ትናንትን በዛሬ መስታወት…

ሕይወት ፈርጀ ብዙ ገጽታዎች አሏት፤ መውጣት እንዳለ ሁሉ መውረድም ይኖራል፡፡ ከመውረድ ውስጥም በትጋት መውጣት ይቻላል፡፡ አግኝቶ ማጣት እንዳለ ሁሉ አጥቶም ይገኛል፡ ፡ ይህ የሕይወት እውነታ ነው፤ በጥቂቶች የህይወት መውጣትና መውረዶች ውስጥ ብዙዎች ይማራሉ፡፡ የህይወትን ፈተናዎችም ያውቃሉ፡፡ በከፍታ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እንዲህም ይኖራል እንዴ?›› ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ፡፡ ለተቸገሩት ያዝናሉ፤ ካላቸው ቀንሰው የሌሎችን ችግር ይካፈላሉ፤ በተጨማሪም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ ከችግር ጋር ተላምዶ ከመኖር ይልቅ ለመፍትሄ የሚታትሩትንም ያበረታታሉ፡፡ በመሆኑም ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ብለን በከፈትነው አምዳችን ህይወትን በየፈርጁ ታስተውሉበት፤¸አስተውላችሁም ትማሩበት ዘንድ ጋበዝናችሁ፡፡ ለአስተያየቶቻችሁ፤ ለመሰል ታሪኮች ጥቆማችሁ እንዲሁም ለድጋፋችሁ የዝግጅት ክፍላችን አድራሻ ትጠቀሙ ዘንድ ጋበዝናችሁ፡፡

ወጣቷ ቆንጆ ዓይነ ግቡ ናት፡፡ ያዩዋት ሁሉ የሚወዷት፣ ለቁምነገር፣ የሚያስቧት ውብ፡፡ እሷ ከእኩዮቿ ትለያለች፡፡ ፍጥነት ቅልጥፍናዋ፣ ጨዋታ ለዛዋ ከብዙዎች ያግባባታል። ይህ ማንነቷ በልጅነት ዕድሜዋ ትዳር እንድትይዝ ጎጆ እንድትወጣ ምክንያት ሆኗል፡፡ ትዳሯ ብዙ አልዘለቀም፡፡ በፍቺ ተለያይታ ብቸኛ ሆነች፡፡፡

ካሠች አደራ ትግራይ ውቅሮ ላይ ተወልዳ አድጋለች። በረጅሙ ዞማ ፀጉሯ በውብ መልኳና ቁመናዋ ብዙዎች ያደንቋታል፡፡ ታላቅ እህቷ ባሕር ማዶ ይመላለሱ ነበርና ለሠለጠነው ዓለም ወሬ ጆሮዋ አዲስ አይደለም፡፡ ባጋጣሚ የካሠች ታላቅ እህት በድንገት ሀገራቸውን ትተው፣ ወዳጅ ዘመድ ተሰናብተው ወደ ጅዳ በረሩ ፡፡

እህት አካሄዳቸው ለመመለስ አይደለም፡፡ ሙሉ ቤት ንብረታቸውን ለካሠች ሰጥተዋል፡፡ ቤት ጠባቂዋ ወጣት የዛኔ ከባሏ ተለያይታ ብቻዋን ነበረች፡፡ ይህ ግዜ በራሷ የምታዝበት፣ በሀሳቧ የምትጓዝበት ነፃነቷ ሆኗል፡፡ ከእጇ አንዳች ያጣችው የለም፡፡ በቂ ገንዘብና ትልቅ መኖሪያ ቤት የራሷ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ልቧ አርቆ ያስባል፡፡ ባታጣ ባትነጣም ባለችበት መቀመጥን አትሻም፡፡ ብቸኝነት ብዙ እያሳሰበ አርቆ ይመልሳታል፡፡

አንድ ሰሞን ባልና ሚስት ጎረቤቶቿ አዲስ አበባ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን ሰማች፡፡ ይህኔ ብዙ አሳቢዋ ካሠች የልቧ ሞላ፡፡ ለጥንዶቹ አብራቸው መጓዝ እንደምትፈልግ ነገረቻቸው፡፡ ባልና ሚስት በውሳኔዋ ቢገረሙም አልከለከሏትም፡፡ ከእነሱ ጋር እንድትሄድ ፈቀዱላት፡፡ አልዘገየችም፡፡ ፈጥና ጓዟን አነሳች፣ ቤቷን ዘግታ ቀልጠፍ ብላ ተከተለቻቸው፡፡

የውቅሮዋ ቆንጆ በአዲስ አበባ

ግዜው የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ነው፡፡ በወቅቱ ጥቂት በሚባሉት እጅ ብቻ ገንዘብና ንብረት ይገኛል፡፡ ሥልጣኔና፣ ዘመናዊነት እምብዛም ባልነበረበት በዛ ዘመን በርካቶች ለባሕልና ወግ ይገዛሉ፡፡ ጨዋነት፣ ሰው አክባሪነት ይሉት ጉዳይ ትርጉሙ ሰፊ ነው፡፡ በተለይ ሴቶች የዚህ እውነት ማሳያና መገለጫዎች ናቸው፡፡

እግሯ አዲስ አበባ የረገጠው ካሠች ከተማውን እንዳየች ተማረከች፡፡ ሀገሩን ወደደችው፡፡ ውላ ስታድር እንግድነቷ ተረሳ፡፡ ከብዙዎች ተግባባች፡፡ ይህኔ ፈጣን አዕምሮዋ አርቆ እያሰበ ብዙ አቀደች፡፡ አሁን በዚህ ስፍራ ራሷን የሚቀይር ሥራ መገኘት ሕልሟ ሆኗል፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግ ዕንቅልፍ የላትም፡፡

አሁን ካሠች ካገሯ ያመጧት ሰዎች ከአንድ ሆቴል ሥራ አስገብተዋታል፡፡ ይህ አጋጣሚ የኑሮ መንገዷን እንድትለይ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡ ጠንካራዋ ወጣት የሥራን ታላቅነት፣ ገንዘብ የማግኛውን ዘዴ አላጣችውም፡፡ ውሎዋ፣ ብዙ ቢያሳያት ስለነገዋ አሰበች፡፡ ራሷን ችላ የምትሠራበትን አጋጣሚ እያቀደች የገንዘብ አቅም ያዘች፡፡

ራስን ፍለጋ…

ከጊዜያት በኋላ ካሠች ከሌሎች ዘንድ መቀጠር ይሉትን ትታ የራሷን ሥራ ጀመረች፡፡ ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ አካባቢ የከፈተችው ቤት የብዙዎችን ዓይን ሳበ፡፡ በ‹‹መቀሌ›› በተባለው ቡናቤቷ በርካታ ደንበኞች ተመላለሱ፡፡ ገበያዋ ደራ፡፡ ከራሷ አልፋ ለሌሎች እንጀራ የከፈተችው ሴት በስሯ በርካታ ሠራተኞች ማስተዳደር ያዘች፡፡ ዓመታትን የዘለቀው ሥራዋ ከብዙዎች አስተዋውቆ አግባባት፣ ታዋቂ ሆነች፡፡ ጥሪት ቋጥራ በቂ ሀብት አፈራች፡፡

ውሎ አድሮ ሥራዋን የሚፈትን አጋጣሚ አላጣትም። ዓመታትን የሠራችበት አካባቢ ሊፈርስ መሆኑን ሰማች፡፡ ካሠች ለዚህ ችግር መፍትሔ አላጣችም፡፡ ስፍራውን ለቃ በሌላ ቦታ ተገኘች፡፡ ሥራ የጀመረችበት ቤት እንደ ቀድሞው የኪራይ አልነበረም፡፡ በጥሩ ዋጋ የገዛችው ታዋቂ ሆቴል እንጂ፡፡

‹‹ማሞ ካቻ›› ከተባሉት ታዋቂ ሰው የተገዛው ባለፎቁ ‹‹ሳሙኤል ሆቴል›› በአጭር ፍጥነት ሥራውን ጀመረ። ሆቴሉ ሰፊ መስተንግዶን ጨምሮ በርካታ ቤርጎዎች ነበሩት። መሐል ከተማ ላይ መሆኑ ደንበኞችን አላሳጣም። ዕለት በዕለት ገበያው ደራ፣ ሠራተኞች፣ ከላይ ታች የሚተራመሱበት ሆቴል ለውቧ ካሠች የሀብት ምንጭ ሊሆን አልዘገየም፡፡

ካሠች አሁን ታዋቂ ባለ ሆቴል ሆናለች፡፡ ‹‹ፔጆ›› መኪናዋን ይዛ ‹‹ሽር›› ስትል አላፊ አግዳሚው ይማረክባታል። ቅላጼዋ ውበት አለው፡፡ ትግርኛን ከአማርኛ ቀላቅላ ስታወራ አንደበቷ ይጣፍጣል፡፡ በዘመኑ በተለይ በሴቶች ዘንድ ያልተለመደው ሀብት ማፍራት በእሷ ዘንድ መሆኑ ለብዙዎች እያስደነቀ ነው፡፡ ቅልፍጥናዋ ይለያል፡፡ ያሰበችውን ከማድረግ ወደ ኋላ አትልም፡፡

ለሥራዋ ከወንዶች በላይ የምትሮጠው ካሠች በወቅቱ በገበያው የሚታወቀውን የሜታ ቢራ በገፍ በማስገባት የሚያህላት አልነበረም፡፡ በአካባቢዋ የሚፎካከሯትን እነ ‹‹አሥመራ ሆቴልን›› ልቃ ለመገኘት መኪናዋ ጉልበቷ ነበረች። ሁሌም የውስኪ አይነትና ልዩ መጠጦች ከእሷ ሆቴል ተጠይቆ አይጠፋም፡፡ ‹‹ሁሉ በእጇ ሁሉ በደጇ›› ነው፡፡

ኑሮዋ መሐል ቦሌ በገዛችው ቪላ ቤት ሆኗል፡ ካሠች ሰው ወዳድና እንግዳ ተቀባይ ናት፡፡ በየበዓላቱ ካህናትን ሰብስባ ታበላለች፤ ሁሌም ሰፊ እጇቿ ለመስጠት አይሰሰቱም፡፡ ድሆችን ታስባለች፣ ላጡ ለነጡት ትቸራለች።

እረፍት አልባዋ ሴት ዛሬን አሸንፋ ከነገ ለመድረስ ሩጫዋ ፈጣን ነው፡፡ በሽንፈታቸው ሰበብ የሚያነውሯትን ሰምታቸው አታውቅም፡፡ ያለ እረፍት በጥንካሬ ትተጋለች። በሆቴሏ ምግብ መጠጡ ይሸጣል፡፡ የቤርጎው አልጋ ይከራያል፡፡ እንግዶች፣ ደንበኞች፣ ሠራተኞች ሲጋፉ የሚውሉበት ቦታ ታዋቂነቱ ጨምሯል፡፡

ካሠች የቦሌውን ቪላ አከራይታለች፡፡ አሁንም የሆቴል ሩጫዋ ቀጥሏል፡፡ የእሷ ኑሮ የግሏ ብቻ አይደለም። በርካታ ሠራተኞች ከእጇ በረከት ያገኛሉ፡፡ ቤቷ የታዋቂ ሰዎች መገኛ፣ የወጣት አዋቂው መናኸሪያ ነው፡፡ አሁን ካሠች በ1960 ዎቹ በአዲስ አበባ ከታዩት ብርቱ ሴቶች፣ ከታወቁ ባለ ሆቴሎች መሐል አንዷ ሆናለች፡፡ ወጣትነቷ ከቁንጅናዋ ተዳምሮ አድናቆት ይጎርፍላታል፡፡

የአብዮቱ ፍንዳታ…

እነሆ! በመላው ሀገሪቱ የለውጡ ነፋስ ተዳርሷል። ንጉሡን ከዙፋናቸው ለማውረድ ያሰቡ ኃይሎች ጦር እየሰበቁ ነው ፡፡ በገጠር ከተማው የአብዮቱ ክንዶች በርትተዋል፡፡ ‹‹መሬት ላራሹ›› ያሉ፣ ‹‹መብታችን ይከበር›› የሚሉ፣ በደል ግፉ ይብቃን ከሚሉት ጋር ተዳምረው የለውጡ አካል ሆነዋል፡፡ ይህ ግዜ ለብዙዎች የልባቸውን ሀሳብ ሞልቷል፡፡ ለበርካቶች ማንነትም የበዛ ስጋት ሆኗል፡፡

ካሠች አሁንም ሥራ ላይ ናት፡፡ ከአብዮተኞች፣ ከለውጥ ፈላጊዎች ወገን አይደለችም፡፡ ሕይወቷ እንደቀድሞው ቀጥሏል፡፡ ቪላ ቤቷ እንደተከራየ ነው፡፡ ሆቴሏ ይሠራል፣ በመኪናዋ ካሠች ደርሳ፣ ካሰበችበት ትውላለች፡፡ ውሎ አድሮ ግን ሁኔታዎች እንደነበሩ አልቀጠሉም፡፡ እሷን በተለየ ዓይን የሚቃኝዋት በዙ፡፡ ቤቷን የሚፈትሹ በጥያቄ የሚያዋክቧት በረከቱ ፡፡

ከቀናት በአንዱ ካሠች ‹‹ለጥያቄ ትፈለጊያለሽ›› በሚል ከቤቷ ተወሰደች፡፡ የትግራይ ተወላጅ በመሆኗ በወቅቱ አጠራር /ለወንበዴዎች/ የስንቅ ድጋፍ እያደረገች ስለመሆኑ ተነገራት፡፡ የተወነጀለችበት ክስ ሐሰት መሆኑን ልታስረዳ ሞከረች፡፡ ሰሚ አላገኘችም፡፡

ጠያቂዎቿ ደርግን ለሚዋጉ ወንበዴዎች ድጋፍ ስለማድረጓና ማስረጃ ስለመገኘቱ አረጋገጡላት፡፡ ካሠች አቅም ጉልበት አጣች፣ የልቧን እውነት የውስጧን ሐቅ ለማሳየት ቃል አጠራት፡፡ መርማሪዎቹ አላዘኑላትም፡፡ እጇን ይዘው ወደ ወህኒ ወረወሯት፡፡ የአብዮቱ ለውጥ ያመጣው አጋጣሚ የቆንጆዋን፣ የባለሆቴሏን ሀብታም ሴት ታሪክ በአንዴ ቀያየረው፡፡

ካሠች ወህኒ ወርዳ ለእስር ስትዳረግ ስላፈራችው ሀብት ንብረት ያሰበ፣ የተጨነቀ አልነበረም፡፡ እሷም ብትሆን በቅርብ ለምታውቃቸው ሰዎች አደራ ከማለት ሌላ ምርጫ አልነበራትም፡፡ መቼ እንደምትፈታ ባታውቅም በአሳሪዎቿ የተፈረደባትን እስር ል ትጀምረው ‹‹ከርቸሌ›› ወርዳለ ች፡፡

ሕይወት በከርቸሌ …

ካሠች ሳታስበው የገባችበት የእስር ሕይወት ታሪኳን ለውጧል፡፡ ትናንት ያለ ድካም የምትሮጠው ሴት ዛሬ ከዓላማ አልባ ኑሮ ላይ ቆማለች፡፡ ያለ ፍርድ የታሰረችበት ክስ ከሌሎች ጋር ደምሯታል፡፡ አብረዋት የንጉሣውያን ቤተሰቦች ታስረዋል፡፡

አንዳንዴ ከቤተመንግሥት ሰዎች ጋር መሆኗን ስታስብ በራሷ ትጽናናለች፡፡ ትካዜ ኃዘኗን ረስታ ‹‹ተመስገን›› ትላለች፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የትናንቱን ከዛሬ አወዳድራ መጨረሻዋ ይናፍቃታል፡፡ የእስር ጊዜው በጨመረ ቁጥር በትካዜ ትዋጣለች፡፡ ያለፈችበት መንገድ የሰነቀችው ዓላማ፣ ያገኘችው ስኬት ሁሉ ውል ይላታል፡፡ አሁን ግን በዚህ ጎዳና ላይ አይደለችም፡፡ ታሪኳ ተቀይሯል፡፡ ሕይወቷ ተለውጧል።

ከካሠች ጋር የጃንሆይ ልጆች፣ የአልጋወራሽ ልዑል መኮንን ባለቤት፣ የሚኒስትሮቹ ሚስቶችና የታዋቂ ሰዎች ቤተሰቦች ታስረዋል፡፡ የጄኔራል አማን አምዶም እህት ወይዘሮ ጽዮንን ጨምሮ የራስ ሥዩም ሚስትም ከወህኒው ይገኛሉ፡፡ በእስርቤቱ የነበረው መተሳሰብ ይለያል፡፡ አንዱ ሌላውን የሚደግፈው በሙሉ ቅንነትና ፈቃደኝነት ነበር፡፡

ካሠች ሀብት ንብረቷን ትታ ወህኒ መግባቷን የሰሙት ታላቅ እህት ከነበሩበት ሀገር ተመልሰዋል፡፡ አመጣጣቸው ስለ እህታቸው ነበርና ያሻትን፣ የጎደላትን እያሟሉ ከጎኗ ቆመዋል፡፡ በወቅቱ ካሠች የእህቷን መመለሰ ባየች ግዜ ከመደንገጥ በላይ አዝናለች፡፡ ‹‹ለምን መጣሽ›› ስትልም ሞግታለች፡፡ እሳቸው ግን እንደ ልጅ ያሳደጓት እናት ነበሩና ድካማቸውን አላዩም፡፡

እህት ስለ ካሠች ፍቅር የእጃቸውን ጥሪት አሟጠዋል። ወርቃቸውን ሳይቀር ሸጠዋል፡፡ ከእሳቸው በቀር ስንቅ የሚያመላልስ የቅርብ ሰው አልነበረም፡፡ ከካሠች ጋር ከሀያ ዓመት በላይ የኖረች ሠራተኛዋም አልካደቻትም፡፡

ካሠች የወህኒ ቆይታዋ ብዙ አሳይቷታል፡፡ የደግ ሰዎችን ውለታ አትረሳም፡፡ የክፉዎቹን ድርጊትም አዕምሮዋ መዝግቧል፡፡ ቤቷን በውክልና የያዘው አንድ አጎቷ ከታሰረች በኋላ በገንዘቧ አዟል፣ በሀብት ንብረቷ ተንቀባሯል፡፡ ለእሷ ቁራሽ ለማቀበል ግን ልቡ አይፈቅድም፡፡ ታማኟ ሠራተኛ ከእሱ እየተናጠቀች፣ ከሰዎች ዱቄት እየለመነች የዕለት ጉርሷን ታቀብላታለች ፡፡

ሰንሰለቱ ሲበጠስ …

ጊዜያት እንደዋዛ አልፈው ሰባት የእስር ዓመታት አንድ ሁለት ብለው ተቆጠሩ፡፡ ሰባቱ ፈታኝ ዓመታት፡፡ የሕይወት የኋልዮሽ ጉዞ ፣ የኑሮ ርምጃ እንቅፋት፣ የጽኑ ዓላማ ስብራት። እነዚህ እውነታዎች በጠንካራዋ ካሠች ማንነት ውስጥ ሲመላለሱ ኖረዋል፡፡ አሁን የትናንቷ ጠንካራ ካሠች ቆማ አትታይም፡፡ ዛሬ ላይ ብዙ ታሪኮች ተቀይረዋል፡፡ የስኬት የሕልም ድልድዮቿ ተሰባብረዋል፡፡

ከሰባት ዓመታት የአስር ቆይታ በኋላ ካሠችና አብረዋት የታሰሩት አንዳንዶች ከወህኒ ቤት በነፃ ተሰናበቱ፡፡ እሷ በተፈታች ግዜ ውስጧ በድብልቅልቅ ስሜት ተዋጠ፡፡ ዛሬ ሌላ ሰው ሆናለች፡፡ እንደቀድሞው በራስ የመተማመን ማንነቷ ከእሷ የለም፡፡ ያለፍርድ ዓመታትን የገፋችው ሴት ግን ‹‹ነፃ ›› ተብላለች፡፡

ካሠች ከእስር መፈታቷ በኋላ ወደ ትናንቱ ሆቴሏ ተመለሰች፡፡ ግቢዋ በደረሰች ግዜ ‹‹እንኳን ተፈታሽ›› ያሉ ወዳጆቿ በአክብሮት ተቀበሏት፡፡ ቀናት አልፈው ቀናት ተተኩ፡፡ እንግዳው ጋብ ሲል ወደ ጓዳዋ ገብታ ያለውን ከጎደለው ቃኘች፡፡ አጎቷን አስጠርታም ስለሰጠችው አደራ ጠየቀች፡፡ ያገኘችው ምላሽ አስደንጋጭ ነበር፡፡

አጎት ለሰባት ዓመታት በሆቴሉ ገቢ ሲጠቀም ኖሯል፡፡ የሚጠበቀውን ግብር ግን በወጉ አልከፈለም፡፡ በየአጋጣሚው ቤቱን በብድር እያስያዘ ዕዳ ሲያስቆጥርበት ነበር፡፡ ይህን ሁሉ የማታውቀው ካሠች ከቤቷ ተመልሳለች። ብዙ ያልዳኑ ችግሮቿ ከፊቷ ናቸው፡፡ እነሱን በወጉ አክሞ ነፍስ ለመዝራት አጋር ትሻለች፡፡ ከሰባት ዓመታት በኋላ ሕይወትን በአዲስ መጀምሩ ይከብዳል፡፡ ብዙ የጠፉ፣ የተበላሹ፣ የጎደሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ካሠች ያለፉትን ዓመታት በወህኒ ማሳለፏን ለበጎ ቆጥራዋለች፡፡ ዘመኑ ቀይ ሽብር የተፋፋመበት ነበርና አጋጣሚውን ለማምለጥ አግዟታል፡፡

ካሠች ጊዜ ወስዳ ቤት ግቢዋን ቃኘች፡፡ ቤቱ እንደፊቱ ሙሉ አይደለም፡፡ ብዙ ሀብቷ ባክኗል፡፡ የሞላችው ጎድሏል፡፡ የሚያምረው ሕንጻ አርጅቶ ተጎሳቁሏል፡፡ ይህን ስታይ ውስጧ አዘነ፡፡ በላብ በወዟ ያፈራችው ንብረት ባክኖ መቅረቱ አስከፋት፡፡ በአደራ የተቀበለው አጎት እንደቃሉ አልተገኘም፡፡ ይህ ሁሉ እውነት ለካሠች ከባድ ሆኖ ከረመ።

ሌላው መርዶ…

አንድ ቀን የሀገር ውስጥ ገቢ ሰዎች ከሆቴሏ ደረሱ። አመጣጣቸው ለበጎ አልሆነም፡፡ ሆቴሉ የዓመታት ዕዳ እንዳለበት ዘርዝረው ነገሯት፡፡ የሰማችውን አላመነችም። በወቅቱ ዕዳዋን ከፍላ ከችግሩ ማምለጥ አልተቻላትም። ዓይኗ እያየ ብዙ የለፋችበት ፣ልጅነቷን የከፈለችበት ሆቴሏ በሐራጅ ተሸጠ፡፡

አሁን የካሠች ታሪክ ተቀይሯል፡፡ ከእስር መፈታት ማግስት የሆነባትን ሁሉ ማመን ባትችልም ተቀብላዋለች። አሳዳጊ ጠያቂ እህቷን ቀብራለች፡፡ አግኝታ አጥታለች፡፡ ከዚህ በኋላ ያላት ተስፋ መሐል ቦሌ ላይ የሠራችው ቪላ ብቻ ነው፡፡ ይህን ቤት ከመታሰሯ በፊት ለአንዲት ሴት አከራይተዋለች፡፡

አካባቢው ስትደርስ የተመለከቷት ሁሉ ተገረሙ፡፡ አብዛኛው መሞቷን እንጂ በሕይወት መኖሯን አያውቅም፡ ከግቢው ደርሳ ወይዘሮዋን አናገረች፡፡ ቤቱን ልትኖርበት መሆኑን ተናግራም እንዲለቀቅላት በትህትና ጠየቀች፡፡ ይህን የሰማችው ሴት የካሠችን ቃል አልተቀበለችም፡፡ ቤቱ የእሷ ባለመሆኑ እንደማትለቅ ነገረቻት፡፡

ካሠች ለምን? ማለቷ አልቀረም፡፡ ተከራይዋ ቤቱን የሰጣት ደርግ እንጂ እሷ እንዳልሆነች ተናግራ ከደጅ መለሰቻት፡፡ ሴትየዋ በሽማግሌ ተጠየቀች፡፡ ‹‹እምቢኝ አሻፈረኝ›› አለች፡፡ የነበረው እንዳልነበረ የሆነባት ሴት ቤቷን ለማስመለስ ጠበቃ አቁማ ፍርድቤት ተመላለሰች። ዓመታት የፈጀው ክርክር የቤቱን ባለቤትነት ለካሠች ሲወስን ንብረቷን ተረከበች፡፡ ቤቱ በትናንት አቋሙ አይደለም፡፡ ብዙ ጎድሎበታል፡፡ እንዲያም ሆኖ ዘመናዊነቱ ዓይን ይስባል፡፡

በወቅቱ ካሠችን የሚዞሯት አንዳንዶች ቤቱን ብትሸጠው እንደምትጠቀም አሳመኗት፡፡ ‹‹እምቢ›› አላለችም፡፡ የወደፊቱን አስባ ለገበያ አቀረበችው፡፡ ግዜው ደርሶ ሲሸጥ ግን አንዲት ሳንቲም ከእጇ አልገባም። የቀረቧት የዋህነቷን አይተው አታለሏት፡፡ ከዚህ በኋላ በቀላሉ የማይነገሩ የችግር፣ የመከራ፣ የመራብ ዓመታት አለፉ፡፡

እማማ ካሠች…

የወደቁትን አንሱ የነዳያን መርጃ ማዕከል ተገኝቻለሁ። ዓይኖቼ አንዲት ቀጭን አዛውንት ላይ አርፏል። ልግባባቸው አልቸገረኝም፡፡ ሴትዬዋ ቀልጣፋና ንቁ ናቸው። ልብሳቸው ፀዓዳ ነው፡፡ በትግርኛ ቋንቋ የተዋዛው አንደበታቸው ይጣፍጣል፡፡ ዕድሜያቸው ዘጠና መሙላቱን ነግረውኛል። እማማ ካሠችን ጠጋ ብዬ አስተዋልኳቸው። ዕድሜ የተሻገረው ቁንጅናቸው አሻራው እንዳለ ነው፡፡ ጥርሶቻቸው በወጉ አልታዩኝም፡፡ በቦታው ስለመኖራቸው ተጠራጠርኩ፡፡

እማማ ካሠች እርጅና ተጭኗቸዋል፡፡ እግርና ወገባቸው ጤና ውሎ አያድርም፡፡ በዚህ ስፍራ የተገኙት ጧሪና ረዳት በማጣታቸው ነው፡፡ ያለፉባቸውን ክፉ ደግ አጋጣሚዎች በትዝታ ከማውሳት በቀር ፈጽሞ አያማርሩም፡፡ ፊታቸው ሳቅ ፈገግታ ሞልቶታል ፡፡

እማማ ሁሌም ፈጣሪንና ሰዎችን አመስጋኝ ናቸው። ሕይወት ማለት በእሳቸው ማንነት እንዲህ ተገልጧል። ካሠች ዝቅ ብሎ መነሳት፣ ከፍ ብሎ መውደቅ መኖሩን አሳይተውናል ፡፡ የትናንቷ ሀብታምና ቆንጆ ዝነኛ ባለታሪክ የዛሬዋ ተመጽዋች አዛውንት እማማ ካሠች አደራ ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You