ኢትዮጵያ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የቅርስ ሀብቶች በስፋት ከሚገኝባቸው ቀዳሚ ሀገራት ተርታ ትመደባለች። ይሁን እንጂ እነዚህን ሀብቶች በሚፈለገው መጠን የማስተዋወቅ፣ የማልማትና ከሀብቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አቅም አሁንም ድረስ እንዳልጎለበተ ይታመናል። ሀገሪቱ ለዓለም በኪነ ጥበብ፣ በባህል፣ በተፈጥሮ፣ በኪነ ሕንፃና ስነ ፅሁፍ እውቀት ያበረከተች መሆኗም እሙን ነው። ለዚህ እንደ ጥሩ ማሳያ የሚሆኑት ቀደም ያሉ የስልጣኔ አሻራዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ ለምድራችን የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ በቅርስነት ተመዝግበው የሚገኙ ባህላዊ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች፣ የስነ ፅሁፍ ውጤቶች፣ የዲሞክራሲ መገለጫዎችና ልዩ ልዩ እሴቶችን አበርክታለች። ሀገሪቷ ለመላው የሰው ልጆች ዛሬ ላይ የመድረስ ምክንያት እንደነበረች ህያው ምስክር የሆኑ ዛሬም በምሳሌነት የሚቀርቡ በርካታ ማስረጃዎችን ማንሳት ይቻላል።
ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነን ከትናንት በስቲያ በኦሮሞ ማህበረሰብ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የአባ ገዳ ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር መመልከት ይቻላል። የገዳ ሥርዓት በኦሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ የነፃነት፣ የመከባበር፣ ታላላቆችን የማድመጥ እንዲሁም ህግና ህግጋቶችን ሳይተላለፉ የማክበር መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ እሴት እንደሆነ ያመለክተናል። የዝግጅት ክፍላችንም ይህንን ዲሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር በስፍራው ተገኝቶ የተከታተለ ሲሆን ሥርዓቱ በምን መልክ እንደሚከወንና ያሉትን እሴቶች እንደሚከተለው ዳሰሳ አድርጎበታል።
የገዳ ሥርዓት- ዲሞክራሲያዊ ስልጣን ሽግግር
በኦሮሞ ባህል እና የታሪክ መሰረቶች ሲነሱ ሁሌም ገዳ እና የገዳ ሥርዓት አብሮት ይነሳል፡፡ በበርካቶች ዘንድ ገዳ እና ኦሮሙማ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ተብለውም ይታሰባሉ። ይህንንም በርካታ ምሁራንና የታሪክ አጥኚዎች በተለያየ አውድ ገልፀውታል፡፡ የገዳ ሥርዓት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ከሚደረግባቸውና በዓለማችን ከሚደነቁ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓቶች አንዱ መሆኑ ይገለፃል። በሥርዓቱ መሰረት የአንድ አባ ገዳ ስልጣን ዘመን በስምንት ዓመት የተገደበ ሲሆን፤ ለቀጣዩ አባ ገዳ ስልጣን የሚሰጠው ደግሞ በመመራረቅ ነው። አንዳንድ ምሁራንም የዘመናዊ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ በግሪክ ፈላስፎች ሳይታወቅ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲን ይተገብር ነበር፤ በፍልስፍናውም የቀደመ ነው ሲሉም ያሞካሹል፡፡
ሰሞኑንም የጉጂ አባ ገዳዎች ላለፉት ስምንት ዓመታት ያገለገሉትን አባ ገዳ ጂሎ ማንዶ ለአገልግሎታቸው አመስግኖ አባ ገዳ ጃርሶ ኡጎ ለጉጂ ኦሮሞዎች 75ኛው አባ ገዳ አድርጎ የ‹‹ባሊ›› ስልጣን ርክክብ አድርጓል፡፡ ይህም በስልጣን ሽግግሩ ከሐርሙፋ አባገዳ ወደ ሮበሌ አባ ገዳ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል ማለት ነው፡፡ በጉጂ ዞን አዶላ ከተማ አቅራቢያ ሚኤ ቦኮ አርዳ ጂላ በሚባለው ስፍራ በተከናወነው በዚህ መርሐ ግብር በርካታ ክንውኖችና ትዕይንቶችም ነበሩ፡፡
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑትና ለበርካታ ዓመታት የገዳ ሥርዓትን በተመለከተ ምርምር እያደረጉ ያሉት ደንቢ ቱርጬ እንደሚሉት፤ የገዳ ሥርዓቱ የኦሮሞ ሕዝብ የልብ ትርታ ሲሆን ዘመናትን ያሳለፈበት በመሆኑ ትልቅ ትርጉም ይሰጠዋል። ሰሞኑንም በ75ኛው የጉጂ አባ ገዳዎች የ‹‹ባሊ›› ስልጣን ርክክብ ላይ ያለው ሁነት ይህን ያሳያል፡፡ በሥርዓቱ መሰረት አንድ የጉጂ አባ ገዳ ከተመረጠ የስልጣን ዘመኑ በስምንት ዓመታት የተገደበ ነው፡፡ ይህ የተመረጠ አባ ገዳ ታዲያ አራቱን ዓመታት በመላው ጉጂ እየተንቀሳቀሰ ይመለከታል፣ በእኩል ዓይን ይዳኛል፣ ያስታርቃል፣ ስለ ገዳ ግንዛቤ ይፈጥራል፣ የተረከበውን የጉጂ ወሰን ያከብራል፤ ያስከብራል፡፡ ዋነኛ ተልዕኮውም ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ነው፡፡ ቀሪዎቹን አራት ዓመታት ደግሞ በአንድ ቦታ ይቀመጣል፡፡ በዚህ ጊዜ የአስተዳደር ሥራውን እየሰራ ለቀጣይ አባገዳም አስቻይ መሰረትን አስቀምጦ ይሄዳል።አንድ አባ ገዳ እጅግ ከሚከፋባቸው ነገሮች መካከል በአስተዳደር ዘመኑ፤ ፀብ እና ጥላቻ ሲበረታ፣ ጦርነትና ቅያሜዎች ሲበራከቱ፣ ድርቅና ረሃብ የጠና እንደሆነ እጅግ ያሳስባቸዋል፡፡ አባ ገዳዎች ደስታቸው ሰላምና መረጋጋት ሲሆን፤ ለዚህ ሌት ተቀን አበክረው ይሠራሉ፡፡ በዚህ ላይ የጉጂ አባ ገዳዎች ብዙ እንደሰሩና እርሳቸውም ጥናቶችን እንዳደረጉ ይናገራሉ፡፡
አባ ገዳው ለሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት በሚያስተዳድርበት ግዛት ውስጥ የተከበረ፣ የሚደመጥና የመወሰን አቅም ጭምር ያለው ነው። ማህበረሰቡም አባ ገዳዎች የደነገጉትን የመተላለፍ ልምድ የለውም፡፡ ለዚህም ሲባል ያገለግሉኛል ብሎ ስለሚያምን ለባህሉ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ አባ ገዳዎች ወደ ስልጣን የሚመጡት ስለፈለጉ ብቻ ሳይሆን ከልጅነት ስማቸው ጀምሮ በሥርዓቱ ሁሉም እርከኖች አልፈውና ተኮትኩተው አድገው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በሥራ ታታሪ እና ከራሱ አልፎ ለሌላው ማድረግ የሚችል የኢኮኖሚ አቅም፣ በማህበረሰቡ የተወደደና ተቀባይነት ያለው፣ ቤተሰቡም ጨምሮ በዕዳ እና ክስ የማይታወቁ ለሥርዓቱ ታማኝ እና ምስጢር ጠባቂ መሆን አለበት፡፡
አባ ገዳዎቹ በመጨረሻዎቹ የስልጣን ርክክብ ሂደትም ረጅምና ጥልቅ ነው የሚሉት ተመራማሪው፤ ብዙ ውጣ ውረዶች የሚታለፉ ይሆናል፡፡ በመጨረሻው የ‹‹ባሊ›› ስልጣን ርክክብ ሳምንት የሚሰነብቱበትን ጎጆ በሚኤ ቦኮ አርዳ ጂላ ይቀልሳሉ። ይህ ጎጆ ‹‹ቀጫ›› ይባላል፡፡ ይህ ቤት በተመረጡ ሰዎችን በተመረጠ እንጨት የሚሰራ ነው፡፡ ቀጫ ሲሰራ ወይንም መሰረቱ ወይንም የምሰሶ መቆሚያ ጉድጓ በማር፣ ቅቤ እና ወተት ይደፋበታል። ይህም ጉጂ ያለውን ሀብት ለማመላከት እና የበረከት መገለጫ ነው፡፡ አባ ገዳዎቹም በዚህ ቀጫ ውስጥ ሆነው የተለያዩ ሥርዓቶችን ይፈጽማሉ፡፡ ቀጫ ውስጥ ከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጭ መሰስ ብሎ አይገባም፤ የተነወረ ነው፡፡ የአባገዳው ሚስት ‹‹ሀዳ ቦላ›› ከአባገዳው ያልተናነሰ ሚና ያላት ሲሆን ከቀጫ ውስጥ አብረው ይመክራሉ፡፡ በስልጣን ርክክብ ሂደት ደግሞ ዘርፈ ብዙ ትርጉም ያላቸው ሁነቶችም አሉ። ይህ የስልጣን ርክክብ የሚካሄድበት ስፍራ ልዩ ቦታ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ በዚህ አካባቢ የተነወሩ ድርጊቶችን መፈጸም የተከለከለ ነው። በዚህ ስፍራ መጣላት፣ ርግማን፣ ስርቆትና የመሳሰሉት ፈጽሞ የማይታሰቡ ናቸው፡፡
በጉጂ አባ ገዳዎች ሥርዓት መሠረት፤ ስልጣን አስረካቢው በማር፣ በቅቤ እና ወተት መግቦ እና በጋራ በልተው ነው ሽግግሩ የሚደረገው፡፡ ይህም ከልብ የሆነ መሰጠትን የሚገልጽ ሲሆን፤ ማር ቅቤ እና ወተቱ ደግሞ የበረከት፣ የሞልቶ መፍሰስ የመልካም ምኞት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን በ‹‹ባሊ›› ርክክብ ሂደት ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ለመገናኛ ብዙኃን ሆነ ለሕዝቡ ይፋ የማይደረጉ ነገር ግን አባ ገዳዎች ብቻ የሚፈጽሟቸው ሥርዓቶችም አሉ፡፡
በመጨረሻዎቹ የስልጣን ርክክብ ወቅት ግን ጉባዔው ‹‹ጉሚ›› በጋራ የወሰናቸው ድንጋጌዎች በተደጋጋሚ እና በስፋት ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ይታወጃል። ለአብነትም የጉጂ አባ ገዳዎች ሰሞኑን በተደጋጋሚ ድንጋጌዎችን አሳውቀዋል፡፡ ይህን ድንጋጌም የሚናገሩት ህግ ደንጋጌዎች ወይንም ‹‹ዩባዎች›› ይባላሉ፡፡ ዩባዎች በገዳ ሥርዓት ውስጥ ድንጋጌዎች ለማሳወቅ ወይንም ለማስረጽ በተደጋጋሚ የአባ ገዳው የምክክር አባላት ወይንም ጉባኤ የወሰነው ይህ ነውና እወቁ ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ለአብነትም ሰሞኑን የጉጂ አባ ገዳዎች ሴትን በተመለከት፣ መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን በተመለከተ፣ ጋብቻን በተመለከተ፣ ሰላምና መረጋጋትን በተመለከተ ትኩረት አድርገውባቸው ከመከሩባቸው ጉዳዮችና በዩባዎች አማካይነት ለሰባት ቀናት ሲነገሩ የሰነቡት ናቸው፡፡ የደን ሀብትን በተመለከተ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፤ ሰማይ እና ምድር ከተፈጥሮ ጀምሮ አራዊቶች መጠለያቸው ደን ስለሆነ እነዚህን ማፈናቀል ከሰብዓዊነት አኳያም አግባብ አለመሆኑን ደጋግመው አሳውቀዋል፡፡
አባ ገዳዎች የወሰኑት ወይም የደነገጉትም የሚከበር መሆኑ ነው የሚሉት አቶ ደንቢ፤ በተለይም ደንን እና የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ የሚተላለፈው መልዕክት ህብረተሰቡ ይተገብረዋል። ደኑንም ያለ አግባብ አይመነጠርም፡፡ በዚህም የተነሳ የጉጂ ዞን እጅግ ከፍተኛ ጥቅጥቅ ያለ የደን ክምችት ያለበት ነው፡፡ ይህን ተላልፎ የተገኘም እስከ ስምንት የቀንድ ከብቶችን የሚቀጣ ይሆናል፡፡ ሴት ልጅን ያለ ፍላጎቷ ጋብቻ እንድትመሰርት ማድረግ፣ በትዳር ላይ መባለግና የመሳሰሉትም በገዳ ሥርዓት ውግዝ ነው፡፡ የጉጂ አባ ገዳዎችም ይህን በተመለከተ ከሁለት ቀንድ ከብት ጀምሮ እንደየጥፋቱ ሁኔታ ሌሎች ቅጣቶች እንደሚኖሩ ደንግገዋል፡፡
እነዚህ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሥልጣኑን የተረከበው አባ ገዳ ደግሞ በርካታ የቤት ሥራዎች ይሰጡታል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው አባ ገዳ የጉጂ ወሰን ስለማስከበሩ፤ በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ ግጭቶችን በሰላም ስለመፍታቱ ገዳ ሥርዓት የሚያዛቸውን ግዳጆች ስለመፈጸሙና ሌሎችን ጉዳዮች ያነሳል፡፡ በመጨረሻ ግን በእነዚሀ የስልጣን ዘመን ያልተሳኩት እነዚህ ጉዳዮች ናቸው በማለት ለስልጣን ተረካቢው ያስረዳል። ይህም በገዳ ሥርዓት ጥንካሬን ብቻ ሳይሆን ጉድለቶችን ማመላከት አግባብ በመሆኑና ስልጣኑን የሚረከበው አባ ገዳ የበለጠ ተግቶ እንዲሰራ የሚያደርግ ነው፡፡ ስልጣን የተረከበው አባ ገዳም ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ‹‹ጉድለቶችን እንዴት ማስተካከል ይቻላል›› በሚለው ላይ በጥልቀት የሚመክር ሲሆን ጠንካራውን የበለጠ ለማጎልበት ይሰራል፡፡ በተጨማሪም ከስምንት ዓመት በኋላ ስልጣን ለሚረከበው አባ ገዳ አመቺ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይሄዳል፡፡
አቶ እያሱ በሳዬ በጉጂ ዞን የባህላዊ ፍርድ ቤት አባልና የታሪክ ተመራማሪ ሲሆኑ፤ በገዳ ሥርዓት አመጋገብም፣ ስጦታም ሆነ አለባበስ ፈርጅ አለው ይላሉ፡፡ አባ ገዳዎች ስለሚከበሩ አቅም በፈቀደ መጠን የአካባቢው ማህበረሰብ ለአባ ገዳዎች የሚሹትን ይሰጣሉ፡፡ ከሚበላ ምግብ ጀምሮ እስከ ሰንጋ በሬ በስጦታ መልክ የሚቀርቡ አሉ። ይህም ‹‹ጉማታ›› ይባላል፡፡ አባ ገዳዎችም ይህ አነሰ፤ ይኸኛው በዛ ሳይሉ መርቀው ይቀበላሉ፡፡ የዚህ ስጦታ ትልቁ ዓላማ አክብሮትን ለመግለፅ ጭምር ነው፡፡ ዋነኛ ምግባቸው ማር፣ ገንፎ፣ ቅቤ እና ወተት ብሎም ሥጋ ሌሎች የእንስሳት ተዋፅዎችን ነው፡፡ በመጠጥ ረገድ ደግሞ ‹‹ቦካ›› የማር ብርዝ ነው፡፡ ‹‹ቡና ቀላ›› ወይንም ድፍን ቡና ተቆልቶ እና በነጠረ ቅቤ ውስጥ ይጨመር እና ባህላዊ ብርጭቆ ወይንም ስኒ ውስጥ ይጨመራል፡፡ ይህ በጣም የተለመደ እና ዘወትር ማለዳ የሚዘወተር ነው፡፡ ይህን ምግብ ለማዘጋጀት ትልቁን ኃላፊነት የሚወስዱት እንስቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ሌሎች የምግብ ዓይነቶች የተለመዱ ናቸው፡፡ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ከስልጣን ማስረከብ ጀምሮ እስከ አመጋገብ ብሎም ስጦታ ማበርከት ያለው ሂደት ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ የሚሄድ ነው፡፡ በጉጂ አባ ገዳዎች ዘንድ የሚፈፀመው 75ኛው የ‹‹ባሊ›› ሥልጣን ርክክብ መርሐ ግብር በዚሁ መሰረት የተከናወነ ነው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016