁም በሱሉልታ አካባቢዎች ሲያደርግ የቆየውን ዝግጅት መጠናቀቅ ተከትሎ ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ የሽኝት መርሐ ግብር አድርጓል፡፡ በሽኝት መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ለብሔራዊ ቡድኑ ‹‹ሁላችሁም በመተጋገዝ፣ ለጋራ ድል በአንድነት ኢትዮጵያን የምትወክሉ አትሌቶቻችን፤ የምንወዳትን የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በማውለብለብ የበኩላችሁን እንድትወጡ አደራ›› በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

በኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተወካዮች እንዲሁም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትም በሽኝት መርሐግብሩ ላይ በመገኘት አትሌቶችን አበረታተዋል፡፡

በዚህ ውድድር ላይ የተካፈሉ አትሌቶች በዘንድሮው የጃንሜዳው አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ተሳትፈው ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆኑ፤ በመጪው ወር በሰርቢያ ቤልግሬድ በሚደረገው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ በድጋሚ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉም ይሆናል፡፡

በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚደረገው ይህ ውድድር በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ቢሆንም ላለፉት አራት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ እአአ በ1985 ለመጀመሪያ ጊዜ በኬንያ የተካሄደው ይህ ውድድር ከዚያ በኋላ መቀጠል ባለመቻሉ ለዓመታት ሳይካሄድ ቆይቷል፡፡ እአአ በ2011 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በድጋሚ ቢጀመርም በድጋሚ ተቋርጦ ዘንድሮ ዳግም ይካሄዳል፡፡

ኮንፌዴሬሽኑ በተለያዩ ችግሮች ሻምፒዮናውን በተከታታይ ለማዘጋጀት አዳጋች ቢሆንበትም እንደ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን በየዓመቱ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ጭምር የሚያሳትፍ የሀገር አቋራጭ ውድድሮችን ያከናውናሉ፡፡

ነገ ለስድስተኛ ጊዜ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ቱኒዚያ በምታዘጋጀው ሻምፒዮናም ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 ሃገራት ተሳታፊ ሲሆኑ፤ አዘጋጇን ሀገር ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ሊቢያ፣ ኬንያ፣ አንጎላ፣ ሲሼልስ፣ ላይቤሪያ፣ ኮንጎ፣ ኬፕቨርዴ እና ዑጋንዳ ተፎካካሪ ይሆናሉ፡፡ በርቀቱ ለረጅም ዓመታት ውጤታማ ሆነው የዘለቁት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ዘንድሮም ውጤታማ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ በተለይ በዚህ ርቀት ከአህጉር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዑጋንዳ አትሌቶች የተዘጋጁት ሜዳሊያዎች ባለቤት እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡ በዚህ ሻምፒዮና በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ኬንያ ቀዳሚ ስትሆን እአአ በ2018 ኢትዮጵያ በድብልቅ ሪሌ (ዱላ ቅብብል) አሸናፊ ነበረች፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You